አንዳንድ የኪነ ጥበብ ሥራዎች የሀገር ታሪክ ይሆናሉ፤ ሀገርን ያስተዋውቃሉ። ከእነዚህ የኪነ ጥበብ ሰዎች ውስጥ ባለቅኔ፣ ሰዓሊ፣ ገጣሚ.. የሆነው ገብረክርስቶስ ደስታ እና የቤተ ክህነት ሊቅ፣ ደራሲ፣ አርበኛ፣ መምህር፣ ዲፕሎማት … የነበሩት የክብር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ የዚህ ሳምንት ክስተቶች ናቸው። የሁለቱን ከያኒዎች ታሪክ ከማየታችን በፊት ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን እናስታውስ።
ስመ ጥሩው አርበኛ እና የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሊቀ መንበር የነበሩት ደጃዝማች ኪዳኔ ወልደመድኅን ያረፉት ከ44 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 9 ቀን 1972 ዓ.ም ነበር።
ሻምበል ማሞ ወልዴ በሜክሲኮ ኦሊምፒክ፣ በማራቶን ሩጫ የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈው ከ55 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 10 ቀን 1961 ዓ.ም ነበር። ከህመሙ ጋር እየታገለ በውድድሩ ላይ የተሰለፈው አበበ ቢቂላ 17 ኪሎ ሜትር እንደሮጠ ውድድሩን አቋረጠ። አበበ ማሞን ጠርቶ ‹‹እኔ ሩጫውን አልጨርስም፤ ላቋርጥ ነው። ማሞ አደራህን እንድታሸንፍ፣ ወርቁ ከኛ ማለፍ የለበትም። አደራ!›› ብሎ ነግሮት ነበር። ማሞም አሸንፎ አበበንም ኢትዮጵያንም አኩርቷል።
የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዘመናዊ ሐኪም የሚባሉትና በብሪታኒያ የኢትዮጵያ ዋና መልዕክተኛ የነበሩት አዛዥ፣ ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ (Dr. Charles Martin) ያረፉት ከ71 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 11 ቀን 1945 ዓ.ም ነበር።
ሻምበል አበበ ቢቂላ በቶኪዮ ኦሊምፒክ፣ በማራቶን ሩጫ የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈው ከ59 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም ነበር።
ገብረክርስቶስ ደስታ
ባለቅኔ፣ ሠዓሊ፣ ገጣሚ እና ሁለገብ የጥበብ ባለሙያ የነበረው ገብረክርስቶስ የተወለደው ጥቅምት 5 ቀን 1924 ዓ.ም ሐረር ከተማ ውስጥ ነው። አባቱ አለቃ ደስታ ነገዎ የቤተ ክህነት ትምህርት የተማሩ የራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል (የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አባት) ባለሟል ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪም በብራና የእጅ ጽሁፎቻቸውና በባህላዊው ሥዕሎቻቸው የተደነቁ ሰው እንደነበሩ ይነገራል። የአባቱ የሥዕል ሥራዎች ተፅዕኖ ሳያሳድሩበት እንዳልቀረም ይገመታል። በእርግጥ በአንድ ወቅት ባደረገው አጭር ቃለ መጠይቅ ስለ አባቱ እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበር።
‹‹ … አባቴ ቅዱሳን መጽሐፍትን በእጁ ይጽፍ ነበር። በዘመኑ ዘመናዊ የህትመት መሣሪያ በሀገራችን የነበረ ቢሆንም በኖረው ባህል መሠረት በእጅ የተዘጋጁ መጽሐፍቱ ተመራጭ ነበሩ። ለመጽሐፍቱ ዝግጅት የሚያስፈልገውን መጻፊያም ሆነ ቀለሙን ያዘጋጅ የነበረው እራሱ ሲሆን በቅዱሳን መጽሐፍቱ ውስጥ የሚካተቱ ምስሎችን ይሠራ ነበር። በልጅነት ጊዜዬ የአባቴን ሥራዎች እያየሁ እደነቅ ነበር። በየቀኑ ሥዕል እንድሠራም ያበረታታኝ ነበር።››
ገብረክርስቶስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በሐረር ካጠናቀቀ በኋላ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ ወደ አዲስ አበባ አቀና። ወደ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት ገብቶ ከነመንግሥቱ ለማ ጋር መማር ጀመረ። ከትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ጋር በመጋጨቱ ትምህርቱን አቋረጠ። አጋጣሚው ግን ከውጭ አገር ሠዓሊያንና የሥነ ጥበብ ታሪክ ጋር እንዲተዋወቅ ረዳው። ከንባቡም ጎን ሥዕሉን እንደልብ መሳል የቻለውም በዚህ ወቅት ነበር። ያቋረጠውን ትምህርት ጀኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ገብቶ ቀጠለ። በሦስተኛው ዓመት ላይ የተማሪዎች በዓል ተከብሮ በተከፈተው የተማሪዎች የስዕል ኤግዚቢሽን ላይ ገብረክርስቶስ አዲስ የአሳሳል ስልት (እውነታዊ፣ ስውር ቀመስ እና ዓይነ ግቡ አልባ) ይዞ ብቅ አለ።
ገብረክርስቶስ ከፍተኛ የስዕል ፍላጎት ቢኖረውም በወቅቱ በሀገሪቱ የተደራጀ የስዕል ጥበብ ትምህርት ቤት እንዲሁም፣ ስዕልን እንደሙያ ለማጥናት የሚገፋፋ ሁኔታ ስላልነበርና የሀገሪቱ የኢኮኖሚ መሠረት ግብርና በመሆኑ የእርሻ ትምህርት ለማጥናት ወስኖ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባ። ይሁን እንጂ ትምህርቱን ስላልወደደው የኮሌጅ ትምህርቱን አቋርጦ ወጣ። በተለያዩ ድርጅቶች ሥራ ቢጀምርም የሕይወት ጥሪው ስዕልና ግጥም ናቸውና ተረጋግቶ መሥራት አልቻለም። በመጨረሻም ሌላውን ሥራ ሁሉ ትቶ በስዕል ሥራው ላይ ላይ ብቻ ተጠመደ። ሥዕሎቹንም ለኤግዚቢሽን አቅርቦ ውጤት አገኘባቸው።
በ1949 ዓ.ም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ጀርመን ተልኮ በኮሎኝ የሥዕል አካዳሚ ስዕልና ግራፊክስ ተምሯል። ትምህርቱን በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቁ የስዕል መስሪያ ስቱዲዮ ተበርክቶለታል። በዚህ ስቱዲዮ ውስጥም 90 የተለያዩ ስዕሎችን በማዘጋጀት የአንድ ሰው የስዕል አውደ ርዕይ ለማቅረብ ችሏል።
በትርኢቱ አድናቆት ከማትረፉም በላይ፣ በጀርመን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊና የመጀመሪያው ድንቅ አፍሪካዊ ሠዓሊ የሚል ማዕረግ አስገኝቶለታል። ይኸው ክብርና ዝና ከጀርመን ዓለም አቀፍ አርቲስቶች ዘንድ ሞገስ አስገኝቶለት በስታድትሆል አዳራሽና በጉድስበርግ የ90 ስዕሎቹን ትርኢት የማሳየት ተጨማሪ ክብር አገኘ።
ትምህርቱን አጠናቆና በተለያዩ አካባቢዎች ከታዋቂ ዓለም አቀፍ ሰዓሊያን ጋር በመሆን የስዕል ኤግዚቢሽን አሳይቶ ወደ ሀገሩ እንደተመለሰ ስለወደፊት ዓላማው ተጠይቆ ‹‹ … አስተማሪ መሆን ነው የምፈልገው። ሰዓሊዎች ስእል መሥራት ብቻ አይበቃቸውም፤ የስዕልን ምስጢርና ውበት ማስተማር አለባቸው። ለተማሪዎች ስለጠቅላላ የስዕል ዓይነትና በተለይ ስለዘመናዊ ስዕል የሚገልፅ ጠቃሚ መጽሐፍ ለማዘጋጀት ሃሳብ አለኝ …›› ብሎ ነበር። ከዚያም በወቅቱ በትምህርትና ስነ ጥበብ ሚኒስቴር ስር ይገኝ በነበረው የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት በመምህርነት ተቀጠረ። እንደተመኘውም በ12 ዓመታት የመምህርነት ዘመኑ በርካታ ሰዓሊያንን ማፍራት ችሏል። ‹‹ሞዴል አርቲስትና መምህር›› ስለነበርም በ1963 እና 1964 ዓ.ም ከወቅቱ የትምህርትና የስነ ጥበብ ሚኒስቴር እንዲሁም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ጽሕፈት ቤት ‹‹የዓመቱ ምርጥ መምህር›› ተብሎ ተሸልሟል።
ገብረክርስቶስ ደስታ ሰዓሊ ብቻ ሳይሆን ገጣሚ መሆኑም ይታወቃል። ግጥሞቹ የራሳቸው የግጥም ባህሪ ያላቸው በመሆናቸው የስነ ጽሑፍ ሰዎችን አክራክረዋል። ቅኔዎቹ በየመድረኮች ቀርበዋል። በተለይም ‹‹ሀገሬ›› የሚለው ግጥሞ በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል።
በኪነ ጥበብ ሥራዎቹ ሀገሩን ያስተዋወቀውና ለሀገሩ ክብርና ፍቅር የነበረው ሠዓሊውና ገጣሚው ገብረክርስቶስ ደስታ መጋቢት 21 ቀን 1973 ዓ.ም በስደት በነበረበት አሜሪካ ውስጥ አርፎ ሥርዓተ ቀብሩም እዚያው ተፈፅሟል።
ሀዲስ አለማየሁ
የዚህ ሳምንት ክስተት የሆኑት ሀዲስ አለማየሁ፤ የቤተ ክህነት ሊቅ፣ ደራሲ፣ አርበኛ፣ መምህር፣ ዲፕሎማት እና የብዙ ሙያዎች ባለቤት ናቸው። ይሁን እንጂ ሀዲስ አለማየሁ በብዙዎች ልብ ውስጥ የሚታወቁት በደራሲነታቸው ነው። ከደራሲነታቸውም በፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፋቸው ነው። ይህ መጽሐፋቸው ከእርሳቸው በላይ ይታወቃል ማለት ይቻላል። ለመሆኑ የዚህ መጽሐፍ ፈጣሪ የሆኑት ሀዲስ አለማየሁ ማን ናቸው?
ደራሲ የክብር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ ከአባታቸው ከቄስ አለማየሁ ሰለሞን እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ደስታ ዓለሙ በደብረ ማርቆስ አውራጃ፣ በጎዛመን ወረዳ፣ በእንዶዳም ኪዳነ ምህረት ቀበሌ፤ ከ114 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 7 ቀን 1902 ዓ.ም ተወለዱ።
ሀዲስ ገና በጨቅላ ዕድሜያቸው በቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን ትምህርት በቤተሰባቸው አጠገብና በአባታቸው የትውልድ አካባቢ ደብረ ኤልያስ ሄደው የግዕዝ ትምሕርት ቤት ቅኔ ተቀኝተዋል። የቤተክርስቲያን ሥርዓታትንና መንፈሳዊ ትምህርትን በጎጃም ገዳማት በደብረ ኤልያስ፣ በደብረ ወርቅና በዲማ ጊዮርጊስ ከቀሰሙ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ በስዊድን ሚሽነሪ ትምህርት ቤት በኋላም በራስ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታተሉ። ለትንሽ ጊዜ በአስተማሪነት ሥራ ተሰማርተው እንዳገለገሉ በኢትዮጵያ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ተከሰተ።
የኢጣልያ ወረራ ሲከሰት ከልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ጦር ጋር በምዕራብ ኢትዮጵያ በአርበኝነት ሲዋጉ ቆይተው በመያዛቸው ጣሊያን ከልዑል ራስ እምሩ ጋር በግዞት ለሰባት ዓመታት በፖንዞ ደሴትና በሊፓሪ ደሴት ታስረው ቆይተዋል።
ከዚያም የተባባሪ ኃያላት ወታደሮች በ1935 ዓ.ም ሲያስመልጧቸው በተመለሱበት ጊዜ በትምህርታቸው እንደገና በኦክስፎርድ ከገፉ በኋላ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በተለይም በትምህርት ሚኒስቴር ለረጅም ጊዜ አገልግለዋል። ሀዲስ ያገለገሉባቸው የመንግሥት ተቋማት የሚከተሉት ናቸው።
በ1936 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኛ::
ከ1937 ዓ.ም እስከ 1938 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቆንሲል በኢየሩሳሌም::
በ1938 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ቴሌኮምኒኬሽን ኮንፈረንስ አትላንቲክ ከተማ፣ ኒው ጄርዚ ወኪል::
ከ1938 ዓ.ም እስከ 1942 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ቢሮ ኒው ዮርክ ሠራተኛ::
ከ1942 ዓ.ም እስከ 1948 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ዳይሬክተር እና ዋና ዳይሬክተር::
ከ1948 ዓ.ም እስከ 1952 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር
1952 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስትር::
ከ1952 ዓ.ም እስከ 1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ አምባሳደር ወደ እንግሊዝና ሆላንድ::
ከ1957 ዓ.ም እስከ 1958 ዓ.ም የልማት ሚኒስትር
ከ1960 ዓ.ም እስከ 1966 ዓ.ም ሴናቶር::
ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ በርካታ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን አበርክተዋል። ከእነዚህም ውስጥ ታላቅ አድናቆትንና እውቅናን ያተረፈው ሥራቸው በ1958 ዓ.ም የታተመው ፍቅር እስከ መቃብር ነው። ፍቅር እስከ መቃብር በሁለት የተለያዩ መደቦች ውስጥ የሚገኙ የሁለት ሰዎች የፍቅር ታሪክ ላይ ሲያተኩር፤ በጊዜው የነበረውን ወግና ልማድ ይገልጻል። በፖለቲካ ይዘቱ ደግሞ የፊውዳሉን ሥርዓት ይገልጻል።
ከፍቅር እስከ መቃብር በተጨማሪ ከጻፏቸው መጻሕፍት፤ በ1970 ዓ.ም ወንጀለኛው ዳኛ ይጠቀሳል። በ1980 ዓ.ም ደግሞ ስለ ማህበራዊ ጉዳዮችና ስለ ጣሊያን ውርስ የሚዳስሰውን ‹‹የልም እዣት›› የተሰኙትን ልብ ወለድ ታሪኮች ለንባብ አቅርበዋል። ከእነዚህ መጻሕፍት ባሻገር፤ የአበሻና የወደ ኋላ ጋብቻ (ተውኔት)፣ ተረት ተረት የመሰረት፣ ትዝታ… የተሰኙት ጽሑፎችና የሌሎች በርካታ ሥራዎች ባለቤት ናቸው።
ሀዲስ አለማየሁ በሥነ ጽሑፍ መድረኮች ሁሉ ስማቸው ይነሳል። በፍቅር እስከ መቃብር ላይ ብዙ ጥናቶች ተሠርተዋል። በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
ሀዲስ አለማየሁ በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከታቸውም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል። ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ኅዳር 26 ቀን 1996 ዓ.ም በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። እነሆ በሥራዎቻቸው ሲታወሱ ይኖራሉ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11 ቀን 2016 ዓ.ም