ጭር ሲል የማይወደው ሠዓሊ

የዘወትር ትራንስፖርቱ የኤሌክትሪክ ሞተር ነው። ግን ሞተሩን በአዲስነቱ ከገበያ አልገዛውም። ከቀድሞ ባለቤቱ ጋር እያለ ከፍተኛ አደጋ ደርሶበት ከጥቅም ውጭ መሆኑን ብዙዎች ተስማምተውበታል። የኤሌክትሪክ ሞተሩ ነብስ ዘርቶ ያገለግላል ብሎ ያልጠበቀው የቀድሞ ባለቤትም ለሠዓሊ ሰለሞን ከበደ በሰባት ሺህ ብር ሸጠለት። ለእድሳቱ መኪና የሚገዛ ብር አውጥቼበታለሁ ቢልም ሞተሩን ለመጠገን የሄደበት ርቀት ርካታ እንደሚሰጠው ይናገራል። አብዛኛው እቃ በሀገር ውስጥ ስለማገይገኝ ከውጭ እያዘዘ በርካታ ጊዜም ወጪ አድርጎበታል።

በኤሌክትሪክ ከሚሰራው ሞተር በፊት በኤሌክትሪክ የሚሰራ ስኩተር ነበረው። ብስክሌት ከከተማ አልፎ በየመልካምድሩ መንዳት ዋና መዝናኛው ነው። ግን ከሥሙ በፊት ማዕረግ የሆነው፤ እንዲሁም መተዳደሪያው ሥዕል ነው። ሠዓሊ ሰለሞን ከበደ ውልደቱ አዲስ አበባ ሰሜን ማዘጋጃ ነው። በቤታቸው አራት ናቸው፤ እናትና አባቱ እሱና ታናሽ እህቱ። እድለኛ ሆነን ዘመናችን ቆንጆ ነበር የሚለው ሠዓሊው በዘመኑ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ውስን ስለነበሩ አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፈው ነገሮችን በመቆራረጥ፣ በመፍጠር እንዲሁም ብዙ እንቅስቃሴ ያላቸውን ጨዋታዎች በመጫወት መሆኑን ያስታውሳል። ለቡሄ ከቆርኪና ከዱላ መሳሪያ አዘጋጅቶ ሆያ ሆዬ ጨፍሮ፤ ለእንቁጣጣሽ አበባ ሥሎ ወዳጅ ቤተሰብን እንኳን አደረሳችሁ ብሎ ልጅነቱን በደንብ ኖሮታል።

ጥበብ እድገት የሕዝብ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለበት ነው። ከዘጠነኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርቱን ድል በትግል ትምህርት ቤት ተከታትሏል። በትምህርቱም የተሻለ ውጤት የሚያመጣ ጎበዝ ተማሪ ነበር። ለዛም ይሆናል ወላጆቹ በሚሰራቸው ሥዕሎች እየተደነቁ ከማበረታታት ውጪ አጥና፣ ጊዜህን አታባክንና መሰል በብዙ የኪነጥበብ ፈላጊ ልጆች ቤት የሚሰሙ ጭቅጭቆች እነሱ ቤት አልነበሩም። ሥዕል ይወዳል፤ ለዚህም ለሥዕል ትምህርትም ለየት ያለ ትኩረት ያደርጋል።

ሆኖም እሱ በተማረባቸው ትምህርት ቤቶች አብዛኛውን ጊዜ በሥዕል መምህርነት የሚመደቡት መምህራን በቋሚነት የሌላ ትምህርት መምህራን የሆኑና ሥዕል ሙያቸው ባይሆንም በተደራቢነት ማስተማር ይገደዱ ነበር። ሆኖም እድለኛ ሲሆን ጥበብ እድገት የሕዝብ ትምህርት ቤት እየተማረ ሳለ ሥዕል ሙያው የሆነ መምህር ገጠመው። ያኔ ሥዕልን የተማረ በዘርፉ እውቀት ያለው መምህር ሲገጥመው የተሻለ ድጋፍ ነበረው። በትምህርት ቤት ውስጥ የሥነ-ጥበብ ክበብ ነበረ፤ በዛም ተሳታፊ ነበር።

“ቤተሰቦቼ በምሰራው ነገር ደስተኞች ነበሩ፤ ለዚህ ያበቃኝም የነሱ ድጋፍ ነው።” የሚለው ሠዓሊው፤ የልጅነት ጨዋታዎች ቢስቡትም ባገኘው አጋጣሚ ሥዕል መሣል መለያው ነበር። የመጀመሪያው ቆንጆ ሥራዬ በማለት የሚያስታውሰው የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እያለ በበላው የአቡወለድ ብስኩት ካርቶን ላይ የሣለውን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሥል ነው። በወቅቱ እናቱ በልጇ ሥራ በመደሰቷ ለሰፈር ሰው እየዞረች “እዩት ልጄ የሳለውን” በማለት ማሳየቷ ይበልጥ ሞራል እንደሆነው ያስታውሳል።

በትምህርት ቤት ቆይታው ከመሰሎቹ ጋር የትምህርት ቤታቸውን ግድግዳ ያስውባሉ። ከዚህ በተጨማሪ ደብተሩ ገለጥ ሲደረግ በሚመለከቱት አስደናቂ ሥዕል የሚገረሙ ሰዎች አንተማ ሠዓሊ ነው የምትሆነው እያሉ የወደፊቱን ተነበዩለት። ያኔ እሱም ሠዓሊ መሆን እንዳለበት ተረዳ። የሰውም ማበረታታት እሱም በውስጡ ያለው ችሎታና ፍላጎት ተደምሮ 12 እንደጨረሰ በቀጥታ አለ ፈለገ ሰላም የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤትን ተቀላቀለ። በትምህርት ቤቱ የነበረውን ቆይታ ነጻነት የተሞላበትና ስለጥበብ ለማሰብ ብዙ ጊዜ የሚገኝበት፤ አስፈላጊው ድጋፍ ስለሚገኝ እምቅ አቅምና ተሰጥኦን ለማውጣት የሚቻልበት ጊዜ በማለት ያስታውሰዋል። የአራት ዓመቱን ትምህርተ አጠናቆ በ2001 ዓ.ም በፔይንቲንግ በዲግሪ በጥሩ ውጤት ተመርቋል።

በአለፈለገሰላም ተማሪ እያለ ያስበው የነበረውና ከተመረቀ በኋላ የገጠመው ነገር አልገጥም ብሎት ትንሽ ተቸግሮ ነበር። ተማሪ ሳለ ያስብ የነበረው ትምህርቱን እንደጨረሰ የራሱን ስቱዲዮ ከፍቶ ሥዕል መሳልን ብቻ ነበር። እናም እንደተመረቀ አደረገው። የተወሰነ ጊዜ የሙሉ ጊዜ የስቱዲዮ ሠዓሊ በመሆን ኑሮን ታግሏል። ግን ሲያየው በባዶ ኪስ ሥም ያልተከለ ጀማሪ ሠዓሊ ሆኖ የሙሉ ጊዜ የስቱዲዮ ሠዓሊ መሆን ሊያወላዳው አልቻለም። የስቱዲዮ ወጪን ለመሸፈንም ሆነ ለስዕሉ አስፈላጊ የሆኑትን ቀለምና መሰል ግብዓት ለማሟላት ገንዘብ የግድ ያስፈልግ ነበር። ቀለሞቹ ደግሞ ከውጭ የሚመጡ ስለሆነ ዋጋቸው ወደድ ይላል። ቀለሞቹን ለመግዛት ሥዕል መሳያውን ሸራ ለማዘጋጀት እንዲሁም የዕለት ወጪን ለመሸፈን ገንዘብ ያስፈልጋል። ይሄን ለማሟላት ግዴታ ገቢ እንደሚያስፈልገው ሲረዳ በአንድ የግል ትምህርት ቤት ማስተማር ጀመረ።

ሠዓሊ ሰለሞን ሰዓቱን አብቃቅቶ በመምህርነትና በስቱዲዮ ሠዓሊነት ላይ ተሰማራ። ያኔ የተማረውን ሥዕል በትምህርት ቤቶች ለልጆች ያስተምራል፤ በሚቀረው ጊዜ ሥዕሉን ይስላል። በማስተማር ከሚያገኘው ገቢ እየቀነሰ ለሥዕሉ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ማሟላት ጀመረ። በዚህ ሁኔታ ሥዕሉን እየሸጠ ገቢ ማግኘት ሲጀመር ከሚያስተምርበት ሰዓት እየቀነሰ አብዛኛውን ጊዜ ለሥዕል ሥራ መስጠት ጀመረ። በሂደት በሥራው እየዳበረ በሥዕል አድናቂዎች ዘንድም ሥሙን እያኖረ ሲሄድ ኑሮም ሥራም ቀለለው።

ሠዓሊው በግሉ ሦስት ኤግዚቢሽኖችን አሳይቷል። በግሩፕ ከሌሎች ሰዓሊያን ጋር በመሆን በርካታ ኤግዚብሽኖች ላይ ሥራውን አሳይቷል። በዓመት አንዴ በሂልተን ሆቴል በሚዘጋጀው “ቢግ አርት ሴል“ ላይ በቋሚነት ሥራዎቹን ያቀርባል። በጎልፍ ክለብ፣ በመኮንኖች ክበብ በሚዘጋጁ የአርት ኤግዚቢሽኖች ላይ ይሳተፋል። በሚዘጋጁ የሥዕል ውድድሮች ላይ ይሳተፋል። በቅርቡ በፈረንሳይ ኤምባሲ አዘጋጅነት በተካሄደው ግንብ ላይ በሚሰራ ሥዕል (ስትሬት አርት) ውድድር ላይ ተካፍሎ አራተኛ በመውጣቱ አሌያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ የሥዕል ኤግዚቢሽን የማሳየት እድል አግኝቷል። አንድ ወር በቆየው ኤግዚቢሽንም በርካታ ሥራዎቹን የመሸጥ እድል አግኝቷል።

ለሥዕሎቼ ብዙ ጊዜ ዋጋ አላወጣም የሚለው ሰዓሊው፤ ሰው ሥራዬን ወዶት አቅም ስለሌለው ብቻ እንዳይገዛው አላደርግም ይላል። ሥዕሉን የወደደው ሰው ገንዘብ ከሌለው እሱ አለኝ ብሎ የሚጠራው ዋጋ የሥራውን ክብር የማይቀንስ ከሆነ እንደሚስማማ ይናገራል። በትናንሽ ሳይዝ (30 በ30) የሚሰሩት ስዕሎች ከስምንት ሺህ ብር አንስቶ መጠናቸው ከፍ ያሉት እስከ 80ሺ ብር ይሸጣሉ። ሥዕልን ሸራ ላይ ከመሳል በተጨማሪ ሆቴሎችን ካፌዎችንና መኖሪያ ቤቶችን በደንበኞቹ ፍላጎት የማስዋብ አገልግሎት ይሰጣል። የሥዕል ሥራው መደበኛ ገዢ የሆኑ ሰዎች የወደዱትን ሥዕል ወስደው በሂደት ክፍያ የሚፈጽሙበት ሁኔታ መኖሩን ይናገራል።

አርጅተው ጥቅም እንዳይሰጡ ተደርገው የተጣሉ ነገሮችን በመሰብሰብ ድጋሚ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የሶል መለያው ነው። ሞተር ሳይክል ብስክሌት የሚወዳቸው ነገሮች ናቸው። ከጥቅም ውጭ የሆኑ ሞተሮችን በመሰብሰብ ሙሉ የውጭ ገጽታቸውም ሆነ የውስጥ አካላቸው አድሶ ሙሉ ግልጋሎት እንዲሰጡ ያደርጋል። “አድቬንቸር ደስ ይለኛል” የሚለው ሰዓሊው ያነሳሳኛልም ይላል፤ ብስክሌት የሚወደውም ለዛ መሆኑን ይናገራል።

በብስክሌቱ የማይዳስሰው መልካምድር የለም። ተራራ፣ ጫካ፣ ሜዳ ሸንተረሩን በብስክሌት ያቆራርጣል። መጀመሪያ አካባቢ ብስክሌቱና እሱ ነበሩ የሽርሽሩ አካላት። ከቆይታ በኋላ አዲስ አበባ ማውንቴን ባይከርስ ግሩፕ የተሰኘ የሱ መሰል በብስክሌት ከከተማ ወጣ የማለት ፍላጎት ያላቸውን አባላት ሲያገኝ ተቀላቅሎ አብረው ጉዞ ማድረግ ጀመሩ። በጋራ መሆኑ ረዥም ጉዞ ለመጓዝ እንደሚያስችልና እሱም ከግሩፑ አባላት ጋር በመሆን ከአዲስ አበባ ሐዋሳ፣ ወንጪ ድረስ መጓዛቸውን ያስታውሳል። ጉዞ በሚያደርጉበት ሰዓት የተለያዩ በዓሎችንና ማሕበረሰቦች በቅርበት ማየት ይቻላል። ይሄ ለሠዓሊ አሪፍ ግብዓት እንደሚሆን በመጥቀስ እሱም በጉዞው ፎቶ እንደሚያነሳና በተጓዘበት አካባባቢ ከሚኖሩ ማሕበረሰቦች ጋር ሲያወራ በርካታ ነገሮችን እንደሚያገኝና ለሥዕል ሥራው ጥሩ ግብዓት መሆኑን ይናገራል።

ሶል ለሥዕል ሥራው የሚሆን ተመስጦ የሚያገኘው ከግርግር ነው። እንደሌሎች የኪነጥበብ ሰዎች “ዛሬ” መታለችና ዝም በሉልኝ፤ ብቻዬን ተውኝ ይሉት ነገር እሱጋ ቦታ የለውም። በራሱ ቃል እንዲያውም “ጭር ሲል አልወድም” በማለት ይገልጸዋል። መኖሪያ ቤቱ ውስጥ በሚገኘው ስቱዲዮ ሲሰራ ጓደኞቹ መተው ቡና ተፈልቶ እየተጠጣና እየተጫወቱ እንደሚሰራ ይናገራል። እሱና ስከች ቡኩ አይነጣጠሉም። በሄደበት አብራው ትጓዛለች፤ እናም የሀሳብ መምጫው አይታወቅምና በሄደበት ሀሳብ ከመጣለት እዛው ይነድፋል። ዘመኑ የማሕበራዊ ሚድያ ነውና እሱም ዘመን ያመጣቸው ማሕበራዊ የትስስር ገጾች አሉት። በዛ ላይ ሥራዎቹን ይለቃል፤ የወደዳቸው እነሱን ስለመግዛትም ሆኖ ሌላ ስለማሳል በማሕበራዊ ሚድያ ያናግሩታል።

ከትዳር አጋሩ ወይዘሮ ጣዕሞ ብርሀኑ ጋር ከተጣመረ ሁለት ዓመት ሞላው። በቅርቡ ደግሞ የሴት ልጅ አባት ሆኗል። አብዛኛው ሥራዬን የሚገዙት ለጉብኝት የሚመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ናቸው የሚለው ሠዓሊው ሰለሞን፤ ሥራውን በቋሚነት ለማኩሻ አርት ጋለሪ እንደሚያስረክብ ይናገራል። በጋለሪው ሥራቸው በኮሚሽን የሚሸጥ ሲሆን አብዛኛው ገዢ ቀጥታ ከሰዓሊው ጋር አይገናኝም። ሆኖም ስዕሉን በጣም የወደዱት ሸማቾች ሰዓሊውን ማግኘት እንፈልጋለን እያሉ እንደሚያገኙት ይናገራል። ከዛ ውጭ በኤግዚብሽንና በቀጥታ እሱን በማግኘት የሚገዙትን ካልሆነ በጋለሪ የሚገዙት አብዛኛው የሥዕሉ ገዥዎችን ማንነት እንደማያውቅ ይናገራል። ከገቢያቸው ቆጥበው፣ አልሞላ ሲል ተበድረው ሥዕሉን የሚገዙ ኢትዮጵያውያን ደንበኞቹም በርካቶች ናቸው።

በገበያ ላይ ለመቆየት በተቻለ አቅም ሰዓሊው ባገኘው አጋጣሚ ተጠቅሞ ሥዕል እንደሚስል ራሱን ማሳወቅ አለበት። እኔ የማውቃቸው ጎበዝ ሰዓሊዎች ሆነው ዘግተው የተቀመጡ ሰዓሊዎች አሉ የሚለው ሠዓሊው፤ ሰው የግድ ስለሠዓሊው ማወቅ አለበት ይላል። ስለሠዓሊው ማንነት ምን እንደሚሰራ መታወቅ አለበት። በሀገራችን ገበያ የማፈላለግ ገዥዎችን የማፈላለግ (የኔትዎርኪንግና የማርኬቲንግ) ሥራ ባለሙያው ራሱ መስራት ይጠበቅበታል። በውጭው ዓለም ጋለሪዎች እንዲሁም ሥዕል ሰብሳቢዎች አፈላልገው ቤቱ ድረስ የሚመጡ መሆኑን በመጥቀስ በሀገራችን የግድ ሠዓሊው መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅበት ያነሳል።

ስዕል ከጀመረ ቶሎ አይነሳም፤ ለዚህም ይመስላል አብዛኞቹ ሥዕሎቹን በቶሎ ያጠናቅቃል። ለዚህም አብዛኞቹ ሥዕሎች ቢበዛ በሦስት ቀናት ይጠናቀቃሉ። ሆኖም እስከ ሦስት ወራት የወሰዱበት ሥራዎችም አሉት። አብዛኞቹ ስዕሎቹ ተፈጥሮና (ኔቸር) መልካ ከተማ (ሲቲ ስኬፕ) ላይ ያተኮሩ ናቸው። የሚስልበት የአሳሳል ዘይቤ “ኢምፕሬሽኒዝም″ ይሰኛል። የሱ ስዕሎች ትክክለኛውን ነገር አስመስሎ መሳል ሳይሆን የስዕሉን ስሜት ማምጣት ላይ ያተኮረ ነው። በአብዛኛው በተለይ ለትልልቅ ስዕሎቹ አክለሪክ ቀለም ምርጫው ነው። አክለሪክ ቶሎ የሚደርቅ የቀለም አይነት በመሆኑ ይበልጥ እንዲጠቀመው ምክንያት ሆኗል። የሥዕሎቹ መጠን አነስተኛ ሲሆንና ለቀማ የሚፈልጉ ስዕሎች ሲሆኑ የዘይት ቀለም ይጠቀማል። የዘይት ቀለም ለመድረቅ እስከ አንድ ወር ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑ ብዙም ምርጫው አይደለም።

“አልሸጣቸውም፤ የግል ስብስቦቼ ናቸው” ብሎ ለሚያስቀራቸው ሥዕሎች ርዕስ ይሰጣል። ለገበያ የሚያወጣቸው ሥዕሎች ላይ ርዕስ ከመሰየም ይቆጠባል። ተመልካች የፈለገውን እንዲሰይም ሙሉ ነጻነት ይሰጣል። ለተመልካች ርዕስ ማስቀመጥ ይገድባል ብሎ ስለሚያስብ ተመልካች የመረጠውን ርዕስ እንዲሰይምና እንዲተረጉም ነጻነት መስጠትን ይመርጣል። ሥዕል መሣልም፣ ማስቀመጥም ይወዳል። ለዚህም ይመስላል ከ35 በላይ የራሱን ሥዕሎች የማይሸጡ ብሎ ወስኖ ለይቷቸዋል። ሆኖም ከዚህ ቀደም አንድ የሥዕል ገዢው ቀድሞ የገዛቸውን ሥዕሎቹን የያዘበት መንገድ ስለገረመው አይሸጡም ብሎ ከለያቸው ሥዕሎቹ መሃል አንዱን በነጻ፣ በስጦታ አበርክቶለታል። ቤት ውስጥ ያስቀመጣቸውን ሥራዎቹን ሲያይ ለሌላም ሥራ እንደሚያነሳሱት ይናገራል።

“አድቬንቸር እወዳለሁ” የሚለው ሰዓሊው ለዚህም ሳይክሉ እንደሚረዳውና የተበላሹ የተባሉ ነገሮችን ጠግኖ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስደስተው መሆኑን ይናገራል። በተለይ እሁድ ቀን መርካቶ ከሚገኘው ምናለሽ ተራ አይጠፋም። ምናለሽ ተራ አይሰሩም ተብለው የተጣሉ እቃዎች በብዛት ለገበያ ይቀርባሉ። ከገበያው ላይ ቀልቡን የሳቡትን እቃዎች ሸምቶ ይመለሳል። ከዛ እነሱን በፈርጅ በፈርጁ “እንዴት ቢሆኑ ይሻላል?” ብሎ ማሰብና እነሱን መጠገን ጊዜ ሰጥቶ የሚሰራው መዝናኛው ነው። “በዚ መልክ የምሰራቸውን እቃዎች አልሸጣቸውም፤ አስቀምጣቸዋለሁ” የሚለው ሠዓሊው፤ ነገር ግን ለራሱ ከመጠገን ባለፈ ይሄን ችሎታውን የሚያውቁ ሰዎች የድሮ እቃ ሲበላሽባቸው እንዲጠግንላቸው ያመጡለታል። እሱም እንደነበረ አድርጎ መጠገኑን ተክኖበታል።

ከልጅነቱ አንስቶ መፍቻ ይዞ መታገል የወደቀን እቃ ለመጠገን መጣር መታወቂያው ነበር። በዚህም ልምድ ትምህርት ቤት ሆኖለታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በዩቲዩብ ቪድዮዎችን በማየት እራሱን ማስተማሩ የበለጠ አግዞታል። ምግብ አልመርጥም ያገኘሁትን እበላለሁ የሚለው ሠዓሊው፤ ሆኖም ከምግብ አትክልትና ፍራፍሬ አይሰለቸኝም ይላል።

አዳዲስ ነገር መሞከር ያስደስተዋል፤ ከሙከራዎቹ ውስጥ በካሴት ክር ላይ የሰራቸው የበርካታ ታዋቂ ሰዎች ምሥሎች ይገኛሉ። የካሴት ምርጫው በካሴት ሙዚቃ እየሰማ ከማደጉ ጋር ይገናኛል። ቤት ውስጥ አጎቱ ሙዚቃ ይወድ ስለነበር በርካታ ካሴት እንደነበር ያስታውሳል። ሲያድግ ካሴት እየነካ፣ እንዲሁም እየሰማ በማደጉ በይበልጥ በዘመኑ ይሰማቸው የነበሩትን ከ50 በላይ ድምጻውያንና የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾችን የካሴት ክርን በማጣበቅ ምሥላቸውን በማስፈር አስታውሷቸዋል። በቀጣይ ከሀገር ተሻግሮ ሥራዎቹን ማሳየትን ያልማል፤ እኛም ይህ ውጥኑ ይሰምርለት ዘንድ በመመኘት አበቃን።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2016

Recommended For You