በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ቀደም ያለ ታሪክ ቢኖረውም ብዙም አልተስፋፋም። በተለይ ከአፍሪካ አህጉር አኳያ ሲታይ ታሪኩ ቢጎላም አሰራርና እድገቱ ቀርፋፋ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ የኋሊትም ይመለሳል፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁን የሚታየው የትምህርት ጥራት ጉድለት እንደምክንያት ይጠቀሳል፡፡
የቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከራሱ አልፎ በርካታ አፍሪካዊ ልሂቃንን እስከ ማፍራት ድረስ ዘልቆ እንደነበር ከበቂ በላይ ተመስክሮለታል። በርካታ አፍሪካዊ ሀገራት መሪዎችን ማፍራቱ ሁሉ በበርካታ ሰነዶች እማኝነት ተረጋግጦለታል፡፡
የመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብዛት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስፈንጥሮ 50 አካባቢ ደርሷል። ይህም ዩኒቨርሲቲዎችን ብቻ ያካትታል። የጥራት ችግር ቀስ ብሎ የሚመጣ መሆኑ ከግምት ውስጥ ገብቶ የዩኒቨርሲቲ ቁጥር ማሻቀብ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል። እንዲያም ሆኖ የትምህርት ሚኒስቴር “ለለውጥ እየተጋሁ ነው” ባለው መሠረት እየሰራ ከሆነ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለውጥ ይመጣል ተብሎ ይታሰባል።
ወደ ግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲመጣም ተመሳሳይ ችግር ይታያል፡፡ እንደውም በእነዚህ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ችግሩ ብሷል። ተቋማቱ እንደ ፋሽን ቀሚስና ሱሪ የአንድ ሰሞን ዩኒቨርሲቲዎች በመሆን ብቻ ከጥቂት ዓመታት በኋላ እየከሰሙ ከመሄድ አላመለጡም። ሥራቸውም አስተምሮ ማስመረቅ ሳይሆን ዲግሪና ዲፕሎማ እያሳተሙ መቸብቸብ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይህም አሁን ላይ ሀገርን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ከነዚህ ተቋማት ዲግሪና ዲፕሎማ የተቀበሉትንም የሥነ ልቦናና ሌሎችም ጉዳቶች እያደረሰባቸው ይገኛል፡፡ በተለይም ከሰሞኑ በየተቋማቱ “የትምህርት ማስረጃን ማጣራት።ጋር በተያያዘ እየታየና እየተሰማ ያለው ጉድ ለሰሚም ሆነ ለተመልካች ግራ ያጋባል፡፡
ነገር ግን በተናጠል ማየት ከተቻለ አሁንም በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ፣ ከራሳቸውም አልፈው ለሌላውም እየተረፉ ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሉ። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ ነው። ኮሌጁ ባለፈው ቅዳሜ 943 ተማሪዎቹን ያስመረቀ ሲሆን፣ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኮሌጁ አጠቃላይ እንቅስቃሴና የመጣበት መንገድ በኮሌጁ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ደርበው በለው አማካኝነት ተገልጿል፡፡
ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ በድህረ ምረቃ፣ በቅድመ-ምረቃ፣ በTVT (ቴክኒክና ሙያ እና በሰርተፊኬት ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ለአስረኛ ዙር ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ∙ም በስካይ ላይት ሆቴል በደማቅ ሥነ ሥርዓት አስመርቋል።
ኮሌጁ የናሽናል ኢንቨስትመንት ግሩፕ አባል እና የናሽናል አየር መንገድ (National Airways) እህት ኩባንያ ሲሆን፣ ሀገራችን በአቪዬሽን፣ በሆቴልና ቱሪዝም እያደገ የመጣውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት ከማሟላት አኳያ በሚሰጣቸው መርሃ ግብሮች አማካኝነት ብቁ ሙያተኞችን በማፍራት ለዘርፉ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን እውቅና ባገኘበት በአውሮፕላን ጥገና ቴክኒሽያንነት (Aviation Maintenance Technician) ተማሪዎችን ተቀብሎ ማሰልጠን የጀመረ፣ በሀገሪቱ ብቸኛ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነው።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተገለፀው፣ ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ በቅርቡ ናሽናል ዩኒቨርሲቲ የመሆን አላማን ሰንቆ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ከዚሁ አዲስና ትልቅ ግብ ጋር በተያያዘ ኮሌጁ የስልጠና ዘርፎችን በማስፋት በጤናው ዘርፍ፣ በነርሲንግና በፋርማሲ ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡ በእለቱ በተሰጠው መግለጫ ላይ እንደተነገረው፣ ስለ ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ ሲነሳ ናሽናል አየር መንገድን ማንሳት ግድ ይላል።
ኮሌጁ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ደርበው በለው እንደተናገሩት፣ ናሽናል አየር መንገድ በኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ከሚንቀሳቀሱ የግል አየር መንገዶች መካከል ግንባር ቀደም ሲሆን፣ ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ የመንገደኛና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት፤ በእድገት ግስጋሴ ላይ የሚገኝ ግዙፍ ተቋም ነው፡፡
አየር መንገዱ በሀገራችን በፍጥነት እያደገ የመጣውን የአቪዬሽን፣ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች ተወዳዳሪነት በዘላቂነት ለማሳደግ ለሀገራዊ ልማቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ጉልህ ድርሻ ያለውን የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ከ10 ዓመት በፊት የራሱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሆነውን ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ አቋቋመ።
ናሽናል አየር መንገድ ከተቋቋመ ጀምሮ በሀገር ግንባታ ላይ ተሳታፊ እየሆነ መጥቶ በልዩ ልዩ ዘርፎች ላይ እየተሳተፉ ያሉ 10 የሚሆኑ ድርጅቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። ከአንድ ዓመት በፊት እነዚህ 10 ኩባንያዎችን ለማስተዳደር አመቺ በሆነ መልኩ በናሽናል ኢንቨስትመንት ግሩፕ (NIG-Holding Company) ጥላ ስር ሆነው ተዋቅረዋል። በአሁኑ ጊዜ በናሽናል ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሥር በተዋቀሩ ራስ ገዝ ድርጅቶች በቴክኖሎጂ፣ በአየር ትራንስፖርት፣ በግብርና፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም፣ በአቪዬሽን፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በማማከርና ጥናት፣ በአጠቃላይ ንግድ፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ እንዲሁም በቴሌኮም አገልግሎት ላይ ተሰማርቶ ለሀገርና ለወገን የሚጠቅሙ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። (የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት በናሽናል ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር ካሉት ተቋማት አንዱ ነው።)
የኮሌጁ ፕሬዚዳንት ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ ከምስረታው ማግስት ጀምሮ፣ ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት ከግብ ለማድረስ በትጋት እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረትም የሚሰጣቸው የትምህርት ዘርፎች ሀገራችን ለምታካሄደው ሁለ-ገብ ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው በርካታ ምሁራንን ማፍራቱንም ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥ ሰፊውን የተሳትፎ ደረጃ የያዙትን ሴቶች ጨምሮ፤ ምሩቃኖቹ በሥራቸው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ በመሆን ላፈራቸው፣ ለናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅም ሆነ ለሀገራቸው መልካም አምባሳደር ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
በጽሑፍ በተነበበው መልእክት ላይ እንደሰፈረው፣ በኮሌጁ ለትምህርት ጥራት የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ በየጊዜውም የትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፤ የዘንድሮው የ10ኛው ዙር ምሩቃንም የዚሁ ውጤቶች ማሳያ ናቸው።
ኮሌጁ በዘንድሮ የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና (Exit Exam) ካስፈተናቸው ተማሪዎች ውስጥ 64 በመቶ የሆኑትን ማሳልፉ ኮሌጁ በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሆነ አንድ ጥሩ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
በአጠቃላይ ኮሌጁ ከኢፌዴሪ ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ባገኘው እውቅና መሠረት በሁለተኛ ዲግሪ Aviation Management, Hospitality Management, Logistics and Supply Chain Management, Business Leadership, Strategic Management, Banking and Finance, Risk and Insurance, International Trade and Economics, እንዲሁም በመጀመሪያ ዲግሪ በመደበኛ Aviation, Hotel Management, Marketing Management, Accounting and Finance በTVT የተለያዩ ዘርፎች በሆቴልና ቱሪዝም፣ በበረራ መስተንግዶ፣ በጤና በመደበኛ መርሃ ግብር የሚያስለጥን ሲሆን፤ በርቀት መርሃ ግብር ደግሞ Economics, Business Management, Accounting and Finance, Educational Planning Management, Rural Development ፕሮግራሞች ሥልጠና በመስጠት በየዓመቱ በማስመረቅ ላይ ይገኛል።
በተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎች ጉልህ ተሳትፎ እያደረገ የሚገኘው ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለየ “International Air Transport Association (IATA) & International Commercial Management (SM) በአገኘው እውቅና መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸውን ስልጠናዎች እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን፣ በሚሰጠው የስልጠና ጥራትም ከAA እና CM የ2016፣ የ2017 እና የ2018፤ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት “Africa Top Performing IAIA Authorized Training Center” የሚል ሽልማት ማግኘቱ ተገልጿል፡፡
በዚህ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተመራቂ ወላጆች፣ የኮሌጁ ማህበረሰብ አባላት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ እንዲሁም ከጎረቤት ሀገር ኬንያ እውቅ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ተጋባዥ ፕሮፌሰሮች ተገኝተዋል፡፡ በምረቃ በዓሉ ላይ አዲስ ዘመን ተገኝቶ ያነጋገራቸው ምሩቃንም ኮሌጁ በጥሩ ሁኔታ አሰልጥኖ ለምረቃ እንዳበቃቸው ገልጸዋል፡፡
ከነዚህ ተመራቂዎች ውስጥ አንዷ የስድስት ወር ኮርሷን በማጠናቀቅ በቲኬቲንግ የተመረቀችው አትጠገብ የወንድወሰን ናት፡፡ እርሷ እንደምትለው በተቋሙ የነበራት ቆይታ ደስ የሚል ነበር፡፡ በኮሌጁ ታታሪ መምህራኖች አማካኝነት በሰለጠነችበት ሙያ ጥሩ እውቀት ይዛ ወጥታለች። ይህንን እውቀቷንም ወደ ሥራ የመቀየር ፍላጎቷ ከፍተኛ ነው። ለሥራም ዝግጁ ነች። በመሆኑም ወደ ሥራ ዓለም በመሰማራት የእለቱ ደስታዋ ዘላቂ እንዲሆን ትመኛለች፡፡ በሌሎች የጥናት መስኮችም ትምህርቷን የመቀጠል ፍላጎት አላት። ለዚህ ያበቋትን ቤተሰቦቿንም ታመሰግናለች።
ሌላው በኮሌጁ የInternational Trade and Economics ክፍለ ትምህርት ተመራቂ የሆነው ሙሉቀን ደስታው በመመረቁ እጅግ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል። እርሱ እንደሚለው ይህንን የሁለት ዓመት ጊዜ የሚጠይቀውን የጥናት መስክ የተከታተለውና የሁለተኛ ዲግሪ (ኤምኤ) ባለቤት ሊሆን የቻለው በምርጫውና ፈልጎት በመማር ነው። “ትምህርቱ አዋጭ ስለሆነ ሥራ የመሥራት እቅዴ በግል ነው። ስለዚህ ተቀጥሬ መሥራት አልፈልግም” ሲል ተናግሯል፡፡
ለወጣቶች ምክሩን ሲያስተላልፍም “ወጣቶች ወደ ትምህርት ዓለም (ዩኒቨርሲቲ) ሲመጡ ማዳመጥ ያለባቸው ራሳቸውን ነው፡፡ የሚፈልጉትንና የሚችሉትን ማጥናት ይኖርባቸዋል። በቤተሰብ ወይም በሌላ ሰው ግፊት መሆን የለበትም። እራሳቸውን አዳምጠው፣ ፍላጎታቸውን አውቀው ከሆነ ነው ውጤታማ መሆን የሚችሉት” በማለት ሃሳቡን አካፍሏል። መመረቁን ተከትሎም ከሚገባው በላይ ቤተሰቦቹ መደሰታቸውን፤ ጓደኞቹም በእሱ መመረቅ የተሰማቸውን ደስታ እየገለፁለት እንደሆነ ተናግሯል፡፡
ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ በግስጋሴ ላይ ነኝ እያለ ነው፡፡ ግስጋሴው ታዲያ ያለ ምንም መደነቃቀፍና እንከን እንዲሆን፤ ሀገርና ወገንንም የሚያገለግል፣ ስምንም የሚያስጠራ ተቋም እንዲሆን የሁሉም ሀገር ወዳድ ህብረተሰብ ምኞት ነው፡፡
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም