የእደጥበብ ባለሞያዋ

 

ከቢለዋ ከፍ ባለ የሥለት መሣሪያ በመጠቀም፤ ቀርከሃውን እየሰነጠቁ ያዘጋጃሉ። ሥራቸውን በፍጥነት ሲያከናውኑ፤ የሚጠቀሙበት ሥለታም መሣሪያ ለአደጋ እንዳጋያልጣቸው የሚል ስጋት ውስጥ ይጨምራል። እጃቸው ሥራውን በመልመዱ ሳት እንኳን ሳይሉ፤ በፍጥነት በያዙት የሥለት መሣሪያ የመሰንጠቁን ሥራ ያከናውናሉ።

የተሰነጠቀው ቀርከሃም ቢሆን እጅ መውጋቱ አይቀርም። ቀርከሃውን ለማለስለስ ጥቅም ላይ የሚውለው ኬሚካልም ለመተንፈሻ አካል ጠንቅ መሆኑ አይቀሬ ነው። እነዚህን ሁሉ ነገሮች እያየ ያሰበ ሰው መጨነቁ አይቀርም። እርሳቸው ግን ከሥራው ጋር ከመለማመዳቸው የተነሣ አይጠነቀቁም። አልፎ አልፎ የሚጠቀሙበት ሥለታም መሣሪያም ሆነ የተሰነጠቀው ቀርከሃ እጃቸው ላይ ጉዳት ቢያደርስባቸው እንኳን በአልኮል ጠርገው ሥራቸውን ይቀጥላሉ፤ ጉዳቱን ምክንያት አድርገው ሥራቸውን አያቋርጡም።

በሥለታሙ መሣሪያ እየሰነጠቁ ባዘጋጁት ቀርከሃ በእንሥራ ቅርጽ ለጌጥና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ እንዲሁም የመብራት አምፖል መያዣ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ማስቀመጫ፣ ማቅረቢያዎችና የተለያዩ ቁሶችን ይሠራሉ። የሥራ ውጤቶቻቸውም ለእይታ የሚስቡና ውበት ያላቸው ናቸው። ጥንካሬያቸውም ቢሆን ከእንጨት ውጤቶች ያልተናነሰ እንደሆነ ገልጸውልናል። እንዲህ ያለውን የእጅ ጥበብ ሙያ የተካኑት ከታዳጊነት እድሜያቸው ጀምሮ በመሆኑ በሙያው ውስጥ ለረዥም ዓመታት ቆይተዋል።

በቀርከሃ የተለያዩ ነገሮችን መሥራትን በሥልጠና ያዳበሩት ሙያ ሲሆን፤ ሥራ የመቀጠር ዕድልም አስገኝቶላቸዋል። በኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው መሥራት የጀመሩት የቀርከሃ ባለሙያ በተፈለገበት ዘመን ነበር። ክህሎቱ፣ ልምዱና የሙያ ፍላጎቱ በሥራው ላይ ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ አድርጓቸዋል።

የእጅ ጥበበኛዋ ወይዘሮ ሙሉ ወንድሙ ይባላሉ። ሥለ የእጅ ጥበብ ሥራቸው፣ ልጅነታቸውንና እድገታቸውን፣ የቤተሰባቸውን ሁኔታ፣ ስለወደፊት እቅዳቸው አንስተን በሰፊው ተጨዋውተናል። የሙያ ባለቤት ብቻ ሳይሆኑ፤ የኑሮ ፈተናንም ተጋፍጠው ለመወጣት ያደረጉት ውጣ ውረድና ሥራ ወዳድነታቸው፣ ለሚሰሩበት ድርጅትም ያላቸው ተቆርቋሪነት ለሌሎችም አርአያ ሆነው አግኝተናቸዋል።

ተወልደው ያደጉበት አካባቢና የኑሮ ሁኔታ

ወይዘሮ ሙሉ ወንድሙ እንዳጫወቱን፤ የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ መርካቶ አካባቢ ነው። እድገታቸው ደግሞ ፈረንሳይ ለጋሲዮን በተለምዶ 41 እየሱስ ወይም አስራተ ካሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰም ትምህርት ቤት ገብተዋል። ይሁን እንጂ 8 ክፍል በላይ አልዘለቁም። የቤተሰባቸው የኑሮ ሁኔታ በጣም ያስጨንቃቸው ነበር። አባታቸው የቀን ሥራ ይሠሩ ነበር።

ገቢያቸው ቋሚ ባለመሆኑ ባዶ እጃቸውን ወደ ቤት የሚገቡበት ጊዜ ቀላል አልነበረም። እናታቸው የቤት እመቤት ናቸው። እናታቸው በስንደዶና አለላ ሰፌድ፣ መሶብና የተለያዩ የሥፌት ሥራዎችን እየሰሩ በመሸጥ በተጨማሪም በመኖሪያቸው አካባቢ ከሚገኝ ጫካ ውስጥ ቅጠል ጠርገው ለገበያ በማቅረብ ኑሮን ለመደጎም ጥረት ቢያደርጉም የሚገኘው ገቢ የቤተሰብ ኑሮን የሚያሻሽል አልሆነም። የቤተሰቡ የኑሮ ሁኔታ ከእለት ወደ እለት እየከበደ የእለት ጉርስም ለማሟላት ፈተና ሆነ። በዚህ የተነሳ የእርሳቸውና እህታቸውም የተለያዩ ፍላጎቶች ሊሟላላቸው አልቻለም። ወይዘሮ ሙሉ በየጊዜው የሚያዩትን ነገር መቋቋም አልቻሉም። ቤተሰባቸውን ለመርዳት፣ ለእርሳቸውና ለእህታቸው የሚያስፈልጋቸውንም ለማሟላት ትምህርታቸውን አቋርጠው ገቢ ሊያስገኝላቸው በሚችል ሥራ ላይ ለመሰማራት ወሰኑ።

የቤተሰባቸው የችግር ሁኔታ አስገድዷቸው ትምህርታቸውን እስከመተው ደረጃ የደረሱት ወይዘሮ ሙሉ፤ የሥራ ምርጫም አልነበራቸውም። እቅዳቸው እናታቸው ይሰሩ የነበረውን ከጫካ ውስጥ ቅጠል በመሰብሰብ ሸጠው ገቢ ለማግኘት ነበር። በመኖሪያ አካባቢያቸው በሚገኘው ደን ውስጥ ገብተው የረገፈ ቅጠል ጠርገው በማዳበሪያ ሞልተው አንዱን ሸክም በሁለት ብር ከሃምሣ ሣንቲም በመሸጥ ገቢ ማግኘት ጀመሩ። በወቅቱ ገንዘቡ ብዙ ነገር የመግዛት አቅም ስለነበረው የእለት ኑሮአቸውን መሸፈን ቻሉ።

ቅጠል ተሸጦ በቀን የሚገኘው ሁለት ብር ከሃምሣ ሣንቲም ከእለት ጉርስ ባለፈ የተሻለ ኑሮ ለመኖር የሚያስችል አይደለም። ነገር ግን አባታቸው በቀን ሸክም ደክመው፣ እናታቸው ደግሞ ስፌቱንም ቅጠል መልቀሙንም ጎን ለጎን በማስኬድ ቢሰሩም ኑሮ አልሞላ ብሏቸው ሲቸገሩ ማየታቸው ልባቸውን ይነካው ስለነበር ቤተሰባቸውን ማገዝ መቻላቸው ትልቅ ደስታ ፈጠረላቸው።

ለእርሳቸውና ለእህታቸው ጫማ እና አንዳንድ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በማሟላት ቤተሰብ አለማስቸገራቸውም ሌላው እፎይታ ነበር። ጫማም ሆነ ልብስ ከእህታቸው ጋር ተጋርተው በመጠቀም ለጊዜውም ቢሆን የነበረባቸው ችግር ተቃለለላቸው። ወይዘሮ ሙሉ እንዲህ ኑሮን ለመደጎም ለአራት ዓመታት ያህል ቅጠል ለቅመው ሸጡ።

የእደጥበብ ሙያ ባለቤት የሆኑበት አጋጣሚ

ቅጠል ለቅመው መሸጡ የቀረላቸው፤ የተባበሩት መንግሥታት፣ የትምህርት፣ የሳይንስና ባሕል ድርጅት (ዩኒሴፍ) ውስጥ የእደጥበብ የሥልጠና ዕድል ካገኙ በኋላ ነበር። ድርጅቱ ትምህርታቸውን ላቋረጡ ተማሪዎች ስልጠና በመስጠት የሙያ ባለቤት እንደሚያደርግ ከእናታቸው መረጃ አገኙ። በድርጅቱ የሥልጠና ዕድል ለማግኘት ግን ነገሩ ቀላል አልነበረም። በወቅቱ ድርጅቱ የሚጠይቀውን የእድሜ መሥፈርት አያሟሉም ነበር።

ድርጅቱ ፍላጎታቸውንና ችግራቸውንም ግምት ውስጥ በማስገባት በእድሜያቸው ላይ አንድ ዓመት ጨምረው ለመመዝገብ ቻሉ። ድርጅቱ ተባብሯቸው እንጂ የሚቀበለው፤ 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆኑትን ነበር። ይህ እድል ለወይዘሮ ሙሉ ተስፋን የሰነቀ ነበር። ትልቁ የልባቸው መሻት የቤተሰብን ኑሮ መቀየር በመሆኑ፤ የአንድ ባለሙያ ባለቤት ሆነው፣ በሙያው ገቢ በሚያስገኝ ሥራ ላይ መሰማራት በጣም የሚፈልጉት ስለነበር፤ ባገኙት ዕድል በጣም ተደሰቱ።

ድርጅቱ ሥልጠናውን ያመቻቸላቸው ቦታ ወይም ማዕከል ያኔ ሕዝባዊ ኑሮ እድገት ይባል እንደነበርም ያስታውሳሉ። እርሳቸው እንዳሉት፤ በድርጅቱ ይሰጥ የነበረው ሥልጠና የእንጨት ሥራ (ውድ ዎርክ) ሲሆን፤ ምርት ማምረትንም በአንድ ላይ ያጣመረ ስለነበር እንደዥዋዥዌ ያሉ የልጆች መጫወቻዎች የመሳሰሉ ለመዋዕለ ሕፃናት የሚሆን የእንጨት ውጤቶችን ያመርቱ ነበር። እንጨት ከመላግ ጀምሮ እስከ መግጠም ድረስ ያለውን ሂደት በመሰልጠናቸው የተሟላ ሥራ ይሰሩ ነበር።

ምርቶቹንም ድርጅቱ ድጋፍ የሚያደርግላቸው አካባቢዎች ድረስ በመሄድ የመትከሉንና የመግጠሙን ሥራ ጭምር ያከናውኑ ነበር። በዚህ ሥራም በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ሄደዋል። የመጀመሪያውን ተሞክሯቸውን ግን አይዘነጉትም፤ ከቤተሰብ ተለይተው ከአዲስ አበባ ከተማ ወጥተው ሲሄዱ ፍርሃት አድሮባቸው ነበር። በወቅቱ በድርጅቱ ውስጥ የነበሩት ዝናሽ የሚባሉት አሰልጣኛቸው ኃላፊነት በመውሰዳቸው ቤተሰቦቻቸውም ፈቃደኛ ሆኑ። ድርጅቱ የእንጨት ውጤቶቹን ለእርዳታ የሚያውላቸው ቢሆንም፤ ክፍያ ያገኙ ስለነበር በሚያገኙት ገቢ ቤተሰባቸውን ይረዱ ነበር። ዓላማቸውንም ማሳካት ቻሉ። ይሁን እንጂ የሚያገኙት ገንዘብ ያሰቡት ያህል ኑሮ የሚቀይር ሆኖ አላገኙትም። በዚህ ሁኔታ ለአምስት ዓመታት በእንጨት ሥራ ላይ ቆዩ።

የእንጨት ሥራውን በዚህ ሁኔታ እያከናወኑ፤ ድርጅቱ የልዩ ስልጠና ፍላጎት አመቻቸ። የሥልጠናው አይነት ቀርከሃ፣ብረታ ብረት፣ አስሮ መንከር (ስዕል ስክሪን) ያካተተ ነበር። ወይዘሮ ሙሉ ከነዚህ የስልጠና አይነቶች ምርጫቸው ቀርከሃ ነበር። ነገር ግን የመረጡት ስለሙያው በቂ ግንዛቤ ኖሮአቸው አልነበረም። ባሳዩት ፍላጎት መሠረት ድርጅቱ እርሳቸውን ጨምሮ አምስት ሴቶች በምርጫቸው በቀርከሃ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ሰለጠኑ። ሙያውን ለመቅሰምም ጊዜ አልወሰደባቸውም።

ፍላጎቱና ልጅነቱም ስለነበር፤ እንዲሁም በሙያው ተክነው የገቢ ማስገኛ በማድረግ ችግርንም ለመወጣት ጭምር አስበው ነበርና ስልጠናውን በትጋት ተከታተሉ። በሥልጠናውም ከአምስቱ ሰልጣኞች መካከል የተሻሉ ሆነው በመገኘታቸው አንደኛ ሆነው አጠናቀቁ። ድርጅቱ ውስጥ በቀርከሃ ግብአት የተለያዩ ነገሮች ቢሰሩም ሰልጣኞች እንዲሰለጥኑ የሚደረገው የተወሰነውን ብቻ ነበር። እርሳቸው ግን በሥልጠና ያላገኙትንም በመሞከር ለመሥራት ጥረት ያደርጉ ነበር።

ወይዘሮ ሙሉ አምስት ዓመት ከቆዩበት የእንጨት ሥራ በቀርከሃ ሰልጥነው ያገኙት ሙያ የተሻለ ሆኖ እንዳገኙት ይናገራሉ። እርሳቸው እንዳሉት የእንጨት ሥራ ማሽን ይፈልጋል። ቀርከሃ ደግሞ በአንድ ቀላል የእጅ መሣሪያ ወይንም በቢላዋ በመጠቀም የተለያዩ የቀርከሃ ውጤቶችን መሥራት ይቻላል። በልጅነታቸው እናታቸው በስንደዶና አክርማ የስፌት ሥራዎችን ሲሰሩ ስንደዶና አክርማውን በመሰንጠቅ ያግዟቸው ስለበር ይሄ ልምዳቸው የቀርከሃውን ሥራ ቀላል አድርጎላቸዋል።

ወይዘሮ ሙሉ፤ የአንድ ሙያ ባለቤት የሆኑት በዚህ ሁሉ ሂደት ነበር። ስልጠና ሰጥቶ የሙያ ባለቤት ባደረጋቸው ድርጅት ውስጥ እየሰሩ ያቋረጡትን ትምህርት ለመቀጠል በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ መከታተልም ጀምረው ነበር። ትምህርቱ ግን አልሆነላቸውም። በተለያየ ምክንያት አቋረጡ።

በኢትዮጵያ ንግድ ሥራ ድርጅት ውስጥ የመቀጠር ሂደት

የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት በቀርከሃ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን እንደሚፈልግ ማስታወቂያ ማውጣቱን በተመለከተ መረጃው ደርሷቸው የተመዘገቡት አንድ በሚያውቃቸው ሰው አማካኝነት ነበር። በቀርከሃ ሙያ አብረዋቸው የሰለጠኑት ሴቶችም ለመወዳደር አብረዋቸው ተመዝግበው ነበር። በወቅቱም ያወዳደራቸው ሕዝባዊ ኑሮ እድገት የሚባል ተቋም ሲሆን፤ የሚፈለገው ሙያተኛ ሁለት ብቻ ነበር። በወቅቱ ስለነበረው ፈተናም እንዳስታወሱት፤ ፈተናውን የሰጣቸው የጃፓን ዜግነት ያለው ሰው ሲሆን፤ ፈታኙ በፊታቸው ሰርቶ ያሳያቸውን ዲዛይን መልሶ ደግሞ መሥራት ነበር። በተጨማሪ ደግሞ በአንድ ኢትዮጵያዊ የቃል ፈተና ቀረበላቸው። በውድድሩ ላይ ከቀረቡት መካከል አንዷ ሆነው አለፉ። ሌላኛዋ ደግሞ ወይዘሮ ሁሉሀገርሽ ዓለማየሁ ናቸው።

ሌሎች ተወዳዳሪዎች አብረዋቸው ለምዝገባ ቢቀርቡም፤ መስፈርቱን ባለማሟላታቸው ለፈተና ሳይቀርቡ ተሰናበቱ። እርሳቸውና የሙያ አጋራቸው ግን በእንጨት ሙያም መሰልጠናቸው መስፈርቱን ለማሟላት አግዟቸዋል። በዚህ ሁኔታ ወይዘሮ ሙሉና ሁሉሀገርሽ ፈተናውን አልፈው በኢትዮጵያ ንግድ ሥራ ድርጅት ተቀጥረው በእደጥበብ ሥራ ክፍል ውስጥ ተመደቡ። ከተቀጠሩበት 1983 . ጀምሮ በዚሁ ክፍል ውስጥ በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ወይዘሮ ሙሉ አሁን የሚሰሩበት ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት እርሳቸው በተቀጠሩበት ዘመን፤ ቦሌ አካባቢ ይገኝ ነበር። በዚህ ተቋም ውስጥ መቀጠራቸው ብቻ ሳይሆን፤ አካባቢውም ለእርሳቸው የተሻለ ሆኖ አገኙት። እርሳቸው የሚኖሩበት ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ እንደዛሬው የለማ ባለመሆኑ፤ የማሕበረሰቡ አኗኗር ከገጠር የተለየ አልነበረም። ውሃ ከምንጭ እየቀዱ ይጠቀሙ ነበር። የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ቢኖርም በአንድ ቆጣሪ ብዛት ያለው ሰው ይጠቀም ነበር። የኤሌክትሪክ ኃይል ሲቋረጥ እንኳን ማሕበረሰቡ የሚጠቀመው ኩራዝ ነበር። ሻማ እንኳን አልነበረም። የትራንስፖርት አገልግሎትም ባለመኖሩ፤ በእግር መጓዝ የተለመደ ነው።

የትዳር ሁኔታ

መኖሪያቸው የቀበሌ ቤት ቢሆንም፤ አባታቸው በሕይወት እያሉ ግቢው ውስጥ ሰፊ ልማት ያካሂዱ ስለነበር አኗኗሩ ወደ ገጠርነት ያመዝናል። እርሳቸው ሥራ ከመቀጠራቸው ከሁለት ዓመት በፊት አባታቸው አርፈው፤ ‹‹ይህች ልጅ የሴት ልጅ እንዳትባል ባል ማግባት አለባት›› ተብለው በቤተሰብና በጎረቤት ግፊት ነበር ያለምርጫቸው ወደ ትዳር የገቡት። የትዳር አማጭያቸውም በእድሜ የሚበልጧቸው ግን ደግሞ እንደ ጓደኛ የሚቀርቧቸው በአቅራቢያቸው የሚኖሩ ሴት እንደነበሩና እኝህ ሴትም የባላቸውን ጓደኛ እንዲያገቡ ግፊት በማድረጋቸውና የእናታቸውንም ፈቃድ ለመሙላት ሲሉ ለትዳር እንደበቁ አጫወቱን።

የትዳር አጋራቸው ሥራቸው ጥበቃ በመሆኑ ደመወዛቸው ሁለቱንም በበቂ ሁኔታ ሊያኖር የሚችል ባለመሆኑ የቤት ኪራይ ወጪን ለመቀነስ በቤተሰባቸው ግቢ ውስጥ መኖር ግድ ነበር። ትዳር መሥርተው መልሰው ከቤተሰብ ጋር መኖሩ፤ በኑሮም ቢሆን የተሻለ ነገር ስላልገጠማቸው ጥሩ ስሜት አልፈጠረባቸውም። በተለይም ከቤተሰባቸው ጋር ሲኖሩ የኑሮ ሁኔታው ያስከፋቸው ነበር።

የሕይወት እጣ ፈንታን ከመቀበል ሌላ ምርጫ አልነበራቸውም። በፈቃዳቸው ባይሆንም፤ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ የሆነውን የትዳር ኃላፊነትንም ተያያዙት። በተራራቀ ጊዜ ቢሆንም አራት ልጆች ተወለዱ። ዛሬ ልጆች አድገው ኃላፊነቱ ሲቀል ነገሮች እንደዋዛ ያለፉ ይምሰሉ እንጂ በአነስተኛ ገቢ ኑሮን ማሸነፍ ለወይዘሮ ሙሉ ከባድ ነበር።

ወይዘሮ ሙሉ እንዲህ ካለው የኑሮ ውጣ ውረድ እና የአኗኗር ዘይቤውም ቢሆን የገጠር አይነት ከመሰለው፤ አካባቢ ውስጥ በማሳለፋቸው ሥራ ሲቀጠሩ በወቅቱ የተቀጠሩበት መሥሪያ ቤትም ሆነ ድርጅቱ የሚገኝበት አካባቢ የተለየ ሆኖ አገኙት። በወቅቱ የፍርሃትም የደስታም የተዘበራረቀ ስሜት ነበራቸው። ፍርሃቱ ከገጠር ቀመስ አካባቢ መምጣታቸው ከሥራው አካባቢ ጋር እስማማለሁ አልስማማም? የሚል ነበር።

ደስታው ደግሞ በከተማ ውስጥ በትልቅ ድርጅት ውስጥ ሥራ ማግኘታቸው ነበር። ሌላው የባለቤታቸው የገቢ ምንጭ አነስተኛ በመሆኑ ሥራ መያዛቸው እፎይታን ስለፈጠረላቸው ተደሰቱ። በወር የሚያገኙት ደመወዝ 285 ብር መሆኑ ደግሞ ደስታቸው ወደር አልነበረውም። እርሳቸው እንዳሉት በዛ ጊዜ ከዩኒቨርሲቲ በዲፕሎማ የተመረቀ የሚያገኘው የደመወዝ መጠን ነበር። ደስታቸውን በታዳጊነት እድሜያቸው ሆነው ጫካ ውስጥ ቅጠል አብረዋቸው ሲለቅሙ ለነበሩ ብቻ ማካፈል በቂ ሆኖ አላገኙትም። ‹‹ለማን ልንገር?›› እስከማለት ደርሰው ቅጠል የሚለቅሙበት ጫካ ውስጥ በመሄድ ለጉቶ ሳይቀር እስከመናገር ደርሰዋል። የያኔው ደስታቸውን ዛሬም አልፎ እምባ እየተናነቃቸው በሲቃ ያስታውሱታል።

በወቅቱ በተመደቡበት የሥራ ክፍል ውስጥ ያገኗቸው አንድ ኢትዮጵያዊና የጃፓን ዜግነት ያለው ሰውን ነበር። ሥራውን በማለማመድም ሆነ በማበረታታት በጥሩ ሁኔታ ተቀበሏቸው። ጃፓናዊው ግን ብዙ አብሯቸው አልቆየም። 1983 . የነበረው ወታደራዊ የመንግሥት ሥርዓት በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሲተካ፤ በነበረው የሥርዓት ለውጥ ምክንያት ወደ ሀገሩ ተመለሰ።

ወይዘሮ ሙሉ፤ መሥሪያቤታቸውንም አካባቢውንም እየተለማመዱ ሲሄዱ ፍርሃቱ እየለቀቃቸው፤ በሥራቸውም ትጉህ እየሆኑ ረጅሙን የእድሜውን ጊዜያቸውን በኢትዮጵያ የቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ውስጥ አደረጉ። በነበራቸው የሥራ ቆይታም ከቀርከሃ አልጋ፣ መደርደሪያ፣ ወንበር፣ ለተለያዩ ማስዋቢያዎችና አገልግሎቶች የሚውሉ ሥራዎችን በመሥራት ለድርጅቱ አንድ የገቢ ምንጭ እንዲሆን በማድረግ የሙያ ግዴታቸውን ተወጥተዋል። አሁንም በሥራቸው እየተጉ ይገኛሉ።

የቀርከሃ ሥራ ጥንቃቄና ፍላጎት እንደሚያስፍልገውም ነግረውናል። ቀርከሃ በባሕሪው ስኳርነት ስላለው በብል ይጠቃል። በብል እንዳይበላ ይጠቀሙበት የነበረው በእሳት መለብለብ፤ አሁን ላይ ግን በኬሚካል በመዘፍዘፍ ችግሩ እንዲወገድ ያደርጋሉ። በዚህ መልኩ ከተዘጋጀ በኋላ አልጋ፣ ወንበርና ለሌሎችም አገልግሎቶች የሚውሉ ሥራዎችን ይሰሩበታል። በተለያየ ቀለም መጠቀም ሲያስፍልግም ቀለም አዘጋጅተው በመንከር ይጠቀማሉ።

ለመብሻ የሚውል ድሪል ከሚባለው መሣሪያ ውጭ ሥራው ባሕላዊ እንደሆነ ወይዘሮ ሙሉ ነግረውናል። ዋና የሥራ መሣሪያቸው ከቢለዋ ከፍ ያለው ለመሰንጠቂያ ሲጠቀሙበት የነበረው መሣሪያ ነበር። ሥራ ሲቀጠሩ በጀመሩበት መሣሪያ አሁንም እየተጠቀሙበት ነው። ሥለታም መሣሪያው ከጃፓን የመጣ ነው።

በዘመናዊ መሣሪያ አጠቃቀም ያልተተካውና በዚህ ባሕላዊ አሰራር የመቀጠሉን ሁኔታ እርሳቸው ምላሽ የሚሰጡበት ባይሆንም፤ ተቋማቸው በተለያየ አካባቢ እንዲዘዋወር መደረጉ አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ።

ወይዘሮ ሙሉ ለተቋማቸው ልዩ ስሜት አላቸው። በሥራ ቆይታቸው ለእርሳቸው ትልቁ ቁምነገር ልጆቻቸውን ማሳደግ መቻላቸው ነው። እርሳቸው እንዳሉት የመጀመሪያ ልጃቸውን በሆቴል አስተዳደር አስተምረው በመጀመሪያ ዲግሪ አስመርቀዋል። ሁለተኛ ልጃቸው በትምህርቱ ባይገፋም የእርሳቸውን የእጅ ሙያ ቀስሞ እየሰራበት ይገኛል። ሁለቱ ሴቶች ልጆች ገና ተማሪ ናቸው። ልጆቻቸው ከእርሳቸው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ በምክርም ጭምር የሚችሉትን በማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው።

ለሙያቸውና ለሚሰሩበት ተቋም ያላቸው ተቆርቋሪነት፤

የቀርከሃ ሙያ ሁሉ ነገሬ ነውየሚሉት ወይዘሮ ሙሉ፤ ሙያውን ከኑሮቸው ጋር በእጅጉ አቆራኝተውታል። ተቀጥረው የሚሰሩበት ድርጀት የሚጠብቅባቸውን ኃላፊነት ይወጣሉ። ከሥራ በኋላ ወደቤታቸው ሲመለሱም የጓዳ ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ መኝታ ሳይሆን፤ ወደ ሥራ ያመራሉ። ኑሮን ለመደጎም ተጨማሪ ገቢ ግድ በመሆኑ ከመኝታ ጊዜያቸው ቀንሰው ለሥራ ያውላሉ።

ለሙያው ያላቸው ፍላጎት እንቅልፍ ይነሳቸዋል። ለየት ያለ ዲዛይን ሲያዩ አያልፉም። በሌላ ግብአት የተሰራ እንኳን ቢሆን፤በቀርከሃ ግብአት ለመሥራት ጥረት ያደርጋሉ። አዲስ ዲዛይን ለመሥራት ድርጅታቸው ውስጥ ፍቃድ ባያገኙ እንኳን በግላቸው ሰርተው ለተጠቃሚ ያቀርባሉ። ስለሙያቸውም ሆነ ሥለትጋታቸው የሚያውቋቸው አንዳንድ ድርጅቶችም ለሙያ ተሞክሮ እየጋበዟቸው ሙያቸውን ያካፍላሉ። እግረ መንገዳቸውንም ከድርጅታቸው ውጭ እና እርሳቸውም በግላቸው ሰርተው ከሚያቀርቡት የተለየ ነገር ለመፈተሽ ዕድል የሚያገኙበት አጋጣሚን ያገኛሉ። ወደ ኋላ መለስ ብለው በትምህርት አለመግፋታቸው ይቆጫቸዋል። ተምረው ቢሆን አንዳንድ ቴክኖሎጂዎችንና የሌሎች ሀገሮችንም ተሞክሮ ለማወቅ ትምህርቱ ይጠቅማቸው እንደነበር የተገነዘቡት አሁን ነው። የትምህርት ጊዜ ቢያልፍባቸውም ክሕሎታቸውን ለመጠቀም ግን ወደኋላ አይሉም። አእምሮአቸውም አዳዲስ ነገር ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነ ይናገራሉ።

የቀርከሃ ሥራ በሚፈለገው ልክ አድጓል ብለው አያምኑም። ብዙ መሰራት እንዳለበት ይሰማቸዋል። ሙያው ግለሰብንም ሀገርምን የሚጠቅም እንደሆነና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ትምህርት ሊሰጥ ይገባል ይላሉ። በተለይ ደግሞ ብዙ ነገር አግኝቼበታለሁ ብለው የሚመሰክሩለት የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት የበለጠ ሙያውን የሚያሳድግበት እድሉ ቢኖረውም ግን ስሙን ተጠቅሞበታል የሚል እምነት የላቸውም። ድርጅቱ በእርሳቸውም እንደተጠቀመ አድርገው አያስቡም።

ወይዘሮ ሙሉ ስለድርጅታቸው ተናግረው አይጠግቡም። በጥሩ ስም የተገነባ ነው ይላሉ። እርሳቸው ባይደርሱባቸውም ኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅትን የመሠረቱት አቶ ኃብተስላሴ ታፈሰ እንደሚባሉ፤ ኢትዮጵያ 13 ወር ፀጋ ተብላ ስሟ እንዲጠራ ያደረጉ፣ የቱሪዝም አባትም እንደሚባሉ፣ የእደጥበብና የሥነጥበብ ውጤቶችም በውጭው ዓለም ሳይቀር እንዲታወቅ በማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ታሪኩን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ድርጅታቸው የቀድሞውን ገናና ስሙን ይዞ ጥሩ የሆነውን ታሪክ በተሻለ አስቀጥሎ ቢያዩ ምኞታቸው ነው።

አሁን ላይ ግን አንዳንድ ክፍተቶች ማየታቸው እያሳዘናቸው ነው። ድርጅቱ በተለይ በእደጥበብ ክፍል ውስጥ ይሰሩ የነበሩና ስም ካገኘባቸው አንዱ የሆነው አሻንጉሊቶች እንደነበሩ ያስታውሳሉ። እርሳቸው እንዳሉት በሚሰሩት አሻንጉሊቶች የባህል አልባሳት፣ ሙዚቃና ሌሎችም የኢትዮጵያን ባህል የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቶ ይቀርብ ነበር። አሁን ላይ አሻንጉሊቶች እየተሰሩ አይደለም። ባለሙያዎች በጡረታና በተለያየ ምክንያት ከተቋሙ ሲወጡ ሌሎች ባለሙያዎች አይተኩም። ምክንያቱን ባያውቁም የድርጅቱ የሥራ ቦታ በአንድ ላይ አለመሰባሰቡ አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይጠረጥራሉ።

በአጠቃላይ ድርጅቱ እንደቀዳሚነቱ ትኩረት አልተሰጠውም ብለው ያምናሉ። በሌሎችም ዘርፎች ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች እንዲሁ በቁጥር አነስተኛ እንደሆኑና እርሳቸው በሚሰሩበት ክፍልም እርሳቸውና አለቃቸው ወይዘሮ ሁሉሀገርሽ ብቻ መቅረታቸውን ነው የነገሩን። ባለሙያዎችን መተካት ካልተቻለ ድርጅቱ ስም ያፈራባቸውን ሥራዎቹን እንዳያጣ ይሰጋሉ።

በሥራ ዓለም ክፉም ደግም ያልፋል። ወይዘሮ ሙሉም በሁሉቱም ያሳለፏቸውን እንዲህ አስታውሰዋል። ‹‹ ይሄን ያህል እንደክፉ በቅሬታ የማነሳው ነገር የለም። በሥራ ያደኩበት፣ ኑሮዬንም የመራሁበት ድርጅት በመሆኑ የሚበልጡብኝ መልካም የሆኑ ነገሮች ናቸው። ግን ደግሞ ቅሬታ አይጠፋም። ገና ሥራ እንደተቀጠርኩ ነበር ልጄ በእሳት ቃጠሎ ጉዳት ደርሶበት ለማስታመም፤ የቅርብ አለቃዬን ፍቃድ ጠየኩት። አልፈቅድም አለኝ። በጣም ከፋኝ። አለቀስኩ። ከአቅሜ በላይ ሆኖብኝ ወደ በላይ ሄድኩ። ከአለቃዬ የበላይ የነበሩ ሴት ኃላፊ ግን አይዞሽ ብለው ፈቅደውልኝ ልጄን ለማስታመም ቻልኩ። የእርሳቸው መልካምነት ተሰምቶኝ የነበረውን መጥፎ ስሜት እንድረሳው አደረገኝ።

የዛሬ ሰባት ዓመት ደግሞ ሌላ ከባድ ነገር ገጠመኝ። እናቴ በጠና ታማብኝ እርስዋን ለማስታመም አሁንም ፍቃድ ያስፈልገኝ ነበር። በዚህ ጊዜም ድርጅቴ የዋለልኝን ውለታ አልረሳውም። እናቴን ለሶስት ወራት ያህል ሳስታምማት ታግሶኛል። እንደአጋጣሚ እናቴ በሕይወት ልትተርፍልኝ አልቻለችም። በሞት ስትለየኝ። ድርጅቴ በሀዘኔም ጊዜ ከጎኔ ነበር። መላው የድርጅቱ ሰራተኛ የሀዘኔ ተካፋይ ነበር። ይሄ የማልረሳው ውለታ ነው። በማለት በመልካም አንስተዋል።

በአንድ ወቅትም በውስጥ በተካሄደ የሥራ ውድድር በትምህርት ምክንያት እድገት ሳያገኙ የቀረቡትን አጋጣሚም አንስተው፤ ሞራላቸው ተነክቶ እንደነበር ገለፁልን። እርሳቸው እንዳሉት፤ ድርጅቱ የአገልግሎት ዘመን ይያዝላችኋል የሚል ተስፋ አሳድሮባቸው ትኩረት አድርገው ሲሰሩ የነበረው በሙያቸው ላይ ብቻ ነበር። ለትምህርት ትኩረት እንዳይሰጡ በመዘናጋታቸው ባለሙያ በሚል መደብ መቆየታቸውን አጫወቱን። በወቅቱ ቅሬታ ቢፈጥርባቸውም ‹‹የሙያ ባለቤት ነኝ። በግሌም ሰርቼ እኖራለሁ›› በሚል እራሳቸውን እንዳጽናኑም ነግረውናል። አብረዋቸው ሥራ የተቀጠሩትና አሁንም አብረዋቸው እየሰሩ ያሉት ወይዘሮ ሁሉሀገርሽ ዓለማየሁ ግን ትምህርት ተምረው ስለበለጧቸው አሁን አለቃቸው ሆነዋል።

የወደፊት እቅዳቸው

በግላቸውም ቢሆን የቀርከሃ ሥራን አንድ ደረጃ በማድረስ የልባቸውን ለመሙላት ፍላጎት አላቸው። 55 ዓመት ሲሞላቸው የጡረታ መብታቸውን አስከብረው እድሜያቸው እስከፈቀደላቸው ድረስ በመሥራት ሙያውን ማስቀጠል፣ ለሀገራቸውም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት፣ በኑሮአቸውም ቢሆን ተሽሎ የመገኘት እቅድ አላቸው፤ አሁን 54 ዓመት እድሜ ላይ ስለሆኑ በሚቀጥለው ዓመት እቅዳቸውን ለማሳካት አስበዋል። አድሜና ጤና ሰጥቷቸው የልባቸው መሻት እንዲሞላላቸው ተመኝተንላቸው ተሰነባበትን።

ለምለም መንግሥቱ

 

አዲስ ዘመን ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You