ዘናጩ ቴስ- ከአዲስ አበባ እስከ ቬሮና

እሱ በሥራው ልክ፣ ለሀገሩ ባለው መቆርቆር ልክ በሀገሩ አልታወቀም:: ግን ሙዚቃዎቹን ዘፈን አልሰማም የሚል ሰው እራሱ ያውቃቸዋል:: በተለይ የተወሰኑ ሙዚቃዎቹን አለማወቅ አይችልም:: ያኔ እንዳሁኑ የመገናኛ ብዙኃን ሳይበዙ አንድ ለእናቱ በነበረው የኢትዮጵያ ሬድዮ “ስፖርት″ የተሰኘው ዘፈኑ ለበርካታ ዘመናት የስፖርት ፕሮግራም ማድመቂያ በመሆን አገልግሏል:: ይህ ዘፈኑ በበርካታ ትውልዶች ልብና አዕምሮ ውስጥም ቀርቷል:: በርካታ ሥራዎች ቢኖሩትም “ስፖርት″፣ “አዲስ አበባ″፣ “የፍቅር ምግብ″፣ “መጋቢት 28″ እና “ውድ ሀገሬ″ የተሰኙት ሙዚቃዎቹ በኢትዮጵያውያን የሙዚቃ ወዳጆች ዘንድ ይበልጥ ይታወቃሉ::

ድምፃዊው ተስፋዬ ገብሬ:: እሱ እንደመድረክ መጠሪያ የሚጠቀምበት ቴስ ገብሬ፣ በተለይ የሕይወቱን አብዛኛውን ጊዜ በኖረበትና ዝነኛ በሆነበት ጣሊያን የተከበረ ሥም ነው:: ቴስ ካረፈ 41 ዓመታትን ተቆጥረዋል:: ድምፃዊ ነው፣ ያውም ምን የመሰለ ድምፅ ያለው:: ደግሞም የዜማና ግጥም ደራሲ፤ ጊታር ተጫዋች:: ጣሊያንን መቀመጫው ቢያደርግም ከጣሊያን ተነስቶ በአሜሪካና በተለያዩ ሀገሮች ሥራዎቹን አቅርቧል::

መጋቢት 28

የድላችን ቀን

ይከበር ዘላለም

በሀገራችን

መጋቢት 28

በያመቱ ይምጣ

የናንተም መሣሪያ

ጦር ጋሻችሁ ይውጣ

እያለ የሚቀጥለው ዘፈኑ በቀድሞ ጊዜ በየዓመቱ መጋቢት 28 በሬዲዮ፣ እንዲሁም በየቦታው ይሰማ የነበረ ዘፈን መሆኑን በርካቶች ያስታውሳሉ:: ነጋዴ ከሆኑት አቶ ገብሬ ምንዳዬና ከእናቱ ወይዘሮ ብዙነሽ ሞላ ለቤቱ የበኩር ልጅ በመሆን ይችን ምድር መኖሪያቸው በነበረው በአዲስ አበባ፣ አራት ኪሎ ተቀላቀለ:: ከመኖሪያቸው ብዙም ሳይርቅ በሚገኘው የሥላሴ ቤተክርስቲያን ውስጥ ይገኝ በነበረ የቄስ ትምህርት ቤት ፊደል ቆጥሯል፤ ዳዊት ደግሟል:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በአስፋው ወሰንና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሽመልስ ሀብቴ ትምህርት ቤቶች ተከታትሏል::

የሰፈሩ የቡሄ ግጥም አውራጅ ነው:: በ12 ዓመቱ በሰፈር ሠርግ ላይ ሲዘፍን የሰሙት የተለየ ድምፅ ባለቤት እንደሆነ መረዳት ችለዋል:: ከዛ ጊዜ ጀምሮ የሰፈር ጓደኞቹም የሱን ፍላጎትና ችሎታ ስለተረዱ ኳስ እንጫወት፣ ባስኬት ቦል እንጫወት ብለው እሱን ማስቸገራቸውን ተዉ:: ከዛን ጊዜ ጀምሮ የሱን ተሰጥዖ ስለተረዱ እነሱ ከኳስ ጋር ሲጫወቱ እሱ ከጉሮሮው ጋር እንዲጫወት መተው ጀመሩ::

ያኔ በስፋት ይንቀሳቀስ በነበረውና አራት ኪሎ በሚገኘው የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወወክማ) ተሳትፎ ነበረው:: በወወክማ ቆይታው ይዘፍናል፤ ትያትር ይጽፋል፤ ያዘጋጃል፤ ይደርሳል፤ የስፖርት እንቅስቃሴዎች ላይም ተሳታፊ ነበር:: በተለይ በቦክስና በክብደት ማንሳት ውጤታማ ተወዳዳሪ ነበር:: ተስፋዬ ከሲኒማ ቤት የማይጠፋ፤ በፊልሞች ያያቸውን አለባበሶች የሚከተል ዘናጭ ነበር:: ደግሞም ለውጭ ቋንቋዎች ቅርብ ጆሮ ያለው እንግሊዝኛ የሚናገር ቀልጣፋ ነበር:: ጣሊያንኛም መግባቢያው ነበር:: ቋንቋ ይችላልና በወወክማ ቆይታው በእንግሊዘኛም ሆነ በጣሊያንኛ የሚዘፍን ድምፃዊ፤ ብሎም በአማርኛ ግጥምና ዜማ የሚደርስ ድንቅ የጥበብ ሰው ነበር::

ታናሽ እህቱ ወይዘሮ አበራሽ ገብሬ፤ “አባታችን ፍላጎቱ ሁላችንም ዶክተር እንድንሆን ነበር::” ይላሉ:: ሆኖም እናታቸውም ድምፃቸው ማራኪ ነበርና የድምፅ ነገር ከእናቱ የተላለፈለት ሳይሆን እንደማይቀር ይገምታሉ:: በሠፈሩ የቡሄ ጨፋሪ ሕጻናት አለቃ ነበር:: ጥምቀት ያለተስፋዬ አትደምቅም ነበር:: የሠፈሩን ሠርግ እንዲያሞቅ ካለበት ተፈልጎ የሚጠራ ድምፀ መረዋ ነበር::

በወወክማም ሆነ በራሱ ተነሳሽነት የሙዚቃ ችሎታው ዳብሯል:: የሱን ድምፀ መረዋነትና ቅልጥፍና ያዩ “ለምን ክለብ አትሞክርም?″ በማለት ላማስኮስ ክለብ ወሰዱት:: በወቅቱ ተደማጭ የነበሩትን የኤልቪስ ፕሪስሊን፣ የፍራንክ ሲናትራንና የሌሎችንም ዓለም አቀፍ ድምፃውያንን ዘፈኖች በግሩም ሁኔታ ይጫወት ነበርና ዝናው ናኘ:: የውጭ ቋንቋዎች መቻሉ ከሱ ቅልጥፍና ጋር ተደምሮ በመዲናዋ “ተስፋዬ ገብሬ″ የሚለው ሥም ታዋቂ ሆኗል:: ይሄን የሱን ዝና የተረዱት የሀገር ፍቅር ማኅበር አመራሮች እነሱ ጋ እንዲጫወት አግባቡት:: እሱም ብዙም ሳያቅማማ የሀገር ፍቅር ማኅበር ድምፃዊ ሆነ::

ተስፋዬ ገብሬ ከድምፅ አወጣጡ አንስቶ አለባበሱ ለምዕራባውያን የሚያደላ ቢሆንም የተቀላቀለው የሀገር ፍቅር ማኅበር ሙሉ በሙሉ የባሕላዊ ዘፈን የሚፈልግ በመሆኑ ብዙም ደስተኛ አልሆነም:: ሆኖም በማኅበሩ ቆይታው አሁን ድረስ የሚሰሙትን “የፍቅር ምግብ″ እና “የፍቅር ሰላምታ″ የተሰኙ ዘፈኖቹን በዋሽንትና በእጅ ጭብጨባ ብቻ ታጅቦ በግሩም ሁኔታ ሠርቷል:: እሱ የባሕል ዘፋኝ በመሆኑ ብዙም ባይደሰትም የማኅበሩ ዋና ድምፃዊ ሆኖ ነበር:: በመሆኑም ማኅበሩን ለመልቀቅ ጥያቄ ቢያቀርብ እሱን ለመልቀቅ ፍቃደኛ አልሆኑም:: አንድ ዓመት ከስድስት ወር አካባቢ እንደሠራ፤ እንዲያውም ሁሉም ይቅርብኝ በማለት በተግባረ እድ ትምህርቱን መከታተል ጀምሮ ነበር::

ከሀገር ሳይወጣ ከሀገር ፍቅር ማኅበር በተጨማሪ ከመጀመሪያ የራስ ባንድ አባላት ጋር ለተወሰነ ጊዜ ሠርቷል:: የጣሊያኖች ምሽት ክበብ የነበረው ላማስኮስና ጁቬንቱስ ክለብ ሠርቷል:: ከነርሲስ ናልባንዲያን ጋር “ሒሩት አባቷ ማነው?″ ለተሰኘው ፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ ሠርቷል:: ስደትን የጀመረው የ25 ዓመት ወጣት ሳለ ነው:: ለጉብኝት በሚል ሰበብ የሆዱን በሆዱ ይዞ በባቡር ወደ ጅቡቲ አመራ:: ከጅቡቲ በመርከብ ተሳፍሮ ወደ ጣሊያን ገሰገሰ::

ጣሊያን እንደደረሰ የመጀመሪያ የሙዚቃ ግሩፑ ኦርኬስትራ ዲ አሥመራ ይሰኛል:: አብዛኛው አባላቱ አሥመራ የተወለዱ ጣሊያናውያን ነበሩ:: ከዛ ኦርኬስትራ ስፔታኮሎ የሚሰኝ የቤተሰብ የሙዚቃ ቡድንን ተቀላቅሎ ለሁለት ዓመት ሠርቷል:: ባንዱ በዓመት እስከ 100 ሺዎች የሙዚቃ ሥራዎችን ይሠራ የነበረ በመሆኑ በጣሊያን ዝናው እንዲናኝ በር ከፍቷል:: የባንዱ አመራር የነበረው ካሲዴ በአስደማሚ ድምፁና በዘፈን መሐል በሚናገረው ሃይማኖታዊ ስብከት ተማርኮ መቅጠሩን በጻፈው መጽሐፍ ላይ ገልጿል:: መጨረሻ ላይ ከባለቤቱ ጋር “ብራውን ኤንድ ዋይት ኤንጅል″ የተሰኘ ባንድ አቋቁመዋል::

ቴስ የጃዝ ሙዚቀኛ የሆኑት ሊዊስ አርምስትሮንግ ፍራንክ ሲናትራ ጋር በአንድ መድረክ አብሮ የመሥራት እድል ነበረው:: የእውቁ ድምፃዊ የፍራንክ ሲናትራን መድረኮች ላይ በከፋች ድምፃዊነት ሠርቷል:: በጣሊያን የጃዝ ሙዚቃ ታሪክ ሲነሳ “ቴስ ገብሬ″ የሚል ታሪክ አብሮ ይነሳል:: ተስፋዬ በአስር ቋንቋዎች ያዜማል:: ጃዝ ቢሉ ሬጌ፣ ፈንክ ቢሉ ሀገር ቤት ሳለ ሀገርኛውንም ተክኖታል፤ ለረዥም ጊዜ የኖረባትን ጣሊያን ባሕላዊ ሙዚቃዋን የራሱ አድርጎታል:: ጣሊያንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ዓረብኛ፣ ሩሲያኛ፣ ስፓኒሺ፣ እንግሊዝኛና አማርኛ ከሚዘፍንባቸው ቋንቋዎች ጥቂቶቹ ናቸው:: በአንድ ዘፈን ሁለትና ከዛ በላይ ቋንቋዎችን ቀላቅሎ መዝፈንን አውቆበታል:: በአንድ ዘፈኑ ላይ በእንግሊዝኛ፣ በጣሊያንኛ እና በስፓኒሽ አዚሟል::

አብዛኛውን የስደት ዘመኑን የኖረው በጣሊያን ነው:: ሁሉንም የጣሊያን ከተሞች በሥራው አዳርሷል ማለት እስኪቻል ድረስ በርካታ የጣሊያን ከተሞች ተዘዋውሮ ሠርቷል:: በአሜሪካ ኒውዮርክ፣ ላስቬጋስ እና ሎስአንጀለስ ሥራውን ለታዳሚ አቅርቧል:: በአውሮፓ ጀርመን፣ ስዊዲን፣ ስዊዘርላንድ፣ ግሪክ፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን እና ክሮሽያ ካዜመባቸው ሀገራት መካከል ይገኛሉ:: በሊባኖስ እና ታይላንድ አስደማሚ ብቃቱን አሳይቷል::

ብዙ መድረክ ቢሠራም፤ በርካታ ሙዚቃዎች ቢጫወትም በርካታ አልበሞችን ግን አልሠራም:: ሁለት የሸክላ አልበምና ሕይወቱ ካለፈ በኋላ በሀገር ውስጥ ለገበያ የቀረበ “ሰላም ለኢትዮጵያ″ የተሰኘ አንድ የካሴት አልበም አለው:: በርካታ አልበም ላለማውጣቱ በጣሊያን ያሳተመውን የሸክላ ሲዲ ተከትሎ የመጣበት ቅጣት አንዱ ምክንያት መሆኑን ብዙዎች ይገምታሉ:: በስንት ውጣ ውረድ በጣሊያን ስደት ላይ እያለ ያሳተመው ሸክላ ለገበያ በቀረበ በሦስት ቀናት ሙሉ በሙሉ ከገበያ ተሰብስቧል:: በተጨማሪም በወቅቱ ከያንዳንዱ ሸክላ መክፈል ያለብህን ሳንቲም አልከፈልክምና ያለፈቃድ የጣሊያንን የኮፒ ራይት ሎጎ ተጠቅመኃል በሚል በጣሊያን መንግሥት ለእስር ተዳርጎም ነበር::

ከሦስት ቀናት የገበያ ቆይታ በኋላ ሸክላውም ከገበያ ተሰብስቦ ተወገደ:: ከእስሩና ከገበያ ከመሰብሰቡ በተጨማሪ በወቅቱ ፍርድ ቤት ቀርቦ በወቅቱ ብዙ የነበረውን 2ሺህ 500 ሊሬ እንዲከፍል ተበይኖበታል:: ይህም ከዛ በኋላ አልበም የማሳተም ሞራል እንዲያጣ አንዱ መንስኤ ነው:: ከዛ በኋላ የናይት ክለብ ሥራው ላይ አተኮረ:: ያም ቢሆን በየጊዜው አዳዲስ ሙዚቃዎች መሥራቱን አላቆመም ነበር:: ሆኖም የጣሊያን አድማጭ የሚፈልገው ጣሊያንኛ ቋንቋን ነውና ከሠራቸው ከ100 በላይ ሙዚቃዎች ውስጥ አብዛኞቹ ጣሊያንኛ ነበሩ:: ከሀገሩ ለረዥም ጊዜ ተራርቆ ቢቆይም ሀገሩን ጭራሽ አልረሳም ነበር::

እናት ኢትዮጵያ

ውቢቷ ሀገሬ

በጣም ይወድሻል

ተስፋዬ ገብሬ……

ሰላም ለኢትዮጵያ

ውቢቷ ሀገሬ

ይኸው ተመለስኩኝ

ብዙ ዓለምን ዞሬ።

እያለ ለሀገሩ ናፍቆቱን ቢገልጽም ወደ ሀገሩ ግን አልተመለሰም:: ሆኖም የአንጀት ካንሰር እንደያዘውና በሽታው የማይድን እንደሆነ ካወቀ በኋላ ከሠራቸው ሙዚቃዎች በተጨማሪ ለሀገር ውስጥ ወገኖቹ የሱ ማስታወሻ የሚሆኑ የአማርኛ ሥራዎችን ቀድቷል:: ከበሽታው ጋር እየታገለ በሽታው ፋታ ሲሰጠው ስቱዲዮ እየገባ ከሠራቸው ሙዚቃዎች ውስጥ 25ቱን በድጋሚ ቀድቷል:: ተስፋዬ በሠራቸው አብዛኞቹ ሙዚቃዎች ላይ የሀገሩን ሥምና ታሪክ እንዲሁም መልክዓ-ምድር አስተዋውቋል:: በዚህም በዓለም አቀፍ ሙዚቃዎች ለዓለም አቀፍ አድማጮች ሀገሩን በጥሩ በማንሳት የሀገሩን ገጽታ ገንብቷል::

ድምፃዊው ሀገሩን ለማስተዋወቅ ካለው ፍላጎት የተነሳ ከሙዚቃው በተጨማሪ ስለሀገሩ በእንግሊዝኛና በጣሊያንኛ መጽሐፍ ጽፎ ነበር:: በአማርኛም የራሱን ታሪክ ጽፎ ነበር:: ከመሞቱ በፊትም ሲሞት መጽሐፎቹ ታትመውና ሙዚቃው ለገበያ ቀርቦ የሚገኘው ገቢ በሀገሩ መብራትና ውሃ ለሌለባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ወገኖቹ እንዲውሉ ተናዞ ነበር::

ቴስ ግጥም ለመጻፍ እሩቅ ቦታ አይሄድም፤ ከቤተሰቡ ተራርቋልና በናፍቆት እናትና አባቱ ጋ መሄድ ምርጫው ነው:: “ሰላም ለኢትዮጵያ″ በሚለው ዘፈኑ፡-

ሰላም ለአባቴ

ታላቁ አቶ ገብሬ ∙ ∙ ∙

እንደምን ሰነበትሽ

ብዙነሽ እናቴ

ደስታዬ ታላቅ ነው።

እያለ ቤተሰቡን ያስተዋውቃል:: የፍቅር ሰው ነው፤ አብሮ ጊዜ ያሳለፋቸውን የፍቅር ጓደኞቹን አይረሳም:: ከዛ ውስጥ የመጀመሪያ ልጁ እናት ለነበረችው “ሮማ ናት፣ ሮማ ናት″ የተሰኘ ሙዚቃ፤ ሕይወቱ እስኪያልፍ ድረስ ለሦስት ዓመታት ያለመታከት ላስታመመችው የትዳር አጋሩ አንጀሊና፣ እንዲሁም ለልጅነት ፍቅረኞቹ ሁሉ ዘፈን ዘፍኗል:: በዘፈኑ መከፋቱን፣ ምስጋናውንም ሆኖ ናፍቆቱን ገልጾላቸዋል::

ስለተወለደባት፣ ልጅነቱንና ወጣትነቱን በከፊል ስለኖረባት አዲስ አበባ አራት ሙዚቃዎችን ተጫውቶላታል:: የመጀመሪያው ከሀገር ፍቅር ማኅበር ጋር የተጫወተው “አዲስ አበባ″ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በካሴት ከወጣው ውስጥ የሚካተተው “አዲስ አበባ ውብ ከተማ″ ሳይታተም በጣሊያን የቀረው የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እና እዚህ ነው የተወለድኩት የሚሉ ሙዚቃዎችን ለአዲስ አበባ ዘፍኗል:: ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው “ተመለስኩልሽ″ ብሎ ያላት ሀገሩን ተመልሶ ሳያያት እ.ኤ.አ. በ1982 እዛው በጣሊያን፣ ቬሮና አረፈ:: በጣሊያን ስሙን በሥራው ተክሏልና ሞቱን መገናኛ ብዙኃን ዘግበውለታል። እንዲሁም፣ በርካታ አድናቂዎቹ ተገኝተው ሥርዓተ ቀብሩ ተከናውኗል::

ድምፃዊው ሁለት ወንድ ልጆች ቢኖሩትም ልጆችን በማሳደግ ረገድ አልታደለም:: የመጀመሪያ ልጁ አያሌው ተስፋዬ እንደተወለደ ድምፃዊው ብዙም ሳይቆይ ወደ ጅቡቲ፣ ቀጥሎም ወደ ጣሊያን ተሰደደ:: በዚህ የተነሳ አባትና ልጅ ከስልክና ከፎቶ የዘለለ ብዙም ሳይገናኙ ኖረዋል:: በጣሊያን ቆይታውም ከጣሊያናዊት ሴት ወንድ ልጅ ቢያገኝም ከልጁ እናት ጋር መስማማት ባለመቻላቸው ልጁን የማሳደግ እድል አልነበረውም:: ጭራሽ በእናትየው ተፅዕኖ የአባትየውን ጥቁርነት መቀበል ተቸግሯል ብሎ በማሰቡ አባትና ልጅ ተቆራርጠው ቀርተዋል::

የሀገራችን የሙዚቃ ባለሙያዎችና ሐያሲያን “ድምፁን እንደፈለገ ማዘዝ የሚችል የተለየ ድምፃዊ″ በማለት ይጠሩታል:: በሀገራችን ሀገሩን ያልረሳው ተስፋዬ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ስለታሪኩ ብዙም መረጃ አልነበረም:: አስታዋሽ አያሳጣ ነውና ታላላቅ ወንድሞቼ ሲሰሙት አብሬ እየሰማሁት በማደጌ የሱ አድናቆት ተቀርፆብኛል በሚለው ማርቆስ ተግይበሉ ከቤተሰቦቹ ጋር በመተባበር ከቅርብ ዓመታት በፊት የተስፋዬ የፎቶ ኤግዚቢሽን ተዘጋጅቶ አድናቂዎች የተስፋዬን መልክ እንዲያውቁ አስችሏል:: ከሞተ 41 ዓመታት ቢቆጠርም በያዝነው ዓመት ተስፋዬን ፍለጋ “ከአራት ኪሎ እስከ ቬሮና″ የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ በማቅረብ አድናቂዎቹ በቅርበት እንዲያውቁት በር ከፍቷል:: ደራሲው የድምፃዊ ተስፋዬን ታሪክ ፍለጋ ከአዲስ አበባ እስካረፈበት የጣሊያኗ ቬሮና ከተማ በመሄድም ታሪኩን ሰብስቧል::

ቤዛ እሸቱ

Recommended For You