ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በድል የደመቁባቸው የጎዳና ላይ ውድድሮች

ከትላንት በስትያ በተለያዩ የዓለም ከተሞች በተካሄዱ የአትሌቲክስ የጎዳና ላይ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ማሸነፍ ችለዋል። ኢትዮጵያን በድል ከደመቁባቸው ውድድሮች መካከል የቶሮንቶ፣ አምስተርዳምና ኬፕ ታውን የማራቶን ውድድሮች ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ በሕንድ ዴልሂ የግማሽ ማራቶን ውድድርም ድል ቀንቷቸዋል።

በሕንድ በተካሄደው የዴልሂ ግማሽ ማራቶን ውድድር በሴቶች የዓለምና የኦሊምፒክ ቻምፒዮናዋ አትሌት አልማዝ አያና አሸንፋለች። በጉዳት ምክንያት ለስድስት ዓመት ከውድድር ርቃ የቆየችው አልማዝ ዩጋንዳዊቷን አትሌት ስቴላ ቼሳንግን ከ1 ሰከንድ ባላይ በመቅደም ውድድሩን ማሸነፍ ችላለች። አልማዝ ርቀቱን 1:07:59 በሆነ ሰዓት ስታጠናቅቅ ዩጋንዳዊቷ አትሌት 1:08:28 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ፣ ኬንያዊቷ አትሌት ቪኦላ ቼፕንጌኖ 1:09:09 ሰዓት ሶስተኛ ደረጃን መያዝ ችለዋል። በተለየ የሩጫ ስልት የምትታወቀው አልማዝ ሁለት ጊዜ የዓለም ቻምፒዮንና አንድ ጊዜ የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳለያን ማጥለቅ ብትችልም ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ትኩረቱን በጎና ላይ ውድድሮች አድርጋለች። አልማዝ ለመጀመሪያ ጊዜ 2017 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በድልሂ ግማሽ ማራቶን ማሸነፋ የሚታወስ ሲሆን ዘንድሮ ሁለተኛ ድላን ካስመዘገበች በኋላ ውድድሩ በሙቀት ምክንያት ከባድ እንደነበረ ተናግራለች።

ኬንያዊው አትሌት ዳንኤል ኤቤንዮ አሸናፊ በሆነበት በወንዶች ተመሳሳይ ውድድር አዲሱ ጎበና 3ኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሆናል። ኤቤንዮ ርቀቱን 59:27 በሆነ ሰዓት ሲያጠናቅቅ ሌላኛው ኬንያዊ አትሌት ቻለስ ማታታ 1:00:05 በሆነ ሰዓት 2ኛ፣ ኢትዮጵያዊው አዲሱ ጎበና 1:00:51 በሆነ ሰዓት 3ኛ በመሆን ጨርሷል። የውድድሩ አሸናፊዎች 27 ሺ የአሜሪካን ዶላር ሽልማትም አግኝተዋል።

በእውቁ ቶሮንቶ ዋተር ፍሮንት የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውን አትሌቶች በሴቶች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃን በመያዝ ሲያሸንፉ በወንዶች 2ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችለዋል። በሴቶች በተደረገው ውድድር ቡዜ ድርቤ 42 ኪሎ ሜትሩን 2:23:11 በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ ቀዳሚ ስትሆን፣ ዋጋነሽ መካሻ 2:23:12 በሆነ ሰዓት 2ኛ እና አፌራ ጎፋይ 2:23:15 በሆነ ሰዓት 3ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በወንዶች ኬንያዊው ኤልቪስ ኪፕቾጌ 2:09:20 ሰዓት ቀዳሚ በመሆን ያሸነፈ ሲሆን ኢትዮጵያዊው አትሌት አዱኛ ታከለ 1 ደቂቃ ዘግይቶ በ2:10:26 በሆነ ሰዓት 2ኛ ደረጃን ይዞ ፈጽሟል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሳተፉ ሌላኛው የፕላቲኒየም ደረጃ የተሰጠው የአምሰተርዳም ማራቶን የተለያዩ ውጤቶች ተመዝግበውበታል። ኢትዮጵያውያን በሴቶች ድል አድርገዋል። ሞክሼዎቹ አትሌቶች ተከታትለው ሲገቡ ኬንያዊቷ አትሌት 3ኛ ደረጃን ይዛለች። አትሌት መሰረት በለጠ 2:18:19 በሆነ ሰዓት ቅድሚያውን ደረጃ ይዛ ስታጠናቅቅ አትሌት መሰረት አበባየሁ 2:19:47 ሰዓት 2ኛ ሆና ፈጽማለች። አሼቴ በከሪ፣ አንቺዓለም ሀይማኖት፣ መሰረት ጎላና ሶፍያ አሰፋ ከ4ኛ እስከ 7ኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው። በወንዶች ኬንያዊው ጆሽዋ ቤሌት ቀዳሚ ሲሆን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ4ኛ እስከ 8ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችለዋል።

በደቡብ አፍሪካ የተካሄደው የኬፕ ታውን የማራቶን ውድድርም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በድል የደመቁበት ሆኗል። ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሴቶች ከ1ኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ሲያጠናቅቁ በወንዶች አንደኛ ደረጃን በመያዝ መፈጸም ችለዋል። በወንዶች በተካሄደው ፉክክር አትሌት አዳነ ከበደ ርቀቱን 2:11:28 በመሮጥ አሸንፏል። እሱን በመከተል ደቡብ አፍሪካዊ አትሌት እስቴፈን ሞኮካ 2:11:33 ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ጨርሷል። ኬንያዊው ቤናርድ ኪፕኮሪር በ2:11:51 ሰዓት ሶስተኛ ሆኖ ሲጨርስ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ዘውዱ ሀይሉ፣ ባየልኝ ተሻገርና ዳኛቸው አዴሬ ከ5-7 ያለውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል።

በሴቶች በተደረገው ውድድር አትሌት ጽጌ ኃይለስላሴ 2:24:17 ሰዓት በማስመዝገብ በአንደኝነት ስታጠናቅቅ አትሌት መለሰች ፀጋዬ 2:26:23 በሆነ ሰዓት 2ኛ ደረጃን በመያዝ ጨርሳለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሸዋረግ አለነ 2:27:27 በሆነ ሰዓት ናት።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2016

Recommended For You