ከወደ አፍሪካና ደቡብ አሜሪካ የተገኙ በርካታ ከዋክብት የኋላ ታሪክ ዛሬ ላይ ጊዜ አልፎ ሲወሳ በጥሩ ደራሲ እንደተፃፈ ልብ አንጠልጣይ ልብ ወለድ ሊመስል ይችላል። እንዲህ አይነት ታሪክ ያሳለፉ ከዋክብት ዛሬ ላይ የዝናና የሀብት ማማ ላይ ሆነው ያለፈ ታሪካቸውን ሲያጋሩ ግን እንደነሱ አይነት የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ለሚገኙ የድሃ ሀገራት ታዳጊ እግር ኳስ ተጫዋቾች በገንዘብ የማይገኝ ብርታትና ተስፋ ነው።
ዛሬ ታሪኩን ከብዙ በጥቂቱ መዘን ልንመለከተው የወደድነው ወጣት የዓለማችን ኮከብ ለታላቅ ስኬት ሲበቃ ያላየው ውጣ ውረድ ያላሳለፈው ችግር የለም። ከስደተኞች ካምፕ እስከ አስከፊ የእርስበርስ ጦርነትና ስር የሰደደ ድህነት በአጭር ሕይወት ጉዞው ተፈራርቀውበታል። በገጠሙት ተስፋ አስቆራጭ የሕይወት ፈተናዎች ግን ተስፋ አልቆረጠም፣ የገጠሙት እንቅፋቶች ፈገግታውን ከፊቱ ላይ አላጠፉትም፣ ሁሉንም ተሻግሮ ለቤተሰቡ የገባውን ቃል በአጭር እድሜው ፈፅሞ ከሰቆቃ ሕይወት ታድጓል።
ታላቁ የዓለማችን ክለብ ሪያል ማድሪድ በቅርቡ አዲስ ውል ሲያስፈርመው ኮንትራት ማፍረሻውን ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ ሪከርድ አንድ ቢሊዮን ፓውንድ ዋጋ የለጠፈበት የኤድዋርዶ ካማቪንጋ ያለፈ የሕይወት ውጣ ውረዱ አስገራሚም አስተማሪም ነው። ይህ የብዙዎች ቀልብ ያረፈበት ወጣት በከዋክብቶቹ ካምፕ ቤርናቦ የተገኘው ከስደተኞች ካምፕ ተነስቶ ነው።
ካማቪንጋ የተወለደው በአንጎላ ሚኮንሄ በተባለ አነስተኛ ማህበረሰብ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ነው። ቤተሰቦቹ ወደ ስደተኛ ካምፕ የመጡት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተፈጠረውን የእርስበርስ ጦርነት ሸሽተው ነበር። የመጪው ዘመን ተስፋ የተጣለበት ኮከብ በዚህ የስደተኞች ካምፕ ነው የተወለደው። ይህ ጨቅላ ወደዚህች ዓለም ሲቀላቀል ብቻውን አልነበረም። የኋላ ኋላ ለቤተሰቡም ማለፊያ የሆነ የራሱን ገድ ይዞ ነበር የተወለደው። ይህም ለዓመታት በስደተኛ ካምፕ መኖሪያቸውን ያደረጉ ቤተሰቦቹ 2003 ላይ በፈረንሳይ ሬኔስ ሃምሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ስፍራ መኖሪያቸውን የሚያደርጉበት የተሻለ ሕይወት እንዲያገኙ አድርጓል። የዛሬው የዓለማችን ኮከብ የካማቪንጋም የልጅነት ሕይወትም ከዚህች መንደር ይጀምራል።
ዛሬ የእግር ኳሱ ዓለም ውድ ተጫዋች የሚያደርገው ሪከርድ የሰበረ ውል ማፍረሻ ዋጋ የተለጠፈበት ኮከብ በትንሿ መንደር ሲያድግ ከስድስት እህትና ወንድሞቹ መካከል ለቤተሰቡ ሶስተኛ ልጅ ሆኖ ነው። ይህም ለስደተኛው ቤተሰብ ቀላል ፈተና አልነበረም። በልጅነቱ ረባሽ የሚባል አይነት ታዳጊ የነበረው ካማቪንጋ ብዙ ጊዜውን ቤት ውስጥ ነበር የሚያሳልፈው። በዚህም ፊት ለፊቱ ያገኘውን የቤት እቃ በማተራመስና በመስበር ሲያስቸግር በተለይም እናቱ የጁዶ ስፖርት ቢያዘወትር ብለው መላ ዘየዱ። የእናት ፍላጎት ታዳጊ ልጃቸው ከፍ እያለ ሲሄድም በጁዶ ስፖርት እንዲገፋበት ነበር ፍላጎታቸው። ይሁን እንጂ ታዳጊው ካማቪንጋ ከጁዶው ይልቅ የኋላ ዘመኑ የሕይወቱ ጥሪ በሆነው እግር ኳስ ተማርኮ ያገኘውን ኳስ በእግሩ ማንከባለል ነበር የሚቀናው። ይህን ያስተዋሉት አባቱ ካሌስቲኖ አቅራቢያቸው ወደ ሚገኘው ድራፕ ፊዩገርስ ወደ ተባለ ዘመናዊ እግር ኳስ ክለብ ገና በሰባት ዓመቱ ይዘውት ነጎዱ።
የክለቡ አሰልጣኞችም ትንሹ ካማቪንጋ ልዩ የእግር ኳስ ተሰጥኦ እንዳለው ለማወቅ ጊዜ አልፈጀባቸውም። በእድሜ ከሚበልጡት ጋር እያጫወቱት ይበልጥ አቅሙን አውጥቶ እንዲጠቀም አገዙት፣ እሱም በዚህ መደሰት ቀጠለ። ከሰባት ዓመቱ ጀምሮ ዓይኑን ተክሎ በትኩረት ይከታተለው የነበረው የፈረንሳዩ ክለብ ሬኔስ በታዳጊው ልጅ አስደናቂ የእግር ኳስ ክህሎት መማረኩን ቀጥሏል። አሁን ታዳጊው ካማቪንጋ የአስራ አንድ ዓመት ተስፈኛ ሆኗል። ሬኔስም በአንድ ክረምት የረፍት ቀን ይህን ታዳጊ ወደ ታዳጊ ቡድኑ ጋብዞ የእግር ኳስ ችሎታውን በቅርቡ ሊመለከት እድል ሰጠው። በዚያ አጋጣሚ ከታሰበው በላይ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ታዳጊ የአካባቢውን ትልቅ ክለብ የታዳጊ ቡድን ለመቀላቀል በር ተከፈተለት። በድህነት ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ለሚገፋው ስደተኛ ቤተሰብ ከዚህ በላይ የሚያስፈነጥዝ ብስራት የለም።
አንዳንድ የሕይወት ፈተናዎች ግን በአንዳንድ ሰዎች ላይ ይበረታሉ፣ ይደጋገማሉ። አንዱን አለፍኩ ሲሉ ሌላ ይመጣል። ካማቪንጋና ቤተሰቦችም ተስፋ ባደረጉበት ልጃቸው ደስታ ማግስት እንዲህ አይነት ነገር ነበር የገጠማቸው። ታዳጊው ልጅ በእግር ኳስ ትልቅ ተስፋ እየታየበት ሲመጣ በ11 ዓመት እድሜው በእሱና በቤተሰቡ ላይ አሳዛኝ ክስተት በራቸውን አንኳክቶ መጣ። ካማቪንጋ ለሬኔስ ታዳጊ ቡድን ለመፈረም ሁሉንም አስፈላጊ ሂደቶች ለመጨረስ ተቃርቦ በነበረበት ወቅት ትምህርት ቤት እያለ መኖሪያ ቤታቸው በእሳት ወደመ። ስደተኛውና ምስኪኑ ቤተሰብ በእሳት አደጋው አንድም ነገር ማትረፍ ሳይችል ባዶ እጁን ቀረ። ዓይናቸው እያየ ከስደተኞች የካምፕ ኑሮ የገላገላቸው መኖሪያ ቤት የእሳት ሲሳይ ሲሆን ቆሞ መመልከት እጣ ፋንታቸው ሆነ። ከእጅ ወዳፍ በሆነ ኑሮ የቆጠቡት ርዝራዥ ባለመኖሩ ቤተሰቡ አደጋ ላይ ወድቆ አስጨነቃቸው።
“ሁሉንም ነገር አጡ፣ በእሳት የጋየው የቤት ፍርስራሽ በእንባ ባህር ታጠበ” ይላል ካማቪንጋን ገና ከጅምሩ ኳስ ሲያሰለጥነው የነበረው ኒኮላስ ማርቲንስ የተባለ ሰው ቤተሰቡን ተስፋ ስላስቆረጠው የእሳት አደጋ ሲያስታውስ። በአሳዛኙ ክስተት የካማቪንጋ ቤተሰቦች መሠረታዊ ፍላጎታቸውን የሚሞሉበት ነገር ከረድኤት ድርጅቶች ማግኘታቸው ግን ለጊዜውም ቢሆን እፎይታ ሆናቸው።
ካማቪንጋ ያ የሰቆቃ መቼም አይዘነጋውም። “ያን የእሳት አደጋ ልክ እንደ ትናንት አስታውሰዋለሁ፣ ትምህርት ቤት ሆኜ የእሳት አደጋ ሠራተኞች እየተጣደፉ ሲሄዱ በመስኮት እመለከት ነበር፣ የእለቱ ትምህርት ሲጠናቀቅ መምህራን መጥተው እኔና እህቴን ስለተፈጠረው ነገር አረዱን፣ አባታችንም መጥቶ ወሰደን፣ ቤታችን ስንደርስ ሁሉም ነገር በእሳት እንዳልነበር ሆኖ ጠበቀን” ይላል። ካማቪንጋ ተስፋ አስቆራጩን ክስተት በዓይኑ ከተመለከተ በኋላ አባቱ የነገረውን ቃል ግን የወደፊት እጣፋንታውን አቅጣጫ የለወጠ ትልቅ የሕይወት ስንቅ እንደነበር አይረሳውም። “አትጨነቅ የዓለማችን ምርጥ ተጫዋች ስለምትሆን ቤታችንን መልሰህ ትገነባዋለህ” በማለት አባት ሰማይ የተደፋበት ያህል የተጨነቀውን ወጣት በተስፋ ሞሉት። በዚህ የአባት ምክር ታታሪ እንደሆነና እንደጠነከረ ካማቪንጋ ይናገራል። “የቤተሰቤ ተስፋ ነበርኩ፣ ይህም የተሻለ ደረጃ ለመድረስ አነሳሳኝ፣ ሁሉም በእኔ ደስተኛ ነበር ይበልጥ ደስተኛ ለማድረግም ተነሳሁ” የሚለው ካማቪንጋ ዛሬ ላይ ያሰበውን ገና በጊዜ ማሳካት ችሏል። እድሜው ሃያ ሳይሞላ የዓለማችን ከዋክብቶች የዘወትር ህልም የሆነውን የሃያሉን ክለብ የሪያል ማድሪድ ማለያ ከስደተኞች ካፕ ተነስቶ ለመልበስና በታላቁ ሳንቲያጎ ቤርናቦ ለመታየት በቅቷል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11 ቀን 2016 ዓ.ም