የማለፊያ ሠርግና ምላሽ

ወርሃ ጥቅምት እና ኪነ ጥበብ በእጅጉ የተዋደዱ ይመስላሉ። ክረምቱን አልፎ በመስከረም አደይ አበባ እያበበ የመጣው ኪነ ጥበብ፤ ባጋመስነው የጥቅምት ወር በየጥበብ ደጁ እየፈነዳ በርካታ መድረኮች ከወዲሁ ተንቆጥቁጠዋል። ከክረምቱ ብርድ ተሸሽገው ከጸሐይዋ ጋር እየወጡ በአየሩ ላይ ቱር…እንደሚሉቱ ውብ ቢራቢሮዎች፤ ከየጥበብ ዋሻው የሚወጡት ልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎችም እንዲሁ እየወጡ የጥበብ መንደርን በማሟሟቅ ላይ ናቸው። ጥቅምትም እንደ አበባዋ ሁሉ ጥበብንም ማስቀሰም ጀምራለች። በጸደይ መምጣት እየተፍነከነኩ ከአፈሩ ስር ወደላይ እንደሚምዘገዘጉት እጽዋትም፤ በአዲሱ ዓመት አዲስ መንፈስ በመነቃቃት ጥበብም ከየመድረኩ ወደላይ መፈንጠቅን ተያይዛዋለች። ከዚህ ሁሉም ገሚሱን በመታደም አንዳንዶች ሠርግና ምላሽ በሚመስል መልኩ በቀይ ምንጣፍ፤ በአበባው ክምር ሲንጎማለሉ አስመልክቶናል። አጃኢብ! ነው ብለን ካሳለፍናቸው ጥበባዊ ጉዳዮች መካከል ለዛሬ አንዱን እናድርሳችሁ።

ከጸደዩ ልምላሜ፤ ከጥቅምቱ አበባ፤ ከብሩህ ሰማይና በጥበብ ጓዳ ከተከወኑት አንዱ በሆነው ባሳለፍነው ቅዳሜ ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም ላይ አርፈናል። በእለቱ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ከሙዚቃው መንደር የጥበብ ችቦ የተለኮሰበት ብርሃናማ ምሽት ነበር። በሐምሌ ወር 2015ዓ.ም ተወዳጁ ድምጻዊ ብስራት ሱራፌል ከአራት ዓመታት ዝግጅት በኋላ ግሩም የሙዚቃ ሥራዎቹን በአልበም ይዞልን መመለሱ የሚታወስ ነው። ታዲያ ይህንንም ተከትሎ ከአልበም ሥራውና ከድምጻዊው ጋር በተያያዘ የተስተናገዱ ጉዳዮች አሉ። አልበሙም ከብዙ ነገሮች አንጻር ምናልባትም የተዋጣለት ነው ለማለት እንችላለን። ከጊዜያዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች የተነሳ አልበሙ በተለቀቀበት ወቅት ድል ባለ ዝግጅት ተመርቆ ወደ አድማጭ ጆሮ እንዲደርስ ባይደረግም፤ አሁን ግን በሠርጉ መልስ እንገናኝ ማለቱ አልቀረም። የሠርጉ ምላሽ የሆነው የአልበሙ ምርቃት የተከናወነው በዚሁ የቅዳሜ ምሽት ላይ ነበር። ከዚሁ ከምርቃቱ ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ፤ ሐሙስ ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም የጥሪ ካርዱ የተበተነበትና የቅዳሜ ምሽቱ ብስራት ለሚዲያዎች እና ለተለያዩ አካላት የተበሰረበት ዕለት ነበር። የወለዱትን ሲስሙለት የደገሱትንም ሲበሉለት ሰው ደስ እንደሚለው እንደዚሁ የአዘጋጆቹም እንግዶች ጥሪ አክባሪ ነበሩ፡፡ ጥሪውንም ያደረጉት የዚህ ታላቅ ዝግጅት አጋፋሪና ደጋሽ የሆኑት ደግሞ ብላክ ፐርል ባርና ላውንጅ ከኤላ ቲቪ ጋር በመተባበር ሲሆኑ በሐሙሱ ጥሪ በጉዳዩ ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተውበት ነበር፡፡

ሁለቱ አካላት በተቋም ደረጃ የተለያዩ ቢሆኑም፤ ባላቸው ተመሳሳይ አላማ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንደ አንድ ሆነው በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ናቸው። አሁን እየሰሩበት ባለው የብስራት ሱራፌል አልበምን ተከትሎ የመጡ አዳዲስ ነገሮች ቢኖሩም ሥራው ግን የመጀመሪያቸው አይደለም ይልቁንስ ከዚህ ቀደም የበርካታ ድምጻውያን የሙዚቃ ሥራ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት እንዲደመጡና አርቲስቶቹ እውቅናን እንዲያገኙ በብርቱ ሲተጉም ነበር። ብላክ ፐርል በሀገራችን አልፎም በምሥራቅ አፍሪካ የሙዚቃው ኢንዱስትሪ አሉ ከሚባሉት አንዱና ግንባር ቀደሙ ነው። ከእውቁ ድምጻዊ ብስራት ሱራፌል ጋርም “ማለፊያ” በተሰኘው አልበም አማካኝነት በመጣመር ለድምጻዊው ብቻም ሳይሆን ለሀገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪም መወጣጫ ድልድዩን ለመሥራት እጅ ለእጅ ተያይዘን እነሆ ተነስተናል ሲሉ አስታውቀዋል። የቅዳሜው ምሽትም ለዚሁ ማሳያ ከመሆኑም ሌላ አንደኛም ሆነ ሁለተኛ ምስክር ተደርጎ ቢቀርብ ቅጥፈት አይሆንም። መድረኩ ከአንጋፋ እስከ ወጣት ድምጻውያን በሙዚቃ ሥራዎቻቸው ወደተንቦገቦገበት ወደዚሁ የቅዳሜ ምሽት ከማውጋታችን በፊት ከበስተጀርባው ስለነበሩ ጉዳዮች ጥቂት በማለት ግብራችንን ፈጽመን እንመለስበታለን።

ድምጻዊ ብስራት ሱራፌል ከዚህ ቀደም የሰራቸው የሙዚቃ ሥራዎች ከአድማጭ ጆሮ ከገቡ በኋላ ተቀባይነትና ተወዳጅነትን ለማግኘት እምብዛም ጊዜ አልፈጀበትም ነበር። ከቅርብ የሚከታተሉት ካልሆኑ በቀር በኢትዮጵያ የዘመናዊ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ገና ስሙ ሳይነሳ መግነጢሳዊ በሆነ መልኩ ተነስቶ ከፊተኞቹ ጋር የተገኘ ትጉህ ሙዚቀኛ ነው። ካማረ ድምጹ ጋር ባማረ ሥራው ወደ ሙዚቃው ቤት ሲገባ በአክብሮት ‘ኖር’ እያለ ተነስቶ በአድናቆት ያልተቀበለው አድማጭ አለ ለማለት ያዳግታል። በግሉም ሆነ ከሌሎች እውቅ ድምጻውያን ጋር በመጣመር ያቀረባቸው ሥራዎቹ ለብዙኃኑ አድማጭ እንከን የለሽና ይህ ቀረሽ የማይባል ነበር። አሁን የሠራው ማለፊያ አልበም በግሉ ሁለተኛው ሲሆን ከሌሎች ድምጻውያን ጋር በጥምረት የተሳተፈበተን አንድ አልበም ጨምሮ በድምሩ ሦስት አልበሞችን ሠርቷል። ከሰራቸው ሥራዎች መካከል ከስድስት ዓመታት በፊት ለአድማጭ ጆሮ ያደረሰው “የቤት ሥራ” አሊያም ‘ሆንሽብኝ የቤት ሥራ…’ ከሙዚቃ ምቱ አንስቶ ግጥምና ዜማው ከአፋችን የማይጠፋ ሆኖብን የከረምን ብዙ ነን። ‘ተንኳኳ… ተንኳኳ’ በሚለውም ዜማ ቢሆን ሙዚቃዊ የስሜት በራችን ያልተንኳኳብን ያለን አይመስለኝም። እንግዲህ ለማስታወስ ያህል ነውና በዚህኛው የ”ማለፊያ” አልበምም ‘እረፊን’ እንዲሁም ስለ ሀገር ያቀነቀነውን “ሀገሬ መልኬ”ን ጨምሮ ሌሎቹንም ዜማዎች በየመንገዱና ታክሲው፤ በየሄድንበት በአንደኛው አጋጣሚ በሽውታም ቢሆን በጆሯችን ጨልፈን ሰምተነዋል አሊያም ደግሞ አድምጠነዋል የሚል ተስፋ አለኝ። ብስራት ሱራፌል በሙዚቃው ውስጥ ያበረከተውና እያበረከተ ያለው በድምጹ ብቻም አይደለም። ከዚህ ባለፈም ከራሱ አልፎ አዳዲሶቹን ጨምሮ ለበርካታ እውቅ ድምጻውያን ግጥምና ዜማ በመስጠት ይታወቃል። ለአብነት ያህል ኩኩ ሰብስቤ፣ ሔለን በርሄ፣ ሃይማኖት ግርማ፣ ቬሮኒካ አዳነ፣ ሀብቴ አሻጋሪ፣ ሀሌሉያና ‘ጆሲ ኢን ዘ ሀውስ’ ወይንም ዮሴፍ ገብሬን መጥቀስ ይቻላል። የጥምር ተሰጥኦ ባለቤትነቱ በጥምር ዕድል የተሳካ የሙዚቃ ሕይወት እንዲኖረው አድርጎታል።

በአሁኑ ሰዓት ድምጻዊ ብስራት ሱራፌልና የታቀፈበት ብላክ ፐርል የተሰኘው ድርጅት /ከበስተጀርባው ኤላ ቲቪ እንዳለው ሆኖ/ በሁለቱም መካከል የስምምነት ፊርማ አኑረዋል። በውሉ መሠረትም ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ድረስ የሚሰነብት የሥራ ቆይታ የሚያደርጉ ይሆናል። ድርጅቱ ከውጭ በኩል ከሚያደርገው ግንኙነት ባሻገር በሀገር ውስጥ ወደ ሙዚቃ ኢንዱስትሪው መግባት የሚፈልጉ ጀማሪ ወጣት ሙዚቀኞችንም በማሰልጠን ብቁ የማድረግ በጎ ዓላማም ስላለው በማብቃት ሂደቱ ብስራት ሱራፌልም በሙያው በማገዝ በእንቅስቃሴው የድርሻውን ይወጣል። በተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችም ግንባር ቀደም በመሆን ይሳተፋል። በአጠቃላይ የተቋሙ ትልቁ ራዕይ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ወደ ልህቀት መንገድ ማስገባት እንደሆነ አስቀምጠውታል። ቀደም ሲል በመግለጫው እለት ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው አንድ ጥያቄ ነበር፤ “የድምጻዊውን ማለፊያ የተሰኘውን አልበም ሙሉ ለሙሉ ተረክባችሁታልና ለዚህ ሥራው የፈጸማችሁለት ክፍያ ምን ያህል ነው?” “ሁለታችንም የጋራ ስምምነት በማድረግ በቂ ክፍያ ፈጽመንለታል። እሱም ቢሆን በክፍያው ደስተኛ ነው” ሲሉ መልሰዋል። ብዙውን ጊዜ በእንዲህ ዓይነት ስምምነቶች ውስጥ የሙያው ባለቤቶች የሚጎዱበት ሁኔታ ስላለ በእርግጥም ጥያቄው ትክክለኛ ነበር። ከዓመታት በፊት ተወዳጁ ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ካቀረበው አንድ ኮንሰርት በኋላ ለማግኘት የተስማማሁትን ገንዘብ አላገኘሁም በማለት ከአዘጋጆቹ ጋር ወደ ፍርድ ሸንጎ መቅረባቸውን እናስታውሰው ይሆናል። የዳኝነት ሙግቱ ተጠናቆ የፍርድ ውሳኔ የተላለፈውም በዚሁ የጥቅምት ወር ከቀናት በፊት ነበር።

ድምጻዊ ብስራት ከሰሞኑ የተሞሸረበት “ማለፈያ” የተሰኘው አልበም የእውነትም ማለፊያ ድልድይ ሆኖታል። በማለፊያ አልፎ በብላክ ፐርል አሳልጦ ከዓለም አቀፍ መድረኮችና አቀንቃኞች ጋር ለመገናኘት በዝግጅት ላይ ነው። ብላክ ፐርል በመግለጫው እለት ሹክ እንዳለው ከሆነም ወደዚሁ የሚገባበትን ትኬት ቆርጧል። ከአልበም ምርቃቱ በኋላ በሀገር ውስጥ በተለያዩ የክልል ከተሞች፤ ከዚያም በምሥራቅ አፍሪካና የአውሮፓ ሀገራት እየተዘዋወረ አዳዲስና ነባር ሥራዎቹን እንደሚያቀርብ ተናግረዋል። እንግዲህ ጥበብም በእናትነት ወግ ምራቋን እንትፍ አድርጋና መርቃ እንደምትሸኘው፤ እሱም ለሀገሩ ባህልና የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ኮሶና እሬቱን ሳይሆን ማርና ወተቱን ይዞ ይመለሳል የሚል ተስፋዊ እምነትን እንቋጥራለን።

ማለፊያ በቅዳሜው ምሽት እንደምን አለፈ… በህብረ ቀለማዊ ብርሃን ያሸበረቀው የሸራተን አዲስ ጋዝ ላይት አዳራሽ ከወትሮ በተለየ ፈገግታን አብዝቶ ነበረ። ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የመድረኩ ግርማ ሞገስ የነበሩ ድምጻውያንና የተለያዩ አርቲስቶች በቀጠሮው ሰዓት በመድረስ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ልዩ ነበር፡፡ ሰማዩ እየጠቆረ በመጣ ቁጥር ሸራተን ግን ይበልጥ ፈገግ እያለች በደማቁ ስትብረቀረቅም ነበር። በምሽቱ በተከፈተው ሙዚቃዊ የጥበብ በር አንዳች ነገር እየገባ መድረክና አዳራሹን አጥለቅልቆት አምሽቷል። ከወጣት እስከ አንጋፋ ድምጻውያን በመድረኩ ሽር ብትን እያሉ ታዳማዊን ባማረ ሁኔታ አዝናንተውታል። ከአልበም ምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ባለፈ ወደ 16 ለሚደርሱ ልዩ ልዩ አካላት ስለ አበርክቷቸው ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ዝግጅቱን በጥምረት ያሰናዱት ሁለቱ አካላትም አልበሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭ እንዲሆን በአሁኑ ሰዓት ከ’ትሬስ ሙዚክ’ ጋር በጋራ እየሰሩ ስለመሆናቸው ተናግረዋል። እንዲሁም ቀጣይነት ባለው መልኩ ሌሎች የሀገራችን የሙዚቃ ሥራዎችም ከዚሁ ዕድል ተቋዳሽ እንዲሆኑ በትጋት የሚሰራ ስለመሆኑም አውስተዋል። እንደሚታወቀው ‘ትሬስ ሙዚክ ኢትዮጵያ’ የዓለም አቀፉና የአውደ ሰፊ ስርጭት ባለቤት የሆነው የ’ትሬስ ሙዚክ ወርልድ’ አንደኛው የሥርጭት መስመር ነው። በ’ትሬስ ሙዚክ’ የሚቀርቡ የሙዚቃ ሥራዎች የእይታ አድማሳቸው ዓለም አቀፋዊ እንደመሆኑ የሀገራችንን ሙዚቃ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ሁነኛው መንገድ ነው። የሙዚቃውን ኢንዱስትሪውንም በማነቃቃትም ወደተሻለ የታዋቂነት ደረጃ ከፍ ያደርገዋል።

ሠርጉ ተሰርጓል የ’ማለፊያ’ ባለቤትም ከነአልበሙ ተመርቆ ወደ ቀጣዩ ዓለም አቀፍ መድረክ በክብር ተሸኝቷል። ምላሹ ግን ገና አላበቃም። ከአንዱ ሠርግ ወዲያ ማዶ እልፍ ድግስ እልፍ ምላሽ አለ፡፡ ሲሄድ በእናትነት ወግ ምራቅ እንትፍ አድርጋ በመመረቅ ማርና ወተቱን አሲዛ የምትሸኘው የሀገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ተመልሶ ሲመጣ ከእርሱ የምትጠብቀው ሌላ ስጦታ ይኖራል። መሄድን ብዙዎች ሄደዋል ነገር ግን መመለሻው ጠፍቷቸው በምድረ በዳ ሲናውዙ የባዕዳን አሞራ ተቀራምቷቸው ሌጣቸውን የቀሩም አሉ። ወደ ዓለም አቀፉ የሙዚቃ መድረኮች በመቀላቀል ሰበብ የሀገሬን ሙዚቃ አሳያለሁ እያለ ወጥቶ፤ የማያጠግበንን በመጎምዠት ባህልና ሥርዓቱን፤ የያዘውንም የሀገሩን ሙዚቃ እንደ ልብስ አውልቆ መለመሉን የቀረም ብዙ ነውና ። በማለፊያ አልፎ የሚሄደውንም ሠርጉን በምላሹ ያድርገው በማለት አበቃን።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You