በፈረንጆቹ የመጨረሻው ወር የመጀመሪያ ሳምንት የቫሌንሺያ ማራቶን ይካሄዳል። ታዲያ በዚህ ሩጫ ላይ ድንቅ ብቃታቸውን በተለያዩ ውድድሮች ላይ ያሳዩ አትሌቶች እንደሚፋለሙ ከወዲሁ ተረጋግጧል። ይሁንና የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ በይበልጥ የሳበው የረጅም ርቀቶች ንጉሱ ቀነኒሳ በቀለ በዚህ ማራቶን መሳተፉ ነው። በርቀቱ ሶስተኛው የፈጣን ሰዓት ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያዊው አትሌት በርካቶች ተስፋ እንደሚያደርጉት የማራቶንን ንግስና ከእጁ ሊያስገባ አሊያምየመጨረሻውን የኦሊምፒክ ተሳትፎውን ሊያሳካ የሚችልበት እድል እንደሚኖረው ይታመናል።
በመም፣ በሀገር አቋራጭ እንዲሁም በማራቶን ተደራራቢ ስኬቶችን ማጣጣም የቻለው አንጋፋው አትሌት የሰው ልጅ 42 ኪሎ ሜትርን ከ2ሰዓት በታች መግባት ይችላል የሚለውን እምነት ሊያሳኩ ከሚችሉ አትሌቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው። እንደሚታወቀው በሁለት ኦሊምፒኮች እንዲሁም በአራት የዓለም ቻምፒዮና መድረኮች በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች 8የወርቅ፣ 1የብር እና 1 የነሃስ በጥቅሉ 10 ሜዳሊያዎችን ማጥለቅ የቻለ ጀግና አትሌት ነው። ከመም ባለፈም በሀገር አቋራጭ ውድድር በዓለም የእሱን ያህል በድል የተንቆጠቆጠ አትሌት አልታየም። ወደ ማራቶን ከተሸጋገረም በኋላ በለንደን እና በርሊን ማራቶኖች ተደጋጋሚ ፉክክር በማድረግ በርቀቱ ክብረወሰኑን ለማሻሻል ከጫፍ ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም። እአአ በ2019 በርሊን ማራቶን ላይ ያስመዘገበው 2:01:41 የሆነ ሰዓት በወቅቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ከነበረው ኬንያዊው አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ በ2 ሰከንዶች ብቻ የዘገየ ነበር።
ይህ እንዲሁም ቀነኒሳ ካለው የሩጫ ብቃት አንጻርም በመም ውድድሮች ሁሌም አስከትሎት ይገባ ከነበረው ኪፕቾጌ እጅ ክብረወሰኑን ሊረከብ እንደሚችል የበርካቶች ግምት ነበር። በርግጥ የስፖርት ባለሙያዎች እንዲሁም ራሱ ቀነኒሳም በርቀቱ አዲስ ታሪክ የመጻፍ ችሎታ እንዳለው ሲያረጋግጡ ቆይተዋል። ይሁንና በተደጋጋሚ ጉዳት እየፈተነው መሆኑ በጉጉት ከሚጠበቅበት ውድድር ሳይቀር አቋርጦ ለመውጣት ሲገደድ ቆይቷል። በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የውድድር ዓመትም በቫሌንሺያ በሚካሄደው ማራቶን ላይ እንደሚካፈል ታውቋል። ይኸውም ሁሌም የአትሌቱን ድንቅ ብቃት ለመመልከት ለሚጓጉ የስፖርቱ ወዳጆች መልካም ዜና ነው።
ቀነኒሳ በዚህ ውድድር የሚካፈለውም ሁለት ዓላማዎችን ይዞ ሲሆን፤ የመጀመሪያው በሩጫ ሕይወቱ ተጨማሪውንና እጅግ ታሪካዊ ሊሆን የሚችለውን አዲስ ክብረወሰን ወደኢትዮጵያ ለመመለስ ነው። በቅርቡ በማራቶን ክብረወሰኑን የጠቀለለው ኬንያዊው አትሌት ኬልቪን ኪፕቱም በዚህ ውድድር ላይም ይሳተፋል በሚል ይጠበቃል። ይህም ፉክክሩን የሚያልቀው ሲሆን፤ ሰዓት ለማሻሻልም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ሌላኛው ደግሞ ወራት ብቻ ለሚቀሩት የፓሪስ ኦሊምፒክ ለራሱና ለሀገሩ ሶስተኛውንና ምናልባትም የመጨረሻውን ተሳትፎ ለማድረግ ነው። አትሌቱ ከዚህ ቀደም በማራቶን ቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ ሀገሩን ለመወከል ተመርጦ ዝግጅት ሲያደርግ ቢቆይም በወቅቱ በነበረው ውዝግብ ምክንያት ከቡድኑ ጋር አለመጓዙ የሚታወስ ነው።
ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ የዚህ ውድድር ተሳትፎው ካለፈው ጊዜ ለየት የሚያደርገው ሌላኛው ጉዳይ ለሁለት አስርት ዓመታት ከቆየበት ማኔጅመንት ተለይቶ ከአዲስ የማኔጅመንት ጋር ውል በተፈራረመበት ማግስት መሆኑ ነው። ከዚህ ቀደም በርካታ ውጤታማ ኢትዮጵያዊያን እና ኬንያዊያን አትሌቶችን ባቀፈው ‹‹NN የሩጫ ቡድን›› ይሰለጥን የነበረው አትሌቱ ስፖንሰሩም ናይኪ የተሰኘው የስፖርት ትጥቅ አምራች ነበር። ያለፉትን ስኬቶች ያጣጣመውም በዚሁ ቡድን ውስጥ ነበር። አሁን ደግሞ የቻይና መሠረት ያለውና ‹‹ANTA›› ከተሰኘ ትጥቅ አምራች ጋር ለመሥራት ውል ያሰረ ሲሆን፤ የመጀመሪያውን ውድድር ከወር በኋላ ቫሌንሺ ላይ ያደርጋል።
ከቀድሞ ቡድኑ ጋር መለያየቱን ተከትሎም ‹‹ቀነኒሳ ስለቀጣዮቹ የሩጫ ዘመኖችህ መልካሙን ሁሉ እንመኛለን። ባለፉት ዓመታት ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን ሁሌም አብረንህ ነን›› ሲል ምርጥ አትሌቱን ሸኝቷል። አዲሱ ቡድኑና በግዝፈቱ ከናይኪ እና አዲዳስ ቀጥሎ የሚቀመጠው የትጥቅ አምራች ደግሞ ከቀነኒሳ ጋር መዋዋሉን ተከትሎም በማህበራዊ ድረገጹ ‹‹ቀነኒሳ ስለተቀላቀለን ተደስተናል። ከአትሌቱ ጋር በመሆንም አፍሪካ ላይ የስልጠና ማዕከል በመገንባት እንዲሁም በቀነኒሳ ሪዞርት ላይ አትሌቶችን የሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ እናተኩራለን›› ሲል አስፍሯል። ይህም ስምምነቱ ከአትሌቱ ባለፈ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንንም ሊጠቅም የሚችል እንደሚሆን ይገመታል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም