አዲስ ዘመን ድሮ

 አዲስ ዘመን ድሮ፤ ዛሬም ለየት ያሉና ‘ወቸው ጉድ!’ የሚያስብሉ ብዙ ጉዳዮችን ይዞ ቀርቧል። በደቡባዊው የአፍሪካ ክፍለ ሀገራት የሚገኙ ባለሥልጣናት የስብሰባ አጀንዳቸው አቦሸማኔ የተሰኘው የዱር አራዊት ሆኗል። አቦሸማኔ የስብሰባው ርዕሰ ጉዳይ ለመሆን ያበቃውስ ምን ይሆን…የመሃል ቦሌዋ ጠንቋይ ከነ አስጠንቋዮቿ ለፍርድ ቀርባለች፤ አፋሮች ደግሞ አድኃሪያንን ለማጥፋት እቅድ አውጥተዋል…ከበርቴው ሲቀልበው የነበረን አንድ ዘንዶ ገበሬው ጨፍጭፎ ገድሎታል…እነዚህን ርዕሰ ጉዳዮች በማካተት ለማሳረጊያ ይሆን ዘንድ የሰማይ ቤት ዶሮ ‘ቅምሻ ቅምሻ’ ከተሰኘው ዓምድ ላይ ሌላ አንድ ቅምሻ እናክልበታለን።

በከበርቴው ይቀለብ የነበረው ዘንዶ በገበሬው ተገደለ

በኢሉባቦር ክፍለ ሀገር ዱጳ በተባለው ቀበሌ አንድ የቀድሞው የመሬት ከበርቴ ከአንድ ገበሬ ላይ እየወሰደ ይቀልበው የነበረ አንድ ዘንዶ ሰሞኑን በገበሬው ተገደለ፡፡

ነጋሽ ተመመ የተባለው የቀድሞው የመሬት ከበርቴ ከገበሬው በግ እየነጠቀ ቆሎ ተብሎ በተሰየመ እንጨት ሥር እያደረ ዘንዶውን ይቀልብ የነበረ መሆኑን ተገልጦአል፡፡

ዘንዶው ሰሞኑን ነጋሽ ተመመ በሌለበት እንደልማዱ ወደ እንጨቱ ሲመጣ በአካባቢው የተሰማሩትን የገበሬውን ከብቶች በማግኘቱ ከመካከለቻው አንዱአን በግ ሲይዛት ደርሶ ገበሬው በጦርና በመጥረቢያ ጨፍጭፎ ገድሎታል፡፡

ዘንዶው ቁመቱ ስምንት ሜትር ጎኑ 60 ሳንቲ ሜትር ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ቆዳው በኤግዚቢትነት በአካባቢው የገበሬ ማኅበር ጽ/ቤት የሚገኝ መሆኑን የዳሪሙ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ገልጸዋል፡፡

 (አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 1979 ዓ.ም)

አፋሮች አድኃሪያንን ለመደምሰስ እቅድ አወጡ

በወሎ ክ/ሀ/ ከ4 ተዋሳኝ አውራጃዎች የተውጣጡ 35 የአፋር ሕዝብ ተወካዮች በአብዮቱ እንቅስቃሴ ያላቸውን ብሔራዊ ተሳትፎ በማይወላውል ኅብረታዊ አቋም ለማሳወቅና በአካባቢያቸው የሚተናኮሉትን ፀረ ሕዝብ አድኃሪያንን ለመደምሰስ የተስማሙበትን እቅድ ለወሎ ክ/ሀ/ አስተዳዳሪ ለኮሎኔል ጌታሁን እጅጉ ከትናንት በስቲያ አቅርበዋል፡፡

(አዲስ ዘመን ሰኔ 10 ቀን 1975 ዓ.ም)

7490 የቤት ኪራይ የተከፋፈሉ የቀድሞ የቀበሌ መሪዎች ተያዙ

አሥራ አራት የሐረር ሹማምንት ከትርፍ ቤቶች ከሚሰበሰበው ከስድሳ እስከ ዘጠና ብር ለየራሳቸው ደመወዝ መድበው ሰባት ሺህ አራት መቶ ዘጠና ብር ስለበዘበዙ ተይዘው በፖሊስ ምርመራ ላይ መሆናቸው ተገለጠ፡፡

(አዲስ ዘመን ጥር 13 ቀን ቀን 1975 ዓ.ም)

በቅሎዋ ደንብራ ኮንትሮባንዲስቶቹን አጋለጠች

በወሎ ክፍለ ሀገር በወረባቡ ወረዳ አዳሜ ቀበሌ 730 የሚያወጣ ናይለን ጨርቅ ከኮንትሮባንዲስቶች ደንባራ በቅሎ ላይ የዘረፉት 4 ሰዎች በቀበሌው የገበሬ ማኅበር ሊቀመንበር አማካኝነት ባለፈው ዓርብ ተይዘዋል፡፡

አራቱ ሰዎች ሊያዙ የቻሉት ሌሎች ኮንትሮባንዲስቶች ቀረጥ ያልተከፈለበትን ናይለን ጨርቅ በ6 በቅሎዎች ጭነው በሚመላለሱበት ጊዜ ከደነበረች በቅሎ ላይ አራግፈው ጨርቁን ከተከፋፈሉ በኋላ በጫካ ውስጥ እንደተደበቁ ነው፡፡

……

አራቱ ሰዎች ለፖሊስ በሰጡት ቃል በቅሎዋን ወደ ጫካ አስገብተው ጨርቁን አራግፈው መከፋፈላቸውን አምነው አድራጎቱ አይደረስብንም በሚል ድፍረት

 የፈጸሙት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 24 ቀን 1975 ዓ.ም)

4 ጎሳዎች ተባብረው ለመኖር ተስማሙ

ከከረዩ፣ ከአዳል፣ ከኢቱና ከአሩሲ ጎሳዎች የተውጣጡ በርከት ያሉ የአገር ሽማግሌዎችና የገበሬ ማኅበራት ሊቃነ መናብርቶች ባለፈው እሑድ በኤች ቪ ኤ መተሐራ ስኳር ፋብሪካ አዳራሽ ስብሰባ አድርገው በመካከላቸው ያለውን ቅራኔ በማስቀረት በኅብረተሰባዊነት ፍልስፍና መሠረት በሰላም ተባብሮም ለመኖር ስምምነት በማድረግ አጥፊዎችን ከየመሃከላቸው መንጥሮ የሚያወጣና ለሕግ የሚያጋልጥ ከየጎሣው የተውጣጡ ሽማግሌዎች የሚገኙበት አንድ ኮሚቴ አዋቅረዋል፡፡

(አዲስ ዘመን ህዳር 12 ቀን 1979 ዓ.ም

ጠንቋይና 32 አስጠንቋዮች በቀበሌ ማኅበር ተያዙ

በቦሌ ወረዳ በ03-በ04-31 ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የሆነች ወ/ሮ ዘሐራ ፋንታ የተባለች ሴት ሕዝቡን ሥራ በማስፈታት ሕገ ወጥ የሆነ የጥንቆላ ተግባር ስትፈጽም ተገኝታ ለማስጠንቆል ከሔዱት ሰላሳ ሁለት ሰዎች ጋር ተይዛ ፖሊስ ጣቢያ ትገኛች፡፡

…….

በአንደኛዋ ተከሳሽ ቤት ይህንኑ አስነዋሪ የሆነ የማስጠንቆል ተግባር ሲፈጽሙ ከተገኙት 32 ሰዎች መካከል 22 ሴቶችና 10 ወንዶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህም ውስጥ ሁለት ወታደሮች እንደሚገኙ ምርመራውን የያዘው ወታደር ኪሮስ ሞልቶት አስረድቷል፡፡

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 10 ቀን 1975 ዓ.ም)

ሀሳብ ቀረበ

የደቡብ አፍሪካ ክፍል ሀገሮች አቦሸማኔ የተባለው የዱር አውሬ በገበሬዎች ላይ ችግር በማስከተሉ እየታደነ እንዲገደል ጥያቄ አቀረቡ፡፡

 ይህን ጥያቄ ያቀረቡት የዚምባብዌ መልዕክተኛ ሲሆኑ የቦስትዋና፣ የኬንያ፣ የሞዛምቢክ፣ የማላዊ፣ የታንዛኒያና የዛምቢያ መልዕክተኞች ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡

……

የዚምባብዌ መልዕክተኛ ዘራቸው እንዳይጠፋ ስለሚያሰጉት በዱር አራዊት ለሚያወያየው ኮሚቴ በሰጠው መግለጫ አቦሸማኔ የተባለው አውሬ በሣምንት አምስት ሰዎችና የቤት እንስሳትን እንደሚገድል ከማስረዳታቸውም በላይ የዚህ አውሬ ዘር በሌላው የአፍሪካ ክፍል እንዳይጠፋ የሚያሰጋ ቢሆንም በምሥራቅ አፍሪካ በብዛት እንደሚገኝ ገልጠዋል፡፡

እንዲሁም አቦሸማኔ እንዲገደል የቀረበውን ሀሳብ የሚቃወሙት አገሮች መልዕክተኞች አቦሸማኔ የእርሻ ሰብል ተፃራሪ የሆኑትን ዝንጀሮዎችን በማጥፋት የተፈጥሮ ሚዛኑን የሚጠብቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

(አዲስ ዘመን ሚያዚያ 15 ቀን 1975 ዓ.ም)

ቅምሻ ቅምሻ

የሰማይ ቤቱ ዶሮ

ዲያቆን፡- አባ መንግሥተ ሰማያት ያሉ ሰዎች ሰዓቱን የሚያውቁት እንዴት ነው?

ቄስ፡-ዶሮ ሲጮህ ነዋ ልጄ፡፡

ዲያቆን፡-መንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የጸዳች ስፍራ እየተባለ እንዴት ቁንቁንና ኩሱን በየቦታው የሚጥል ፍጡር እዚያ ይኖራል?

ቄስ፡-ቁንቁንና ኩሱንማ ወደ ገሀነም ዞሮ ይጥለዋል፡፡

ዲያቆን፡- ገሀነም እሳቱ ሰባት ክንድ የሚንቦገቦግና ያገኘውን ሁሉ የሚፈጅ ነው ይባላል፡፡ ታዲያ ዶሮው ቁንቁንና ኩሱን ዞሮ ሲያራግፍ እሳቱ አያቃጥለውም?

ቄስ፤ (ቆጣ ብለው)፡- እንግዲህ ካላረፈ ያንገበግበዋል ልጄ! አሉት ይባላል፡፡

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 20 ቀን 1975 ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You