የሰልጣኞች ቅበላና ስልጠና በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ

በጣሙን ከመለመዱ የተነሳ ይመስላል ካለ ዩኒቨርሲቲ መመረቅ ያለ አይመስለንም። ዩኒቨርሲቲ ያልገባ ሁሉ ምንም አይነት እውቀት የታጠቀ ሁሉ እስከማይመስለን ድረስ በዩኒቨርሲቲዎች ተማርከናል። ግን ደግሞ ሕይወትን ስንቃኛት ምንጯ አንድ አይደለም፤ መንገዷም የተለያየ ነው። ያንዳንዱ ሰው ሕይወት መሰረቱ የቆመው በንግድ ላይ ሊሆን ይችላል። ያንዳንዱ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ሊሆን ይችላል። ያንዳንዱ ደግሞ ድምፃዊነት፤ የሌላው ደግሞ ስፖርተኛነት ሊሆን ይችል። በመሆኑም፣ ሕይወት ሁሉ ስኬታማ ለመሆን የተለያዩ እውቀቶች፣ ክህሎቶች ወዘተ እንጂ ለሁሉም አንድ ሙያ በቂ አይደለም።

የዚህ እውነታ ደግሞ በዘንድሮው ዓመት ያለፉትና የወደቁት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ውጤት ሲሆን፤ በተለይ ውጤት ያልመጣላቸውን በተመለከተ ልክ ሕይወት እንዳበቃላቸው ሁሉ ተደርጎ ሲታዘንላቸው ነው የተከረመው።

እርግጥ ነው፣ እንደ ሚኬኤል (Michael W. Ni­cholson) 30 ዲግሪዎች ቢኖሩን፣ ወይም እንደ ቤንጃሚን (Benjamin Bradley Bolger) የ17 ዲግሪዎች ባለቤት ብንሆን አንጠላም። ያ ማለት ግን ለመኖር ዲግሪ ብቻውን ወሳኝ ነው ማለት አይደለም። ለሁሉም እንደየ ፍላጎቱ፣ ዝንባሌና አቅሙ በርካታ የጥናት (የሙያ) መስኮች አሉ። በመሆኑም፣ ሁሉም የሕይወት ጥሪውን አዳምጦ መሰማራት ነው እንጂ ያለበት “የግድ‘ ባለ ዲግሪ መሆን የለበትም።

አሜሪካ ሃብታም አገር ነች፤ ያ ማለት ከሌሎቻችን ጋር በንፅፅር ሲታይ አሜሪካኖች በጣም ሀብታሞች ናቸው። ይህ ሀብታምነት ግን የዲግሪ ባለቤት ከመሆን የመጣ አይደለም። በራሳቸው፣ በአሜሪካውያኑ በዚህ በያዝነው ዓመት የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው ከአጠቃላይ አሜሪካውያን መካከል ባለ ዲግሪዎቹ 37.7 በመቶ (በ2020 ከነበረበት 37.9 በመቶ ቀንሶ) ያህሉ ብቻ ናቸው። በእርግጥ በ1960 ከነበረበት 7∙7 በመቶ ጋር ሲነፃፀር አገሪቱ ከፍተኛ እመርታን አሳይቷል ማለት ይቻላል። (ለዝርዝሩ፣ “The Percentage of Americans with College Degrees in 2023‘ን ይመልከታል) ለመግቢያ ያህል ይህንን ካልን ወደ ተነሳንበት፣ ወደ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሰሞኑ አቢይ ዜና እንምጣ።

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት 600ሺህ ተማሪዎችን ለመቀበል መዘጋጀታቸው የሰሞኑ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ መሰንበቱ ይታወሳል። የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ይፋ እንዳደረገው፣ 12ኛ ክፍል ካጠናቀቁ ተማሪዎች ውስጥ በዘንድሮው ዓመት በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚገቡ 600ሺህ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል። በሚኒስቴሩ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፣ የትምህርት ተቋማቱ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ የ2016 ዓ.ም የቴክኒክና ሙያ ሠልጣኞችን ይቀበላሉ።

በዘንድሮው ዓመት 600ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሠልጠን የሚያስችል በቂ የትምህርት ግብዓት ዝግጅት መደረጉም የተገለፀ ሲሆን፣ በቴክኒክና ሙያ በመደበኛ ፕሮግራም ከሚሰለጥኑ በተጨማሪ በአጫጭር ስልጠናዎች ለሁለት ሚሊዮን ዜጎች ስልጠና ለመስጠት መታቀዱንም ተነግሯል።

በኢትዮጵያ ከ700 በላይ የመንግሥት እና ከ900 በላይ የግል የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት እንደሚገኙም ተገልፇል። ዝግጅቱ ይህንን ከመሰለ፣ ስለ “የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና‘ ለአጠቃላይ ግንዛቤ አንዳንድ ጉዳዮች በማንሳት እንወያይ፤ ከማዕከልም እንጀምር።

“ቻይና በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የቴክኒክና ሙያ የልህቀት ማዕከል ከፈተች‘ በሚል ቀርቦ በነበረ ዜና ላይ በሚመለከታቸው አካላት እንደ ተብራራው፣ “ከአፍሪካ ጋር ያለንን ትብብር ማሳደግ እንፈልጋለን‘ በሚል የቻይና መንግስት የአፍሪካ መሪዎችን በ2020 በቤጂንግ ጠርቶ ባደረጉት የግንኙነት መድረክ ውይይት ላይ የአፍሪካ መሪዎች አፍሪካን ለማሳደግ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ እገዛ እንዲደረግላቸው ከጠየቁት ጥያቄ አንዱ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ነበር።‘ በመሆኑም፣ “በኢትዮጵያም ሆነ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ለሚገኙ አገሮች ሊጠቅም የሚችል የመጀመሪያው የሉባን የሥልጠና ወርክ-ሾፕ ማዕከል በኢትዮጵያ‘ ተከፈተ (ሉባን በቻይና የሚገኝ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ የስልጠና ማዕከል ነው)። “ቻይና በአፍሪካ እንዲሰሩ ከፈቀደቻቸው አሥር ማዕከላት አንዱና የመጀመሪያው‘ መሆኑም እንደዛው።

የቴክኒክና ሙያ የልህቀት ማዕከል “ዓላማው የሳይንሥና ቴክኖሎጂን በኢትዮጵያና በአፍሪካ ለማስፋፋት እና በዘርፉ እውቀትና ክህሎት ያለውን የሰው ኃይል ለማፍራት፣ የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ለመደገፍ‘ መሆኑም ተነግሯል። ከዚህ አኳያ ዘንድሮ ብቻ ወደ ስልጠና ማዕከላት የሚገቡት ከ600ሺህ በላይ ሰልጣኞች ለአገራቸው አለኝታ ከመሆንም ባለፈ ለተለያዩ ተቋማት የጀርባ አጥንት ስለ መሆናቸው መከራከር አይቻልም።

“የሀገራችን የማምረቻ፣ የንግድና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በቴክኒክና ሙያ ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ቀጥሮ በማሰራት ብቁ፣ ተወዳዳሪና ዘላቂነት ያለው ድርጅታዊ አቋም እንዲኖራቸው ማስቻል አስፈላጊ ሆኖ‘ በመገኘቱ ምክንያት በ1996 አዋጅ (የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና አዋጅ ቁጥር 391 /1996) እንዲወጣለት የተደረገው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የሕግ ማዕቀፍ ያለው መሆኑ በራሱ ባለ ሀብቶች በዘርፉ ተሰማርተው እንዲሰሩ የሚገፋፋ ከመሆኑም አልፎ መተማመኛም ጭምር ነውና በትምህርት ዘርፍ የሚሰማሩ ወገኖች ይህንንም ሊያስቡበት ይገባል።

የቴክኒክና ሙያ የልህቀት ማዕከላት የሚያፈሩት የሰው ኃይል “በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ በሳይንሥና ቴክኖሎጂ፣ በኤሌክትሮኒክስ እና አሌክትሪካል ማኑፋክቸሪንግ የምናሰለጥነው የሰው ኃይል አሁን ላይ እየተስፋፉ ላሉ ኢንዱስትሪዎች በደንብ የሚያግዝና ከቻይና እና ቱርክ የሚመጣውን የሰው ኃይል የሚቀንስ‘ እንደሚሆን ታውቋል።

የልህቀት ማዕከሉ “ስልጠና ያስፈልገኛል‘ ብለው ጥያቄ ለሚያቀርቡ ኢንዱስትሪዎች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ከልህቀት ማዕከሉ ስልጠና ፈልገው በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ከሚገኙ አገሮች ለሚመጡም በክፍያ አገልግሎት እንደሚሰጥም ታውቋል። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ጉዳይ አንገብጋቢ መሆኑን ነው።

የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በማጠናከር እና ገበያ መር የሆነ የስልጠና ማዕቀፍ በማዘጋጀት ወጣቶች የልዩ ልዩ ሙያ ባለቤት እንዲሆኑ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራ የሚገልፀውና ለዚሁ ተግባር የተቋቋመው የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር “የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በማጠናከር ገበያ መር የሆነ የስልጠና ማዕቀፍ በማዘጋጀት እና ወጣቶችን በማሰልጠን የልዩ ልዩ ሙያ ባለቤት እንዲሆኑ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ‘ በፓርላማ ሳይቀር ገልፇል። “የምጣኔ ሃብቱን ዕድገት ለማፋጠን ሚኒስቴሩ በሰው ሃብት ላይ በሥራ ባሕል እና ባሕሪ ለውጥ የሚታዩ የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት አተኩሮ ለመስራት ማቀዱን፤ የቴክኒክና ሙያ ስልጠናውን ከገበያ ፍላጎት ጋር በማጣጣም በአገር ውስጥና በውጭ የሥራ አማራጮችን የማስፋትና አቅም መገንባት የሚኒስቴሩ የትኩረት መስኮች መሆናቸው‘ም እንደዚሁ በተወካዮች ምክር ቤት ደረጃ ለውይይት ቀርቦ እንደ ነበር ይታወሳል።

ባለፈው ዓመት (2022) “በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በታንዛኒያ መካከል ሲደረግ የነበረው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ምዘናን፣ ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሳድጋል የተባለው ፕሮጀክት በሦስቱ አገሮች ተፈርሞ‘ መፅደቁን፤ “በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና የሚመረቁ ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን፣ በሦስቱ አገሮች እንደ ልብ ተንቀሳቅሰው የመሥራት ዕድል‘ የሚያስገኝ መሆኑን፤ የተፈረመው ስምምነት “በዘርፉ ቀጣናዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ያላቸው ምሁራንን ለማፍራት‘ የሚያስችል እንደሆነ፤ ለዚህም ሲባል “የሦስቱ አገሮችን የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ለማሳደግ በዓለም ባንክ ድጋፍ፣ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የክህሎት ሽግግር (EAS­TRIP) የተባለ ፕሮጀክት ተቀርፆ ወደ ሥራ መገባቱ‘ን፤ “በዚህ ፕሮጀክት አማካይነት ሦስቱ አገሮች የተስማሙበት ወጥ የሆነ የጋራ የምዘና ሥርዓት ሲሠራ“ መቆየቱን፤ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰግድ ጌታቸው “ስምምነቱ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያላቸው ሙያተኞችን ለማፍራት የሚያስችል ነው።

ከዚህ በፊት በአንዳንድ የቴክኒክና ሙያ ዘርፎች ምዘናና ዕውቅና ለማግኘት መምህራኖቻችንን ጭምር ውጭ አገሮች ለመላክ እንገደድ ነበር፣ ይህ ፕሮጀክት ይህንን ያስቀርልናል። ኢትዮጵያ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ “ቀጣናዊ የምዘና መስጫ ማዕከል‘ ትሆናለች፤ “ዓለም አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ምዘና መስጫ ማዕከል በኢትዮጵያ ለመገንባትም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጥረት እያደረገ‘ ነው ማለታቸውን ወዘተ ስንመለከት ዘርፉ አህጉራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ትኩረትንም ስለ ማግኘቱ ግንዛቤ ይኖረን ዘንድ ያስችለናል።

የፕሮጀክቱ አስተባባሪና የኢትዮጵያ ጥናት ቡድን መሪ የነበሩት ገነነ አበበ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሦስቱ አገሮች የተፈረመው ስምምነት በኢትዮጵያ የሚሰጡ ደረጃዎችን ቁጥር እንደሚያሳድግ “ኢትዮጵያ እስካሁን በቴክኒክና ሙያ እስከ ደረጃ ስምንት ብቻ ነው ሥልጠና የምትሰጠው፡፡ ስምምነቱ እስከ 10 እና 11 ደረጃዎች ከሚሰጡ አገሮች ጋር በመደረጉ፣ ይህን ለማሳደግ ያግዘናል። ዜጎች በተለያየ የዓለም አገሮች ተንቀሳቅሶ የመማር ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳድሮ የመሥራት ዕድል‘ ያገኛሉ በማለት ገልፀው የነበረ መሆኑን ስንመለከት የዘርፉን ግዝፈት ከማሳየት በተጨማሪ፣ ዘንድሮ ወደ ተቋማቱ የሚገቡትን 600ሺህ ሰልጣኞች ጨምሮ፣ ወጣቶች ከፊት ለፊታቸው የሚጠብቃቸውን እድል ከወዲሁ እንዲያዩት ያግዛል።

ወደ ክልሎችም እንሂድና ወካይ ይሆናሉ ያልናቸውን እንመልከት። ከደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግስት ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የቀጣይ 10 ዓመት ስትራቴጂያዊ ግቦች ያሉት ሲሆን፣ እነሱም፡-

ግብ-1 የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተደራሽነትንና ፍትሀዊነትን ማረጋገጥ፤

ግብ-2 ጥራትና አግባብነት ያለው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠናን ማረጋገጥ፤

ግብ-3 የጥናትና ምርምር፣ የአገር በቀል ዕውቀት አጠቃቀምና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማጠናከር፤

ግብ-4 የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ሰብዓዊ ሃብትና የተቋማትን አቅም መገንባት፤

ግብ-5 የአጋርና ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎና ትስስር ማጠናከር፤

ግብ-6 ዓለም አቀፍ ግንኙነትንና ትስስርን ማስፋፋትና ማጠናከር፤

ግብ-7 የተሟላ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት መስጠት፤

ግብ-8 የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትን የገቢ ምንጭ ማስፋትና ማሳደግ፤

ግብ-9 ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ተጠያቂነት ያለው አመራርና አደረጃጀትን፤ እንዲሁም፣ አሰራርን ማጠናከር፤

ግብ-10 የትምህርትና ስልጠና ፋይናንስና ወጭ አሸፋፈን ስርዓት ማጠናከር፤

ግብ-11 ሁለንተናዊ እድገቱ የተረጋገጠ፣ ስልጠናውን በአግባቡ አጠናቃቂ ኃይል ማውጣት፤

ግብ-12 በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና አገልግሎትን ማስፋፋትና ማጠናከር፤ ናቸው።

ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እንሂድ።

በዚሁ በያዝነው ወር፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ማኔጅመንት አባላት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በአርባ ምንጭ ከተማ ውይይት አካሂደው ነበር። በውይይቱም፣ የመስክ ሪፖርት፣ የ2016 ዕቅድ እና የመሳሰሉት ዙሪያ የተነጋገሩ ሲሆን፣ የክልሉ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት ደምሴ ቴክኒክና ሙያ ሀገራችን የምታደርገውን የብልፅግና ጉዞ የሚያሳካ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። ወደ አዲስ አበባ እንመለስ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ

የአዲስ አበባ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ከ6ሺህ በላይ ሰልጣኞችን ባስመረቀበት ወቅት “የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የቴክኖሎጂ ሽግግር ፈጠራ ማዕከላት እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት ሲሰራ“ መቆየቱን በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ የተገኙት የከተማው ከንቲባ አዳነች አቤቤ መናገራቸው፤ የከተማ አስተዳደሩ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ለኢኮኖሚው ዘርፍ የሚኖራቸውን ሚና በመገንዘብ በውጤት ላይ የተመሰረተ ስልጠና እንዲሰጥና ማሰልጠኛ ተቋማቱም የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ማጎልበቻ እንዲሆኑ ለማድረግ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን መግለፃቸው ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ብቻ ሳይሆን የሚያመለክተው፣ ከተቋማቱ የሚወጡ ባለሙያዎች ለአገር እድገትና ብልፅግና የሚኖራቸው የማይተካ ድርሻ ጭምር ነው።

በመዲናዋ ከየካቲት 27 እስከ መጋቢት 1/2011 ዓ.ም፣ የተዘጋጀው “9ኛው ከተማ ዓቀፍ የቴክኒክና ሙያ የንቅናቄ ሳምንት‘ ፕሮግራም “ለኢንዱስትሪ ዕድገታችን ቴክኒክና ሙያ የመጀመሪያ ምርጫችን!” በሚል መሪ ቃል መከበሩ የሚናገረው የራሱ ታሪክ አለውና ዘርፉን ለማጠናከር ሁሉም እየተረባረበ ይገኛል ማለት ይቻላል።

የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ረቡዕ የካቲት 22፤ 2015 በዋና መስሪያ ቤቱ ሰጥቶት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 20፤ 2015 ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ያጸደቀው አዲሱ “የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲ” የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማቱ የሚሰጡትን የስልጠና ደረጃ በሶስት አሳድጎታል። አዲስ የተጨመሩት ሶስት ደረጃዎች፤ በመደበኛው የትምህርት ስርዓት ውስጥ “የመጀመሪያ፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ” የሚል ስያሜ ያላቸው ደረጃዎች አቻ እንደ ሆኑ ተገልፇል። የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና የሚወስዱ ተማሪዎች በእነዚህ ደረጃዎች እንዲሰለጥኑ መደረጉ፤ ተቋማቱ “ያልተሳካላቸው ሰዎች ማረፊያ ናቸው” የሚለውን አስተሳሰብ የሚቀይር መሆኑም ተነግሯል። የአዲሶቹ ደረጃዎች መጨመር “ዘርፉን ተወዳዳሪ፣ ተፈላጊ በማድረግ ረገድ ትልቅ ትርጉም የሚኖረው መሆኑም እንደዛው።

በመስከረም 2011 ዓመተ ምህረት “የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ስራ በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆን ከተፈለገ መጀመሪያ አመራሩ ለተልዕኮ ብቁ መሆን አለበት፡፡‘ የሚለውን ታሳቢ በማድረግ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ለተወጣጡ ከ600 በላይ አመራሮች ስልጠና መሰጠቱ ይታወሳል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ህዳር 3/2016

Recommended For You