መንታ ነፍስ

ኤልሳ የዛሬ 15 ዓመት የማውቃት ሴት ናት፡፡ ይሄን ሁሉ ዘመን ኖራ እንዴት አትረሳኝም..ስለምን አትርቀኝም? እላለው፡፡ ትካዜ የሚደፍረኝ እሷ ባለችበት ትላንቴ በኩል ነኝ፡፡ በእሷ በኩል መጥቶብኝ ትካዜዬን አሸንፌው አላውቅም፡፡

ትውውቃችን እንደዘበት ነበር፡፡ አንድ ማለዳ ነው..በስራ ማጣት ተስፋ ቆርጨ ራሴን እንዴት ላጥፋው? ምን አይነት ሞት ልሙት? እያልኩ ምርጥ ሞት ፍለጋ ላይ እያለሁ፡፡ በዛን አይነት ትውውቅ የቀረቧትን ሴት አለመርሳት ማለት ለእኔ ብቻ ነው የተቻለው፡፡ ለቤተሰቤ ሰባተኛ ልጅ ነኝ፡፡ አባቴ ሁሉንም ልጆቹን ድል ባለ ድግስ አስመርቋል፡፡ ሲያስመርቅ ግን ለእኛ አስቦ ሳይሆን ለራሱ ተጨንቆ ነበር፡፡

አባቴ ከሰይጣን ቀጥሎ ሁለተኛው ተንኮለኛ ሰው ነው፡፡ ሲወልደን ጀምሮ በእኛ በኩል የሚያገኘውን ትርፍ አስልቶ እንደሆነ እኛን አሲዞ በሚቆምረው ቁማር ደርሼበታለው፡፡ ትርፍ ይኑረው እንጂ ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይልም፡፡ ጌታን እንደሸጠው ይሁዳ ብዙ ጊዜ ስሞ ሊሸጠን ሞክሮ አልተሳካለትም፡፡ የሰፈሩን ሰው የሚበዘብዘው በእኛ በኩል ነው፡፡ እንደጉድ በቀጠነ ጠላ፣ እንደ ጉድ በቀጠነ ወጥ፣ ፊትና ኋላው በማይለይ የዘንጋዳ እንጀራ የሚያውቀውንም የማያውቀውንም ጠርቶ ልጆቼን መርቁልኝ ሲል በራሪ ወረቀት ያስልካል። እኔም ሆንኩ ወንድምና እህቶቼ ዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ሶስትና ከዛ በላይ ዓመታትን ስንማር ከአባታችን የተላከ ገንዘብ አናውቅም፡፡ በዓመት አንድ ጊዜ ለእረፍት ስንሄድ ነው አባታችንን በአካለ ስጋ የምናየው፡፡ ከዛ ውጪ ደውሎም ደውለንም አናውቅም፡፡

ምርቃት የማልወድ ብሆንም ከአባቴ ጋር በተደረገ የሁለት ሳምንት ዝግ ሙግት በኋላ ተሸንፌ ድግስ ተደገሰ። እኔ ስራ ፍለጋ ስንከራተት አባቴ ያስገባውን ገቢ ያሰላ ነበር፡፡ በተመረኩኝ በሰልስቱ ስራ ፍለጋ አዲስ አበባን ከእግር እስከራሷ ዞርኳት፡፡ በእኔ እግር የተረገጠችውን ያክል በማንም አልተረገጠችም፡፡ አንድ ቀን ምርር አለኝና..ከዚህ ቤተሰብ (በተለይ ከአባቴ) የሚገላግለኝን ነገር ሳወጣ ሳወርድ አስኮናኝ ፊቱን ይዞ ሞት ፊቴ ድቅን አለ፡፡ ሞት ከመች ጀምሮ ነው አስኮናኝ ፊት ያለው? ሲገልም ሆነ ከገደለ በኋላ ምን እንደሚመስል የማላውቀው መስሎት ነው? እያልኩ በሞት አስኮናኝ ገጽ ስወጣና ስወርድ በተቀመጥኩባት የአስፓልት ዳር ብዙ ቆየሁ፡፡ ሞትን ሞኝህን ብላ ልለው ፈለኩ፡፡ ግን ከእሱ ሌላ የምገላገልበት ሁነኛ መላ ስለሌለ አላልኩትም፡፡ ደሞ ማን ላይ ነው የምታሾፈው? ብሎ አልወስድህም ቢለኝ ምን ይውጠኛል ስል እንዳሻህ አልኩት፡፡

እንዴት ብሞት ይሆን ቀባሪ የሚያዝንልኝ? እንዴት ብሞት ነው በትውልድ ልብ ውስጥ የማልረሳው? እያልኩ ምርጥ ሞት ፍለጋ ላይ ሳለሁ…ከኋላዬ በመጣች በአንዲት ሴት ዜማ በቀላቀለ ሳቅ ተደነቃቅፌ ሞትን ረሳሁት፡፡ ሳቋን በደንብ እንዳጣጣመው በሞት የደከመ አእምሮዬን ላንጠራራ ቀና ስል ከፊት ለፊቴ ሞት አንገቷን ያስደፋት ጥቁር በጥቁር የለበሰች ሴት አየሁ፡፡ ሁለት ደስተኛና ሀዘንተኛ ነፍሶች እኔን መሀል አድርገው ከፊትና ከኋላዬ አስተዋልኩ፡፡ የእናቴ ይሆን መቼም የአባቴ ውቃቢ አይሆንም..ከሞት ሊታደገኝ ሁለት በሞትና ህይወት መከራና ፈንጠዝያ ውስጥ ያሉ ሴቶችን የላከልኝ መሰለኝ። አንድ ልቤን ለጥንድ ነፍሳቸው ሰጥቼ ለሌላ ሀሳብ ተዳረኩ፡፡

ከፊት ለፊቴ ያለችው ሴት ሞት አንገቷን አስደፍቷት፣ ሀዘን ደስታዋን ቀምቷት፣ ባቀረቀረ አንገት አልፋኝ ሄደች። እየመጣ በሚሄድ እንባ፣ አልረሳ ባለ ናፍቆት፡፡ በዛች ሀዘንተኛ ነፍስ ላይ ባለመኖር ውስጥ የታመቀ ናፍቆትና ትዝታ አስተዋልኩ..ሴትነቷን ለሁለት ከፍለውት፡፡ ጀርባዋ ላይ አይኔን ተከልኩ..እንዲመለስ የሚፈልገው ግን ያልተመለሰ የማይመለስም የሆነ ነገር አየሁበት፡፡ እንደነፍሷ ግርጥት ብሏል፡፡ ከንፈሩን እያወዛወዘ አንድ ነገር ሲል አየዋለው..ጀርባዋ፡፡ ደግሞም ያለቅሳል..በጸሞነ ለቅሶ እንባውን እያዘራ ላትመለስ የሄደችን አንዲት ነፍስ ይከጅላል፡፡

ወደ ነፍሴ የሆነ ነገር ተማገደ፡፡ በነፍሷ ነፍሴን ያሻርኩ መሰለኝ፡፡ ሞት የሚሉት ሀሳብ ከሆዴ ውስጥ ብን ብሎ ሲወጣ ታወቀኝ፡፡ በሀዘንተኛዋ ሴት ከሻትኩት ሞት ተቆራረጥኩ፡፡

ወደ ሳቂታዋ ሴት አዘነበልኩ፡፡ ሞትን ንቃ፣ ህይወትን ናፍቃ ታስካካለች፡፡ ከድምጽዋ ኩሬ ውስጥ የሚፈልቅ የአጥቢያ መሳይ እግዚኦታ ነፍሴን አረሰረሳት፡፡ በእሷ በኩል መኖር ከጀልኩ..ሞትን የት አባትክ አልኩት። ከአንደበቷ ዋሻ የሚነሳውን አንቂ ድምጽዋን ሳታየኝ ሰማሁት፡፡

ወደ ሀዘንተኛዋ ሴት ቀና አልኩ…እንዳቀረቀረች በርቀት አየኋት፡፡ ጀርባዋ አሁንም አልሻረም እንደተሰበረ ነው፡፡ ከተቀመጥኩበት ተፈናጥሬ ወደጀርባዬ ዞርኩ፡፡ ባላያት ያስመኘኝን እጹብ ውበት ልጅነትን በተሻገረ ፊቷ ላይ አየሁት፡፡ ከድምጽዋ ማማር ተንቀሳቃሽ በቤተክሲያን መሰለችኝ፡፡ ቄስና ገበዝ ይዛ ይዛ የምትዞር፡፡ ብቻዋን ናት። ይሄን ሁሉ ወሬ ከማን ጋር ስታወራ እንደነበር ግራ ገባኝ፡፡ መንፈስ መሰለችኝ፡፡ ላማትብ የመስቀል ቅርጽ የሰራ ጣቴን ወደ ግንባሬ ስሰድ አጠገቧ ትንሽዬ ቡችላ አየሁ..እግሯ ላይ እየተንደባለለ ሰርከስ እየሰራ፡፡ በእድሜ እንደምትበልጠኝ ወጣትነትን የሸሸ ፊቷ ነገረኝ፡፡

ወዳለችበት ሄጄ እሷንም ጓደኛዋንም እጅ ነሳኋቸው። ከእሷ ቀድሞ ፈጣን ቡችላዋ ጭራውን ቆላልኝ፡፡ እኛ ሰዎች ሁልጊዜም በውሻ እንደተበለጥን ነው፡፡

‹እዚህ ሰፈር ነሽ? የመጀመሪያ ቃሌን በጥያቄ ጀመርኩ፡፡

‹አይደለሁኝም..

‹እና ያለሰፈርሽ፣ ለዛውም ሰው በር ላይ በወንጀል እንደምትጠየቂ አታውቂም? ስል የማውቀውን ከማላውቀው ጋር ቀላቅዬ ዘላበድኩ፡፡

‹ፍቅር ሲመራን ጠላቶቻችን ላይ ድንጋይ ለመወርወር አቅም አናገኝም፡፡ የእኔ እዚህ መቆም ሌሎችን እንደማያስከፋ ርግጠኛ ስለሆንኩ ነው የቆምኩት› አለችኝ፡፡ እኔ ብሆን የተጠየኩት ከመኖር ውጪ ምንም ቢያደርጉኝ በደስታ ነው የምቀበለው እል ነበር፡፡

‹ድካምሽን በማረፍ ነው የምታሳልፈው? ስል ድንገተኛ ጥያቄ ሰነዘርኩ፡፡

ራሷን እየነቀነቀችልኝ ‹ሲደክመኝ በማረፍ ነው የምበረታው፡፡ ደክሞኝ መቆምን አስቤው አላውቅም› ስትለኝ ባህር ከከፈለው ሙሴ ጋር የማወራ ነበር የመሰለኝ፡፡

‹መኖር ታክቶኛል፣ መኖር የሚያስናፍቅ ምን አለሽ? አልኳት እንደቀልድ፡፡

‹እኔ ለአንተ የሚሆን ምንም የለኝም፡፡ ሁሉም ሰው ከአንተ ቀጥሎ ነው ለአንተ፡፡ ለአንተ ከአንተ የቀደመ ማንም የለም፡፡ በራስህ ላይ ሌሎችን ፊተኛ ስታደርግ ወደኋላ እየቀረህ ነው፡፡ እናም ራስህን አንቃው› አለችኝ፡፡

በድን ሆኜ ስሰማት ነበር፡፡ እንደዛ በሚያማምሩ ቃሎች፣ ሞገስ በሚሰጡ አንደበቶች ማንም ተናግሮኝ አያውቅም፡፡ ካንቀላፋሁበት ስነቃ ታወቀኝ፡፡

‹የደስታ በሮችህ መቼም እንዳይከፈቱ አድርገህ ከዘጋሃቸው መቼም አይከፈቱም፡፡ መቼም እንዳይዘጉ አድርገህ ከከፈትካቸውም መቼም በማንም አይዘጉም። በሮችህን ዘግተህ ቁልፉን አርቀህ ወርውረህ ያን በር ማን የሚከፍትልህ ይመስልሀል? መጀመሪያ በሮችህን ላለመዝጋት ሆነህ ኖር፡፡ ከዘጋሃቸው በኋላ ንፋስ እንዲያስገቡ ትንሽ ገርበብ አድርጋቸው፡፡ በዛ ገርባባ በር የሚገባ ስለሚኖር›

ስትለኝ..

ለዘመናት ከተላመድኩት የአለመኖር ሱስ ራሴን ስመነግል፣ ከአባቴ ውቃቢ ስቆራረጥ ራሴን በራሴ ውስጥ አገኘሁት፡፡

‹ማንም ለአንተ ከአንተ ቀጥሎ ነው፡፡ የደስታህ ፊተኛ፣ የስኬትህ ቀዳማይ አንተ ነህ፡፡ ሌሎች እንዲያሻግሩህ፣ ሌሎች እንዲመሩህ አትፍቀድ እንደዛ ካሻህም አእምሮና ልብህን ከፍተህ ይሁን፡፡

ዝምታ ወረሰኝ..አሁን ብቻ አይደለም ከዚህ በኋላም እሷን ሳስብ ዝም የምል ይመስለኛል፡፡ የሚነፍሰው ንፋስ ወሬዋን እንዳይሻራርፍብኝ በተጠንቀቅ ቆሜ ሰማኋት፡፡

‹ራስህን የትም አትሻው..በአንተ ውስጥ ስላለ በአንተ ውስጥ ፈልገው፡፡ መከራዎችህን በሞት ለመርሳት አትሞክር፡፡ ሕይወት እንጂ ሞት መቼም አለ፡፡ እናም ትግልህ ብርሀን እስኪያሳይህ ድረስ መከራህን ናቀው። ቀኖች በሰው ልጅ ልክ ተከፋፍለው ነግተው የሚመሹ ናቸው፡፡ በዙሪያችን ያሉ ደስተኛና ስኬታማ ሰዎች በነሱ ቀን ላይ እንደሆኑ ልብ በል፡፡ ቀንህ እስኪመጣ በትዕግስት መጠበቅ ነው› አለችኝ፡፡ የመጨረሻ ወሬዋ ባልሆነ እያልኩ ስሰጋ ‹ደህና ሁን› የሚል የስንብት ድምጽዋን አስከተለች፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2016

Recommended For You