ቴክኖሎጂና አዲስ የፈጠራ ሥራ የሰው ልጆችን ሕይወት በብዙ አሻሽሏል። ከትምህርት ከጤና፣ ከግብርና እና ከሌሎች ዘርፎች አንፃርም የሚሰጠውን ጠቀሜታና የአጠቃቀም ሂደቱን ብንመለከት እንደ ዘርፎቹ ዓይነት ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድም ይለያያል። የሚጠቀምባቸው መሳሪያዎችም እንዲሁ እንደ አገልግሎቱ ዓይነትና ስፋት ይለያያሉ።
እንደ ኢትዮጵያ ላሉና በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ደግሞ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራ ፋይዳው ከምንለው በላይ ትልቅ ነው። በተለያዩ ዘርፎች ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የማደግ ዕድል እንዳላት ሀገር፣ የማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለመሻሻል፣ ለትምህርት ለግብርና ለጤና ለወታደራዊ አገልግሎት፣ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂና በአዳዲስ የፈጠራ ሥራ መታገዝ የግድ ሆኗል፤ ያለ ቴክኖሎጂ ያለሙበት መድረስ የማይታሰብ ከሆነ ሰነባብቷል።
ወጣት ታምራየሁ አየለ ይበላል፤ ትውልድና ዕድገቱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን በምትገኝ ሞርሱጦ በተባለች አነስተኛ የገጠር ከተማ ነው። በአሁኑ ወቅት ደግም ነዋሪነቱ በዞኑ መዲና ሆሳዕና ከተማ ውስጥ ነው። ወጣቱ ገና ከመነሻው ጀምሮ ለፈጠራና ለቴክኖሎጂ ነክ ሥራዎች ዝንባሌ የነበረው ሲሆን ይህም ተሰጦ አድጎ ተስፋ ሰጪ የሆነ የፈጠራ ሥራ እንዲያበረክት አብቆቶታል።
ወጣት ታምራየሁ በከተማው ”ታሜ የብረታብረት ሥራ” በተባለ ድርጅት ላለፉት ጊዜያት እየሰራ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በዙሪያው የሚያገኛቸውን የወዳደቁ ብረታ ብረቶችን በመጠጋገን አነስተኛ መጠን ያላትን ተሽከርካሪ መሥራት ችሏል።
ከልጅነቱ ጀምሮ የፈጠራ ሥራዎችን ይሰራ እንደነበር የሚናገረው ወጣት ታምራየው ፤ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ወቅት ማለትም የሰባት እና የስምንት ዓመት ሕፃን ሳለ በሽቦ መልክ የተሰሩ መኪኖችን በራሱ ሰርቶ በጨዋታ መልክ ይገለገልባቸው እንደነበር ትውስታውን ይናገራል።
ለቴክኖሎጂና ለአዲስ የፈጠራ ሥራ ያለው ፍላጎት የጀመረው በመኖሪያ አካባቢያቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ዝርጋታ በሚከናወንበት ወቅት እንደነበር የሚናገረው ወጣት ታምራየሁ፤ ከባለሙያዎቹ ጋር በልጅነት ዕድሜ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማለትም ውሃ፣ መፍቻና መሰል ነገሮችን በመላላክ እያቀረበ ወዳጅነት ፈጠረ። ይህ ነገርም ቀልቡን ስለገዛው ወደ ፈጠራ ሥራ ተሳበ።
በወቅቱ የ12ዓመት ታደጊ የነበረው ታምራየሁ በትውልድ አካባቢው የመብራት መሠረተ ልማት ከተዳረሰ በኋላ እርሱ ቀደም ሲል አብሮ በመዋል፤ የሚያወሩትን ነገር በመስማት፤ ያልገባውን ነገር ደግሞ በመጠየቅ በርካታ ዕውቀቶችን ጨብጧል። ባገኘው እውቀትም በወቅቱ በአካባቢያቸው የኤሌክትሪክ ባለሙያ ዕጥረት ስለነበር በአካባቢው ከቤት ቤት ኤሌክትሪክ በመዘርጋት ገቢውን ማሳደግ ችሏል።
ወጣት ታምራየሁ የልጅነት ጊዜውን ወደኋላ መለስ ብሎ አስታውሶ ሲናገር፤ ቤተሰቦቹ ከኤሌክትሪክ ጋር ያለው መቀራረብ ስላልወዳዱት በተደጋጋሚ ሥራውን እንዲያቆም ቢነግሩትም እርሱ ሊያቆም ባለመቻሉና የቤተሰብን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለቱ ለግርፋት ተደርጎ እንደነበር ይናገራል። በኋላ ላይ ግን ኤሌክትሪክ በጥንቃቄ ከተሰራ የማይጎዳ መሆኑን በማስረዳትና ቤተሰቡም ሁኔታውን በመገንዘቡ ሥራውን ስለመቀጠሉ ይናገራል።
ወጣቱ እንደሚናገረው፤ ለአዳዲስ ፈጠራዎች ሁልጊዜ ጉጉ በመሆኑ የ8ኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት ከወላጅ አባቱ ጋር ከመኖሪያ አካባቢው ወጣ ብለ ወዳለች ከተማ በሄደበት ወቅት ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ ባጃጅ እንደተመለከተ ይናገራል። በወቅቱ ለወላጅ አባቱ “አባቴ ይህንን ባጃጅ እኔ መሥራት እፈልጋለሁ” የሚል ሃሳብ ይሰነዝራል።
ወላጅ አባቱም ‹‹እንዴት አድርገህ ነው የምትሰራው ?›› የሚል ጥያቄ ያቀርቡለታል።“ ቤት ውስጥ ያለውን የአሮጌ ሬዲዮ በመፍታት እንዲጠቀም ከፈቀድክልኝ አንቀሳቅሼ ማሳየት እችላለሁ” በማለት ከወላጅ አባቱ ባገኘው መልካም ምላሽ ወደ ሥራው እንደገባ ይገልፃል።
ከሬዲዮ ዲናሞ በማውጣት ዲናሞ ነክ ነገሮች negative ከpositive ጋር ሲሆን ወደፊት positive ከnegative ጋር ሲሆን ደግሞ ወደ ኋላ የመሽከርከር ባህርይ ስላላቸው እርሱን በመጠቀም ከችንጋ ጋር በማገናኘት የኋላና የፊት ማርሽ በማድረግ መሥራት እንደቻለ ወጣት ታምራየሁ ያስታውሳል።
ወጣት ታምራየሁ እንደሚናገረው፤ ወላጅ አባቱ ልጃቸው በልጅነቱ በሠራው የፈጠራ ሥራ ከፍተኛ ደስታ ስለተሰማቸው ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ ሙያውን መለማመድ እንዲችል በማሰብ ከአካባቢው ብዙዎች ወደሚሄዱበት ደቡብ አፍሪካ እንደላኩት ይናገራል። ወጣቱ እንደሚገልፀው፤ የእርሱን የውጭ ጉዞ ከሌሎች የአካባቢው ወጣቶች ለየት የሚያደርገው የፈጠራ ሥራውን ክህሎት ወደ ውጭ ሀገር በመሄድ ማዳበር እንዲችል ተስቦ የመጣ መሆኑ ይናገራል።
በደቡብ አፍሪካ ቆይታው ከሌሎች የሀገሩ ወጣቶች በተለየ መልኩ በተለያዩ የመኪና ጋራዦች ውስጥ ተቀጥሮ በመሥራት ሙያውን ለማሳደግ ጥረት ስለማድረጉ የሚናገረው ወጣት ታምራየሁ፤ በመጀመሪያ አካባቢ እንደውም ያለ ደመወዝ ክህሎቱን ከፍ ለማድረግ ባለው ፍላጎት ብቻ ለረዥም ጊዜ ሲሰራ እንደቆየ ይገልጻል።
ታምራየሁ እንደሚለው ፤ በደቡብ አፍሪካ ቆይታው ከአንድ የሀገሩ ልጅ ጋር በመሆን በተለያዩ ጋራዦች ጥቂት ገንዘብ እየተከፈላቸው ሲሰሩ በቆዩበት ጊዜ በቀሰሙት እውቀት የራሳቸውን ጋራዥ በመክፈት በግጭትና በተለያዩ ጉዳቶች አገልግሎት የማይሰጡ መኪኖች በኢንሹራንስ በኩል በጨረታ ስለሚሸጡ እነኚህን መኪኖች በጨረታ በመግዛት ወደ እነርሱ ጋራዥ በመውሰድ፤ በመጠገንና በማስጠገን መኪኖችን ለኢትዮጵያውያን የመሸጥ ሥራ ሲሰራ እንደነበር ይናገራል።
ከደቡብ አፍሪካ ወደ ሀገር ውስጥ በመመለስ በስደት እያሉ ባካበቱት እውቅት ከጓደኛው ጋር በመሆን ”ታሜ የብረታብረት ሥራ” የተባለ ድርጅት በመቋቋም የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች የታከሉበት ሥራ ሲሰሩ እንደቆዩ የሚናገረው ወጣት ታምራየሁ፤ የተለያዩ ነገሮችን ሲያከናውን ባገኘው ክህሎት ከወዳደቁ ብረታብረቶች አነስተኛ መኪና መሥራት ስለመቻሉ ያስረዳል።
ይህንን ሥራ ለመሥራት ምን እንዳነሳሳው ወጣቱ ሲናገር፤ ‹‹ኢትዮጵያ ከሸማችነት ወደ አምራችነት በምታደርገው ጉዞ ላይ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት አለብን በሚል እና ተሽከርካሪዎች ከውጭ ሲመጡ ከቀረጥና ታክስ ጋር ተያይዞ ያለውን የዋጋ ንረት ከግንዛቤ በማስገባት ይህንን ሥራ ለመሥራት ተነሳስቻለሁ። በዋነኝነት ደግሞ ኢትዮጵያ ካላት አነስተኛ የውጭ ምንዛሬ አንፃር ለመኪና ግዥ የምትወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት በማለም ወደ መኪና ማምረት ላይ ትኩረቴን አድርጌለሁ››ሲል ይገልፃል።
ሌላኛው ጉዳይ በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል የሥራ ዕድል እንዲያገኝ በማሰብ ወደዚህ ሥራ እንደገባ የሚናገረው ወጣት ታምራየሁ፤ ገና ከጅምር ባለው ሥራ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሮ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማሰብ ሥራውን አጠናክሮ ስለመቀጠሉ ያስረዳል።
ወደፊት የኤሌክትሪክ ቻርጅ እንጅኖችን ከውጭ ሀገር በማስመጣት ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ያላትን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ሀገሪቱ ለነዳጅ ግዥ የምታወጣውን ከፍተኛ ገንዘብ ለመቀነስ ዕቅድ እንዳለው የሚናገረው የፈጠራ ባለሙያው ወጣት ታምራየሁ፤ የሻንሲና የተቀሩ የመኪና ክፍሎችን እዚሁ በመገጣጠም ለማህበረሰቡ መኪና ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ ገልጿል።
1300 ሲሲ የፈረስ ጉልበት ስላላትና በእርሱ እጅ ስለተሰራችው ተሽከርካሪ ወጣቱ ሲናገር፤‹‹ ከ50ና 60 ዓመት በላይ አገልገሎት ሰጥተው ከተጣሉ ተሽከርካሪዎች ብረት በመሰብሰብ ሻንሲውን ደግሞ ሙሉ በሙሉ እንደገና ዲዛይን በማድረግ የመንገድና የአካባቢውን መልከዓ ምድር ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለመሥራት ሞክሬአለሁ። የመኪናውን የቦዲ ክፍል ደግሞ በሃይድሮሊክ ተገፍቶ በማሽን አማካኝነት እንጂ በሰው እጅ መምጣት የሚከብዱ ከርቮችን በመሥራት ዕውን ማድረግ ችያለሁ። በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ዲዛይኑን ሙሉ እንዲሁ የወደፊት የድርጅታችንን ምርቶች ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲሰራ አድርጌለሁ።›› ብሏል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ እስከ መሥሪያ ቤታቸው ድረስ በመምጣት ድጋፍና ክትትል በማድረግ ለተሰሩ ሥራዎችም የምስክር ወረቀቶች የድጋፍ ደብዳቤ በመስጠት እንዳበረታቱት የተናገረው ወጣት ታምራየሁ፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ፣ የዞኑና የክልሉ መንግሥት ለሥራው አጋርነት በማሳየት ድጋፋቸውን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ጠቁሟል።
ወደፊት በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን የረዥምና የአጭር ጊዜ እቅዶችን በመውጣት እየሰራ እንደሆነ የሚናገረው ወጣቱ፤ በረዥም ጊዜ የሞተር ክፍሎችን ከውጭ በማስመጣት የተሽከርካሪ ማምረቻ ለመክፈትና አቅም ማጎልበት ሲቻል ደግሞ ሙሉ በሙሉ ሀገር ውስጥ መኪና የማምረት ግብ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
ወደዚያ ደረጃ ለመሸጋገርም ባለው ጊዜ ውስጥ የከተማ ቆሻሻ ማስወገጃ ማሽን፣ በግብርና ዘርፍ ደግሞ የእርሻ ትራክተር ለገበሬዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማድረስ እየሰራ እንደሆነ እና በአሁኑ ወቅትም ምንም ዓይነት አቧራ በሌለው መልኩ የከተማ ቆሻሻ ማስወገድ የሚችል መኪና ሰርቶ በመጠናቀቅ ለሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ለማስረከብ በዝግጅት ላይ እንዳለ ተነግሯል።
መንግሥት በየአካባቢው እንደ እርሱ ዓይነት የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶች ሥራቸውን ማጎልበትና ማሳደግ የሚችሉባቸውን የፈጠራና የቴክኖሎጂ ማዕከላት ቢኖሩ የተሻለ ሥራ መሥራት እንደሚቻል እና የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራ በይበልጥ ድጋፍና ክትትል የሚያገኝበት መንገድ ቢኖር መልካም ነው ይላል።
የልጅነት ህልሙን ለመኖርና ሥራውን ለመሥራት ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ከሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች አንዱ ከአንዳንድ ግለሰቦች የሚሰጥ አሉታዊ አስተያየት ነው። በተለይም «መኪና ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት የማይታሰብ ነው አንተ መኪና እሰራለሁ ብለህ አትልፋ» የሚሉ አሉታዊ አስተያየቶችም ይደርሱት ነበር። እርሱ ግን ያንን ፋይዳ አልባ አስተያየት ለመስማት ጆሮ እንዳልሰጠ ይናገራል።
አሁን ያለንበት ዘመን ሁሉንም ነገር በቀላሉ በእጃችን ማግኘት የምንችልበት የቴክኖሎጂ ዘመን ነው የሚለው ወጣት ታምራየሁ የማይቻል ነገር የለ ም ይላል።
‹‹ገንዘብ የለኝም፤ የሚያግዘኝ ሰው የለም” በማለት የተቀመጡ ወጣቶች አሉ። ይህ መሆን የለበትም። የተወሰነ ዕውቀት ካለ ያንን በማዳበር ባላቸው ግብዓት ብቻ ከቀላል ነገር በመጀመር ለመሥራት ዝግጁ መሆን አለባቸው።›› የሚል ምክሩን ይለግሳል።
ሕልምን ለማሳካት ሁልጊዜም ዋጋ መክፈል ይኖራል የሚለው ወጣቱ፤ ጠንክረው ከሰሩ ከሳቡበት መድረስና ያለሙትን ግብ ማሳካት እንደሚቻል ይናገራል። ስለዚህ “ኢትዮጵያን አንድ ደረጃ ላይ የማድረስ ግዴታና ኃላፊነት እስካለብን ድረስ” ወጣቶች ለዓላማቸው መሳካት መክፈል ያለባቸውን መስዋዕትነት ሁሉ መክፈል እንዳለባቸው ተሞክሮውን በመጥቀስ ያስረዳል።
በተለይም ለአሉታዊ አመለካከቶች ቦታ ባለመስጠት ፤ የነገው ራዕያቸውን ከግብ ለማድረስ ቀን እና ሌሊት ተስፋ ሳይቆርጡ መትጋት እንደሚኖርባቸው ምክሩን ይለግሳል። ጠልፈው ለመጣል ከፊት የሚቀድሙ መሰናክሎች ቢኖሩም ነገን አሻግሮ መመልከት እንዳለባቸው መልዕክቱን ያስተላልፋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2016