ሰው በሚል መጠሪያ በፈጣሪ አምሳል የተሠራው ሰው ተወልዶ ሙሉ እስኪሆን በብዙ እጆች ተደግፎ ብዙዎች ዋጋ ይከፈልበታል። በበርካታ ሰዎች ርብርብ ሰው አድጎ ሙሉ ከተባለ በኋላ በአንድም በሌላም ጉዳይ ከተፈጥሮ ሞት ቀድሞ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ እንመለከታለን።
ውዱን የሰው ሕይወት ሊያስከፍሉ የሚችሉ ነገሮችን ስንመለከት ሰው ለሚለው ክቡር ፍጡር መጥፊያው ያን ያህል ቀላል መሆኑ ያስገርማል። አሁን ታይቶ አሁን ለመጥፋት ሰው በእጁ የሠራቸው መጥፊያዎች ነገሮችን ቀለል ማድረጋቸው ደግሞ እጅን በእጅ አያስብል ይሆን የሚል ጥያቄ ያስነሳል።
ለዛሬ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መዝገብ የተገኘውም ታሪክ እንደሚያሳየው ሰው በራሱ መዘዘም ሕይወቱን እዴት በቀላሉ እንደሚያጣ የሚያሳይ ነው::
ነገሩ እንዲህ ነው። አንዲት አነስ ቀለል ያለች ግሮሰሪ ያላቸው ጎልማሳ ከእኩለ ቀን ጀምረው ለማታ ሥራቸው ተፍ ተፍ ሲሉ ያመሹና ምሽቱን ሙሉ የተለያዩ መጠጦችና ምግቦችን በማቀረብ አገልግሎት እየሰጡ ያመሻሉ። የእለቱ ሥራ እኩለ ሌሊት ላይ ያበቃ ቢመስልም የተወሰኑ ጠጪዎች ቤቱ ውስጥ በመኖራቸው ግሮሰሪውን ለመዝጋት ይቸገራሉ። ሰአቱ እየገፋ ሲሄድ ግን ሰው ሁሉ አንድ አንድ እያለ ከወጣ በኋላ መጨረሻ የቀረው ጠጪ አልጋ ይዞ እዛው ማደር እንደሚፈልግ ተናግሮ አልጋ ተይዞለት ወደ ክፍሉ ይገባል።
በወቅቱ በጣም ሰክሮ ስለነበር ከአስተናጋጆቹ ጋር የፀብ አይነት ስድድብ ስለጀመረ ቤቱ እንዳይረበሽ በማስብ ከገባ በኋላ የመኝታ ክፍሉን በር ከውጭ በኩል ለመቆለፍ የግሮሰሪው ባለቤት ሠራተኞቻቸውን ቁልፍ ሲጠይቁ ይሰማል። በሩ ከመቆለፉ በፊት በንዴትና በስካር መንፈስ ወደ ውጭ የወጣው የግሮሰሪው ደንበኛ ፀብ ከመጀመሩ በፊት ተመልሶ ወደ ክፍሉ እንዲገባ ለማደረግ በተደረገ ሙከራ ላይ የተወሰነ እሰጣ ገባ ውስጥ ይገባል። ያን ጊዜ እሰጣ ገባው መካከል ፀብና ክርክሩ ሲጠነክር በመጠጥ የተደፋፈረው ሰው ወደ መኝታ ከፍሉ ገብቶ መሣሪያ ይዞ ይመለሳል።
ሌሊት ነው። ውድቅት ላይ። ሰው ሁሉ በጠለቀ እንቅልፍ ውስጥ በወደቀበት ሰአት የተኩስ ድምፅ ተሰማ። ሰፈሩ ለወትሮው ከየመዝናኛ ቤቶች የሚወጣው ሙዚቃ ድምፅ እንጂ የተኩስ ድምፅ ተሰምቶበት አያውቅም ነበር። የግሮሰሪው ደንበኛ መሣሪያው ከትራሱ ስር ላጥ አድርጎ የግሮሰሪውን ባለቤት አንበርከኮ በቁጣ ይጮህ ጀመር። የቁጣ ድምፁን ተከትሎ ነበር የተኩሱ ድምፅ የተሰማው። የተኩሱ ድምፅ እንደተሰማ ሁሉም ጆሮውን ነቃ አድርጎ ሲያዳምጥ ቢቆይም ተኩሱ አልተደገመም። የተኩሱን አለመደገም ያረጋገጠው መንደርተኛ ወደ ጥልቅ እንቅልፉ ለመመልስ ጊዜም አልፈጀባቸውም ነበር።
ምንም እንኳን ሰው ተመልሶ ቢተኛም ያባነነው የተኩስ ድምፅ ነገር የከነከነው ሕግ አስከባሪ ግን ነፍሲያው ልትተኛለት ባለመቻሏ ተነሰቶ ድምፅ ወደ ሰማበት አቅጣጫ ሮጠ። በቦታው ሲደርስ ያየውን ማመን ከበደው:: አንድ ሰው ግንባሩን በጥይት ተመቶ ወድቋል። አካባቢው ግን ፀጥ ረጭ ብሏል። በዓይኑ ዙሪያውን ሲያማትር የጥይት ቀለሀና እርሳሰ መሬት ላይ ወድቆ ይመለከታል።
ይህን የተመለከተው የፀጥታ አስከባሪ በፍጥነት ባልደረቦቹን ጠርቶ ለተጨማሪ መረጃ ፊት ለፊቱ ወደ ተከፈተው የሺ ገነት ግሮሰሪ ዘው ብሎ ይገባል። በገባበት ቅፅበት ግሮሰሪው ውስጥ በፍርሃትና በድንጋጤ ፈዘው የቆሙትን የግሮሰሪ ሠራተኞች ይመለከታል። ሠራተኞቹ በድንጋጤ የሆነውን ነገር ማስረዳት ከብዷቸው ቢርበተበቱም በእጃቸው ግን ወደ ግሮሰሪው ጀርባ ማመላከታቸውን አላቆሙም ነበር።
የሰዎቹን የፍርሃት ጥቆማ የተመለከተው ሕግ አስከባሪ ወደ ጓሮ ሲመለከት አንድ ግለሰብ ሾልኮ እግሬ አውጪኝ ብሎ ሲያመልጥ ያያል። ሰውየው በሄደበት አቅጣጫ ሮጦ ሊከተለው ቢሞክርም ሊደርስበት አልቻለም ነበር።
ሕግ አስከባሪውም ተጠርጣሪው እንዳመለጠው ካረጋገጠ በኋላ ቆም ብሎ ዙሪያ ገባውን የተመለከተው የፖሊስ አባል የተጠሪጣሪውን ጫማ ፤ ቀለሃና እርሳስ በማግኘት ምርመራውን ከሚያደርጉት ባልደረቦቹ ጋር ሥራ ይጀምራል።
የቀን ጎዶሎ የገጠማቸው የግሮሰሪ ባለቤት
ከግሮሰሪ አስተናጋጅነት እስከባሬስታ ድረስ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርተዋል። ትንሽ ትልቅ ሳይሉ ያገኟትን ጥሪት ሲያጠራቅሙ የኖሩት አቶ አሻግሬ ሙሉ አስራት በለስ ቀንቷቸው በማምሻ እድሜያቸው የተወሰኑ የአልጋ ክፍሎች ያሉት ግሮሰሪ ለመክፈት ችለዋል። እኚህ ግለሰብ ከትንሽ ትልቁ ጋር በአክብሮት የሚተያዩ ከሥራ በቀር ፀብ የማይወዱ ሰውን ማገዝ ልዩ ምልክታቸው የሆኑ መልካም ሰው ነበሩ።
አንድ ዕለት ቀን ሀገር አማን ብለው ለማታው ገበያ አስፈላጊውን ቅደመ ሁኔታ ሲያሟሉ ነበር የዋሉት። በእለቱ ገበያው ደርቶ ስለነበር ቤት ካሉት አስተናጋጆች እኩል ነበር እየተሯሯጡ ስያስተናግዱ የቆዩት። ሥራው ቀለል ሲል እርፍ ብለው ሃሳብ ማስላት የጀመሩት ባለግሮሰሪው የእለቱ ገቢ ከፍ ያለ ስለነበር ደስ ብሏቸዋል። ድካምም ስለተሰማቸው ደንበኞቻቸው እስኪወጡ ባንኮኒውን ተደግፈው በመጠባበቅ ላይ ነበሩ።
የግሮሰሪው ደንበኞች አንድ አንድ እያሉ ቢወጡም አንደ ሰውዬ ግን ከገቢ ወጪው ጋር እየተጠላ ቤቱን እየበጠበጠ በግምት ከሌሊቱ ስምንት ሰአት ድረስ ቆይቷል። ምንም እንኳን ድካም ቢሰማቸውም ሠራተኞቻቸው እንዳይረበሹ በማሰብ ይህ በጥባጭ ሰው እስኪወጣ በመጠባበቀ ላይ ነበሩ።
ሰውየው የመኝታ ከፍል እንደሚፈልግ ጠይቆ ወደ ክፍሉም ከገባ በኋላ በመጮህ ሲረብሽ ከውጭ በኩል በተንጠልጣይ ቁልፍ የመኝታ ክፍሉን ለመቆለፍ በማሰብ ቁልፍ እንዲያቀብሏቸው ትእዛዝ መስጠት ጀመሩ። ያንን የሰማው የግሮሰሪው ደንበኛ ወደ ደጅ በመውጣት አንባ ጓሮ ተፈጠረ። በዚህም መካከል ንዴቱን መቆጣጠር ያቃተው የግሮሰሪው ደንበኛ ወደ ክፍሉ ተመልሶ ይገባል። መኝታ ክፍሉ ውስጥ ገብቶ ምንም ሳይቆይ በአንድ እጁ ክላሽንኮቭ ሽጉጥ በመያዝ ወጥቶ የግሮሰሪውን ባለቤት እየዳፋ ወደ ውጭ ይዟቸው ይወጣል።
ከግሮሰሪው ፊት ለፊት እንደደረሱ በጉልበታቸው አንበርክኮ እየተሳደበና እየጮኸ በሥራ ቦታው በር ላይ በግምት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰአት ከሰላሳ አካባቢ ግንባራቸው ላይ በያዘው መሣሪያ በመምታት ገሏቸው ወደ መኝታ ክፍሉ ተመለሰ።
የፖሊስ ምርመራ
የፖሊስ አባል የሰማውን ድምፅ ተከትሎ ቦታው ላይ ቢገኝም ተጠርጣሪውን ሊይዝ አልቻለም። ተጠርጣሪው ግድያው መፈፀሙን የሚያሳዩ መረጃዎችንና የዓይን እማኞችን ምስክርነት ተቀብሎ ፖሊስ ወደ ምርመራ ይገባል። በምርመራው ወቅትም የተገኘው ቀለሃና እርሳስ የየትኛው ሽጉጥ መሆኑን ሲያረጋግጡ ለሥራ ተብሎ የተሰጠው የፌዴራል ፖሊስ አባል ስም የተመዘገበ መሆኑን ለመመልከት ይችላሉ። የጣት አሻራውንም በሚመረምሩበት ወቅት ይኼው ሽጉጡ በስሙ ከተመዘገበ ተጠርጣሪ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ይመለክታሉ።
ይህን ተጠርጣሪ በየትኛው ከፍል ተመድቦ እንደሚሠራ በምርመራቸው ከደረሱበት በኋላ አዘናግተው ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ያውሉታል። ተጠርጣሪውም ለመደበቅ እየተዘጋጀ ባለበት ቅፅበት በመያዙ ቢደናገጥም ወንጀሉን መፈፀሙን ግን ሊክድ አልፈለገም ነበር።
ምርመራውን ሲያካሂድ የነበረው ፖሊስ እንደተናገረው ወንጀሉ ሆን ብሎ ሰው የመግደል ወንጀል ሲሆን የተፈመበት ቀን መስከረም 8 ቀን 2014 ዓ.ም ከሌሊቱ 9 ሰአት 30 ላይ ነበር። ወንጀሉ የተፈፀመበት ቦታም ቦሌ ከፍለ ከተማ ወረዳ አስራ ሶስት ልዩ ቦታው የሺ ገነት ግሮሰሪ በር ላይ ነው:: ወንጀል አድራጊው የፌዴራል ፖሊስ አባል የሆነ ምክትል ኢኒስፔክተር ቶሎሳ ቆርማ ይባላል። ይህን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ ተገቢው ምርመራው ተካሂዷል።
የዓይን እማኞቸ ምስክር
ተጠርጣሪው ማምለጡን ያረጋገጡት ምስክሮችም ድንጋጤያቸው ቀለል ሲልልላቸው የተመለከቱትን ማስረዳት ጀመሩ። “በወቅቱ ደንበኛው ከመጠጣቱም በላይ በቁጣና በጩኸት ቤቱን እየበጠበጠ ስለነበር የግሮሰሪው ባለቤት ተናደው ነበር። ነገር ግን በትእግስት እስኪተኛ ጠብቀው በሩን ከውስጥ በኩል ሊቆልፉ ሲሉ ነው ወጥቶ ትግል የገጠመው” በማለት የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን ከግብ ግቡ በኋላ ወደ ውስጥ በመመለስ ሽጉጥ አውጥቶ በማስፈራራት ሌሎችን ከበተናቸው በኋላ የግሮሰሪውን ባለቤት ብቻቸውን እደጅ አውጥቶ በጉልበታቸው አንበርክኮ መግደሉን አሳውቀዋል።
የዓይን እማኞቹ እንደሚሉት ሰውየው ቀድሞ ፀብ ፀብ እያለው የነበረ በመሆኑ እንጂ በመካከላቸው ይህን ያህል የከፋ ንግግርም እንዳልነበረ አስረድተዋል።
የተጠርጣሪው የእምነት ክህደት ቃል
ተከሳሹ እድሜው አርባ አምስት ሲሆን ከዚህ ቀደም በመልካም ሥነ ምግባረ የሚታወቅ ሰው ነበር። የሥራ ባልደረቦቹ አልፎ አልፎ መጠጥ ሲቀማምስ ያልተለመደ ባህሪ ያሳይ እንደነበረ የተናገሩ ቢሆንም በመደበኛ ሕይወቱ ግን ሥራውን በአግባቡ የሚሠራ ሃላፊነቱን በተገቢው መንገድ የሚወጣ መሆኑን መስክረውለታል። ይህ የፌዴራል ፖሊስ አባል የሆነ ምክትል ኢኒስፔክተር ቶሎሳ ቆርማ የተባለው ተጠርጣሪ ስለፈፀመው እኩይ ተግባር ሲጠየቅ በዚህ መልኩ አብራርቷል።
“የወንጀል ድርጊቱን ፈፅሜያለሁ ጥፋተኛ ነኝ̋ በማለት የእምነት ክህደት ቃሉን የሰጠ ሲሆን ምክንያት አድርጎ ያቀረበው ነገር” በወቅቱ ስዝናና ቆይቼ ለማረፍ የያዝኩት ክፍል ውስጥ በመምጣት ከውጭ በኩል ሆነው የእስቶር ቁልፍ አምጣ ይህን ሰውዬ ካልቆለፍንበት ሰላም አይሰጠንም በማለት ሲነጋገሩ ሰምቼ ስወጣ ስለመቱኝ ተናደጄ ትራስ ስር ያስቀመጥኩት ለሥራ የተሰጠኝን ሽጉጥ በመጠቀም ግንባሩን ብዬ ገድየዋለሁ”ሲል የእምነት ከህደት ቃሉን ሰጥቷል።
ከዚህም በተጨማሪ የፈፀመው ድርጊት ተገቢ እንዳልነበረ እና በስካር መንፈስ ተነሳሰቶ በመፈፀሙ መፀፀቱንም አስረድተዋል።
ፖሊስ በቦታው የተገኘውን ማስረጃ፤ የሰው ምሰክሮችን ቃል፤ የተጠርጣሪውን የእምነት ክህደት ቃል አንድ ላይ በማድረግ ወንጀሉ ሆነ ብሎ ሰው የመግደል ድርጊት እንደሆነ አመላክቶ ያጠናቀረውን መረጃ በኢትዮጵያ የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ልኳል።
ውሳኔ
አቃቤ ህጉም በመሠረተው ክስ መሠረት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ሁለተኛ ምድብ ችሎት ጉዳዩን ተመልክቶ ውሳኔ ለመስጠት ለጥር ሃያ አራት ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓመተ ምህረት ይቀጥራል።
በእለቱም በዋለው ችሎት ክስና ማስጃውን በግምት ውስጥ በማስገባት ኢኒስፔክተር ቶሎሳ ቆርማ በፈፀመው ሆን ብሎ ሰው የመግደል ወንጀል የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ሁለተኛ ምድብ ችሎት በአስራ አንድ አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም