ሀገራዊ የጋራ ትርክት-ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ወሳኝ ነው!

 የተዛቡ/ከፋፋይ ትርክቶች እንደ ሀገር ላለፉት ስድስት አስርተ ዓመታት ብዙ ዋጋ እስከፍለውናል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለስደት፤ በሺዎች የሚቆጠሩትን ለሞትና ለአካል ጉዳተኝነት፤ ሀገርንም እንደ ሀገር ከፍ ላለ አለመረጋጋትና የሰላም እጦት ዳርገውናል።

ትርክት የሚነገሩ የመረጃዎች፣ የእውነታዎች፣ የታሪኮች፣ የአፈ ታሪኮች እና የክስተቶች ድምር ውጤት፤ የእውቀት እና የስሜት አቅምን የሚገነባ የመረጃዎች ፍሰት ኃይል ነው፡፡ ይህንን ኃይል በአሉታዊም ሆነ አዎንታዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም ተጠቃሚም፤ ተጎጅም መሆን ይቻላል።

በተለይም እንደኛ ባሉ የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ ላላቸው፤ የብዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ ለሆኑ ሀገራት ሕዝቦች ቀጣይ አብሮነት እያንዳንዷ ትርክት ከፍ ባለ ጥንቃቄ መመርመር፤ ለሀገር ሕልውና ለሕዝቦች አብሮ መኖር ያለውን ፋይዳ በአግባቡ ማጤን ያስፈልጋል።

ለዚህም በዋነኛነት የትርክቶችን ትክክለኝነት መመርመር፤ ከአሁነኛ ተጨባጭ እውነታ ጋር ማስተሳሰር፤ ከሁሉም በላይ ሀገራዊ የጋራ (አሰባሳቢ) ትርክትን መፍጠር የሚችሉበትን አቅም ማጎልበት ወሳኝ ነው። ለዚህ ደግሞ የመንግሥት፣ የምሑራን እና የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ከፍያለ ነው።

ሀገራዊ የጋራ ትርክት የመፍጠሩ እውነታ እንደ ሀገር ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር፣ ቅቡልነት ያለው ዴሞክራሲ ለመገንባት፣ በሕዝቦች መካከል ዘላቂ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለመፍጠር፣ የዜጎችን ክብርና ደህንነት ለማስጠበቅ፣ የሕግ የበላይነትና ፍትሕን ለማረጋገጥ፣ የሀገርን ልማት እና ዕድገት ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው፡፡

በርግጥ ከዚህ ቀደም ሲነገሩ የቆዩ ከፋፋይ ትርክቶች እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ አስከፍለውል። የግጭትና የመበተን አደጋ ውስጥ ከተውናል። ችግሩ በብዙ መስዋዕትነት ተጠብቃ የቆየችውን ሀገራችንን ሊያሳጣን እንደሚችል ለመገመትም የሚከብድ አይደለም፡፡

ይህንን እንደ ሀገር ከፊታችን የተደቀነውን ስጋት በማስወገድ ሀገራዊ አንድነትን አጠናክሮ ለማስቀጠል አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን ማቀራረብ እና ለጸብ መንስኤ የሚሆኑ ሃሳቦችን በማስወገድ ዘላቂ ሰላምን የሚያጸኑ ሃሳቦች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል።

እንደ ሀገር የምንፈልገውን ብልጽግና፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማረጋገጥ የሚቻለው ሀገራዊ ትርክትን መገንባት ሲቻል መሆኑን አምኖ መቀበልንና መተግበርን ይጠይቃል፡፡

ሀገራዊ ትርክትን መገንባት ሲቻል የነገሮችን ትስስርና አመጣጥ ማወቅ፣ ለሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ማስቀመጥ፤ ሀገራዊ ዘላቂ ሰላም መፍጠር ከፍ ባለ ብሔራዊ መነቃቃት ልማትን በማፋጠን ወደ ብልጽግና የሚደረገውን ጉዞ ማፋጠን ይቻላል፡፡

በተለይ አሁን ላይ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉት የሽግግር ፍትሕ እና ሀገራዊ ምክክር የተያዘላቸውን ግብ እንዲያሳኩ በማድረግ የነበሩትን ቁርሾዎች አስወግዶ ሀገራዊ ትርክትንና የተሻለች ኢትዮጵያን መፍጠር የሚቻልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡

የሚያራርቅ ትርክትን አስወግዶ ሀገራዊ ትርክትን ለመገንባት ታሪክን ማወቅ፣ የሚከፋፍሉ ሃሳቦችንና ሁኔታዎችን አለመቀበል፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ስፍራ እንዳያገኙና እንዳያድጉ አምርሮ መታገል ከፖለቲካ ተዋናዮች ከምሑራንና ከማኅበረሰቡ የሚጠበቅ ትልቁ አሁነኛ የቤት ሥራ ነው።

ለሀገራዊ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ማስቀመጥ የሚቻለውም ሀገራዊ ትርክትን መገንባት ሲቻል ነው፤ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ማኅበረሰብ መነጋገር፣ መከባበር፣ መደማመጥ፣ መግባባት እና አንድ መሆን ይኖርበታል፡፡

ከዚህም ባለፈ የሚፈጠረውን ሀገራዊ ትርክት ማኅበረሰቡ እንዴት ሊቀበለው እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ፤ ትውልዱ እውነታውን ተገንዝቦ ተግባራዊ እንዲያደርገው የሚያስችሉ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ያስፈልጋል!

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You