የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና…» እየተባለ የተዘፈነለት የኢትዮጵያ ቡና፤ ዛሬም በኢኮኖሚው ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ይዞ እንደቀጠለ ነው፡፡ ሻይ ቅጠልና ቅመማ ቅመም ጨምሮ ቡና ከልማት እስከ ግብይት አሁን ላይ የሚገኝበትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፤- ቡና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ወይም ዋልታነቱ በተግባር እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር አዱኛ፡– ኢትዮጵያ ቡና ለዓለም ያበረከተች ሀገር ከመሆኖም ባሻገር፤ ወደ ስድስት አይነት የቡና ዝርያዎች ይገኙባታል፡፡ ቡና የኢትዮጵያ ሕዝብም ቢሆን ልዩ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ ካለው ድርሻ በተጨማሪ ማሕበራዊ ትስስር በመፍጠር ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ የሰላም መገለጫ ተደርጎም ይወሰዳል። ምክንያቱም ሰዎች ተሰባስበው ቡና በጋራ ሲጠጡ በማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮችና የተለያዩ ሀሳቦች በማንሳት ይወያያሉ፡፡ በሰዎች መካከል ግጭት ሲፈጠርም በቡና ሥርዓት ላይ ችግሩን በመፍታት ጸብ በማብረድ ሰላም ይፈጥራሉ፡፡
ሰዎች እንግዳ ሲመጣባቸው የመጀመሪያ ግብዣቸው ቡና ጠጡ ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ኑሯቸው ወይም ሕይወታቸው ከቡና ጋር የተሳሰረ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በቡና ልማቱ ላይ አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ አርሶ አደሮች ተሰማርተዋል፡፡ የቡና ችግኝ ከማፍላት ጀምሮ ለገበያ እስኪቀርብ ድረስ ባለው ሒደት ብዙ ተዋናዮችን በማሳተፍ፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ ከ25 ሚሊየን በላይ የሚልቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኑሮውን ከቡና ጋር ያቆራኘ ነው፡፡ ቡና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚባለው በላይ ነው፡፡
ቡና በሀገር ደረጃም ኢትዮጵያ ስሟ ገኖ እንዲወጣ ማድረግ ያስቻለ፣ የኢኮኖሚ ዋልታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ የተመሰረተው በግብርና ላይ ቢሆንም፤ ከኢንደስትሪ ምርቶች ከማዕድንና ከተለያዩ የወጪ ንግዶች ውስጥ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ከ35 እስከ 40 በመቶውን ድርሻ በመያዝ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡
አዲስ ዘመን፤- ቡና በኢኮኖሚው ውስጥ ካለው አበርክቶ ለልማቱ የተሰጠው ትኩረት እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር አዱኛ፡- የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከመቋቋሙ በፊት የቡና ልማት የሚመራው በግብርና ሚኒሥቴር ሥር ነበር፡፡ ግብይቱ ደግሞ የሚፈጸመው በንግድ ሚኒስቴር ሥር ነበር፡፡ እንዲህ በተለያየ ተቋም ውስጥ መመራቱ፤ ልማቱና ግብይቱ የማይናበብበት ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ በልማቱ የተገኘው የቡና መጠን፣ የተፈጸመውም የግብይት ሁኔታ በተናበበ መልኩ ይከናወን ነበር ለማለት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ይህ በመሆኑም ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው ቡና እንደሀገር መገኘት የነበረበት የውጭ ምንዛሪ አለመገኘቱን ካለፉ ታሪኮች መገንዘብ ተችሏል፡፡
መንግሥት እንዲህ በዘርፉ ይስተዋል የነበረውን ችግር መፍታት የቻለው፤ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከተቋቋመ በኋላ ነው፡፡ ባለሥልጣኑ በ2008 ዓ.ም ሲቋቋም ልማቱንና ግብይቱን ለማሳለጥ ማስተዳደር የሚችልበት ስልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ባለሥልጣኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ልማቱንና ግብይቱን በመምራት፤ በሁለቱም በኩል ያለውን ችግር ነቅሶ በማውጣት፤ መፍትሄ የተገኘላቸውንም መፍትሔ በማስቀመጥ ምርትና ምርታማነት እንዲጨመር፤ የገበያ መዳረሻዎችም እንዲሰፉ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ተንቀሳቅሷል፡፡
የቡና ልማቱ ሥራ አርሶአደር ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፤ ከግማሽ ሔክታር በታች መሬት ያላቸውን አርሶአደሮች በማስተባበር፣ በማስተማርና በማሰልጠን፣ ለልማቱ የሚያስፈልገውንም ግብዓት በማቅረብ፣ የተለያዩ የድጋፍ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ አሁንም ምርትና ምርታማነት እንዲጨመር በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ባለሥልጣኑ ምርታማነትን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን፤ የሚመረተው ምርት በዓለም አቀፍ ገበያ ተቀባይነት እንዲኖረውና ተወዳዳሪም እንዲሆን በጥራት እንዲመረት ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ በልማቱ ረገድ ያረጁ ቡናዎችን በጉንደላ እና በነቀላ በአዲስ እንዲተካ በስፋት ያከናወነው ሥራ ይጠቀሳል፡፡ ጥራት ያለው ቡና ለማምረት የሚያስችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶአደሩ ተደራሽ በማድረግ፣ የጥራት አጠባበቅ ሥርአትን በማዘመን፣ የአሰራር ሥርአት በመዘርጋት ጭምር ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡
አዲስ ዘመን፤- የጫካ ቡና ከልማቱ ጋር እንዴት ይያያዛል? የጫካ ልማቱ ላይ አጠቃላይ ማብራሪያ ቢሰጡን፤
ዶክተር አዱኛ፡– በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የቡና አመራረት ሥርዓቱ አራት አይነት ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የጫካ ቡና ነው፡፡ የጫካ ቡና በተፈጥሮ የበቀለ ወይም ወፍ ዘራሽ ነው፡፡ የጫካ ቡና ሳይታረም በአካባቢው ሥነምህዳር በጫካ ውስጥ የሚበቅል፤ በየዓመቱ ምርት የሚገኝበት ነው፡፡ የጫካ ቡና ከሰው ንክኪ ነጻ የሆነ፤ በተፈጥሮ የሚገኝ ሀብት ነው፡፡ ቡናው ሲደርስ የሚጠበቀው ለቅሞ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ብቻ ነው፡፡ የጫካ ቡና ከሀገሪቱ የቡና ልማት አምስት በመቶ ድርሻ አለው፡፡
ሌላው ከፊል ደን (ሰሚ ፎረስት) የሚባለው ነው፡፡ ጫካን እና የዛፎችን ጥላ ያካተተ ማለት ነው፡፡ ይሄኛው ከጫካ ቡና የሚለየው በተወሰነ ደረጃ ሥራ ይሰራለታል፡፡ ሰዎች አረም ያርማሉ፤ የጥላ ዛፍንም ያስተካክላሉ፡፡ የሰው ንክኪ አለው፡፡ ከቡና የአመራረት ሥርዓት ወደ 35 በመቶ ድርሻ ይይዛል፡፡
ሶስተኛው የቡና ልማት፤ በአርሶ አደሩ ጓሮ የጥላ ዛፍ በመጠቀም የሚከናወነው ሲሆን፤ አርሶ አደሩ እንሰት፣ አትክልት፣ ቅመማ ቅመሞች የመሳሰሉ ተጨማሪ ልማቶችንም አብሮ በማከናወን ተጠቃሚ የሚሆንበት ልማት ነው፡፡ ይሄኛው የቡና ልማት ዘዴ እስከ 50 በመቶ ድርሻ ያለውና ከፍተኛው ልማት ሲሆን፤ ልማቱም የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም የሚከናወን ነው፡፡
አራተኛው ልማት ደግሞ የጥላ ዛፍ ሳያስፈልግ የሚከናወነው ነው፡፡ ሰፊ ቦታ የሚያስፈልገውና ዘመናዊ የአመራረት ዘዴንም የሚከተል ነው፡፡ ማዳበሪያና ኬሚካል የሚጠቀሙበት ሁኔታ አለ፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይልም ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ እየለማ ያለው ቡና፤ በአርሶ አደሩ ማሣ እና ከፊል ደን (ሰሚ ፎረስት) በሚባለው ሲሆን፤ ወደ 85 በመቶ ምርት የሚገኘውም ከእነዚህ ነው፡፡ ለልማቱ በትኩረት ድጋፍ እየተደረገ ያለውም በእነዚህ በሁለቱ ላይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፤- ችግኞችን የማፍላት ዘዴ የሚከናወነው በምን መልክ ነው?
ዶክተር አዱኛ፡- ችግኝ በሁለት አይነት መንገድ የሚባዛ ሲሆን፣ የሚወጣው በምርምር ነው፡፡ የትኛው ዘር ለየትኛው የአየር ንብረት ወይም ሥነምህዳር ይስማማል የሚለው በምርምር ወቅት የሚለይ ነው፡፡ ምርታማነቱን ማረጋገጥ የሚቻለው በዚህ መንገድ በመሥራት ነው ፡፡
ለአርሶ አደሩ የሚሰራጨው በምርምር የወጣ ዘር ነው። ዘሩ ችግኝ ከሚያፈሉ አካላት በመግዛት ወይም አርሶአደሩ በራሱ በማፍላት ሊጠቀም ይችላል፡፡ በዓመት ከ9 እስከ 12 ኩንታል ዘር ይከፋፈላል፡፡ የቡና ችግኝ አፈላል ዘዴ፣ ለችግኙ መትከያ የሚሆን ጉድጓድ ስንት በስንት መሆን አለበት የሚለውና ሌሎችንም መሥፈርቶች የያዘ ሥልጠናን ያካተተ ፓኬጅ ተዘጋጅቷል፡፡
አሁን ላይ ችግኝ የማከፋፈሉ ተግባር ለእርሻ ምርምር ብቻ የተተወ አይደለም፡፡ ባለሀብቶችም ችግኝ በማፍላት ለአርሶአደሮች የሚሰጡበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ ችግኝ አፍልቶ ከመጠቀም ሌላ አዲስ የዘር ብዜት አሰራር ዘዴም መጥቷል፡፡ የችግኙን ቅርንጫፍ ወይንም ቅጠል በመቁረጥ (ቲሹ ካልቸር) የማባዛት ዘዴም ተጀምሯል፡፡ አዲሱ ዘዴም መልካም ጎኖች አሉት፡፡
ባህሪውን ሳይለውጥ፣ በሽታን ተቋቁሞ መቆየት ይችላል፡፡ በዘር የሚራባው ግን ከተለያየ ቦታ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ወደኋላ የመመለስ ሁኔታ አለው፡፡ ምርታማነቱም ቢሆን በሔክታር ከ12 ኩንታል የበለጠ አይደለም፡፡ በቲሹ ካልቸር ዘዴ የሚባዛው ዘር ምርታማነቱ በሔክታር እስከ 20 ኩንታል ደርሷል።የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ ይህን ማጠናከር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የቡና ዘር ከሌላ ሀገር የማይመጣው ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሀገር በመሆኗ ነው? ወይስ ሌላ ምክንያት አለው?
ዶክተር አዱኛ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረተው አረቢካ የሚባለው የቡና አይነት ነው፡፡ ሮቦስታ የሚባለውን ቡና አናመርትም፤ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባም አንፈልግም። በኮሎምቢያና በብራዚል የሚባዙ አረቢካ የሚባለውን የቡና ዘርም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ማዳቀል አንፈልግም፡፡ የምንፈልገው የራሳችን የሆነውን ሀብት ይዘን መቆየት ነው፡፡ የእኛም ወደ ሌላ ሀገር ሄዶ እንዳይባዛ እንጠብቀዋለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ጠብቃ ያቆየችውንና ወደ ፊትም ለማስጠበቅ ጥረት የምታደርገውን የቡና ዝርያ ሌሎች እንዳይጠቀሙበት ለማድረግ ያለው ጥበቃ ምን ይመስላል?
ዶክተር አዱኛ፡- ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው እሴት የተጨመረበት ሳይሆን ጥሬ ቡና ነው፡፡ ያንን ወስደው አያባዙም ብሎ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ሆኖም ግን እንደሀገር የራሳችንን ዘረመል የመከታተልና የመቆጣጠር አቅም አለን፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት አለ፡፡ ይህ ተቋም ዋና ተግባሩ እነዚህ ዘረመሎች እንዳይወጡ ማድረግ ነው። በተጨማሪ በጅማ ምርምር ማዕከል የማከማቸትና የመጠበቅ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ በተቻለ መጠን የራሳችንን ሀብት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ የተለያዩ የአሰራር ሥርአቶች አሉን፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ቡና ከልማት እስከ ግብይት በአጠቃላይ እዚህ ደረጃ ላይ ይገኛል ተብሎ በጥንካሬ የሚገለጽ ነገር ካለ ቢነግሩን?
ዶክተር አዱኛ፡– ቡና በተለያየ ተቋም ውስጥ ሆኖ ይመረት በነበረበት ወቅት ልማቱ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮች ግብይቱ እንዳይሳለጥ የሚያደርጉ ሲሆኑ፣ ግብይት ውስጥ የሚያጋጥመው ማነቆ ደግሞ ልማቱ እንዳያድግ የሚያደርግበት አጋጣሚ ወይም ችግር ይፈጠራል፡፡ አሁን ላይ ከልማት እስከ ግብይት ያለው በአንድ ተቋም ሲመራ በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉትን ክፍተቶች ከመጀመሪያው ጀምሮ በመከታተል ለችግሩ መፍትሄ መስጠት የሚቻልበት እድል አለ፡፡ በቅርበት በመከታተል በተሰራ ሥራም የወጪ ንግድን መጨመር ተችሏል፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት ለገበያ የሚቀርበው ቡና ከ200ሺ ቶን የበለጠ አልነበረም፤ አሁን ላይ 300ሺ ቶን ደርሰናል። በገቢ ደረጃም ከወጪ ንግድ ይገኝ የነበረው ከ600 እና ከ700 ሚሊየን ዶላር የበለጠ አልነበረም፡፡ አሁን ላይ አንድ ነጥብ ሶስትና አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር ማግኘት ተችሏል፡፡ የቡና ገበያ ገቢያችንን በሚሊየን ከሚቆጠሩ ዶላሮች በቢሊየን ወደ ሚቆጠሩ ዶላሮች ከፍ ማድረግ ችለናል፡፡ የወጪ ንግድ በየጊዜው እየጨመረና እድገት እያስመዘገበ ነው፡፡
በምርት ደረጃም በአጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ከነበረበት 500ሺ ቶን ወደ 800ሺ ቶን አድጓል፡፡ ያረጁ ቡናዎችን በጉንደላ ሙሉ ለሙሉ በማንሳት በአዲስ በመተካት ምርታማነት እንዲጨምር ማድረግ ተችሏል። ቡና የሚለማበት የመሬት ሽፋኑም ከ600ሺ ሄክታር መሬት ወደ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሔክታር ከፍ ብሏል። ይህም ልማቱ እያደገ መምጣቱን ማሳያ ነው፡፡ እነዚህ ለውጦች የተመዘገቡት ባለሥልጣን መሥሪያቤቱ ከተቋቋመ በኋላ በተከናወኑት ተግባራት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በሁለት ዙሮች እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለቡና ልማቱ ያለው አስተዋጽኦ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር አዱኛ፡- በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚከናወነው የዛፍ ችግኝ ተከላ ዛፍ መትከል ብቻ ሳይሆን፤ ጥቅምም እንዲያስገኝ ታስቦ በመሆኑ እንቅስቃሴው ይበረታታል፡፡ ቡና በየዓመቱ የሚተከል ቢሆንም የመርሃ ግብሩን የንቅናቄ መርሃግብር ተከትሎ ግን ብዛት ያለው የቡና ችግኝ ተተክለዋል፡፡ ቡና የዛፍ ጥላ የሚፈልግ በመሆኑም ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እስኪ ወደ ግብይቱ ደግሞ መለስ እንበልና የኢትዮጵያ ቡና ለዓለም ገበያ እየቀረበ ያለው በቡና ያላትን ዝና መሠረት በማድረግ ብቻ ነው ወይስ ተገቢው የማስተዋወቅ ሥራዎችን ተከናውነዋል?
ዶክተር አዱኛ፡– ብዙ ጊዜ እንደሚባለው ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሀገር ናት፤ የቡናውም ጣዕም ተመራጭ ነው በሚል በዝና ብቻ አይደለም፤ ቡና የሚያመርቱ በጣም ብዙ ሀገሮች ናቸው፡፡ አፍሪካን ብቻ ብንወስድ ቡና አምራቾች ከ25 ሀገራት በላይ ናቸው፡፡ የምንወዳደረው ከዓለም ጋር ነው፡፡ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ገበያውን ለመቆጣጠር እራስን በየጊዜው መፈተሽና ዝግጁ መሆን ይጠበቃል፡፡ ተገቢውን የማስተዋወቅ ሥራም መሰራት ይኖርበታል፡፡
አሁን ላይ እያደረግን ያለነው በውጭም በሀገር ውስጥም በሚዘጋጁ ኤግዚቢሽኖች ላይ በስፋት እንሳተ ፋለን፡፡ አምራቾችና ላኪዎች እንዲሳተፉ ይበረታታሉ፡፡ በዓለምአቀፍ ውድድሮች ላይም ቡናቸውን በማቅመስ ተወዳዳሪነታቸውን እንዲጨምሩ ይደረጋል፡፡ በዚህና በተለያየ የማስተዋወቅ ዘዴ በመጠቀም የቡና ገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት ወይም ማሳደግ ተችሏል፡፡
ቀደም ሲል የኢትዮጵያን ቡና ይገዙ የነበሩት ሀገራት አሜሪካን፣ ጃፓን፣ ሳውድአረቢያ፣ ቤልጅየምና ጀርመን ብቻ ነበሩ፡፡ አሁን ላይ መዳረሻዎቹ ወደ 33 ሀገራት ከፍ ብሏል፡፡ በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ ዓለም አቀፍ ላይ ያሉ ቡና አምራቾች፣ ገዥዎችና ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ኤግዚቢሽን ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
እንዲህ በኤግዚቢሽን ከማስተዋወቅ በተጨማሪ ሀገራዊ የሆነ መለያ (ብራንድ) በማዘጋጀትም ኢትዮጵያ በቡና የምትታወቅበት ሥራም ተሰርቷል፡፡ ይህ መለያ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በኤዥያ ሀገርም እንዲመዘገብ ተደርጓል፡፡ መለያውም ኢትዮጵያ ውስጥ ቡና የተገኘበትን ታሪካዊ አመጣጥ የሚያሳይ ነው፡፡
መለያው የኢትዮጵያ ካርታ፣ ፍየል፣ ሰው፣ ዱላ እና ቡና የሚያሳይ ምስል ሲሆን፤ ሰውየውና ዱላው ፍየል የሚጠብቀውን እረኛ ለማሳየት ሲሆን፣ ፍየሏ ደግሞ ቡና ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩ የተረጋገጠው ፍየሏ የቡና ቅጠል በመብላቷ በመሆኑ ይሄንን ታሪካዊ የቡና አመጣጥ ለማሳየት ነው፡፡ መለያውን የያዘ በራሪ ጽሁፍ በማዘጋጀትም በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ ቆንጽላ ጽህፈት ቤቶቻችንና በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት የማስተዋወቅ ሥራ ተጠናክሯል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እሴት የተጨመረበት ቡና ለገበያ በማቅረብ በኩል ስላለው እንቅስቃሴ ቢገልጹልን?
ዶክተር አዱኛ፡– አሁን ባለው የቡና ግብይት 99 በመቶ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ጥሬ ቡና ነው፡፡ እሴት ያልተጨመረበት ምርት ብቻ ይዞ ወደ ገበያ ማቅረብ ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ እንደተጠበቀው ላይሆን ይችላል፡፡ ተቆልቶ የተፈጨ ቡና ለውጭ ገበያ የማቅረብ ጅምር እንቅስቃሴ ግን አለ፡፡ አሁን ላይ የተቆላና የተፈጨ ቡና ለውጭ ሀገር ገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ በውጭ ምንዛሪ እንዲቀርብ ወይንም እንዲሸጥ የአሰራር ሥርአት ዘርግተናል፡፡ የአሰራር ሥርአቱ ደንብና መመሪያ የተዘጋጀለት ሲሆን፤ ተጠቃሚዎችም በደንብና መመሪያው መሠረት ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እስከዛሬ እሴት የተጨመረበት ቡና ለገበያ ማቅረብ ላይ ስኬታማ መሆን ሳይቻል ቀረ?
ዶክተር አዱኛ፡- ያልተሳካው በዋናነት ትላልቅ ቡና ገዥዎች ቡና ቆልተውና ፈጭተው ለገበያ የሚያቀርቡ በመሆናቸው ነው፡፡ ሌሎች ቡና ገዥዎችም ቢሆኑ ጥሬውን እንጂ እሴት የተጨመረበት ቡና መግዛት ፍላጎት የላቸውም። አብዛኞቹ የኢትዮጵያን ቡና የሚፈልጉት ለማጣፈጫ ወይንም ለጥሩ ጣዕም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ጣዕም ጥሩ በመሆኑ ለገበያ የሚያቀርቡት ከሌላ ሀገር ከገዙት ቡና ጋር ቀላቅለው ነው ፡፡ እሴት በተጨመረበት ቡና ተወዳዳሪ እንዳንሆን ያደረጉን፤ እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ናቸው። ያም ሆኖ ግን እሴት የተጨመረበት ቡና ለውጭ ገበያ ከማቅረብ አንቆጠብም፡፡ ቀስ በቀስ ወደ ገበያ በመግባት ከባዱን የገበያ ውድድር ለማለፍ ጥረት እያደረግን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባለልዩ ጣዕም የሚባለው የቡና አይነት በውጭ ገበያ ላይ ዋጋ ሲወርድ በሀገር ውስጥ እንዲቀርብ እየተደረገ ነው የሚል አስተያየት ይሰጣል፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው? ከሆነስ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ተጽእኖ አያሳድርም?
ዶክተር አዱኛ፡– ለውጭ ገበያና ለሀገር ውስጥ የሚቀርቡ የቡና አይነቶች ፍጹም የተለያዩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለውጭ ገበያ የተዘጋጀ ቡና በምንም አይነት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲመለስ አይደረግም፡፡ መላክ ያለበት ለውጭ ገበያ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሀገር ውስጥ በተለይም የቡና ጠጡ ገበያ እየሰፋ መምጣት ለውጭ ገበያ የሚያቀርበውንም እየሳበ እንደመጣና አንዳንድ ነጋዴዎችም ፍላጎት እያሳዩ መምጣታቸው እየተነገረ ነው፡፡ እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር አዱኛ፡– በሀገር ውስጥ የጅምላ ነጋዴ ፍቃድና ለውጭ ገበያ አቅራቢ የንግድ ፈቃድ የተለያዩ ናቸው፡፡ የውጭ ገበያ የንግድ ፈቃድ ያለው የማቅረብ ግዴታ ያለበት ለውጭ ገበያ ብቻ ነው፡፡ ፍላጎት ቢኖርም ስለማይፈቀድ አይቻለም፡፡ ያለባቸው የንግድ ፈቃዳቸውን መቀየር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሕገወጥ ግብይት ጉዳይም በዘርፉ ላይ ይነሳል፡፡ በተለይም በሀገር ውስጥ ሕገወጥነቱ የሰፋ እንደሆነ ይነገራልና አሳሳቢነቱ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር አዱኛ፡- ሕገወጥ ንግድ የለም ማለት አይቻልም። ዓላማውም ይታወቃል፡፡ በአቋራጭ የመክበር ፍላጎት ነው። በተቻለ መጠን የተሻለ አምርቶ በስፋት ለገበያ በማቅረብ፣ አልሚውም ሻጩም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እንዲሁም በቁጥጥርና ክትትል ሥርዓት በማበጀት ለችግሩ መፍትሄ እየተሰጠ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ከአርሶአደሩ ማሣ እስከ ጅቡቲ ለገበያ እስኪደርስ ድረስ በቴክኖሎጂ የታገዘ የምንቆጣጠርበትን ሥርዓት ዘርግተናል፡፡ ከዚህ በፊት በዚህ መንገድ የምንቆጣጠርበት እድል ስላልነበር ሕገወጥነቱ በስፋት ነበር፡፡ አሁን እየተሰራበት ባለው መንገድ ችግሩን መቶ በመቶ ማስቀረት ባይቻልም መቀነስ ግን ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሕገወጥነቱ በስፋት የሚስተዋለው በሀገር ውስጥ በሚቀርበው ነው? ወይንስ ለውጭ ገበያ በሚቀርበው ላይ?
ዶክተር አዱኛ፡- ቡናው ለውጭ ወይንም ለሀገር ውስጥ የሚቀርብ መሆኑ የሚለየው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከደረሰ በኋላ ነው፡፡ ከተለያዩ ቡና አምራች አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ ከተማ ከመጣ በኋላ ማቀነባበሪያና ማዘጋጃ ማሽኖች ለደረጃ ይዘጋጃሉ፡፡ በአብዛኛው ቡና በሕገወጥ መንገድ የሚወጣው አዲስ አበባ ከተማ ሳይገባ በመንገድ ላይ ነው። ወደ ከተማ ሳይገባ ወደ መርካቶ የሚገባበትም ሁኔታ አለ፡፡ አጠቃላይ ቡናው ስለሚወጣ ለውጭ ወይም ለሀገር ውስጥ የተዘጋጀ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከገባ በኋላ ግን ለመንቀሳቀስ ከቡናና ሻይ ባለሥልጣን የሽኝት ደብዳቤ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ።ካልፈቃድ ከአንድ መጋዘን ወደ ሌላው ማዟዟር ወይም ማጓጓዝ አይቻልም። ከተፈቀደለት መሥመር ውጭ ከተገኘ እንደ ሕገወጥ ወይም ኮንትሮባንድ ስለሚታይ በዚህ ሁኔታ ከተገኘ ቡናው ይወረሳል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ጊዜያቶች ኢትዮጵያ በገጠማት የፀጥታ መደፍረስና በሰሜኑ ክፍልም ተካሂዶ የነበረው ጦርነት ይህን ተከትሎም የነበረው የውጭ ጫና በዘርፉ የልማትና የገበያ እንቅስቃሴ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ምን ይመስላል?
ዶክተር አዱኛ፡- ሀገራዊ ችግሮች ቢኖሩም እስካሁን ድረስ ለዘርፉ እንቅስቃሴ እንደተግዳሮት የሚገለጽ ነገር አላጋጠመም፡፡ ለኢትዮጵያ ቡና ትልቁ ተጽዕኖ የዓለም አቀፍ የገበያ ዋጋ ሁኔታ ነው፡፡ ምርት እንዲጨምርም እንዲቀንስም በማድረግ ረገድ ገበያው ተጽእኖ ያሳድራል።
አዲስ ዘመን፡- በቡና ልማት ሥራ ላይ እንደ አውሮፓ ሕብረት ያሉ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃልና እገዛቸው እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር አዱኛ፡– ወደ 15 የሚሆኑ አጋር ድርጅቶች አብረውን እየሰሩ ነው፡፡ ለቡና ጉንደላና ማድረቂያ ማሽኖችና ሌሎች ለልማት የሚውሉ ግብአቶች በማቅረብ፣ የአልሚውንና የላኪውን አቅም በሥልጠና በማብቃት ያግዛሉ፡፡ ሥራዎቻቸው እኛ ከምንሰራው ስትራቴጂ ጋር አብሮ እንዲሄድ በማድረግ እንጠቀማለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከልማት እስከ ግብይት በሚካሄደው የቡና እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሀገር ይቀረናል ተብሎ የሚነሳ ካለ ቢገልጹልን?
ዶክተር አዱኛ፡- ገበያውን በተመለከተ እሴት ጨምሮ ማቅረብ ላይ ይቀረናል፡፡ በስፋት ብንሄድበት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ስለሚፈጥር ጭምር በትኩረት መሥራት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የቡና ግብይት ታሪክ በ2015 ዓ.ም አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ የእዚህ ስኬት መነሻ ምንድን ነው?
ዶክተር አዱኛ፡- በግብይት ስርዓት ውስጥ የነበሩትን ረጅም ሰንሰለቶች በአሰራር በመቀየር፤ ከአርሶ አደሩ እጅ ወጥቶ ቀጥታ ለውጭ ገበያ የሚቀርብበት የአሰራር ሥርዓት በመፍጠር፣ የገበያ አማራጮችንም በማብዛት፣ አርሶ አደር ለአቅራቢ፣ አቅራቢ ደግሞ ለላኪ የሚያቀርብበትን ሁኔታ ምቹ በማድረግ ብክነትን በማስቀረት፣ ጥራትንም በመጨመር የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከፍ ማድረግ ተችሏል።
አዲስ ዘመን፡- የቡና ልማትና ግብይት በአርሶ አደሩ ኑሮ ላይ ለውጥ አስመዝግቧል?
ዶክተር አዱኛ፡– ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ከተሸጠው ቡና አርሶ አደሩ ኪስ የሚገባው ቢበዛ 40 በመቶ ነበር፡፡ ባለሥልጣኑ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሪፎርም በመሥራት ለማሻሻል ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህም ያለ ሶስተኛ ጣልቃ ገብነት አርሶ አደሩ ቀጥታ ኤከስፖርት የሚያደርግበት አሰራር በመዘርጋት ከ80 እስከ 90 በመቶ ወደ ኪሱ ገቢ እንዲያስገባ ተደርጓል፡፡ ቡና ነቅለው ባሕር ዛፍና ጫት ወደመትከል ገብተው የነበሩ አርሶ አደሮች ወደ ቡና ልማቱ ተመልሰዋል፡፡ ቡናን በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴም በስፋት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሻይ ቅጠልና ቅመማ ቅመም በኩል ያለው ልማትና ገበያስ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ዶክተር አዱኛ፡- ሻይ ቅጠልና ቅመማ ቅመም የግብይት ሥርዓት ተዘርግቶላቸው የልማት ሥራ የሚከናወንላቸው ሲሆን፤ እየተከናወነ ያለው ልማት አርሶ አደሩንም ሆነ ሀገርን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡ ሻይ ቅጠል ወደ አራት ሺ ሔክታር ማሣ ላይ እየለማ ሲሆን፣ በገቢ ደረጃም ለውጭ ገበያ ቀርቦ በዓመት እስከ ሶስት ሚሊየን ዶላር ገቢ ይገኛል። ሽያጩም ኬኒያ ሞምባሳ ከተማ በሚካሄደው ጨረታ የሚከናወን ነው፡፡ የገበያ መዳረሻ ሀገሮችም በብዛት ሕንድ፣ እንግሊዝ፣ ፓኪስታን ሞምባሳ ናቸው፡፡
ቅመማ ቅመም ደግሞ ስምንት ሺ ሄክታር ማሣ ላይ እየለማ ነው፤ በገቢም በዓመት እስከ 17 ሚሊየን ዶላር ገቢ ያስገኛል፡፡ ከሁለቱ እስከ 20 ሚሊየን ዶላር በዓመት ገቢ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ያስቀመጠውን እቅድ ቢገልጹልን?
ዶክተር አዱኛ፡- የ15 ዓመት ስትራቴጅ እቅድ አውጥተናል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም በቡና፣ በሻይ ቅጠልና በቅመማ ቅመም ከአራት ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት አቅደን እየሰራን ነው፡፡
አዲስዘመን፡- የ11ኛው ዙር የበጎ ሰው ተሸላሚ ስለመሆኑ እንኳን ደስ አለዎት፤ለዚህ ሽልማት እንዴት በቁ? ሽልማቱ ምን ኃላፊነት ጣለብዎት? መልዕክትም ካለዎት አክለው ይግለጹልን፡፡
ዶክተር አዱኛ፡- ሽልማቱ መንግሥታዊ ተቋማትን በአግባቡ መምራት በሚል ነው፡፡ ምርጫው የራሱ መሥፈርት አለው፡፡ እኔ ግን በኃላፊነት መምራት ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር ለውጥ ለማምጣት ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ውጤትም እየተመዘገበ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ኃላፊነቴን እየተወጣሁ ያለሁት እሸለማለሁ በሚል ባይሆንም ግን ሥራዬ በሌሎች ታይቶ ለሽልማት መብቃቴ አስደስቶኛል፡፡ የበለጠ ለመሥራት ያነሳሳል። የኃላፊነት ደረጃ በቀላሉ አይመጣም፡፡ የተወለድኩት ገጠር ነው ግን በትምህርቴ ጠንካራ ለመሆን ብዙ ታግያለሁ፡፡ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የትምህርት እድል አግኝቼ ለዩኒቨርሲቲ መምህርነትና አሁን ላለሁበት ደረጃ ደርሻለሁ። ወድቆ መነሳት ያጋጥማል፡፡ ግን ደግሞ ፈተናዎችን በዓላማና ትጋት መወጣት ይጠበቃል። በአንዴም ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እንደማይቻልም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በቅንነት ሀገርንም ማገልገልም ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር አዱኛ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2016