‹‹አፋር የኢትዮጵያ የብልፅግና ምልክት እንዲሆንበጋራ እንሠራለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

የሰው ዘር መገኛ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ዳሎል እና ኤርታሌን በመያዙ ተለይቶ የሚታወቀው ሞቃታማው የአፋር ክልል በወረሃ ጥቅምት መግቢያ፤ የሀገሪቱን መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ለመቀበል ሽርጉድ ሲሉ ከራርሟል፡፡ ጥቅምትን አጋምሰው በቀን 17 የሠመራ ሱልጣን አሊሚራህ ሃንፈሬ አየር ማረፊያን የረገጡት ጠቅላይ ሚኒስትር፤ በክልሉ ሕዝብ የሞቀ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

በአቀባበሉ የአፋር ወጣት ወንዶች የፀጉራቸው ውበት የሚያስደንቅ ሲሆን፤ ነጭ ባህላዊ ልብሳቸው እና ጭፈራቸውን አስተውሎ ለተመለከተው በልብ ውስጥ የተለየ የደስታ ስሜትን ይፈጥራል፡፡ ወጣት ሴቶችም በቀይ እና ቢጫ ሻርፕ ፀጉራቸውን ሸፋፍነው ከወገባቸው በታች አብረቅራቂ ቀሚስ አጥልቀው በእልልታ የታጀበ ባህላዊ ጭፈራ ሲያቀርቡ፤ እጅግ የሚያዝናና ነበር፡፡

የሠመራ አየር ማረፊያ ተገኝተው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሞቀ አቀባበል ያደረጉት፣ ወጣቶች እና የክልሉ ባለሥልጣናት ብቻ ሳይሆኑ፤ ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎችም ተገኝተው ነበር። የክልሉ ወጣቶች ባህላዊ ዘፈኑን አቅርበው ሲያጠናቅቁ፤ የአፋር ክልል የፖሊስ ማርሽ ባንድም ሙዚቃዎችን አቅርቧል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ‹‹እንኳን ደህና መጡ›› በሚል የቀረበላቸውን አበባ ተቀብለው፤ በቅርብ ለተገኙት ለክልሉ ባለሥልጣናት እና ለታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምታ ሰጥተው፤ ከአየር ማረፊያው ሲወጡ የክልሉን የባህል ዘፈን በማቅረብ በፈገግታ ከሸኟቸው ወጣቶች ሌላ፤ በአካባቢው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ አቀባበል አድርጎላቸዋል፡፡

ራሳቸው መኪና እያሽከረከሩ፤ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አወል አርባ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከአየር መንገድ ወደ መሃል ከተማዋ ሲገቡ የሕዝቡ አቀባበል የተለየ ነበር፡፡ በግራ እና በቀኝ የተደረደረው የከተማዋ ሕዝብ እያጨበጨበ በእልልታ ደስታውን ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተማውን አልፈው በቀጥታ ያመሩት ወደ ክልሉ የእርሻ ልማት ነበር፡፡ ፓፓያ እና ሌሎችም ፍራፍሬዎች ወደ ተተከሉባቸው እና ምርት ወደ ተሰበሰበበት አካባቢ የተጓዙ ሲሆን፤ ከተሰበሰበው ምርት በተጨማሪ በአምስት ወር ውስጥ ተተክለው ፀድቀው ለማበብ የደረሱ የፓፓያ ተክሎችንም ጎብኝተዋል፡፡ በክልሉ ያለውን የመሬት፣ የውሃ እና የሰው ሀብትን በመጠቀም አፋር ወደ ከፍተኛ አምራችነት እንዲሸጋገር ማድረግን በማሰብ የበጋ ስንዴ በይፋ የተጀመረው በዛው ክልል ነበር፡፡

የበጋ ስንዴ

ለስንዴ እርሻ በማሽኖች እየተዘጋጀ ያለውን መሬት ካዩ በኋላ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ንግግር አድርገዋል፡፡ ኢትዮጵያ እጅግ የማደግ አቅም ያላት ሃብታም ሀገር መሆኗን አስታውሰው፤ የአፋር ክልል ኢትዮጵያ ሊታረስ የሚችል መሬት፤ ያልወጣ እና ወደ ገንዘብ ያልተቀየረ ማዕድን፤ ሰፊ ጉልበት እና መማር እንዲሁም መሥራት የሚችል የሰው ኃይል አላት ለሚለው ማሳያ መሆን እንደሚችል አብራርተዋል፡፡

የአፋር ክልል እሾህ ውስጥ እንዳለ እንደ ክዋኖ ፍሬ ነው፡፡ የክዋኖ ፍሬ በእሾህ ውስጥ ያለ ፍሬ ስለሆነ፤ አግኝቶ ፈልቅቆ ለመጠቀም ያስቸግራል። ነገር ግን አንዴ እሾሁን ተጠንቅቀው ፍሬውን ካወጡ ምግብ ብቻ ሳይሆን መድኃኒትም ማግኘት ይቻላል፡፡ የክዋኖ ፍሬ ለብዙ ነገር ይጠቅማል፤ ያንን እሾህ ውስጥ ያለ ፍሬ ፈልቅቆ ለማውጣት ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ሁሉ በአፋር ምድርም እርሻን፣ ማዕድንም ሆነ ኢንደስትሪ ሲታሰብ መልከዓ ምድሩ በቀላሉ የሚታሰበውን ጣፋጭ ፍሬ ለመቅመስ የሚያስችል አይደለም፡፡ ጥረት እና ሥራ ይፈልጋል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለስንዴ እርሻ እየተዘጋጀ ያለውን የእርሻ መሬት ሲጎበኙ ባደረጉት ንግግር፤ ‹‹እንደ ሀገር የበጋ ስንዴ ዝንባሌ በጣም የሚገርም ነው፡፡ የድሮ ተትቶ የአምና እና የዘንድሮ በሀገር ደረጃ ሲወዳደር፤ የዘንድሮ ሶስት ሚሊየን ሄክታር ነበር፤ ከአምናው በ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር ይበልጣል። ይህ ከእጥፍ በላይ ነው፡፡ በምርትም ደረጃ አምና የሰበሰብነው በጋ ላይ 47 ሚሊየን ኩንታል ገደማ ነበር፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በበጋ ብቻ 100 ሚሊየን ኩንታል ይጠበቃል፡፡ የበጋ እና የክረምት ምርታችን ከስድስት ሚሊየን ሄክታር በላይ አልፏል። ይህ በጣም ተጨባጭ ትልቅ እድገት ነው፡፡›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ ዝናቡ እና የክረምት እርሻው ጥሩ እንደነበር አስታውሰው፤ በስፋት ሁለት ሚሊየን ሄክታር የተጨመረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ምርቱ በጣም ጥሩ መሆኑን እና አሁን በአብዛኛው እየተሰበሰበ እንደሚገኝም ነው የገለፁት፡፡ አሁንም በእዚህ መቆም አይገባም፤ በአግባቡ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡ የክረምቱ ተሳክቶ ሲጠናቀቅ ቶሎ የበጋ ስንዴ ካልተጀመረ እና በክረምት ስንዴ ተዝናንቶ ወደኋላ ማለት ወይም ማቆም ከመጣ ውጤቱ ቀጣይነት እንደማይኖረው አመላክተዋል።

ሶስት ሚሊየን ሄክታር ማልማት በጣም ሰፊ ነው፤ ይህ ቢሆንም በሀገር ደረጃ ሲደማመር የታሰበውን ማግኘት ይቻላል፡፡ አፋር እና ሌሎችም ክልሎች ላይ በጣም ምርጥ አፈር አለ፤ ውሃ አለ፡፡ ይህን አቀናጅቶ በመጀመር ወደ ውጭ መላክ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ነገር ማዋል ይችላል፡፡ ምክንያቱም አሁን የሚመረተው ድሮ ከሚመረተው በጣም በብዙ እጥፍ የበለጠ ነው። ይህን ለማድረግ ሁሉም ቦታ ላይ ያለውን ሀብት ማየት፣ ፈልቅቆ ማውጣት እና መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ አሁን ስላለው ለውጥ ብዙ በትክክል የማይገነዘብ ሰው አለ፡፡ ለብዙ ጊዜ አጋር ተብለው የተከለሉት አፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል እና ሶማሌ የተገለሉት በፖለቲካ ብቻ አልነበረም። ማዳበሪያም አይሰጣቸውም ነበር፡፡ የተገለሉት ፖለቲከኞቹ ብቻ ሳይሆኑ አርሶ አደሮቹም የተከለሉ ነበሩ። ማዳበሪያ የሚሰጣቸው ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች እንጂ ሌሎቹ አያገኙም ነበር፡፡ መንግሥት ማዳበሪያ የተወሰነ በሚሊየን የሚቆጠር ድጎማ ይሰጥ ነበር። ድጎማው የሚሄደው ለኢህአዴግ ክልሎች እንጂ እነቤንሻንጉል፣ አፋር፣ ጋምቤላ እና ሶማሌ ጭራሽ ተቋምም ሆነ ሥርዓት የላቸውም ነበር፡፡

‹‹ማዳበሪያን በተመለከተ አምና ቤንሻንጉል ጀምረናል፤ ዘንድሮ አፋር ጀምረናል፤ አሁን ሶማሌ ላይ እየሰራን ነው፡፡ ቀጥሎ ሶማሌን ካስገባን በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በማዳበሪያውም አርሶ አደሩ የመጠቀም፣ ትራክተር የመግዛት፣ መሬቱን የማልማት ሁኔታው እያደገ ሲሄድ እንደ ሀገር እናድጋለን፡፡ እድገቱ፣ ቱሪዝሙ፣ ኢንዱስትሪው ሁሉም ጋር ይሁን ሲባል አንዱ ማሳያ ይሄ ነው።›› ብለዋል፡፡

መንግሥት እርሻ ላይ ጣልቃ መግባቱ እና የአፋርን መሬት ሰንጥቆ ከአዋሽ ጋር አገናኝቶ እንዲታረስ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ማዳበሪያ ከመንግሥት አግኝቶ የማያውቅ ክልልን ማዳበሪያ ከመንግሥት እንዲያገኝ ማስቻሉ በራሱ በጣም ትልቅ ድል ነው፡፡ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሌላ በኩል ከአፋር የሚሰበሰበውን ስንዴ ሁሉም ይመገበዋል። ምርቱ ወደ ውጭ ከተላከም ሁሉም ይጠቀማል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

‹‹አፋር ሲሰራም ብርቱ ነው፤ ሲዋጋም ብርቱ ነው፡፡ አሁን አይቶ ማረጋገጥ እንደሚቻለው እርሻውም ልዩ ነው፡፡ አፋር በጣም ሃብታም ክልል ነው፡፡ መላው ኢትዮጵያውያን ከአፋር ወንድሞቻችን ጋር በመተባበር ክልሉን ማልማት እና ለሌሎችም እንዲጠቅም ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ይሄ ዛሬ ላይ የታረሰው መሬት አብቅሎ ለመብላት

 ያበቃናል።›› ብለው ተስፋቸውን በመግለፅ የበጋ ስንዴ በይፋ አስጀምረዋል፡፡

በድጋሚ ሶስት ሚሊየን ሄክታር መሬት ዘንድሮ እንደሚታረስ እና ከአምናው በእጥፍ የሚበልጥ መሆኑን በማስታወስ፤ በየክልሉ ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ በትጋት መሥራት ይኖርበታል ሲሉ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡ ከምግብ ልመና ነፃ የወጣች ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ የሚቻለው፤ ይህ ሲሳካ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ክረምት ላይ መሠራቱ ጥሩ ነገር ነው፡፡ እርሱ መሰብሰብ አለበት፡፡ ነገር ግን ክረምት ቢሠራም በጋም ላይ መሠራት አለበት፡፡ ልክ በጋ ላይ ሲጨረስ ደግሞ ክረምት ይቀጥላል፡፡ ሌማትም ሆነ አረንጓዴ ልማት በተመሳሳይ መልኩ ማስቀጠል የግድ ነው፤ ይሄ ሲደማመር የኢትዮጵያን ብልፅግና ያለምንም ጥርጥር መጨበጥ ይቻላል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ገበታ ለትውልድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አፋር ክልል ሄደው የበጋ ስንዴን ከማስጀመር እና የእርሻ መሬት ከመጎብኘት በተጨማሪ ገበታ ለትውልድ የሚል ፕሮጀክት የሚሠራበትን ቦታም አይተዋል። ከዚህ በፊት ከተመረጡት ቦታዎች በሙሉ ሻል ያለ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አርባ ምንጭ በጣም ጥሩ ቦታ ተመርጧል፡፡ በጅማ እና በምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሚዛን አካባቢም በጣም ጥሩ ቦታ ተመርጧል፤ በአፋርም ክልል እንደዚሁ የፓልም እርሻ ያለበት እጅግ በጣም ውብ የሆነ ቦታ ተመርጧል። በወሎም የሐይቅ አካባቢ ተመርጧል፡፡ በትግራይ ገራአልታ ተመርጧል፤ በሶማሌ ጅጅጋ አካባቢ ተመርጧል። አብዛኞቹ ቦታዎች እጅግ በጣም ሳቢ ናቸው ብለዋል፡፡

‹‹ቦታዎቹ ለቱሪስት ውብ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን እኛንም እንዲህ ዓይነት ቦታ አለን ወይ? ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርገን ነው፡፡›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ በአፋር ክልል የሚገኘው ቦታ ከአዋሽ ጅቡቲ የሚሠራው ከአዲሱ የፍጥነት መንገድ በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው ብለዋል፡፡ ልክ ከፍጥነት መንገዱ ሲወጣ አሁን የተመረጠው ቦታ ከሁለት ፓርኮች ማለትም በአሰቦት እና በአዋሽ ፓርክ መካከል የሚገኝ ቦታ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ ቦታው በጣም ብዙ አዕዋፋት፣ የዱር እንስሳት እና ሰፋፊ እርሻዎች የሚገኙበት ነው፡፡ በየትኛውም ዓለም ፓልም እጅግ በብዛት እንደ ማንኛውም ዛፍ ጫካ ሆኖ የሚታይበት አካባቢ አያጋጥምም፤ ይህ ቦታ ግን ፓልም እንደ ጫካ በብዛት የሚገኝበት ቦታ ነው፡፡ ሣሩ የሚገርም ሲሆን፤ ፍል ውሃም አለ፡፡

‹‹በአፋር የተመረጠው ቦታ ሲታይ አሁን ባለበት ሁኔታ እንኳ እኛ ኢትዮጵያውያን ድህነትን ፈልገን፣ መርጠን፣ ተግተን እና ሠርተን ያመጣነው እንደሆነ አንዱ ማሳያ ነው። እንዲህ የሚታረስ ሰፊ ቦታ ኖሮን፤ ንፁህ ውሃ እና ፍል ውሃ ኖሮን፤ እንዲህ ዓይነት ውብ ቦታ ይዞ ‹ተርቤያለሁ እና ምግብ ስጡኝ› ብሎ መለመን ለድህነት ባለ ፍቅር እና ቅርበት በትጋት ተሠርቶ የመጣ ካልሆነ በስተቀር፤ ሰው በረሃን የማይመች ስፍራን ለአራት እና ለአምስት ወራት በበረዶ የተሸፈኑ ቦታዎችን ቀይሮ ራሱን እያበላ እኛ እንዴት ተቸገርን የሚል ጥያቄን ደጋግመን እንድናነሳ ያደርጋል፡፡

ለመገዳደል ብርቱዎች ነን፡፡ ለመተኛት እና ለመተማማት ብርቱዎች ነን፡፡ ለውጊያ አንደክምም። ያለንን የተፈጥሮ ሀብት እና ፀጋ ፈልቅቆ ለማየት እንደክማለን፡፡ እንዲህ ዓይነት ድንቃድንቅ ቦታዎችን ፈልገን አግኝተን ትንንሽ ነገሮችን ጨምረን ለኛ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሳቢ ለማድረግ ደግሞ እንደክማለን። ይሄ ለድህነት ያለንን ቅርበት እና ምርጫ የሚያሳይ ነው፡፡ ቆም ብለን ካስተዋልን ኢትዮጵያውያን ለመበልጸግ ሁሉ ነገር የተሰጠን ነን፡፡ ›› ብለዋል፡፡

አፋርን ብቻ መመልከት ይቻላል፡፡ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አፋር እንደሚታወቀው በጣም ሞቃታማ እና በርሃማ አካባቢ ነው፡፡ ነገር ግን አፋር ከባህር ጠለል በታች በጣም ዝቅተኛ ቦታ አለው። በሌላ በኩል እነዳሎል እና ኤርታሌን የመሳሰሉ ሊጎበኙ የሚችሉ መስዕቦች አሉት። ክልሉ የሉሲ መገኛ ብቻ ሳይሆን የተደረጉት በርካታ ጥናቶች እንዳረጋገጡት፤ ከአዋሽ ጀምሮ እስከ አፋር ባለው ቀጠና ውስጥ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ መሆናችንን ያሳየ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

‹‹በአፋር ታሪክ አለ፤ ለተፈጥሮ የሚሆኑ ቦታዎች አሉ፡፡ የሚገርም የእርሻ ሥራን ማከናወን ይቻላል። አፋር ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች በተለየ ሁኔታ አዋሽን የሚያክል ሰጥቶ እና አጠጥቶ የማይጠግብ፤ አረካለሁ ብሎ የማያስብ፤ አልፈልግም ሲባል ርቆ የማይሔድ እና ራሱን እዛው ደብቆ የሚቀር ውሃ ያለው የለም፡፡ አዋሽ አፋርን ገልብጦ ሊያለማ ይችላል፡፡ የስንዴ እርሻን አየን፤ በአምስት ወር ውስጥ የደረሰ የሙዝ እርሻ በአፋር ምድር ላይ እንዴት ሊስፋፋ እንደሚችል አየን፤ ሐምሌ የተተከለ ሙዝ ከአዋሽ አጠገብ በመሆኑ እንዴት እንዳደገ አይተን አረጋገጥን፡፡

ከእርሻ ሲወጣ ደግሞ ማዕድን እንደ ግብዓት የሚጠቀመውን ኢንደስትሪ አየን፡፡ ይህ በሀገር ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚፈለግ የኢንደስትሪ ውጤት ነው። ከሀገር ውጭም ከፍተኛ ገበያ ያለው ነው። የመንን ጨምሮ ሌሎችም ሀገሮች ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው አሳውቀዋል፡፡ ነገር ግን ያ ብቻ አይደለም፤ አፋር በጣም በርካታ የማዕድን ውጤቶች ያሉበት አካባቢ ነው፡፡ ከዛ በተጨማሪ ከቱሪዝም አንፃር የታዩ አስደማሚ ቦታዎች አሉ፡፡

በአፋር ቱሪዝም፣ ማዕድን፣ ግብርና እና ኢንደስትሪ በዚህ ዘመን በመንግሥት ውስጥ ካሉ ዋና ዋና የትኩረት ዘርፎች መካከል አራቱን በአፋር ክልል ውስጥ ማከናወን ይቻላል፡፡ አምስተኛው የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ(አይ ሲ ቲ) ነው፡፡ እርሱ ደግሞ የማይገባበት ቦታ የለም። ለቱሪዝሙም፣ ለማዕድኑም፣ ለግብርናውም፣ ለኢንደስትሪውም በእጅጉ የሚያስፈልግ ነው፡፡ በመረጥናቸው ዘርፎች ሁሉ ውስጥ በዚህ አካባቢ የጀመርናቸው ሥራዎች ውጤት እንደሚያመጡ የሚያመላክት ነው፡፡›› ብለዋል፡፡

እንደጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ አሁን ወረሃ ጥቅምት ነው፡፡ የአፋር ገበታ ለትውልድ ዓይን ገላጭ ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ በአሰቦት እና በአዋሽ ፓርክ መካከል የሚገኘው ለቱሪዝም የታሰበው ቦታ ላይ ማደር ይቻላል፡፡ ‹‹የምንጀምረው ዝም ብለን አይደለም፤ ያለምንም ጥርጥር ተቆጣጥረን፣ ሠርተን፤ አሠርተን እና ተከታትለን እናስፈፅመዋለን፡፡ ጨርሰን ሰዎች የሚገለገሉበት ይሆናል፡፡ ንፁህ ህሊና ያላቸው ኢትዮጵያውያን ከሁለት ዓመት በኋላ፤ ቦታውን ሲያዩ ‹ እንዴት ከድህነት ጋር ተዋደን ተጋብተን ተስማምተን ኖርን? ምን ነክቶን ነበር?› የሚል ጥያቄ ማንሳታቸው አይቀርም፡፡ ማንኛውም ጤነኛ ሰው እንደዚህ ዓይነት ስጦታ እና መልካም ነገርን ይዘን መራባችንን ሊቀበል አይችልም፡፡›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አፋር ላለፉት 30 ዓመታት አጋር የሚል ስያሜ ይዞ በክልልነት ሲቆይ ለመጀመሪያ ጊዜ ማዳበሪያ በመንግሥት ያገኘው ዘንድሮ ነው። እስከ ዛሬ ልክ እንደ ፖለቲካው ሁሉ ማዳበሪያም ተከልክሎ እንደዚሁ ክልል እና አጋር ተብሎ ቀርቶ ነበር፡፡ አሁን ግን ማዳበሪያ እና እርሻ ብቻ ሳይሆን በቱሪዝምም ሌሎች ክልሎች ያገኙትን እንዲያገኝ ተደርጓል ሲሉ ይህ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ደጋግመው አመልክተዋል፡፡

በፍራፍሬ አስደናቂ ነገር ታይቷል፡፡ በማዕድን በጣም በርካታ ፋብሪካዎች እየተጀመሩ ነው። እነዚህን አሰናስኖ፤ ተግቶ እና ሰርቶ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የሚወስደውን መንገድ በተሟላ መንገድ እንዲሆን የማረጋገጥ ሥራ ይጠበቃል፡፡ ለመሰዳደብ፣ ለመጠላላት እና ለመገዳደል ብርታት ካለ ለሌላው ነገር የሚውለውን ጉልበት ቀንሶ፤ በልማት እና በሥራ ላይ ቢውል ምን ሊመጣ እንደሚችል መገመት ይቻላል ብለዋል፡፡

‹‹ሁልጊዜ እንደምንደነቀው፤ በአፋር በአሰቦት እና በአዋሽ ፓርክ መካከል የሚገኘው ለቱሪዝም የታሰበው ቦታ ሲታይ፤ መላው ኢትዮጵያ ሲቃኝ እንዴት ፈጣሪ አዳልቶ እንደሰጠን እና ሁሉ ነገር ያላት ሀገር መሆኗን እንደምናየው ሁሉ በአፋርም ያለው አስደማሚ መሆኑን በዓይናችን አረጋግጠናል። ሰው የአፋር ክልል ለም ነው ብሎ ላያስብ ይቻላል፤ አይተን እንዳረጋገጥነው ፍልውሃ በአንድ አካባቢ 20 እና 30 ሐይቆችን ሠርቷል፡፡ የሚያስደንቅ እርሻ አለ፡፡ ሪዞርቱ እርሻንም ያካተተ ነው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የብዙ ሰዎች መዝናኛ፣ ማረፊያ፣ ማሰቢያ እና የብዙ ሰዎች የማይረሳ ትዝታ የማሳለፊያ ቦታ ይሆናል፡፡

ከአዲስ አበባ በፈጣን መንገድ በሁለት ሰዓት ውስጥ ሳፋሪ አዋሽን እና ሰቦትን አይቶ ፀዳ ያለ ሪዞርት ላይ አርፎ መሔድ አስደሳች ይሆናል። ከመሃል ከተማ ያለው ርቀትም በየትኛውም መስፈርት ከዓለም ተመራጭ ቦታ ያደርገዋል። ይህንን ለማሳካት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በትጋት ሠርተን ይህንን ቦታ ውብ አድርገን መልሰን ውጤት እናሳያለን፡፡ ›› ብለዋል፡፡

‹‹ላለፈው አንድ ዓመት አካባቢ ብዙ ስንመላለስ ነበር፡፡ መንገድ አልነበረም፡፡ መምጣት ከባድ ነበር። የደከምንባቸው እና የወደቅንባቸው ጊዜዎች ነበሩ።›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን የተሻለ መንገድ እና የሂሊኮፍተር ማረፊያ አለ፡፡ ከዚህ በኋላ የበለጠ የተሻለ ይሆናል፡፡ በእኛ በኢትዮጵያውያን የተደመረ ትጋት፤ በቁርጠኝነት በምንሠራው ሥራ እጅግ ያማረ ነገር እንደምናይ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡›› ሲሉ ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ለአፋር ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ በቅርብ ድንቅ የሆነ የፈጣሪ ስጦታ አላችሁ፡፡ ከአፋር ብርቱ ሕዝብ ጋር ተጋግዘን አፋርን በመቀየር አፋር ለኢትዮጵያ የብልፅግና ምልክት እንዲሆን በጋራ እንሠራለን። አፋርን ስንለውጥ፤ ሶማሌን ስንለውጥ፤ ጋምቤላን እና ቤንሻጉልን ስንቀይር፤ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ስንቀይር ኢትዮጵያ ትቀየራለች።›› ካሉ በኋላ፤ ለዚህ ግብዓት መሆን የሚችል ሥራ ተጀምሯል፤ ከሁለት ዓመት በኋላ በውጤት እንገናኛለን ሲሉ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You