በርካታ የአትሌቲክስ አድናቂዎች ስፖርቱ አንደበት ኖሮት ‹‹በታሪክ ምርጡ አትሌት ማነው?›› ቢባል ኢትዮጵያዊውን ታላቅ አትሌት አበበ ቢቂላን ያስቀድማል ይላሉ። ዘመናትን አልፎ አሁንም ድረስ ስሙ ከገነነበት ያልወረደበት ምክንያትም ማንም ሊደግመው የማይችለው ድንቅ ታሪክ በመጻፉ ነው። ቆፍጣናው ወታደር ከኦሊምፒክ እስከ ፓራሊምፒክ አስደናቂ ገድሎች ያሉት ቢሆንም ጎልቶ የሚጠቀሰው ግን የሩጫ ሕይወቱ ነው። አበበ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ ባለፈው ጥቅምት 15/2016 ሃምሳ ዓመት ሞላው። በዛሬው የስፖርት ማሕደር አምድም የአበበን ሕይወት የቀየረውን ክስተትና ከአትሌቲክስ ባሻገር የነበረውን ሌላኛውን ገጽታ እንዳስሳለን።
አስደንጋጩ የመኪና አደጋ አበበ ቢቂላ ላይ የደረሰው እአአ በ1969 ነበር። በወርሃ የካቲት አንድ ምሽት ቮልስ ዋገን መኪናውን ያሽከረክር የነበረው ታላቁ አትሌት ያልተጠበቀ አደጋ የደረሰበት ስለመሆኑ የዓለም መገናኛ ብዙሃን በዜናዎቻቸው ተቀባበሉት። የአበበን የሕይወት ታሪክ የጻፈው ቲም ጁዳ ስለ አደጋው መንስኤ በርካታ መላምቶች ይነሱ እንጂ በትክክል ሊጠቀስ የሚችል ምክንያት አለመታወቁን ይገልጻል። ድራማዊ በሆነ ሁኔታ ብሄራዊ ጀግናዋን ልታጣ የተቃረበችው ኢትዮጵያ በሃገር ውስጥ ሕክምና ለውጥ ማምጣት የማይቻል በመሆኑ ከጥቂት ቀናት ክትትል በኋላ ወደ እንግሊዝ ሄዶ የተሻለ ሕክምና እንዲያገኝ አፋጣኝ ውሳኔ ላይ ተደረሰ።
እንኳን ተራ ሰው አትሌቶች በቀላሉ የማይደፍሩትን 42 ኪሎ ሜትር ሮጦ ከጨረሰም በኋላ ሳይደክም ተጨማሪ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የሚታወቀው የአበበ ቀልጣፋ ሰውነት በወቅቱ መንቀሳቀስ ተስኖት ነበር። ከቀዶ ሕክምና መልስ ማራቶንን በድል ያጠናቀቀው
ጀግናው ሰው፣ በዚያ ግለት ባዶ እግሩን በመሮጥ በርካቶች እጃቸውን በአፋቸው እንዲጭኑ ምክንያት የነበረው የአበበ እግር አልታዘዝ ብሎ (ፓራላይዝድ) በመሆኑ ምክንያት ለስምንት ወራት ሆስፒታል ውስጥ በክትትል እንዲቆይ ሆነ። ከጊዜ በኋላም ለሩጫ የተፈጠረ እግሩ ደግሞ መራመድ ባይችልም ለበርካቶች ተምሳሌትና መነሳሳት ምክንያት የሆነው ጠንካራ መንፈሱ ግን አብሮት ነበር። እናም በሆስፒታል ውስጥ ሆኖ በዊልቸር ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በመሳተፍ ራሱን ለተወዳዳሪነት ሊያበቃ ችሏል።
የመጀመሪያውን ውድድሩንም በዚያው በለንደን በተዘጋጀ የአካል ጉዳተኞች ውድድር ላይ በቀስት ውርወራ እና በጠረዼዛ ቴኒስ ስፖርቶች ነበር ያደረገው። በእርግጥም ድልን በድል ላይ ሲደራርብ የኖረውና ኪሎ ሜትሮችን እንደቀላል ሲያቆራርጥ የነበረ ሰው በዊልቸር ተገድቦ ማየቱ ልብን ይሰብራል። ሆኖም ለጉዳቱ እጅ ሳይሰጥ ሕይወቱ የሆነውን ስፖርት በሌላ መልክ ሲከውን መመልከት የጥንካሬውን ልክ የሚያንጸባርቅና በርካቶችን ሊያስተምር የሚችል ነው።
ጎበዝ ቀስተኛ የሆነው ጀግናው አትሌት አበበ ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ኖርዌይ ላይ በተደረገ ውድድር በቀስት፣ ጠረዼዛ ቴኒስ እንዲሁም በውሾች በሚጎተት ጋሪ የበረዶ ላይ ሃገር አቋራጭ በመሳተፍ በርካቶችን አስደነቀ። በኢትዮጵያ በማይታወቀው የውሾች ጋሪ ጉተታ ውድድር ላይም 16ቱን ተወዳዳሪዎች ድል በመንሳት 1 ሰዓት ከ16 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ በማስመዝገብ ሊያጠናቅቅ ችሏል። በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ውስጥም በእነዚህ ስፖርቶች በመወዳደር አበበ ምናልባትም ብቸኛው ሰው ነው።
በዚህ ሁኔታ የቀጠለው አበበ እአአ በ1972 በተካሄደው የሙኒክ ኦሊምፒክ በክብር እንግድነት እንዲገኝ በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ተጋበዘ። በመክፈቻው ስነስርዓት ላይ ሲገኝም አትሌቶች እንዲሁም በስፍራው የተገኙ የስፖርት ቤተሰቦች ታላቅ አክብሮትና ክብር ሊያሳዩት ችለዋል። በወቅቱ የማራቶን ውድድር አሸናፊ የነበረው አሜሪካዊው አትሌት ፍራንክ ሾርተር ድሉን ያከበረው የአበበን እጅ በመጨበጥ ነበር። ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ አልፎ በኢትዮጵያ ባልተለመደ መልክ ለመጀመሪያ ጊዜ በታላቁ የውድድር መድረክ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ሃገሩን ያስጠራው ኋላ ላይም በአስከፊ የመኪና አደጋ ዊልቸር ላይ የዋለው አበበ ተገቢው ክብርና ዕውቅና በኦሊምፒክ ከተሰጠው በኋላ በምድር ላይ የነበረው ቆይታ አጭር ነበር።
በቀጣዩ ዓመት የ41ኛ ዓመት ልደት ሻማዎቹን ያጠፋው ጀግና ከመኪና አደጋው ጋር በተያያዘ ከደረሰበት ውስብስብ ጉዳት ጋር በተያያዘ በሰውነቱ ውስጥ ደም መፍሰሱ ሕይወቱ በአጭሩ እንዲቀጭ ምክንያት ሆነ። አደጋውን ካስተናገደ አራት ዓመታት በኋላም በማይቀርበት የሞት እቅፍ አሸለበ። በወቅቱም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሃዘን ታወጀ፤ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለስላሴን ጨምሮ 65ሺ ሰዎች በተገኙበት በታላቅ ወታደራዊ አጀብ በቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን እንዲያርፍ ተደረገ። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጀግና እንደመሆኑ በመቃብሩ ላይ የነሐስ ሐውልት ሲደረግ ስሙ ሕያው ነውና በትውልዱ ውስጥ ሰርጾ ይኖር ዘንድ ትምህርት ቤቶች፣ ስታዲየሞችና ሌሎች ተቋማት ተሰየሙለት።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2016