የተጋረጡበትን ማነቆዎች መሻገር የተሳነው የስጋ ወጪ ንግድ

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በእንስሳት ሀብቷ ዕምቅ አቅም ቢኖራትም በስጋ ወጪ ንግድ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት እንዳልቻለች ይነገራል። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ከምክንያቶቹ መካከልም በእንስሳት አቅርቦትና ጥራት ላይ የሚታየው ክፍተትና የኮንትሮባንድ ንግድ በዋናነት የሚጠቀሱ የዘርፉ ማነቆዎች እንደሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳል። ያም ሆኖ ግን ላለፉት በርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ የስጋ ምርት ወደ ውጭ ገበያ ስትልክ ቆይታለች።

በሀገሪቱ ከሚገኙ 11 ስጋ አምራችና ላኪ የኤክስፖርት ቄራዎች መካከል ሁለቱ በውጭ ባለሀብቶች የሚመሩ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ በሙሉ ሀገር በቀል በሆኑ ባለሀብቶች ይመራሉ። ሀገሪቷ በእንስሳት ሀብት ያላትን ዕምቅ አቅም ተገንዝበው ወደ ዘርፉ እንደገቡ የሚገልጹት ባለሀብቶች በሀገሪቱ ያለውን የእንስሳት ሀብት አሟጦ ለመጠቀም ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉና ይህን ማለፍ እንዳልተቻለ አስረድተዋል።

የስጋ ምርትን ወደ ውጭ ገበያ እየላኩ ከሚገኙ የውጭ ባለሀብቶች መካከል አላና ግሩፕ አንዱ ነው። አላና ግሩፕ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ የሀላል ስጋ አምራችና ላኪ ድርጅቶች መካከል ተጠቃሽ እንደሆነ የአላና ግሩፕ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ከሊፋ ሁሴን ይናገራሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ ሀላል ስጋ በማምረት የሚታወቀው አላና ግሩፕ በሕንድ ባለሀብቶች የሚመራ ሲሆን፣ ዋና መቀመጫውን ሕንድ በማድረግ 72 ለሚደርሱ የዓለም ሀገራት ስጋና የስጋ ምርቶችን ይልካል። ለዚህም 17 የሚደርሱ ኤክስፖርት ቄራዎች አሉት።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ኤክስፖርት ቄራዎች ያሉት ሲሆን፣ አንደኛው ሞጆ ላይ ሁለተኛው ደግሞ አዳሚ ቱሉ ዝዋይ ላይ የሚገኝና በአፍሪካ ትልቁ ቄራ ነው። ኤክስፖርት ቄራዎቹ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገነቡና ሰፊ ገበያ መዳረሻ ያላቸው ቢሆኑም በአሁን ወቅት በአቅማቸው ልክ እያመረቱ አይደለም የሚሉት አቶ ከሊፋ፤ አዳሚ ቱሉ ላይ የሚገኘው ቄራ ብቻ በቀን ዘጠኝ ሺ በግና ፍየል እንዲሁም ሦስት ሺ ከብት አርዶና አቀነባብሮ የመላክ አቅም አለው። ይሁንና በሀገሪቱ ካለው የአቅርቦት እጥረት የተነሳ በቀን ከሁለት ሺ እንስሳ በላይ እያረደ አለመሆኑ ነው ያስረዱት።

ለዚህም ዋናው ችግር የእንስሳት አቅርቦትና ኮንትሮባንድ ንግድ መሆኑን ያነሱት አቶ ከሊፋ፤ ሀገሪቱ በእንስሳት ሀብት ትልቅ አቅም ያላት ቢሆንም ወደ ገበያ የሚመጣው እንስሳት ቁጥር ግን አነስተኛና ጥራቱን የጠበቀም አይደለም ይላሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የእንስሳት ዋጋ ተወዳዳሪ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ ማነቆ እንደሆነ አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅትም በዋጋ ንረቱ ምክንያት እንደ ሀገር የበሬ ስጋ ሙሉ ለሙሉ ኤክስፖርት ማድረግ እንዳልተቻለ አመላክተዋል።

‹‹አብዛኛው ስጋ ላኪ ስጋን በኪሳራ እየላከ ነው›› የሚሉት አቶ ከሊፋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የስጋ ወጪ ንግዱ ይበልጥ እየተቀዛቀዘ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ለዚህም መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ነው የገለጹት። ዘርፉ የመንግሥትን ድጋፍ ካገኘና የተጋረጡበትን ችግሮች መሻገር ከቻለ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ እንደሆነ ነው ያስረዱት።

ሀገር በቀል ከሆኑ ኤክስፖርት ቄራዎች መካከል አንዱ የሆነው የአቢሲንያ ኤክስፖርት ቄራ መሥራችና ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ በበኩላቸው፤ ዘርፉን ከተቀላቀሉ ዘጠኝ ዓመታትን እንዳስቆጠሩ ገልጸው ወደ ውጭ ገበያ የሚልኩት የስጋ መጠን ከዓመት ዓመት እየቀነሰና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የመሆን ዕድላቸው እየቀነሰ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ሀገሪቷ በእንስሳት ሀብት ትልቅ አቅም ያላት ቢሆንም በአቅርቦትና ጥራት ላይ እንዲሁም የኮንትሮባንድ ንግዱ እጅግ ፈታኝ ነው። በተለይም በቁም እንስሳት እየተፈጸመ ያለው የኮንትሮባንድ ንግድ የዘርፉ ዋነኛ ማነቆ ነው። በዚሁ ምክንያት የሚከሰተውን የዋጋ ንረት መቆጣጠር አልተቻለም። የአቅርቦት እጥረትም ሌላው ችግር ሲሆን እንስሳቱን የሚያቀርበው አርብቶአደሩ ነው። አርብቶአደሩ ገንዘብ ሲፈልግ ብቻ የሚያመጣውን እንስሳት ጠብቆ የውጭ ገበያን መወዳደር አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ በዋነኛነት የስጋ ወጪ ንግዱን ለማሳደግና ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ከፍ ለማድረግ ለኤክስፖርት ገበያ ተብሎ ብቻ እንስሳትን ማርባት ያስፈልጋል። ለዚህም ከግል ባለሀብቱ በበለጠ የመንግሥትን ድጋፍና ክትትል ያስፈልጋል ብለዋል።

‹‹የቁም እንስሳት ኮንትሮባንድ ንግድ በተለይም ሀገሪቷ በአሁኑ ወቅት ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ እጅግ የተጠናከረበት በመሆኑ የውጭ ንግዱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው›› የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ዘርፉ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት የሚያስፈልገው እንደሆነ አመላክተዋል። አስፈላጊውን ትኩረት ካገኘና የግብይት ሥርዓቱን ጤናማ ማድረግ ከተቻለ ዘርፉ አሁን ካለበት ደረጃ በእጥፍ ማደግና ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ማምጣት የሚያስችል ትልቅ አቅም እንዳለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ስጋ አምራች ላኪዎች ማኅበር ዋና ጸሐፊ አቶ አበባው መኮንን በበኩላቸው በሀገሪቱ የስጋ ወጪ ንግድ ኢንዱስትሪ ረዘም ያሉ ዓመታትን ያስቆጠረና ከስድስት በማይበልጡ ቄራዎች መጀመሩን አስታውሰው፤ አሁን ያለው የስጋ ወጪ ንግድ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር እየወረደ መሆኑን ነው የገለጹት። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚገኙ የኤክስፖርት ቄራዎች ዝቅተኛ አፈጻጸም እያስመዘገቡ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይሁንና ሀገሪቱ ካላት እምቅ የእንስሳት ሀብት ጋር ሲነጻጸር አሁን ላይ ለውጭ ገበያ እየቀረበ ያለው መጠንና ዘርፉ እያስመዘገበ ያለው የውጭ ምንዛሪ ዝቅተኛ መሆኑን ይገልጻሉ። ምንም እንኳን መንግሥት ባደረገው ጥረት የቄራዎችን ቁጥር ማበራከትና የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢንቨስትመንቱ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠሩ ቢሆንም የኤክስፖርት መጠኑን ግን ማሳደግ አልተቻለም የሚሉት አቶ አበባው፤ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከሚገኙ 11 ኤክስፖርት ቄራዎች የሚገኘው የኤክስፖርት ገቢ በሚፈለገው ልክ እንዳልሆነ ነው ያስረዱት።

በኢንቨስትመንት ልክ ኤክስፖርት ማድረግ እንዳልተቻለ የጠቀሱት አቶ አበባው፤ በ2014 በጀት ዓመት ከስጋ ወጪ ንግድ 120 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታውሰው፤ በ2015 በጀት ዓመት 14ሺ575 ቶን ስጋ ተልኮ፤ 89 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን ተናግረዋል። በ2016 በጀት ዓመት 25 ሺ 607 ቶን ስጋ በመላክ 135 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል።

ለስጋ ወጪ ንግዱ መውረድ አንደኛው የዋጋ ንረት እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አበባው፤ ለዋጋ ንረቱ መባባስም ሀገሪቱ ያለችበት የሠላምና ጸጥታ ችግር አንዱ ሲሆን፤ ሌላው የኮንትሮባንድ ንግዱ መባባስ በዋነኛነት የሚጠቀስ እንደሆነ አመላክተው፣ በዚህም የስጋ ወጪ ንግዱ አፈጻጸም ከዓመት ዓመት ዝቅተኛ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

ኤክስፖርት ቄራዎች ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚጠይቁ በመሆናቸው ባለሀብቶቹ ትልቅ ሀብት ያወጡበት መሆኑን ያነሱት አቶ አበባው፤ በሀገሪቱ ያሉ ኤክስፖርት ቄራዎች ከጥራት አንጻር ተወዳዳሪና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ቄራዎች እንደሆኑም ተናግረዋል። በዘርፉ የተሰማሩት ስጋ አምራችና ላኪዎችም ከአስር ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ እንደመሆናቸው ጥሩ ልምድ ያላቸውና ዓለም አቀፍ ገበያው ውስጥ መግባት እንደቻሉ ተናግረዋል። የስጋ ኢንዱስትሪ በባህሪው ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚፈልግ ከመሆኑ ባሻገር ኢንቨስትመንት ውስጥ ለመግባትም የተለያዩ መስፈርቶችን የሚጠይቅ ነው። በመሆኑም ስጋ አምራችና ላኪዎች በሀገር ውስጥ ተቆጣጣሪዎች ተገምግመው እንዲሁም በተቀባይ ሀገር ዓለም አቀፍ የሆነውን ሂደት አልፈው ወደ ኤክስፖርት ሥራው የሚገቡ እንደሆነም አቶ አበባው አስረድተዋል።

ገበያው ዓለም አቀፍ እንደመሆኑ ስጋ አምራችና ላኪዎች እንደ ሀገር የተሻለና ጥራት ያለው ምርት ይዘው መቅረብ አለባቸው የሚሉት አቶ አበባው፤ ለዚህም ቀሪ የቤት ሥራዎችን መሥራት የግድ የሚል ነው ይላሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ ያለው የስጋ መግዣ ዋጋ ዘርፉን በእጅጉ እየፈተነው ነው። በተለይም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በሀገር ውስጥ ያለው የስጋ መግዣ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመሆኑ ዋጋውን መቆጣጠር አልተቻለም። ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ›› እንዲሉ ሆኖ የእንስሳት አቅርቦት እጥረቱም ከፍተኛ ነው። ኤክስፖርት ቄራዎቹም የደንበኞቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ አላስፈላጊ ውድድር ውስጥ ይገባሉ። በእነዚህና መሰል ምክንያቶች በዓለም አቀፉ ገበያ ያለው የስጋ መሸጫ ዋጋ ከኬንያ፣ ከታንዛኒያና ከሱዳን ጋር ሲነጻጸር የኢትዮጵያ ከፍተኛ ነው። ይህም ኤክስፖርት ቄራዎቹ ተወዳዳሪና አትራፊ ሆነው መቀጠል አላስቻላቸውም።

የአቅርቦት እጥረት ዋነኛው የዘርፉ ማነቆ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አበባው፤ እንደ ሀገር ያለው የእንስሳት ልማት ሥራው ኋላቀርና የግብይት ሥርዓቱም ጤናማ እንዳልሆነ ይናገራሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ላይ ኤክስፖርት ቄራዎች እንስሳቱን የሚያገኙት ከአርብቶ አደሩ ሲሆን፤ አርብቶ አደሩ እንስሳቱን ለኤክስፖርት ቄራ ብሎ የሚያረባ እንዳልሆነና ባህላዊ በሆነ መንገድ በቤቱ ያረባውን ወደ ገበያ ያወጣል። ከዚህም ባለፈ አርብቶ አደሩ ገንዘብ ሲፈለግ ብቻ እንስሳቱን ወደ ገበያ አውጥቶ ይሸጣል። ስለዚህ አርብቶ አደሩ ለኮንትሮባንድም ይሁን ለኤክስፖርት ቄራዎች የተሻለ ዋጋ ለሰጠው የሚሸጥበት መንገድ ነው ያለው። ይህም የገበያ ሥርዓቱን ፈታኝ አድርጎታል።

ለአቅርቦት እጥረቱም ሆነ ለገበያው ችግር መፍትሔ መሆን የሚችለው እንስሳቱን ለኤክስፖርት ቄራ ተብሎ ማርባት ሲቻል እንደሆነ ያመላከቱት አቶ አበባው፤ እንስሳትን ለኤክስፖርት ቄራ ለማቅረብ እስካሁን በመንግሥት በኩል የተደረገ ጥረት አለመኖሩን ገልጸዋል። ሆኖም ግን አንዳንድ ኤክስፖርት ቄራዎች ለራሳቸው ቄራ ግብዓት መሆን የሚችሉ እንስሳትን ለማርባት ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም ባለሀብቱ ብቻውን ሊያሳካው እንደማይችል በመሆኑ ዳር ማድረስ አልተቻለም። ምክንያቱም ትልቅ ኢንቨስትመንት እንደመሆኑ የመንግሥትን ከፍተኛ ድጋፍና ክትትል ይፈልጋል። ለእንስሳት እርባታ ዘርፉ ሰፊ መሬት፣ የውሃ አቅርቦትና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን የሚፈልግ ነው። ለዚህም የመንግሥትን ቁርጠኛ አመራር ይፈልጋል። ይሁንና እስካሁን የተደረጉ ሙከራዎችና ጥረቶች የሉም ብለዋል።

ነገር ግን መንግሥት ለዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ለኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆን እንስሳት ማርባት የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ከቻለ ኢንዱስትሪውን ማሳደግ ይቻላል የሚሉት አቶ አበባው፤ ይህን አሠራር መከተል ካልተቻለ ከአርብቶአደሩ የሚገኝ እንስሳትን ብቻ ጠብቆ ኤክስፖርትን ማሳደግ የማይቻል እንደሆነ አመላክተው፤ ይህም የዘርፉ ማነቆ እንደሆነ በተጨባጭ መታየቱንም ያስረዳሉ።

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች የመንግሥትን ድጋፍ ካገኙ ለእንስሳት እርባታ ሥራው ፈቃደኞች እንደሆኑ ጠቅሰው፤ ከኤክስፖርት ቄራ ውጪ የሚገኝ ማንኛውም ባለሀብትም እንዲሁ እንስሳትን ለኤክስፖርት ቄራ ብቻ አርብቶ ማቅረብ ከፈለገ በሩ ክፍት እንደሆነ ገልጸዋል። ለዚህም ከፍተኛ የሆነ የመንግሥትን ትኩረትና ድጋፍ ይፈልጋል ነው ያሉት።

የገበያ መዳረሻ ሀገራትን አስመልክቶ አቶ አበባው እንዳሉት፤ እስካሁን ባለው የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬትስ፣ ዱባይ፣ ሳውዲዐረቢያና ሪያድ የመሳሰሉ ሀገራት 90 በመቶ ያህል የገበያ ድርሻ ያላቸው ሲሆን፤ ኩዬትና ኳታርም እንዲሁ ድርሻ አላቸው ብለዋል። ቻይናን ጨምሮ ሆንግኮንግና ቬትናም ደግሞ የዕርድ ተረፈ ምርት ገዢ ሀገራት ናቸው።

አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት በዋናነት ሁለት ነገሮች ያስፈልጋሉ የሚሉት አቶ አበባው፣ አንደኛ ምርቱን ማስተዋወቅና በዘርፉ ያለውን ምቹ ሁኔታ ለተቀባይ ሀገራት የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት አንዱ ነው። ሁለተኛው የምግብ ምርት እንደመሆኑ ከእንስሳት ጤና ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ ደረጃውን መሠረት በማድረግ የሚቀመጥ መስፈርት ማሟላት ሲሆን፤ እስካሁን ተሟልቶ እየተላከ ያለውም መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ብቻ ነው። በቅርቡ የቻይና ገበያን ተደራሽ ለማድረግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ስለመኖራቸው ጠቅሰው፤ ይህም ተስፋ ሰጪ እንደሆነ አመላክተዋል። ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን የእንስሳት ጤና አጠባበቅ አጠናክሮ መቀጠል ከተቻለ ወደ ገበያው የመግባት ዕድል አለ ብለዋል።

እንደ ሀገር በእንስሳት ሀብት ትልቅ አቅም መኖሩንና ይህን ሀብት አሟጦ በመጠቀም ሀገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ውጤት ማግኘት እንድትችል ቀሪ የቤት ሥራዎች ስለመኖራቸው ያነሱት አቶ አበባው፤ እስካሁን ባለው ሂደትም ከኢንቨስትመንት አንጻር ኢንዱስትሪው ላይ ትልቅ አቅም መፍጠር እንደተቻለ ገልጸዋል። በመሆኑም በሀገሪቱ የሚገኙ 11 የኤክስፖርት ቄራዎች በዓመት እስከ ሁለት መቶ ሺ ቶን ስጋ አምርተውና አቀነባብረው ለዓለም ገበያ የማቅረብ አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል።

ይህም የስጋ ወጪ ንግዱ ከሌሎች የኤክስፖርት ዘርፎች ባልተናነስ መንገድ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ለሀገሪቱ ማምጣት እንደሚችል የሚያሳይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አበባው፤ ዘርፉ ለሀገሪቱ ከሚያመጣው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ባለፈም አርብቶ አደሩን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን በሙሉ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችል አስረድተዋል። አያይዘውም መንግሥት በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር ተቀራርቦና ተቀናጅቶ መሥራት የሚጠበቅበት እንደሆነ አብራርተዋል።

መንግሥት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ሊከታተለው የሚገባው ዘርፍ እንደሆነ የገለጹት አቶ አበባው፤ በተለይም ከፖሊሲ አንጻር የመንግሥትን ውሳኔ በሚፈልጉ ጉዳዮች ተሳትፎውን ማጠናከር እንደሚገባ አመላክተው እነዚህንና መሰል ችግሮችን መፍታት ከተቻለ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ከፍ ማድረግ የሚቻልበት ሰፊ ዕድል መኖሩን ተናግረዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You