በኢትዮጵያ የጋማ እንስሳትና ህብረተሰቡ በልዩ ልዩ መልኩ ጥብቅ ቁርኝት አላቸው፡፡ በተለይ ለገጠሩ የህብረተሰብ ክፍል የጋማ እንስሳት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አስተዋጽኦዋቸው ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል። የገጠሩ ማህበረሰብ በጋማ እንስሳት ከማሳ እህል ጭኖ ወደ አውድማ ያመጣባቸዋል፡፡ እህል ይወቃባቸዋል። የወቃውን እህል ደግሞ ጭኖባቸው ጎተራ ይሞላል፡፡ በእነዚህ እንስሳት የኢትዮጵያ ገበሬ እህሉን ጭኖና ወደ ከተሞች አጓጉዞ ይሸጣል። በሸጠው እህል ሌላ ሸቀጥ ገዝቶ ጭኖባቸው ዳግም ወደ አካባቢው ይመለሳል፡፡ ይህም የጋማ እንስሳት ለገጠሩ ማህበረሰብ በተለይ ደግሞ ለገበሬው ያላቸው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ያሳያል፡፡
በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሩቅ ሰው ለቅሶ የሚደርሰው በፈረስና በአህያ ተጉዞ ነው፡፡ ሰርግም እንደዛው። ዘመድም ሆነ የታመመ ሰው የሚጠያየቀው በጋማ እንስሳት በመጓዝ ነው፡፡ ይህም የጋማ እንስሳት ጭነት በማጓጓዝ ለገጠሩ ማህበረሰብ ከሚኖራቸው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር ለሰዎች የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠትና ማህበራዊ ኑሮዋቸውን በማሳለጥ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ ይጠቁማል፡፡
የገጠሩ ተነሳ እንጂ በከተሞችም አካባቢ ቢሆን ውሃ በጀሪካን፣ ሸቀጣ ሸቀጦችን፣ አሸዋ፣ ጠጠርና ሲሚንቶ ሳይቀር በጀርባቸው ተሸክመው በማጓጓዝ የሰዎችን ኑሮ የሚደጉሙ በርካታ አህዮች አሉ፡፡ የዛኑ ያህል ደግሞ ጋሪ እየጎተቱ ከቦታ ቦታ ሰዎችን በማመላለስ የትራንስፖርት ድጋፍ የሚሰጡና የባለጋሪዎችን ኑሮ የሚደጉሙ ፈረሶች በርካቶች ናቸው፡፡
በቀደመው የኢትዮጵያ ታሪክም ቢሆን የጋማ እንስሳት ከነዚሁ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦዋቸው ባሻገር ሀገሪቷ በገጠሟት የውጭ ወረራዎች ወቅት ትጥቅና ስንቅ በማጓጓዝ ብሎም በጦር ግንባሮች ጀግኖች አርበኞችን ጭነው ከፊት ሆነው እንዲፋለሙ በማድረግ ትልቅ ታሪካዊና ሀገራዊ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ የእነሱን አስተዋጽኦ ልብ በማለትም ጀግኖች አርበኞች በፈረስ ስሞቻቸው እስከመጠራት ደርሰዋል፡፡
እንግዲህ የጋማ እንስሳት በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ትልቅ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ አሁን ባለው መረጃም በኢትዮጵያ 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ የጋማ እንስሳት እንዳሉ ይነገራል፡፡ ይሁንና የአበርክቷቸውን ያህል ለደህንነታቸውና ለጤናቸው የሚደረገው ጥበቃና እንክብካቤ ዝቅተኛ ነው፡፡ በህብረተሰቡ በኩል ለጋማ እንስሳት ያለው አመለካከትም እጅግ ደካማና ኋላ ቀር ነው፡፡
በጋማ እንስሳት ጤናና ደህንነት አጠባበቅ ዙሪያ የሚሰራው ሥራ እጅግ ደካማና ከናካቴውም የለም በሚባል ደረጃ የሚገለፅ ቢሆንም ችግሩን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ጥናት አልያም ደግሞ የተጠናቀረ የቁጥር መረጃ የለም፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ረገድ የተሰራ ጥናትና የተጠናቀረ የቁጥር መረጃ ባይኖርም ቢያንስ ሀገሪቱ በጋማ እንስሳት ደህንነትና ጤና አጠባበቅ ዙሪያ ፖለሲ የሌላት መሆኑ ብቻ በዚህ ዘርፍ የሚሰራው ሥራ ችላ የተባለ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ትኩረት ተደርጎበት እየተሰራ እንዳልሆነም ያሳያል፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን የእነዚህ እንስሳት ደህንነትና ጤና የሚያሳስበው አንድ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ይበል የሚያሰኝ እንቅስቃሴ በሀገሪቱ እያከናወነ ይገኛል፡፡ አቶ ዮሐንስ ቃሲም ‹‹ብሩክ ኢትዮጵያ›› የተሰኘውና በጋማ እንስሳት ደህንነትና ጤና ጉዳዮች ላይ የሚሰራው ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት ድርጅቱ ዶሮቲ ብሩክ በተሰኘች እንግሊዛዊት በቀደመው ጊዜ በነበረ ጦርነት የእንግሊዝ ወታደሮች ግብፅ፣ ካይሮ ውስጥ ጥለዋቸው የሄዱና የተጎሳቆሉ 20ሺህ የሚጠጉ ፈረሶችን ለመርዳት ታላሚ በማድረግ ‹‹The Brooke Hospital for Animals in Cairo›› በሚል ስያሜ እ.ኤ.አ በ1934 የተመሰረተ ነው፡፡ በሂደት ድርጅቱ በተለያዩ ሀገራት ሥራውን አስፍቷል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ድርጅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአስራ አንድ ሀገራት ላይ ይሰራል፡፡ በእስያ፣ በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካና በሰሜን አሜሪካ ከጋማ እንስሳት ደህንነትና ጤና ጥበቃ ጋር በተያያዘ ሥራዎችን ያከናውናል። በኢትዮጵያም ‹‹Brooke Ethiopia›› በሚል ስያሜ በ2006 ዓ.ም ተመስርቶ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜም በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች (በቀድሞው አጠራር) ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡
“ብሩክ ኢትዮጵያ″ በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በማተኮር በጋማ እንስሳት ደህንነት ጥበቃ ዙሪያ ይሰራል። አንደኛው የእንስሳት ደህንነት፣ ጥበቃና አያያዙ ዙሪያ ለማህረሰቡ አጠቃላይ ግንዛቤ መስጠት ነው። በማህበረሰቡ በኩል የጋማ እንስሳት አያያዝ ችግሮች ይታያሉ፡፡ ይህን ለማስተካከል የእንስሳቱን ደህንነትና ጤና እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው ድርጅቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ይሰራል፡፡
ሁለተኛው የጋማ እንስሳት ባለቤቶች የገቢ አቅማቸውን እንዲያሳድጉና ከሚያገኙት ገቢ ተጠቅመው የጋማ እንስሳቱን ጤንነት ለመጠበቅ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ሥራ ድርጅቱ ይሰራል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ አጠቃላይ የጋማ እንስሳት የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ ለዚህም የእንስሳት ጤና ባለሙያዎችን አቅም በስልጠና ያጎለብታል፡፡ ይህም በተለይ በገጠር አካባቢ ያሉ የእንስሳት ጤና ባለሙያዎችን ያካትታል፡፡ ለእነዚህ ባለሙያዎች ተከታታይ የሙያ ሥልጠናዎችን በመስጠት አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ያደርጋል፡፡
ከወሎ፣ ጅማ እና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን በዩኒቨርሲቲዎቹ ውስጥ የሚገኙ የእንስሳት ሕክምና ተማሪዎች ተገቢው የክሂሎትና አቅም ኖሯቸው ትምህርታቸውን አጠናቀው እንዲመረቁ ጥራቱን የጠበቀ ሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስልጠናዎች እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የእንስሳት ጤና አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተደራሽነቱ ደካማ እንደመሆኑ ተደራሽነቱን ለማሻሻል የእንስሳት ጤና ኬላዎችን ድርጅቱ ይገነባል፡፡ ከገነባ በኋላም ለጤና ኬላዎቹ የሚያስፈልጉትን የሕክምና ግብዓቶች በማሟላት አገልግሎት እንዲሰጡ ያደርጋል። በተመሳሳይ የጋማ እንስሳት መድኃኒት አቅርቦት ችግር ያለ በመሆኑ ችግሩን ለማሻሻል በስልጠና፣ በገንዘብ፣ በማማከርና በመሳሰሉት፤ በተለይ በተዘዋዋሪ መድኃኒት አቅርቦት ፈንድ የእንስሳት መድኃኒት በዘላቂነት እንዲቀርብ የማድረግ ሥራዎችን ይሰራል፡፡ በዚሁ አሰራር መሠረት ለጋማ እንስሳት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ በመድኃኒቶች በዘላቂነት እንዲቀርቡ ከማድረግ አኳያ ድርጅቱ እየሰራ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የጋማ እንስሳትን ጤንነት ይበልጥ ለመጠበቅ ድርጅቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የውሃ ተቋማትን ይገነባል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ለሰዎችም የንፁህ ውሃ ተቋማትን ገንብቶ ያስረክባል፡፡ ሌሎች የጋማ እንስሳት ደህንነትና ጤናን ሊያረጋግጡና ሊያስጠብቁ የሚችሉ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ያከናውናል፡፡
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ በየመንገዱ ቆሳስለው የቆሙ ፈረሶችን ማየት የተለመደ ነው፡፡ እነዚህ ፈረሶች ሊድን በማይችልና /episodic fangaits/ በተሰኘ በሽታ የተጠቁ ናቸው፡፡ ቀድሞ መከላከል ቢቻል እዚህ ደረጃ ላይ ሳይደርስ መከላከል ይቻል ነበር። ነገር ግን ለነዚህ የጋማ እንስሳት ጤና የሚሰጠው ትኩረት በእጅጉ ያነሰ በመሆኑ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ፈረሶች ለረጅም ጊዜ የጋሪ ትራንስፖርት አገልግሎት ከሰጡ በኋላ ለእንዲህ ዓይነቱ በሽታ ከመጋለጣቸው በፊት አስፈላጊው ሕክምና አገልግሎት ስለማያገኙ እጣ ፈንታቸው አስፓልት ላይ በቁማቸው መሞት ነው፡፡
እነዚህ ፈረሶች የገጠማቸውን በሽታ ህመም በመቀነስ የማስወገድ ሥራ ብሩክ ኢትዮጵያ ይሰራል። ይህንንም የሚያደርገው ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች ለመከላከልና የፈረሶቹን ስቃይ ለመቀነስ ነው፡፡ ከከተማ ፅዳትና ውበት አኳያም የቆሳሰሉ ፈረሶችን ማየት ተገቢ ባለመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚመለከታቸው የመንግሥት አጋር አካላት ጋር ድርጅቱ በትብብር እየሰራ ይገኛል፡፡
እነዚህንና መሰል ሥራዎች ብሩክ ኢትዮጵያ እየሰራ የሚገኝ ቢሆንም በዋናነት በጋማ እንስሳት ደህንነት፣ አያያዝና ጤና ዙሪያ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ የውትወታ ሥራ ይሰራል። እንስሳትን የተመለከቱ አዋጆች፣ ሕጎች፣ መመሪያዎችና ደንቦች ሲወጡ የጋማ እንስሳትን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ሥራዎችን ይሰራል፡፡
በብሩክ ኢትዮጵያ የፐርፎርማንስና ካፓሲቲ ዴቨሎፕመንት ሲኒየር ማናጀር ዶክተር ቴዎድሮስ ተስፋዬ በበኩላቸው እንደሚሉት በጋማ ከብቶች አጠቃቀምና አያያዝ ዙሪያ የሚያስፈልጉ ፖሊሲዎች ኢትዮጵያ ቢኖራት ኖሮ በዘርፉ የሚታየውን ችግር በሚገባ መቅረፍ ይቻላል። ይሁንና ሀገሪቷ በዚህ ዙሪያ የተዘጋጀ ፖሊሲ የላትም፡፡ ድርጅቱ በሶስት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ አስራ አምስት ወረዳዎች ላይ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ሥራዎቹ ፕሮጀክት ላይ መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ በዚህም ሥራው በጊዜና በሀብት የተወሰነ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ የተጎዱ የጋማ እንስሳት በተለይ ደግሞ ፈረሶች አሉ፡፡ ይህም ድርጅቱ ተደራሽ ሆኖ ከሚሰራበት አካባቢ ውጭ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ድርጅቱ በሁለት ዓይነት መንገድ የጋማ እንስሳት ደህንነትና ጤንነትን ለመጠበቅ ይሰራል፡፡ አንደኛው የእንስሳት ጤና አገልግሎቱን ማሻሻል ሲሆን የጋማ እንስሳትን ያካተተ ሆኖ ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ማስቻል ነው፡፡ ይህንንም የሚያደርገው በተለይ በመንግሥት የእንስሳት ጤና ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች ተከታታይ የሆነ ስልጠናና ድጋፍ በመስጠት በክሂሎታቸው የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል ነው፡፡ ይህም ለጋማ እንስሳት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የቤት እንስሳቶች የጤና አገልግሎት ያገኛሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ለእነዚህ የጋማ እንስሳት አስፈላጊ የሆኑ መድኃኒትን ጨምሮ ሌሎች የሕክምና ግብዓት እጥረት ችግሮች ይታያሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ድርጅቱ በመድኃኒት ተዘዋዋሪ ፈንድ አማካኝነት በክልል ያሉ ክሊኒኮች የመድኃኒት አቅርቦት እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል። በተመሳሳይ መሠረታዊ የእንስሳት መድኃኒቶች ለኢትዮጵያ እንስሳት ጤና አገልግሎት ከሌሎች አጋር አካላት፣ ማለትም ከግብርና ሚኒስቴር፣ የግብርና ባለስልጣንና ከኢትዮጵያ እንስሳት ሐኪሞች ማህበር ጋር በመሆን የእንስሳት መሠረታዊ መድኃኒቶች ዝርዝር ተዘጋጅቷል፡፡
ይህም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፤ ከተለያዩ ልምድና እውቀት ካላቸው ባለሙያዎች ጋር በመሆን የተዘጋጀ ብሔራዊ ሰነድ ነው፡፡ ከዚህ በኋላም እነዚህን መድኃኒቶች ለኢትዮጵያ ሊኖራቸው የሚችለውን ገቢ የማምጣትና ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግ ሥራ ይጠበቃል፡፡ ይህም በብሩክ ኢትዮጵያ በእንስሳት ጤና ዘርፍ የሚያከናውነው ሥራ ሆኖ ማህበረሰቡ በጋማ እንስሳት ዙሪያ ያሉበትን የግንዛቤና የአያያዝ ክፍተቶች ለመሙላት በሁለት ዓይነት መንገድ፣ በተለይ በገጠራማውና በከተማው የሀገሪቱ ክፍሎች ይሰራል፡፡
አንደኛው በአዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ ይፋ የሚያደርገው ተንቀሳቃሽ የጋማ እንስሳት ሕክምና አገልግሎት ነው፡፡ ይህ አገልግሎት የሚሰጠው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ግብርና ቢሮና ከኤልም ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ነው። በዚህም በከተማዋ ውስጥ በሥራ ላይ የሚገኙ ፈረሶች የማከም ሥራ ይሰራል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ታመው መዳን የማይችሉ ፈረሶችን ህመም ሳይሰማቸው በርህራሄ /Euthanasia/ እንዲወገዱ ይደረጋል፡፡
ሀገሪቱ ወደ ሌላ ዓይነት ቴክኖሎጂ እስካልተሸጋገረች ድረስ የጋማ እንስሳት ከሚሰጡት አገልግሎት ውጭ መሆን አይቻልም፡፡ ይህም ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ ታዳጊ ሀገራት ላይ የሚታይ እውነታ ነው፡፡ ህብረተሰቡ የሚመገበው ምግብ በእነዚህ የጋማ እንስሳት ተጭኖ የሚመጣውን ነው፡፡ አይደለም የገጠሩ ማህበረሰብ በከተማም የሚኖረው የእነዚህ እንስሳት አስተዋጽኦ ተጠቃሚ ነው፡፡ ይሁንና እንስሳቱ ይህን ያህል ጥቅም እየሰጡ ቢሆንም ደህንነታቸውና ጤናቸው በበቂ ሁኔታ እየተጠበቀ ባለመሆኑ የሁሉንም ትኩረት ይሻሉ፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 8/2016