በአሁኑ ወቅት እንደ አግሮ ኢኮኖሎጂው ሁኔታ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመኸር ወቅት አዝመራ መድረስ ጀምሯል። ይህንን የደረሰ የሰብል አዝመራ እንዲሁም በቀጣይ የሚደርሰውንም አዝመራ መሰብሰብ ደግሞ ወቅቱ የሚጠይቀው ትልቁ የግብርና ሥራ ነው።
ለዚህም እንደተለመደው አርሶ አደሩ፣ የግብርና ባለሙያው፣ ሌሎች ከግብርና ጋር ግንኙነት ያላቸው መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የግሉ ዘርፍ ተቀናጅተው በትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ሌሎች የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችም በሚደርሳቸው ጥሪ መሠረት በአዝመራ ስብሰባው እንደሚሳተፉ ተሞክሮዎች ያመለክታሉ።
እንደሚታወቀው የግብርናው ዘርፍ ለሀገራችን የምጣኔ ሀብት ዋና መሠረት ሆኖ ዘመናት አስቆጥሯል። ከዚህም የተነሳ ይህ ወቅት በተለይ ለአርሶ አደሩ ለዘመናት የትኩረት ስበት ማዕከል ሆኖ ቆይቷል።
አሁንም ቢሆን እንደ ሀገር በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል ከጀመርነው ሀገራዊ ጥረት አንጻር ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ ያለ ትኩረት ተሰጥቶት፤ በኃላፊነት መንፈስ መሥራትን የሚጠይቅ እንደሆነ ይታመናል።
እንደሚታወቀው፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ሀገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች። በዚህም እየተመዘገበ ያለው ውጤት ተስፋ ሰጭ ስለመሆኑ በተጨባጭ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች ማሳያ ናቸው።
በተለያዩ አማራጭ የአስተራረስ ዘዴዎች እና ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ በጤፍ ምርት ላይ የታየው ምርታማነት፤ በበጋ ስንዴ እርሻ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያተረፈው ስኬት፤ የሩዝ እርሻን ለማስፋፋት እየተደረገ ባለው ጥረት የታየው መነቃቃት …ወዘተ ለእነዚህ ሁነኛ አብነቶች ሆነው ይቀርባሉ።
ከዚህም ባለፈ በዘርፉ ያለውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በዘር የሚሸፈነውን ማሳ በየዓመቱ ለመጨመር እየተደረገ ያለው ጥረትና ይህን ተከትሎ እየተመዘገበ ያለው ውጤት አበረታች ሆኗል። በተያዘው የምርት ዘመንም 573 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው። 17ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማረስ ታቅዶ 18 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን መቻሉን በቅርቡ የወጣ መረጃ ያመላክታል። ይህም ከፍተኛ መጠን ያለው መሬት በዘር መሸፈኑን ያመለክታል።
ቴክኖሎጂንና ባለሙያን አቀናጅቶ በጋራ ለመጠቀምና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም ግብርናውን ትራንስፎርም ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ታምኖበት እየተሰራበት ያለው የኩታ ገጠም እርሻ እየተስፋፋ ይገኛል። በዚህ የመኸር ወቅት ስድስት ነጥብ ሰባት ሚሊየን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ያስተራረስ ዘዴ ለማልማት ታቅዶ፣ ስድስት ነጥብ 35 ሚሊየን ኩንታል ማረስ መቻሉንም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በአሲዳማነት የተጠቃን መሬት በማከም፣ እንደ በቆሎ ያሉ ሰብሎችን በእሸትነታቸው ለገበያ እንዲውሉ በማድረግና ማሳውን በሌላ ሰብል በመሸፈን፣ ረግረጋማ ቦታዎችን በማረስ፣ ወዘተ.. ከፍተኛ መጠን ያለው ማሳ በዘር ተሸፍኗል። በሰሜኑ ኢትዮጵያ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ጦሙን ያድር የነበረ መሬት በዘር የተሸፈነበት ሁኔታም ተፈጥሯል።
በዚህ ሁሉ ርብርብ በዘር የተሸፈነው ማሳ አዝመራ አሁን እየደረሰ ይገኛል። ይህን አዝመራ በተቀናጀ መልኩ በርብርብ መሰብሰብ ቀጣይ ሀገራዊ የቤት ሥራ እንደሆነ ይታመናል። ለዚህ ደግሞ ሰፊ የሰው ኃይል አሰማርቶ አዝመራ ከመሰብሰብ ጎን ለጎን ቴክኖሎጂን በሚቻለው አቅም አቀናጅቶ መጠቀም ይገባል፤ ይህም አዝመራን ፈጥኖ ከመሰብሰብ ባለፈ በምርት መሰብሰብ ወቅት የሚፈጠር ብክነትን ለመቀነስ ወሳኝ ነው።
ከዚህም ባለፈ በቅርቡ የወጣ የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ እንዳመለከተው፤ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ከመደበኛው በላይ የሆነ ዝናብ ሊጥል ይችላል። ይህ መረጃ በራሱ ለአዝመራ ስብሰባው ከፍተኛ ትኩረት መስጠት የሚያስፈልግ ስለመሆኑ አመላካች ነው።
በተለያዩ ዓመታት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በአዝመራ ላይ ጉዳት እንዳያስከትል የመከላከያ ሠራዊት አባላትን፣ ተማሪዎችን፣ መምህራን፣ የከተማ ነዋሪዎችን ወዘተ..፣ በአዝመራ ስብሰባ እንዲሰማሩ በማድረግ ሰብል እንዲሰበስቡ ሲደረግ ኖሯል። አሁንም ከአየር ንብረት መዛባት ጋር ሊያጋጥም የሚችለውን ስጋት በተመሳሳይ መልኩ ለመፍታት በቂ ዝግጅት ማድረግ ይገባል።
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም