የሀገሪቱን የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ አቅም ያሳየው የንግድ ትርኢት

ሀገራት የተለያዩ አላማዎችን ታሳቢ ያደረጉ ኤግዚቢሽንና ባዛሮችን በማካሄድ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ያገኛሉ። ኤግዚቢሽንና ባዛሮቹ በዋናነት የገበያ ትስስርን በመፍጠር፣ የልምድ ልውውጥ በማድረግና በሀገር ውስጥ ያለውን የቴክኖሎጂና የምርት አቅም ለመረዳት ያግዛሉ። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶችን ማካሄድ አበርክቶው የጎላ ነው። አምራቾች ምርቶቻቸውን ከማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ከመፍጠር ባለፈ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የልምድ ልውውጥ ማድረግ የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥራሉ።

ለዚህም በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ስካይ ላይት ሆቴል ለአራት ቀናት የተካሄደው ዘጠነኛው የአፍሪካ ሶርሲንግ እና የፋሽን ሳምንት (ASFW) ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት አንዱ ማሳያ ነው። ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ የአፍሪካ የቆዳ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳት እና ፋሽን ኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ለዕይታ የቀረቡበት የንግድ ትርዒት እና ኮንፍረንስ ነው። መድረኩ በርካታ የገበያ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት እንደሆነም ተነግሮለታል።

የንግድ ትርዒቱ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ፕሮጀክት አስተባባሪና ከትሬድ ፌርስ ግሩፕ ጋር በትብብር የተዘጋጀ ነው። ላለፉት ስምንት ጊዜያት በተካሄደበት ወቅትም መሻሻል እየታየበት የመጣ ስለመሆኑ በመድረኩ ላይ የተጠቆመ ሲሆን፣ በተለይም ለሀገር ውስጥ አምራቾች ሰፊ የገበያ ዕድል እየፈጠረ ያለና አምራቾቹ ለምርቶቻቸው አስፈላጊ ግብዓቶችን የሚያገኙበት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያደርጉበትና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት መሆኑም ተመላክቷል።

በንግድ ትርዒቱ ከተሳተፉት የሀገር ውስጥ አምራቾች መካከል የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እህት ኩባንያ የሆነው ኢትዮ ሌዘር ኢንዱስትሪ /ኤሊኮ/ አንዱ ነው። የኤሊኮ ማርኬቲንግ ማናጀር ወይዘሮ ኢትዮጵያ ታደሰ፤ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ ለገበያ ትስስርና ለቴክኖሎጂ ሽግግር እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ገልጻለች። ወይዘሮ ኢትዮጵያ እንዳለችው፤ ኢትዮ ሌዘር / ኤሊኮ/ ከ75 ዓመት በላይ የቆየ አንጋፋ ድርጅት ነው። በውስጡም ሁለት የቆዳ ፋብሪካዎች፣ ሁለት የጫማ ፋብሪካዎችና አንድ የቆዳ ውጤቶች ማለትም ጃኬት፣ ቦርሳና የመሳሰሉትን የሚያመርት ፋብሪካ ይዟል።

ድርጅቱ አጠቃላይ የቆዳ ውጤቶችን አምርቶ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ ይገኛል። ከሚያቀርባቸው ምርቶች መካከል ያለቀለት ብትን ቆዳን ጨምሮ ቦርሳ፣ ጫማና ቀበቶ ይገኙበታል። ትልቁን የገበያ ድርሻ የሚወስደው የውጭ ገበያ ሲሆን፤ በተለይም ብትን ቆዳ በስፋት ለውጭ ገበያ ያቀርባል። የኢትዮጵያ የቆዳ ምርቶች በውጭ ገበያ እጅግ ተፈላጊ ሲሆኑ፣ ድርጅቱ ምርቶቹን ከሚልክባቸው ሀገሮች መካከል የአፍሪካ ሀገራት፣ አሜሪካ፣ ጣሊያን፣ ህንድ፣ ቻይና ይጠቀሳሉ።

‹‹ከቆዳ ውጤቶች በበለጠ ብትኑ ቆዳ በውጭ ገበያ ይመርጣል›› የምትለው ማርኬቲንግ ማናጀሯ፤ ለዚህም ዋናው ምክንያት የጫማ ሶልን ጨምሮ የተለያዩ ግብዓቶች /አክሰሰሪዎች/ በሀገር ውስጥ ባለመኖራቸው እንደሆነ ነው ያመላከተችው። በዚህ የተነሳም የቆዳ ውጤቶቹን የውጭ ገበያው በሚፈልገው ጥራት ልክ ማምረት አለመቻሉን ጠቅሳ፣ በዚህ ምክንያት ሀገሮቹ ብትኑን ቆዳ ወስደው እንደፈለጉ ያመርቱበታል ብላለች።

ጫማ፣ ቦርሳ፣ ቀበቶና ሌሎች የቆዳ ውጤቶች ሰፊ ገበያ ያላቸው በሀገር ውስጥ መሆኑን ጠቅሳ፣ በዓለም ገበያ ተወዳድሮ ለመግባት ቴክኖሎጂውን መጠቀምና የተለያዩ የምርት ማጠናቀቂያ ግብዓቶችን ማግኘት የግድ መሆኑን ጠቁማለች። ለዚህም እንዲህ ዓይነት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች እንደሚጠቅሙ ነው የገለጸችው። በንግድ ትርዒቱ ላይ የገበያ ትስስር ከመፍጠር ባለፈ ከአክሰሰሪ አስመጪ ኩባንያዎች ጋር የመተዋወቅና የልምድ ልውውጥ የማድረግ ዕድል እንዳለና ይህም ለሀገር ውስጥ ምርቶች በእጅጉ እንደሚጠቅም ተናግራለች።

በከበሩ ማዕድናት የተለያዩ ጌጣጌጦችን አምርቶ ለገበያ የሚያቀርበው ሎላይስ ጀምስቶን ሌላው በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ የተሳተፈ ድርጅት ነው። ድርጅቱ እነዚህን ምርቶቹን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ የድርጅቱ የማርኬቲንግ ባለሙያ ወጣት ኪያ ሞሲሳ ትናገራለች። የአንገት ጌጥ፣ የጆሮ ጌጥ፣ ብራስሌት፣ የአንገት ሃብልና የተለያዩ ቀለበቶችን ከከበሩ ድንጋዮች አምርቶ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ያቀርባል ስትል ታብራራለች።

እሷ እንደምትለው፤ የከበሩ ማዕድናቱ ከሀገር ውስጥ የሚያገኙ ሲሆን፤ ድርጅቱ በተለይም ከወሎ፣ ከደላንታና ከአክሱም ከሚያመጡ አቅራቢዎች ያገኛል። ድርጅቱ ሁሉንም ዓይነት የከበሩ ድንጋዮችን ይጠቀማል፤ በተለይ ኦፓል የተባለውን የከበረ ድንጋይ በስፋት የሚጠቀም ሲሆን፣ የዚህ የከበረ ድንጋይ ምርቶች ሰፊ ገበያ አላቸው። ምርቶቹ በአብዛኛው ለውጭ ገበያ ይቀርባሉ፤ በአውሮፓና አሜሪካ ሰፊ ገበያ እንዳለው ወጣት ኪያ ገልጻ፤ አሁን አሁን የከበሩ ማዕድናት ከውጭ ገበያ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ ገበያም እየተለመደ መምጣታቸውን አመልክታለች።

ማህበረሰቡ ቀደም ሲል ለማዕድን ብዙም ትኩረት ይሰጥ እንዳልነበር ያስታወሰችው ኪያ፤ መንግሥት ለማዕድን ዘርፉ በሰጠው ትኩረት በተለይም ማዕድን ሚኒስቴር በሚያዘጋጃቸው ኤግዚቢሽንና ባዛሮች አማካኝነት ሰዎች ለማዕድን ትኩረት መስጠት መጀመራቸውን ገልጻለች። አሁን አሁን ኢትዮጵያውያንም ጭምር ከከበሩ ድንጋዮች የሚሰሩ ጌጣጌጦችን ገዝተው መጠቀም መጀመራቸውን ተናግራለች።

ከከበሩ ድንጋዮች የሚዘጋጁት ጌጣጌጦች ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ የሀገር ውስጥ ሸማች በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንዲችሉ ታስቦ እንደሚሰሩም ገልጻለች። በተለይም የሀገር ውስጥ ሸማቾች በውጭ ሀገር ብልጭልጭ ሳይታለሉ በሀገራቸው ምርት እንዲኮሩና በሀገራቸው ውድና ብርቅ በሆኑ ማዕድናት ማጌጥና መዋብ እንዳለባቸው ነው ያመላከተችው።

ወጣት ኪያ እንዳለችው፤ ሀገሪቷ በማዕድን ሀብት እምቅ አቅም ያላት በመሆኑ መሰል ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶችን ሰፋ ባለ መንገድ ማቅረብ ቢቻል ይበልጥ ምርቶችን መሸጥና ማስተዋወቅ ይቻላል። በተለይም የገበያ ትስስር የመፍጠርና ተመሳሳይ ምርት ከሚያመርቱ አምራቾች ደግሞ የዲዛይንና የተለያዩ የልምድ ልውውጦችን ማድረግ ይቻላል። ከዚህ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በርካታ ጠቀሜታዎች እንደሚገኝ ጠቅሳ፣ ለዘርፉ ዕድገትም ወሳኝ መሆኑን ጠቁማለች።

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ጎሹ ነጋሽ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ ኢትዮጵያ ውስጥ መካሄድ ከጀመረ ስምንት ዓመታትን ማስቆጠሩን ጠቅሰው፣ በየዓመቱ መሻሻሎች እየታዩበት መሆኑንና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉትም ተናግረዋል።

ሀገሪቱ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ እንዲሁም በፋሽን ያለችበትን ደረጃ እና በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ማሳየት እንደሚያስችል አስታውቀዋል። የሀገር ውስጥ አምራቾች ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚያስችላቸው ተናግረው፣ ከግብዓት አቅራቢዎች ጋር በሚፈጥሩት ግንኙነትም የተለያዩ /የማጠናቀቂያ ግብዓቶችን/ አክሰሰሪዎችን የሚያገኙበትን አጋጣሚ እንደሚፈጥርም አመልክተዋል። ይህም አጠቃላይ በሀገሪቱ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚያጠናክረውም ነው ያስታወቁት።

ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱም አፍሪካ ውስጥ አሉ ከሚባሉ አውደ ርዕዮች መካከል አንዱ እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ አመላክተዋል። ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ዜጎች በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ እንደሚሳተፉ ጠቅሰው፣ በአብዛኛው ግን የአፍሪካ ሀገሮች እንደሚገኙበት ገልጸዋል። ከ24 የተለያዩ ሀገራት የተውጣጡና ከ300 የሚበልጡ ላኪዎች ይሳተፉበታል። ዝግጅቱም የተለያዩ ምርቶችንና ፈጠራዎችን 6000 ለሚሆኑ የንግድና የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ አቅራቢ ባለሙያዎች እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ታዳሚዎች የሚቀርቡበትና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ነው።

አውደ ርዕዩ ኢትዮጵያን የጨርቃ ጨርቅ መዳረሻ / ሃብ/ እናደርጋታለን የሚል ተልዕኮ ተይዞ ከዓመታት በፊት መጀመሩን አስታውቀው፣ ዓለም አቀፍ ስጋት በነበረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አማካኝነት እንዲሁም ሀገሪቱ በገጠማት የሰላምና ጸጥታ ችግሮች በሚፈለገው ልክ መጓዝ እንዳልቻለ አመልክተዋል። እንዲያም ሆኖ ግን አሁን ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ እንዳለም ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል። አሁን ላይ በተዘጋጀው ላይ 20 የሚደርሱ ሀገር በቀል አምራቾች እንደሚሳተፉበት የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ከኤዥያ፣ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካና ከአፍሪካ የመጡት ተሳታፊዎች ሀገሪቷ በጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ያላትን አቅም ማየትና መረዳት የሚችሉበት ዕድል እንደሚፈጠር አመላክተዋል።

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፤ በርካታ ያደጉ ሀገራት የኢኮኖሚ መሠረታቸውን በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ላይ አድርገው ነው ማደግ የቻሉት። በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ካደጉ ሀገራት መካከልም እንደ ኮሪያ፣ ባንግላዲሽ፣ ቬትናምና ይገኙበታል። እነዚህ ሀገራት በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ በሀገራቸው ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛና መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት የቻሉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ከእነዚህ ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፉ ሙሉ አቅሟን አሟጣ በመጠቀም ውጤት ማምጣት ትችላለች። ለዚህም መሰል ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ወሳኝ ናቸው።

በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ የሀገር ውስጥ አምራቾች ምርቶቻቸውን ሲያስተዋውቁና ከውጭ የሚመጡት የተለያዩ ቴክኖሎጂና ግብዓት አቅራቢዎችም እንዲሁ ምርቶቻቸውን ሲያሳዩ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በብርቱ እንደሚነቃቃ ገልጸው፤ ለዚህም ማህበሩ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል። በተለይም ተኪ ምርቶች ላይ በስፋት እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል። ለአብነትም የመከላከያና የጸጥታ አካላት ዩኒፎርሞች በሀገር ውስጥ መመረት እንዲችሉ ማድረግ በራሱ አንድ ጅምር መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል። ለዚህም ማህበሩ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ መክፈቻ ላይ ተገኝተው የንግድ ትርዒቱን ያስጀመሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፤ መንግሥት በልማታዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንግሥት የረጅም ጊዜ ራዕይ ኢትዮጵያን በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ማድረግና መካከለኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ መገንባት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም የጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ኢንዱስትሪዎች እሴት መጨመር፣ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት፣ የሥራ እድል መፍጠር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል። ኢትዮጵያን የጨርቃ ጨርቅና ፋሽን መናኸሪያ እንድትሆን ከሚያደርጉት ጉዳዮች መካከል የሀገር ውስጥ ገበያ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተደራሽነት መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ እና በአጎራባች አፍሪካ ሀገራት ፋሽንን የሚያውቅ ሕዝብ ጥራት ያለው የአልባሳትና የጨርቃ ጨርቅ ፍላጎት እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና እየሰፋ መምጣቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ምርቶች ፍላጎት የበለጠ እያደገ እንደሚሄድ አስታውቀዋል። በተለይም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢትዮጵያን የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ማዕከል ለማድረግ በተጀመሩ ሥራዎች ትልቅ የኢንዱስትሪላይዜሽን ጉዞ መጀመር መቻሏን አመላክተዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2016

Recommended For You