አለባበስን ሙሉ የሚያደርጉ ጌጣጌጦች

ስለ አለባበስ ውበት ስናነሳ እንደተጨማሪ መዋቢያ የሚያገለግሉት የጌጣጌጦች ጉዳይ መነሳቱ አይቀሬ ነው። በአለባበሳችን የቱንም ያህል ብንዘንጥ፤ ከአለባበሳችን ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል ጌጣጌጥ እስካልተጠቀምን ድረስ የሆነ የጎደለ ነገር ያለ ያህል ይሰማናል። የተለያዩ በዓላት እና የተለያዩ ፕሮግራሞች ሲኖሩን አምረን፣ ተውበንና ደምቀን ለመገኘት ለአለባበሳችን ቅድሚያ ሰጥተን እንደምንጠነቀቅ ሁሉ ከአለባበሳችን ጋር አብረው ሊሄዱ የሚችሉ፤ ጌጣጌጦች መምረጥ ይጠበቅብናል።

የአለባበሳችን ውበት የሚለካው ከምናጠልቀው ጫማ፣ ከምናደርጋቸው የጆሮ፣ የአንገት፣ የእጅ፣ የእግር እና የፀጉር ጌጦች ጋር አብሮ ታይቶና ተመዝኖ ነው። እገሊት እኮ! የለበሰችው ልብስ ከነጌጣጌጦቹ እጅግ ውብ አድርጓታል። አቤት ያጠለቀችው የጆሮ፣ የአንገትና ወዘተ. ጌጥ እንዴት ያምራል፤ እጅግ ውብ ነው! ቁንጅት ብላለች! እያልን አድናቆታችንን የምንቸረው።

ጌጣጌጦች እንደ ተጨማሪ መዋቢያ የሚጠለቁ(የሚደረጉ) ናቸው። እነዚህም የአንገት ሀብል፣ የእጅ አምባር፣ የጣት ቀለበት፣ የጆሮ ጉትቻና የእግር አልቦ በመባል ይታወቃሉ። የሰዎች ጌጣጌጦች ለበርካታ ዓመታት ለመዋቢያነትና ለማጌጫነት ሲጠቀሙባቸው መቆየታቸው የሚታወስ ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት ጌጣጌጦች ለመዋቢያ ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ የሀብት መለኪያና መገለጫ ተደርገው ይወሰዱ እንደነበር ይነገራል።

ጌጣጌጦች እንደየጊዜው ስሪታቸው ሆነ አይነታቸው ይለያያል። በተለይ ዘመናዊ የአለባበስ ሥርዓት የሚከተሉት የፋሽኑን ዓለም ሰዎች ስንመለከት እንደሚለበሰው ልብስ አይነት የሚለበሱት ጌጦችም ሆነ ስሪታቸው ሳይቀር ዘመነኛና ቄንጠኛ ናቸው። መዋቢያ አይነታቸውና ስሪታቸው ብቻ ሳይሆን ለመዋብና ለማጌጥ የሚጠቀሙባቸው የሰውነት ክፍሎች ጭምር ሳይቀር የተለዩ ናቸው።

መዋቢያ ጌጣጌጦች እንደየ ሀገሩ ባሕል ከተለያዩ ቁሳቁሶች የሚሠሩ ሲሆን ቀደም ሲል ለጌጥነት የሚውሉት ጌጣጌጦች አብዛኞቹ ከወርቅ፣ ከአልማዝ፣ እና ከብር ይሠራሉ። አሁን ላይ ግን ከእነዚህ በተጨማሪ የከበሩት ድንጋዮች፣ ከጨሌ፣ ከብረታ ብረት፣ እና መሰል ቁሳቁሶች የሚሠሩ ሲሆን፤ እነዚህ ጌጣጌጦችም የተለያየ ይዘት፣ ቅርጽና ቀለም አላቸው። ጌጣጌጦቹ ከዘመኑ ጋር እየዘመኑና አሠራራቸውም እየተሻሻለ የሚሄዱ ሲሆኑ ዛሬ ላይ ፋሽን ሆኖ አብዛኛው ሰው ሲያጌጥበት የነበረው ጌጥ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ፋሽንነቱ ቀርቶ ሌላ አይነት ጌጥ በቦታ ይተካና የተሻለ የሚያምርና ውብ ፋሽን ሆኖ ብቅ ይላል፡፡

እነዚህ እንደ ተጨማሪ መዋቢያነት የሚያገለግሉት እጅግ ተፈላጊ የሆኑትን ጌጣጌጦች በግለሰቦችም ሆነ በተቋማት ይመረታሉ። ምርቶቹም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ገበያም የሚቀርብበት ሁኔታም እንዳለ ይስተዋላል።

ጌጣጌጦችን ከሚያመርቱት ተቋማት የእንጦጦ ዕደ ጥበብ ማዕከል አንዱ ነው። የማዕከሉ የማርኬቲንግ ባለሙያዋ ወጣት ይዲዲያ ሰለሞን እንደምትለው፤ በማዕከሉ የአንገት፣ የጆሮ፣ የእጅ፣ የእግርና ጸጉር ላይ የሚጠለቁ (የሚደረጉ) የተለያዩ ጌጣጌጦች ይመርታሉ። ጌጣጌጦቹ ባሕላዊ ይዘት ያላቸው ሲሆን፤ ለሰርግ፣ ለምርቃት፣ ለተለያዩ ፕሮግራሞችና ለመሰል ሰዎች ለሚፈልጓቸው ፕሮግራሞች ሁሉ ይውላሉ። ከየትኛውም አይነት አለባበስ ጋር አብረው የሚሄዱ ስለሆኑ ለመዋቢያና ለመዘነጫ ያገለግላሉ፡፡

እነዚህ ጌጣጌጦች ለመዋቢያነትና ለመዘነጫነት የሚያገለግሉ እንደመሆናቸው መጠን እንዲያምሩና ውብ እንዲሆኑ ተደርገው የሚሠሩ ናቸው የምትለው ወጣት ይዲዲያ፤ ጌጣጌጦቹ ከጥይት ቀለሃ የሚሠሩ ሲሆን፣ ሙሉ ለሙሉ በእጅ የሚሠሩ ናቸው፤ ለመሥራት ምንም አይነት ማሽን እንደማይጠቀሙም ትናገራለች። ጌጣጌጦች ለማምረት (አንድ የእጅ ወይም የአንገት ጌጥን) ለመሥራት የሚወስደው ጊዜ እንደሚሠራው ሥራና ዲዛይን አይነት የሚለያይ መሆኑን ጠቅሳ፤ ከግማሽ ቀን እስከ ሦስት ቀናት ጊዜ የሚፈጁ የጌጣጌጥ ሥራዎች መኖራቸው ተናግራለች።

ወጣቷ፤ ጌጣጌጦቹ በአብዛኛውን ሴቶች የሚጠቀሟቸው ቢሆኑም፤ ለወንዶችም እጅ ላይ የሚጠለቅ ጌጦችን እንደሚሠሩ ትናገራለች። ወጣት ይዲዲያ እንደምትለው፤ ጌጣ ጌጦቹ ሁሉንም የሚያማክሉና ባሕላዊ ይዘት ያላቸው መሆናቸው በሁሉም የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሴቶች ያጌጡበታል። በተለይ ከባህላዊ አልባሳት ጋር አብረው የሚሄዱ ስለሆኑ በሁሉም ተመራጭ ያደርገቸዋል። ዋጋቸውም የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው። ጌጣጌጦች የሚሠሩበት ቁሳቁስ፣ የጥሬ እቃው አቅርቦት፣ የሚፈጀው ጊዜና ጉልበት ተለክቶ ዋጋ የሚሰላ ሲሆን በየጊዜው ዋጋ ልዩነት አለው።

አሁን ላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ዜጎች ደንበኞች እንዳላቸው የምትናገረው ወጣት ይዲዲያ፤ ምርቶቹን ከሀገር ውስጥ ገበያ ባለፈ ለውጭ ሀገር ገበያ የሚያቀርቡበት ዕድል ስለመኖሩ ትናገራለች። በከተማው ባሉት ሦስት ሱቆች ምርቶቻቸውን ለሽያጭ እንደሚያቀርቡም ጠቅሳ፤ ከሀገር ውጭ በአሜሪካ፣ በካናዳና በሌሎች ሀገራትም እንዲሁ በመላክ ለገበያ እንደሚያቀርቡ ገልጻለች። ከዚህ በተጨማሪ የጌጣጌጥ ምርቶች ለማስተዋወቅ የተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ (ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ኢንስታግራም እና የመሳሰሉ) አማራጮችን በመጠቀም ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንደሚያደርጉ ትገልጻለች።

‹‹እስካሁን ጌጣጌጦችን የሚገዙ ደንበኞቻችን ስለጌጣጌጦቹ አሠራር የሚሰጡን አስተያየት በእጅጉ የሚያበረታቱ ተጨማሪ ሥራዎች እንድንሠራ የሚያደርጉ ናቸው›› የምትለው ወጣት ይዲዲያ፤ አሁን የምንሠራቸው ዲዛይኖች የበለጠ እንድናሻሽልና በዘመናዊ መንገድ እንድናቀርብ የሚያስችሉ ናቸው ብላለች። አሁን ላይ ደንበኞች ተሠርቶ የቀረበውን አይነት ከመውሰድ ይልቅ የሚፈልጉትን የጌጣጌጥ አይነት በመግለጽ በሚፈልጉት ቅርጽና ዲዛይን በምርጫቸው መሠረት በትዕዛዝ እንደሚያሠሩም ገልጻለች።

የጌጣጌጥ ሥራን የምትሠራው ወጣት ሰላማዊት በቀለ በበኩሏ ወደ ጌጣጌጥ ሥራ የገባችው በኮቪድ ወቅት እንደነበር ገልጻ፤ ከተለያዩ ነገሮች የጆሮ ጌጥ ለመሥራት ያደረገችው ሙከራና ከሠራችላቸው የቅርብ ዘመዶቿ ያገኘችው ምላሽ ውስጣዊ ፍላጎት እንዲያድርባት እንዳደረጋትና በዚያው በሥራው ተመስጣ መቅረቷን አጫውታናለች።

ሰላማዊት፤ ጌጣጌጦችን ከጨሌ፣ ከክር፣ ከብረታ ብረት፣ ከዶቃ እና ከተለያዩ ነገሮች የምትሠራ ሲሆን፤ ጌጦቹን በተለያዩ ቅርጽና ዲዛይን እያሳመረች ሙሉ በሙሉ በእጇ እንደምትሠራቸውና የእጅ ሥራዎች እንደሆኑ ትናገራለች።

የምትሠራቸው ጌጣጌጦች የጆሮ፣ የአንገት፣ የእጅ እና የእግር ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም በበዓላት ጊዜ (ለአሸንዳ፣ ለመስቀል፣ ለእሬቻና ለመሳሰሉት) የሚፈለጉና የሚደረጉ ጌጣጌጦችን እንደምትሠራ ትናግራለች፡፡

እነዚህን የጌጣጌጥ ምርቶች የምትሸጥበት መሸጫ ቦታዎች ባይኖሯትም በተለያዩ ወቅት በሚዘጋጁ ኤግዚቢሽኖች ላይ በማቅረብ እንደምታስተዋውቅና የማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እያደረገች መሆኑን ትናገራለች።

ጌጣጌጦቹ በእጅ የሚሠሩ እንደመሆናቸው ጊዜና ጉልበት የሚጠይቁ ናቸው የምትለው ወጣት ሰላማዊት፤ ሆኖም ግን ለሥራው ካላት ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ሥራውን በፍጥነት እንድትሠራ የሚያደርጋት መሆኑን ተናግራለች። ጌጣጌጦቹን ሁሉም ሰው በሚችለው አቅም ገዝቶ የሚጠቀምባቸው ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ሲሆን፤ ዋጋቸውም 100 እስከ 350 ብር ድረስ የሚሸጡ እንደሆኑ ገልጻ፤ ብዙዎች ያለችበት ቦታ ድረስ ፈልገው በመምጣት እንደሚገዟት ነው ያጫወተችን። በቀጣይም ጌጣጌጦችን ከተለያዩ ነገሮችና በተለያዩ ቅርጽና ዲዛይኖች በመሥራት ተደራሽነቷን የማስፋት እቅድ እንዳላት ነው የገለጸችው።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You