አንድ ሰው ሙሉ ጤነኛ ነው እንድንል የሚያደርገን በየዕለቱ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በአግባቡ መከወን ሲችል ነው:: በስራ ቦታችን፣ በግልም ሆነ በማሕበራዊ ሕይወታችን በኛ መስፈርት ስኬታማ የምንለውን ቀን ለማሳለፍ እና ውጤታማ ለመሆን ደግሞ ከአካላዊ ጤናችን ባሻገር የአዕምሮ ጤና ያለው ድርሻ በቀላሉ የሚተው ጉዳይ አይደለም::
በመሆኑም ይህ ሕይወታችንን ለመምራት ቁልፍ የሆነው የአዕምሮ ጤና መጠበቅ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይም አይደለም:: የዓለም የጤና ድርጅት እ.አ.አ በ2022 ባወጣው ሪፖርት እንዳስቀመጠው በቢሊዮን የሚቆጠሩ የዓለማችን ሕዝቦች መታከም ከሚችል የአዕምሮ ጤና እክል ጋር ይኖራሉ:: እነዚህ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ደግሞ አገልግሎቱን በቅርብ ባለማግኘት፣ አገልግሎቱ ቢኖርም በአቅም ማነስ ምክንያት እና በማህበረሰብ ውስጥ ስለ አዕምሮ ጤንነት ባለው የተሳሳተ ግንዛቤ ምክንያት የሚደርስባቸውን መገለል በመፍራት እርዳታን ሳይጠይቁ ለከፋ የአዕምሮ ሕመም ይጋለጣሉ፤ ባስ ሲልም ራሳቸውን እስከ ማጥፋት ይደርሳሉ::
የዓለም የጤና ድርጅትም የአዕምሮ ጤናን የተመለከቱ አመለካከቶቻችን በማስተካከልና በማሳደግ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው እንዲሁ እውቅና መስጠት እና መደገፍ ያስፈልጋል ሲል በሪፖርቱ አስቀምጧል:: ይህንንም ለማድረግ እንዲቻል በአዕምሮ ጤናችን ላይ ተፅዕኖ ያላቸውን አካባቢዎች በመለወጥና ማህበረሰብ አቀፍ የአዕምሮ ጤና አገልግሎቶችን በማዳበር ለአዕምሮ ጤና ሁለንተናዊ ሽፋን ማግኘት እንደሚቻል ተጠቅሷል::
የአዕምሮ ጤና ዋጋ የሚሰጥበት፣ የሚጠበቅበትና የማይደበቅበት ሁኔታ መፍጠር ከተቻለ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ መብቱን መተግበር እና ተመጣጣኝ ጥራት ያለው የአዕምሮ ጤና ሕክምናን ማግኘት ከቻለ፣ በማሕረሰቡ ውስጥ ያለምንም አድሎና መገለል የፀዳ ማሕበራዊ ኃላፊነት ላይ መሳተፍ ይችላል::
የጨቅላነት፣ የሕጻንነት እና የወጣትነት እድሜ ለአዕምሮ ጤና መጠበቅም ሆነ ለአዕምሮ ጤና መታወክ ተጋላጭ የምንሆንበት ጊዜ እንደሆነ ይነሳል:: በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚኖረን የአኗኗር ዘይቤ በቀጣይ ለሚኖረን የአዕምሮ ጤና ትልቅ ድርሻ አለው:: ለአዕምሮ ጤና እክል ብዙ መነሻዎች ሲኖሩ በዛው ልክ ብዙ አይነት የአዕምሮ ሕመሞች አሉ:: በአሁን ሰዓት በሀገራችንም ሆነ በዓለማችን ብዙውን የማህበረሰብ ክፍል በተለይ ደግሞ ወጣቶችን እያጠቃ የሚገኘው የድብርትና የጭንቀት የአዕምሮ ሕመም ይነሳል:: እነዚህ የአዕምሮ ሕመሞች ተለምዶኣዊ የአዕምሮ ህመሞች (common mental disorder) ከሚባሉት ውስጥ የሚጠቀሱ ሲሆን መነሻቸው ምልክቶቹ ምን ይመስላሉ እንዴትስ መከላከል ይቻላል ስለሚሉት ሀሳቦች በየካ ኮተቤ የአእምሮ ጤና ሕክምና ማዕከል የአእምሮ ጤና ስፔሻሊስት ከሆኑት ዶክተር ዳዊት አሰፋ ጋር ቆይታ አድርገናል::
ዶክተር ዳዊት ለረጅም ዓመታት በአዕምሮ ሕክምና ስራ ውስጥ ያሳለፉ ናቸው:: በተለያዩ የጃላፊነት ደረጃዎች ላይ አገልግለዋል:: ዶክተር ዳዊት በቅርቡ በአዕምሮ ሕክምና ዙሪያ የሚያጠነጥን እና ለሌላው የማሕበረሰብ ክፍል ስለ አዕምሮ ጤና እውቀት ሊሰጥ የሚችል ‹‹ የሁሉ ›› የተሰኘ የመጀመሪያ የልቦለድ መፅሃፋቸውን ለአንባቢያን አድርሰዋል::
ሰዎች በአንድም በሌላም መንገድ የአእምሮ መታወክ ሲገጠማቸው በማህበረሰባችን እነዚህን ችግሮች የሚታይባቸው ሰዎች ሲኖሩ እሱ ወይም እሷ እኮ የአዕምሮ ችግር አለበት ከማለት የዘለለ እርዳታ ስናደርግ አይስተዋልም::
ለመሆኑ የአእምሮ ሕመም ምንድነው ለሚለው ጥያቄ ዶክተር ዳዊት ሲመልሱ የአዕምሮ ህመም ማለት የአዕምሮ ስራዎች መታወክ ነው ሲሉ ይገልጻሉ:: ሁሉም የሰውነት ክፍላችን የሚሰራው ስራ እንዳለ ሁሉ የአዕምሮ መሰረታዊ ስራዎች የምንላቸው ሀሳብ፣ ስሜት፣ ተግባርና ባህሪ የምንላቸው ናቸው:: ከነዚህ ተግባራት ውስጥ በአንዳቸው በሀሳብ፣ በስሜትና በባህሪ ላይ ለውጥ ሲመጣና ይህ ለውጥ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ በዕለት ተዕለት ህይወታችን፣ በስራችን በቤተሰብ፣ በትምህርትና ባለን ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ችግር መፍጠር ሲጀምር ግለሰቡ አስቀድሞ የነበረው ውጤታማነት ላይ ጥያቄ ሲፈጠር እርዳታ የሚሻ የአዕምሮ መታወክ ችግር ገጥሞታል ልንል እንችላለን::
እንደ ዶክተሩ ገለጻ በአሁን ሰዓት ከ360 በላይ የታወቁ የአእምሮ ህመም አይነቶች ሲኖሩ ሁሉም የራሳቸው ምልክቶችና ተጽዕኖዎች አሏቸው ይላሉ:: የአእምሮ ህመም በራሱ እድሜን ጾታን የማይለይ ቢሆንም በእድሜ ልዩነት ምክንያት የሚከሰቱ የአእምሮ ህመሞች አሉ:: ለምሳሌ የመቅበጥበጥ ረግቶ ያለመቀመጥ ችግር ወይም በህክምና ቋንቋ (ADHD)፤ የአእምሮ እድገት ውስንነት በህፃናት ላይ የሚስተዋል ሲሆን፤ ጭንቀት እና ድብርት በህጻናትና ወጣቶች ላይ የሚከሰቱ የአእምሮ ህመሞች ናቸው:: በብዛት ደግሞ በእድሜ በገፉት ሰዎች ላይ የመርሳት የአእምሮ ህመም ሊያጋጥም ይችላል:: የአእምሮ ህመምን በጾታ ምጣኔ ካስተዋልነው የወንድ የአእምሮ ህሙማንና የሴት የአእምሮ ህሙማን የቁጥር ምጣኔ ተመጣጣኝ የሚባል ነው::
የዓለም የጤና ድርጅት የ2022 ሪፖርት እንደሚያሳየው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በብዙዎች ላይ የሚታየው የአዕምሮ ህመም ችግር ከቀላል እስከ ከባድ የሆነ የድብርት እና የጭንቀት ችግር በተለይም ወጣቶች ላይ በስፋት እየታየ የመጣ የህመም አይነት ነው:: ድብርት እና ጭንቀት የሚሉት ቃላት ለሰው ልጅ አዲስ አይደሉም የሚሉት ዶክተሩ በየቀኑ ህይወታችንን ስንመራ የምንጋፈጣቸው እና እንደየጉዳዩ ክብደትና ቅለት እየፈታናቸው የምንሄዳቸው ናቸው:: ነገር ግን እነዚህ ባህሪያት ድብርት አልያም ጭንቀት መጠናቸው ከፍ ብሎ ከቀናት ያለፈ ሲሆንና ህይወታችንን ለመምራት ስንቸገር ወደ ህመም ተቀይሯል እንላለን::
ምልክቱ እንቅልፍ ማጣት ወይንም የበዛ እንቅልፍ፣ ሀዘን፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ከሰዎች ጋር ለመቅረብ አለመፈለግ፣ በዙሪያችን ያሉ የምንወዳቸውን ሰዎች ጭምር ማውራት አለመፈለግ ስራ ለመስራትም ሆነ ደስተኛ ለመሆን አለመፈለግ የድብርትና ጭንቀት ተጠቂ የሆኑ ሰዎች የሚታዩባቸው ምልክቶች ናቸው::
እነዚህ የጠቀሱት ምልክቶች በተጨማሪም ተጠቂዎቹ ለምን እንደበራቸው ምክንያቱን አለማወቅ እና ስሜታቸውን ለመግለፅም ይቸገራሉ:: ዶክተሩ እንደሚያብራሩት ህጻናት እና ወጣቶችን ለድብርትም ሆነ ለጭንቀት ተጋላጭ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች መካከል በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች፣ የማህበረሰብ ቀውሶች እና የድህረ አደጋ መታወክ ለህመሞቹ ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል::
ህጻናት በአስተዳደጋቸው ወቅት በቤተሰብ ወይም በአሳዳጊዎቻቸው የውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች፣ በልጅነታቸው ትኩረት አግኝቶ አለማደግ ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ስለመሆናቸውም ዶክተሩ አክለዋል:: ከዚህም ባሻገር ለሱስ ተጋላጭ መሆን ለድብርት እና ለጭንቀት ህመሞች ሊያጋልጣቸው ይችላል::
ሱስ በራሱ እንደ አንድ የአዕምሮ ህመም የሚጠቀስ ሲሆን ከተጠቃሚው ቁጥጥር ውጪ ሲሆን ማቆም እየፈለጉ ነገር ግን ለመተው ሲቸገሩ በማህበራዊ እንቅስቃሴያቸው፣ በስራቸው ያላቸውን አቅም እንዳይጠቀሙ እና ከሰዎች ጋር የሚኖራቸው መስተጋብር ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ከሆነ እንደ ህመም ይቆጠራል::
በማንኛውም ሱስ ውስጥ ያሉ ሰዎች ለማቆም ሲቸገሩ የበታችነት ስሜት፣ በቂ ያለመሆንና በሰዎች ያለመፈለግ ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል:: በሱስ ውስጥ መዘፈቅ ተፅዕኖው በአካልም በአዕምሮ ላይም ይታያል:: ከዚህም በተጨማሪ በተለምዶ ሱስ ሲባል ከአደንዛዥ እፅ ጋር የተያያዘ ተደርጎ ይወሰድ እንጂ ነገር ግን የባህሪ ሱስ እና ሌሎች የሱስ አይነቶች ሲኖሩ ባለንበት ዘመን ወጣቶች ከስልካቸው ጋር የሚያሳልፉትን ጊዜ መቆጣጠር ባለመቻላቸው ረጅም ሰዓት በማህበራዊ ድህረ-ገጽ ላይ በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ:: ይህም በህይወታቸው ላይ በባህሪያቸው ላይ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ላይ የራሱ ተፅዕኖ እያሳደረ ስለመሆኑ ዶክተር ዳዊት አንስተዋል::
ሌላኛው ወጣቶች በድብርትም ሆነ በጭንቀት እንዲጠቁ የሚያደርጋቸው ራሳቸውን የወደፊት ህይወታቸውንም ሆነ ማንነታቸውን ገና የሚገነቡበት ወቅት ላይ የሚገጥማቸው አለመሳካት፤ በስሜት
አለመጠንከር፤ ደስታ የማጣት ስሜትን እንዲፈጥርባቸው ያደርጋል:: ከዚህም ባሻገር በዚህ ወቅትም የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲሰማቸው ሲያደርግ በብዛትን ወደግላዊነት፣ ብቸኝነት እንዲያመሩ ያደርጋቸዋል::
በነዚህ የአዕምሮ እክሎች እየተባባሱ ሲሄዱ በነዚህ ህመም እየተጠቁ የሚቆዩ ወጣቶች እና ህጻናት ራሳቸውን ወደማጥፋት እንዲያመሩ ሊያደርጋቸው ይችላል:: ከዚሁ ጋር ተያይዞም በአሁን ሰዓት ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል:: በዚህ ሂደትም በብዛት ተጠቂ የሚሆኑት ደግሞ ወጣቶች ናቸው::
እነዚህን የተጠቀሱትን የአዕምሮ ህመሞች አሸንፎ ለመውጣትና ነፃ ለመሆን ዶክተር ዳዊት የአዕምሮ ህመምን ለመታደግ ከሚረዱ መንገዶች ውስጥ አንዱ የቅድመ መከላከል ሂደት ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነ ይናገራሉ:: ስለ አዕምሮ ጤና እና ህመም ግንዛቤው ከፍ ማድረግ በማህበረሰባችን ውስጥ ስለ አዕምሮ ህመምም ሆነ ህክምና የተሳሳተ ግንዛቤ መኖሩን አስታውሰው በማህበረሰብ ውስጥ ስለ አዕምሮ ጤና ትክክለኛ ግንዛቤ መፍጠርና የተለመዱና የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን ማጥራት ይገባል::
በዙሪያችን ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶችን የምናስተውልባቸው ወጣቶች ሲኖሩ ቀርቦ ሀሳባቸውን ለመጋራት መሞከርና እርስ በርስ የሀሳብ መለዋወጥን መለማድ ያስፈልጋል:: ምክንያቱ ደግሞ ለአንዳንድ ሰዎች የከበደው ሀሳብ ለሌሎች ሰዎች አይን መፍትሄ ሊኖረው ይችላል:: የአዕምሮ ጤና በግል ብቻ ሳይሆን የማህበረሰብ ትብብር አስተዋጽኦ የሚጠይቅ በመሆኑ ወደ አቅራቢያቸው ባለ የስነ-ልቦና ባለሙያዎች እንዲሄዱ ማድረግ ይጠበቃል::
ከዚህም ባሻገር እነዚህን ስሜቶች እያስተናገዱ የሚገኙ ወጣቶች ለመዳን ሲያስቡ አስቀድመው ስሜቶቻቸውን ከመረዳትና ያለባቸውን ችግር ከማመን መጀመር ይገባቸዋል:: ከዚያም በቅርባቸው የሚገኙ ሰዎችን ማማከር ሀሳባቸውን ለሌሎች ሰዎች ማካፈል እና እርዳታ ለመጠየቅ መፍራት የለባቸውም:: በድብርትም ሆነ በጭንቀት ህመም ውስጥ መግባታቸውን ማመናቸው የመፍትሄው አንድ አካል በመሆኑ በቀጣይ የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመጋፈጥ ዝግጁ መሆን ይገባቸዋል::
የአዕምሮ ጤና ተከታታይ የሆነ ክትትልን እና ትዕግስትን የሚፈልግ በመሆኑ የህክምና ሂደቱ ላይ ወጣቶች ታጋሽ መሆን ይጠበቅባቸዋል:: በመጨረሻም ዶክተሩ በሀገራችን በአሁን ሰዓት ያለው ከአዕምሮ ጤና ጋር የተያያዙ ህክምናዎች ካለፈው ጊዜ በበለጠ አሁን የተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል:: በዙሪያችን ያሉ የቅርባችን ሰዎች ላይ የምናያቸውን ምልክቶች በቀላሉ አለማለፍ፣ ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ በአቅራቢያቸው ወዳለ የስነ-ልቦና ባለሙያ መሄድ ይገባቸዋል::
ሰሚራ በርሀ እና መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2016