
አዲስ አበባ፡- በተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የተሻለ ሰው ሠራሽ የአካል ድጋፍ የሚያቀርብ ተቋም መገንባቱን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አዲስ የተቋቋመውን የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከልን ትናንት መርቀው ከፍተዋል።
በወቅቱ በኢትዮጵያ እንዲሁም በአፍሪካ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በርካታ አካላቸው የጎደለ ዜጎች መኖራቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብዙውን ጊዜ በቂ ትኩረት ስለማያገኙ ማገልገል እየቻሉ ተረጂና ተመጽዋች የሚሆኑ ዜጎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በለውጡ ወቅት እንደመንግሥት አካል ጉዳተኞችን የሚያስታውስ ሥራ እናከናውን ብለን ስንነሳ ብቁ ባለሙያዎች ቢኖሩም በዘርፉ በቂ ግብዓት የተሟላላቸው ተቋማት እንዳልነበሩ አስረድተዋል።
አሁን ላይ ዘመናዊ መሣሪያዎች ያሉትና ይበልጥ የተማሩ ባለሙያዎች የታከሉበት እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን በማገዝ ረገድ ሰፊ ሥራ የሚከናወንበት ተቋም መገንባት እንደተቻለ ጠቁመዋል።
በጦርነትም ሆነ በተለያዩ አደጋዎች እጃቸውን አሊያም እግራቸውን ያጡ ዜጎች በማዕከሉ ገብተው አጋዥ አካል (ሰው ሠራሽ አካል) ተገጥሞላቸው የሚንቀሳቀሱበትና ማገልገል የሚችሉበት ዕድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።
ተቋሙ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋ ምክንያት የአካል ጉዳተኛ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሀገር ውስጥ አጋዥ ቁሶችን አምርቶ ለማቅረብ የተቋቋመ ማዕከል ነው ብለዋል።
ማዕከሉ በቀጣይ በተለያዩ አደጋዎች ምክንያት የጆሮ ማዳመጥ ችግር ያለባቸውን የማየት ችግር ያጋጠማቸውን ዜጎች ጭምር ማገዝ የሚችልበትን አቅም እንዲያገኝ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ተቋሙ በቴክኖሎጂ አማካኝነት አይነ-ስውራንን የሚያግዙ መነጽሮችን ወደ መሥራት ማደግ አለበት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
ታካሚዎች በተቋሙ ለሕክምና በሚንቀሳቀሱበት ወቅት አዕምሯቸውን የሚያድሱ አረንጓዴ መናፈሻዎች፣ የስፖርት ማዕከላትና ልምምድ የሚሠሩባቸው ንጹህ ስፍራዎች በመገንባታቸው ጥሩ ሥራ ተከናውኗል ሲሉ አወድሰዋል።
የሰው ልጅ ከአካል ስብራቱ ይልቅ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደው የአዕምሮ ስብራቱ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አዕምሯችን ሲጎዳ ነፀብራቁ አካላችን ላይ ስለሚታይ መንፈስን የሚያድሱ መሠረተ ልማቶች በተቋሙ መገንባታቸውን በጥሩ ጎኑ አንስተዋል።
አገልግሎቱን ማሳደግ ከተቻለ ከአፍሪካም ጭምር በዘርፉ አጋዥ የሆነ ሥራ ለማከናወን መነሻ የሚሆን ማዕከል መቋቋሙን አስታውቀዋል። ማዕከሉን እንዲቋቋም የዩናይትድ ዐረብ ኤምሬትና የተለያዩ ሀገራት ላደረጉት ድጋፍም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋሙን የተለያዩ ሥራዎች በመጎብኘት የአገልግሎቱን ተጠቃሚዎች አነጋግረዋል።
የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት በቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ ጥራት ያለውና ደንበኛ ተኮር የሰው ሠራሽና የአካል ድጋፍ አገልግሎቶችን ለኅብረተሰቡ እየሰጠ መሆኑን ተገልጿል።
በምርቃቱ ወቅት የጤና ሚኒስቴር ያዘጋጀውን ዕቅውናና ሽልማት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለማዕከሉ ግንባታ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት አበርክተዋል።
በሥነሥርዓቱ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም