ጎተይቶም ገብረሥላሴ በቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን ለአሸናፊነት ትጠበቃለች

በሳምንቱ መጨረሻ ከሚካሄዱ የጎዳና ላይ ውድድሮች መካከል አንዱ የቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን ሲሆን፤ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ድንቅ አትሌቶች በውድድሩ እንደሚሳተፉ ታውቋል። ፈጣን ሰዓት ከሚመዘገብባቸው የግማሽ ማራቶን ውድድሮች አንዱ በሆነው የቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን በሴቶች የዓለም ክብረወሰን የተመዘገበበት ከተማ ነው። በወንዶችም የርቀቱ ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት የተመዘገበው በዚሁ ከተማ ነው።

በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ይህ ውድድር ዘንድሮ ለ33ኛ ጊዜ ሲካሄድም በርካታ የርቀቱ ከዋክብት እንዲሁም በመም ውድድሮች ስኬታማ የሆኑ አትሌቶች የሚፎካከሩበት ይሆናል። በርካታ ኢትዮጵዊያን አትሌቶች በሚሳተፉበት የዘንድሮው ውድድር በሴቶች አዲስ ክብረወሰን ሊመዘገብ እንደሚችል ተገምቷል። በውድድሩ ከሚካፈሉት መካከል አብዛኛዎቹ ተቀራራቢ የሆነ ብቃት ያላቸው፤ ሶስቱ ደግሞ በርቀቱ ከ1ሰዓት ከ5 ደቂቃ የሆነ ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡ መሆናቸው ክብረወሰን እንዲጠበቅ ያደረገ ምክንያት ነው።

እነዚህ የርቀቱ ፈጣን አትሌቶች የሚያደርጉት ፉክክርም ውድድሩን በጉጉት እንዲጠበቅ ከማድረጉ በተጨማሪ አዲስ ነገር እንዲጠበቅ አድርጓል። በርቀቱ የዓለም ክብረወሰን በዚሁ የቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን ሲመዘገብ እአአ በ2021 ኢትዮጵያዊቷ ድንቅ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ነበረች ባለድል የሆነችው። ያስመዘገበችው ሰዓትም 1:02:52 ሲሆን ከነገ በስቲያ በሚካሄደው ውድድርም ይህንን ሰዓት ሊያሻሽሉ ይችላሉ ተብለው ከሚጠበቁት አትሌቶች መካከል ኢትዮጵያዊያን በቀዳሚነት ተቀምጠዋል።

የፈጣን ሰዓት ባለቤት ከሆኑና አሸናፊም ይሆናሉ ተብሎ ከሚጠበቁት አትሌቶች አንዷ አትሌት ጎተይቶም ገብረሥላሴ ትገኝበታለች። የኦሪጎን የማራቶን ዓለም ቻምፒዮና እንዲሁም በቡዳፔስት የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው ጎተይቶም፤ በግማሽ ማራቶን 1:05:36 የሆነ ሰዓት አላት። ይህ የግሏ ፈጣን ሰዓት እአአ በ2021 ባህሬን ላይ ያስመዘገበችው ሲሆን፤ ስኬታማ የሆነችበትን ይህንን የውድድር ዓመት በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በተካሄደ የግማሽ ማራቶን ሁለተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ መጀመሯ የሚታወስ ነው። ጠንካራዋ አትሌት በአጋጣሚዎችና በሕይወቷ ላይ በደረሱ ከባድ ሀዘኖች ሳትበገር በዓለም ቻምፒዮና መድረክ ውጤታማ መሆኗ ይታወቃል። በማራቶን ስኬታማ ዓመትን ያሳለፈችው ጎተይቶም በዚህ ውድድርም አሸናፊ በመሆን በውድድር ዓመቱ ተጨማሪ ስኬት ለማስመዝገብ ወደ ስፔን ታቀናለች።

ጎተይቶም ውድድሩን አስመልክቶም ‹‹65 ደቂቃ የግማሽ ማራቶን ፈጣኑ ሰዓቴ ነው፤ በዚህ ውድድርም 64 ደቂቃ ለመሮጥ ጥረት የማደርግ ይሆናል›› ማለቷን የምትሰለጥንበት ‹‹ኤሊት ራኒንግ ቲም›› በማህበራዊ ድረገጹ አጋርቷል። በመሆኑም በሰከንዶች ብቻ የሚበልጧትን የጀርመንና የኬንያ አትሌቶችን ፉክክር ከሌሎች የሀገሯ ልጆች ጋር በመሆን በርቀቱ ያላትን ሰዓት ታሻሽላለች ተብላ ትጠበቃለች።

ሌላኛዋ የርቀቱ ስኬታማ ኢትዮጵያዊት አትሌት ንግስት ሃፍቱ በቫሌንሲያ ከጠንካራ ተፎካካሪዎች መካከል ትጠቀሳለች። አትሌቷ በዓመቱ በኔዘርላንድ እና ጀርመን አሸናፊ ስትሆን ሶስተኛ ተሳትፎዋን በምታደርግበት የቫሌንሲያ ማራቶን አሸናፊ የመሆን እድሏም የሰፋ ነው። ዓመቱን በግማሽ ማራቶን እንዲሁም በሌሎች የጎዳና ሩጫ ያሳለፈችው ያለምጌጥ ያረጋል፣ ከወራት በፊት እዚያው ስፔን ላይ በርቀቱ አሸናፊ የነበረችው ትዕግስት ገዛኸኝ፣ ወጣቷ አትሌት ለምለም ኃይሉ እንዲሁም ፍታው ዘራይ በኢትዮጵያ በኩል በውድድሩ ተሳታፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በወንዶች መካከል በሚካሄደው ውድድር በርካታ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተሳታፊ ሲሆኑ፤ አብዛኛዎቹ ለቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን አዲስ አለመሆናቸው ለአሸናፊነት እንዲጠበቁ አድርጓቸዋል። በርቀቱ ባለው 58:32 የሆነ ፈጣን ሰዓት ለአሸናፊነት በቅድሚያ ከተቀመጡ አትሌቶች አንዱ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ነው። በቅርቡ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ያልተሳካላት ዮሚፍ በዳይመንድ ሊግ እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የዓለም የጎዳና ቻምፒዮና ላይ ውጤታማ መሆኑ የሚታወስ ነው።

አትሌቱ አምና በቫሌንሲያ በመሮጥ ያስመዘገበው ፈጣን ሰዓት እንደመሆኑ ዘንድሮም ውጤት ያስመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል። ሌላኛው ወጣት አትሌት ታደሰ ወርቁም ባለፈው ዓመት በቫሌንሲያ ሁለተኛ ደረጃን ያስመዘገበ ሲሆን፤ ዘንድሮ ለአሸናፊነት ይሮጣል። ከታደሰ በሰከንዶች ብቻ የተቀደመው አትሌት ሀጎስ ገብረሕይወት እንዲሁም የኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ቻምፒዮናው አትሌት ሰለሞን ባረጋም በውድድሩ ተሳታፊ መሆኑ ተረጋግጧል። ይህም አትሌቶቹ በተደጋጋሚ በብሔራዊ ቡድን እንዲሁም ሌሎች ውድድሮች ላይ አብሮ የመሳተፍ ልምድ ያላቸው በመሆኑ በውድድሩ የሚኖሩትን ተፎካካሪዎች በቀላሉ በመርታት ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቅድመ ግምቱን አግኝተዋል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2016

Recommended For You