“ትምህርት ትጋትና ጥናት ይጠይቃል”  – ተማሪ ሙሉነህ እንየው

በፈተና ስርቆት እና በኩረጃ ለበርካታ ዓመታት ችግር ሲገጥመው የነበረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተናን ተዓማኒነት ለመጠበቅ ከ 2014 ዓ.ም ጀምሮ በአገሪቱ ባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ ቁጥጥር ስር ሆኖ እንዲሰጥ ሆኗል።

በ2015 ዓ.ም የ 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን 356 ሺ 878 የተፈጥሮ ሳይንስ እና 488 ሺ 221 የማህበራዊ ሳይንስ በአጠቃላይ 845 ሺ 188 ተማሪዎች መውሰዳቸው ይታወቃል። ከ 356 ሺ 878 የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች 22 ሺ 974 ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት አምጥተዋል። ከ 488 ሺ 221 የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች መካከል የማለፊያ ውጤት ያመጡት 8 ሺ 250 ብቻ መሆናቸው ተገልጿል፤ ከዚህ በተጨማሪም የትምህርት ሚኒስቴር በ 2015 ትምህርት ዘመን የ 12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ 845 ሺ 188 ተማሪዎች ውስጥ 27 ሺህ ተማሪዎች ከ50 በመቶ በላይ በማምጣት የማለፍያ ውጤት ማስመዝገባቸውን አስታውቋል።

ፈተናውን ከወሰዱት ውስጥ 3 ነጥብ 2 በመቶ ተማሪዎች ብቻ ማለፋቸውን የገለፀው ሚኒስትሩ ይህም ውጤት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ 0 ነጥብ 01 መቀነሱንም አብራርቷል። ዘንድሮ 3 ሺ 106 ትምህርት ቤቶች ፈተና ያስፈተኑ ሲሆን፣ ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1 ሺ 328 ትምህርት ቤቶች ደግሞ አንድም ተማሪ ማሳለፍ አለመቻለቸውንም አክሏል፤ በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ተምረው ፈተናውን ከወሰዱ 16 ሺ 451 ተማሪዎች መካከልም ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት 12ቱ ብቻ ሲሆኑ፣ ይህም በመቶኛ ሲሰላ 0 ነጥብ 1 ነው።

ይፋ በተደረገው ውጤት መሠረት በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ 649 ነጥብ ከፍተኛ ውጤት ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ደግሞ ከፍተኛው ነጥብ 533 መሆኑ ተገልጿል፤ ይህም በአማራ ክልል ሐዲስ ዓለማየሁ ትምህርት ቤት ነው። ለፈተና ያቀረቧቸውን ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ካሳለፉ ጥቂት ትምህርት ቤቶች አንዱ የሆነው የዚህ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነው ተማሪ ሙሉነህ እንየው የዚህ ከፍተኛ ውጤት ባለቤት ነው።

በምዕራብ ጎጃም በምትገኝና ሰከላ በምትባል አነስተኛ የገጠር ከተማ የተወለደው ተማሪ ሙሉነህ፣ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበረው ቆይታ እንደተናገረው፤ ከመጀመሪያው የትምህርት ደረጃዎች ጀምሮ በትምህርቱ ጥሩ ውጤት ካላቸውና ጎበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል እንደነበር ገልፆ፤ በዘንድሮው ብሔራዊ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ጥሩ ውጤት ለማምጣት ሙሉ ጊዜውንና ሰዓቱን ትምህርቱ ላይ ብቻ በማድረግ ዝግጅት ሲያደርግ እንደቆየ ይናገራል።

ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል አዲስ ዓለም በተሰኘ ትምህርት ቤት ሰባትና ስምንተኛ ክፍልን ደግሞ ሱርበ በተባለ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፤ ተማሪ ሙሉነህ እንደሚናገረው፤ ከእርሱ አንድ ዓመት ቀደም ብለው ካሉ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ጥሩ ውጤት ያመጡ ልጆች በውድድር ተመርጠው ወሎ አዳሪ ትምህርት ቤት መግባታቸውን ተከትሎ ይህ ዕድል እርሱንም የሚጠብቀው መሆኑን በመገንዘብ ጠንክሮ በመማር በስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና 91 ከመቶ በማምጣት ከእርሱ ቀደም እንደነበሩት ጓደኞቹ እስከ ወሎ ድረስ መሄድ ሳይጠበቅበት በደብረማርቆስ ከተማ በተከፈተው የሐዲስ ዓለማየሁ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ችሏል።

ለ 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ቅድመ ዝግጅት ማድረግ የጀመረው የ11ኛ ክፍል ተማሪ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ የሚናገረው ሙሉነህ፤ የአራት ዓመት የትምህርት ቆይታ የሚለካበት እንደመሆኑ በዚህ ውጤታማ ሆኖ ወደሚቀጥለው ደረጃ መሸጋገር የግድ ስለሆነም የተለያየ የአጠናን ዘዴዎችን ተጠቅሞ ፍሬያማ መሆን እንደቻለ ይናገራል።

ሙሉነህ እንደሚናገረው፤ ከጓደኞቹ ጋር በቡድን ማጥናት ያዘወትር ነበር ፤ ይህም አንዱ ከሌላው ዕውቀት እየቀሰመ ማጥናቱ በግል ከሚያደርገው ዝግጅት ባልተናነሰ ሁኔታ ለቅድመ ዝግጅቱና አሁን ለተገኘው ከፍተኛ ውጤት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረው ይገልፃል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ፈተናውን ከወሰዱ ከፍተኛ ቁጥር ካላቸው የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት ማምጣት የተለየ ስሜት እንዳለው የሚናገረው ሙሉነህ፤ ውጤቱ የጠበቀው ቢሆንም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት አመጣለሁ የሚል ግምት ግን እንዳልነበረው ነው የሚገልጸው፤ ይህንን ውጤት ለማስመዝገብ የተጠቀመውን ዘዴና መንገድ ሲያስረዳም፤ ከመጀመሪያው ጀምሮ ብሔራዊ ፈተና የሚሰጥባቸውን የትምህርት አይነቶች ቀደም ብሎ ከስር ከስር በማንበብ መዘጋጀቱ ለስኬታማነቱ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነበር።

“የሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት መግባቴ አንድ ሁለት ብዬ ተናግሬ የማልጨርሰው ጥቅም አስገኝቶልኛል፤ ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት የመግባት ዕድሉ ባይኖረኝና እዛው በተወለድኩበት አካባቢ ትምህርቴን ቀጥዬ ቢሆን ኖሮ በዚህ ደረጃ ውጤታማ መሆን አልችልም ነበር” የሚለው ሙሉነህ፤ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በአካባቢያቸው እንደ አብዛኛው የኢትዮጵያ ክልል አስፈላጊው የመማሪያ ቁሳቁስ ያልተሟላላቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መኖራቸውና የ12ኛ ክፍል ፈተና ደግሞ በክፍል ውስጥ ከሚሰጠው የመማር ማስተማር ሂደት በተጨማሪ የበይነ መረብ (ኢንተርኔት) አገልግሎት አግኝቶ ማንበብ ስለሚጠይቅ ነው። በዚህ ትምህርት ቤት ደግሞ ይሄንን አገልግሎት በቀላሉ ማግኘት ስለሚቻል ለውጤታማነቱ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ ይገልፃል።

የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ በአጠቃላይ በተለይ ደግሞ መምህራኖቻችን ይህንን የመሰለ ውጤት እንድናመጣ ለፍተዋል የሚለው ሙሉነህ ፤ ከሁሉም የትምህርት ዓይነት በማድረግ የተለያዩ የማትሪክ ጥያቄዎችን በመስጠት፣ ተምረው ያለፉትን የትምህርት ክፍሎች ደግሞ እንደገና በመከለስ ለፈተናው ብቁ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት እንዳደረጉ ይገልፃል።

ፈተናው ከሌላው ጊዜ የተለየና ከባድ ነው የሚባል እንዳልሆነ የሚናገረው ሙሉነህ፤ ጥሩ ዝግጅት ከተደረገ የሚሰራ ፈተና እንደነበር ይገልጻል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተገኘው ዝቅተኛ ውጤት ምክንያት ነው የሚለውን ከእነርሱ አካባቢ ሁኔታ አንፃር አይቶ ተማሪ ሙሉነህ ሲናገር፤ አብዛኛው ተማሪ ለፈተናው የሚመጥን ዝግጅት አለማድረጉና ከቤተሰብ ተለይተው ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በአቅራቢያቸው ወዳለ ከተማ ልጆች ስሄዱ የሚቆጣጠርም ስለማይኖር ጊዜያቸውን ያለ አግባብ ማባከናቸውና ለተለያዩ አልባሌ ነገሮች ተጋላጭ መሆናቸው፣ በተጨማሪም በ2014 ዓ.ም በነበረው ውጤት ተስፋ መቁረጣቸው የስነልቦና ዝግጅት ማድረግ አለመቻላቸው ነው ይላል፤ ዝግጅት ማድረግ የሚገባው በፈተናው የመጨረሻ ዓመት ብቻ ሳይሆን ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ነው፤ ነገር ግን ብዙ ቁጥር ያለው ተማሪ ተገቢ ዝግጅት አላደረገም ይላል።

የመምህራን አቅም ማነስና በተለይ በገጠሪቱ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያለው እጅግ ዝቅተኛ የትምህርት መሰረተ ልማት በአንፃራዊነት የትምህርት አቀባበለቸው ጥሩ የሆኑ ተማሪዎች ቢኖሩም እነርሱን የሚያግዝ ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ ያላቸውን አቅም አውጥተው ውጤታማ መሆን እንዳይችሉ ትልቅ ማነቆ እንደሆነባቸው ይናገራል።

የአብዛኛዎቹ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ልክ እንዳልሆነና በውጤታቸውም ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ የሚናገረው ሙሉነህ፤ የእርሱ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ምን ይመስል እንደነበር ሲናገር፤ ከ 9ኛ ክፍል እስከ 10ኛ ክፍል የማህበራዊ ሚዲያን መረጃ ለማግኘትና ለትምህርት አጋዥ ለሆኑ ነገሮች ይጠቀም እንደነበር ከ11ኛ ክፍል በኋላ ግን ሙሉ በሙሉ በማቆም ሙሉ ትኩረቱን የፈተና ዝግጅቱ ላይ አድርጎ እንደቆየ ተናግሯል።

እርሱ ያለበት አካባቢ በባለፉት ዓመታት በነበረው የሠላም ዕጦት ምክንያት በእጅጉ ሲፈተን እንደቆየ የሚናገረው ሙሉነህ፤ ለእንደዚህ አይነት ነገር ጆሮ ባለመስጠት ትምህርቱ ላይ ብቻ ማተኮሩና ማህበራዊ ሚዲያ ከመጠቀም መታቀቡ በጦርነትና ግጭት ዜናዎች ሳይረበሽ ለትምህርቱ ብቻ ጊዜውን በመስጠት ውጤታማ መሆን እንደቻለ ይናገራል።

ትምህርት ትጋትና ጥናት ይጠይቃል የሚለው ተማሪ ሙሉነህ፤ ሁሉም ሰው ካሰበው ዓላማው እስኪደርስ መታገል አለበት ወጣ ገባ የማለት ሁኔታ ካለ ተስፋ መቁረጥ ይመጣል ውጤታማ መሆን አይቻልም ተማሪ ከሆንን አስቀድመን በራሳችን መስራት እንደምንችል አምነን እራሳችንን ከመጀመሪያ ጀምሮ መቅረፅ አለብን ይላል።

ከእሱ ተሞክሮ ተነስቶ የሚናገረው ሙሉነህ፤ በትውልድ አካባቢው ያሉ ሌሎች ጓደኞቹ በትምህርት እስከ መጨረሻው ገፍተው እንዳይጓዙ የሚያደርገው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ችግር መሆኑንና እሱ ግን አዳሪ ትምህርት ቤት መግባቱ በተለይ በገንዘብ በኩል የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ከመጋፈጥ እንዳዳነው ይናገራል። ነገር ግን ምንም አይነት ፈተና ቢኖር ጽናትን ተላብሶ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግም ይመክራል።

ሙሉነህ ፤ በትውልድ አካባቢው በብዛት ወጣቶች ስምንተኛ ክፍል ከደረሱ በኋላ የተለያየ የኢኮኖሚ ችግር ስለሚገጥማቸው ራሳቸውን ለመቻል ወደ ተለያዩ ከተሞች ሄደው የቀን ሥራ በመስራት ገንዘብ ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርጉ ይናገራል፤ እርሱ ይህ ዕድል እንዳያጋጥመው ቤተሰቦቹ በተቻላቸው አቅም ሁሉ ድጋፍ ስላደረጉለትም ስኬታማ ለመሆን አንዳበቃው ይናገራል።

የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ከዚህ ቀደም ባሉ ጊዜያት እንደነበረው ለስርቆት ተጋላጭ አለመሆኑ ጥቂት ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ብቻ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲያልፉ ምክንያት እንደሆነ ተናግሮ፤ ተማሪው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሚጠይቀው ልክ ዝግጅት እንዳላደረገ ይናገራል።

ሙሉነህ ሲናገር፤ ብሔራዊ ፈተና ከክፍል የፈተና ሂደት የሚለየው የአራት ዓመት ትምህርት አካቶ ሰፋ ባለ መልኩ የሚወጣ ነው። ሳምንታት ተዘጋጅቶ በብሔራዊ ፈተና ውጤታማ መሆን አይቻልም ፈተናው የሚለካው የተማሪውን የዓመታት ልፋቱን ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የብዙዎች ዝግጅት ቸልተኝነት የተሞላበትና ለውጤት የሚያበቃ አልነበረም እነዚህ ጉዳዮች ለተገኘው እጅግ ዝቅተኛ ውጤት እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ እንደሆነ ያስረዳል።

“ሙሉ ጊዜዬን በመስጠት አንብቤ ውጤታማ መሆን እችላለሁ የሚል የስነልቦና ዝግጅት ያስፈልጋል፤ ምንም ጥርጥር የለውም ከተነበበ ውጤት ይመጣል፤ ነገር ግን ይህንን ሀሳብ ለራስ መንገርና ሞራል ማዘጋጀት የግድ ነው። ስለዚህ በሁሉም ነገር እራስን ብቁ አድርጎ መዘጋጀት ያስፈጋል” ብሏል።

አንድ ተማሪ ውጤታማ የሆነበት የአጠናን ስልት ለሌላው ላይሰራ እንደሚችል የሚናገረው ሙሉነህ፤ የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት አይነቶች የሆኑትን የታሪክና የጂኦግራፊ ትምህርቶችን ለአብነት ጠቅሶ፤ እነዚህ የትምህርት አይነቶች ረዥም ጊዜ ማንበብና ያነበቡትን እንደገና መከለስ የሚጠይቁ ናቸው። ስለዚህ ቢያንስ ሁለት ዓመት ሙሉ ለብሔራዊ ፈተናው ብቻ ትኩረት ሰጥቶ ማንበብ እንደሚጠይቅ ይናገራል።

ተማሪ ሙሉነህ፤ የተለያዩ የትምህርት አይነቶችን ደጋግሞ ከማንበብ ባሸገር ከዚህ ቀደም የነበሩ የብሔራዊ ፈተና ጥያቄዎችን በመስራት ዝግጅት ሲያደርግ እንደቆየ ገልጾ፤ በዚህ ሂደት አንብቦ ካልሸፈናቸው የትምህርት ዓይነቶች የመጡ ጥያቄዎች እንደነበሩ በመገንዘብ ድጋሚ ክለሳ በማድረግ እያንዳንዱን ምዕራፍ በማዳረስ መጨረሻ ላይ መጨናነቅ በሌለው ሁኔታ ለፈተናው እንደተቀመጠ ይናገራል።

ወደፊት የኢኮኖሚክስ ትምህርት በመማር ራሱን ቤተሰቡንና ሀገሩን መጥቀም እንደሚፈልግ ገልጾ፤ ለዚህም ያበቃው ዘንድ ይህንን በሁለተኛ ደረጃ የነበረውን ጉብዝና አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያብራራል።

ተማሪ ሙሉነህ ባስተላለፈው መልዕክት በሁሉም መስክ ጊዜያችንን የምንጠቀምበት መንገድ ለነገ ስኬታችንም ሆነ ውድቀታችን የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው። ማሳካት ለምንፈልገው ነገር ጊዜ ከምንም በላይ ትልቁና ወሳኙ ነገር በመሆኑ፤ ሁሉም ተማሪ አንድ ጊዜ ካለፈ የማይመልሰው መሆኑን መገንዘብ እንዳለበትም አብራርቷል።

 ክብረአብ በላቸው

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2016

Recommended For You