አለመግባባትን መፍቻ ቁልፍ – ሰላማዊ ንግግር

ብዙዎች ለሰላም ተመን የለውም ይላሉ። አስፈላጊነቱም በየተወሰነ ጊዜ አሊያም በየደቂቃውና በየሰከንዱ ብቻ እንዳልሆነም ያስረዳሉ። ለዚህም በምክንያትነት የሚያስቀምጡት ሰላም ልማት፣ እድገት እንዲሁም አብሮነትን ማረጋገጥ የሚችል መሆኑን ነው። ሰላም ሁሉም መልካም የሆኑ ነገሮች ባለቤት እንደሆነም ያስረዳሉ።

በተለይም በአብሮነት ጉዞ ውስጥ በጋራ መሰብሰብና ማከማቸት ስለሚኖር ተከታታይ የሆነ እድገት ማስመዝገብ ይቻላል። ጎዶሎ የሆነውን ነገር መሙላት ያስችላል። በወቅታዊ ስሜቶችም ከመነዳት ያድናል። የፖለቲካም ሆነ የታሪክ ስብራትን ለመፈወስ ጉልበት ይሰጣል። ጥላቻ እና ጥርጣሬንም ያስወግዳል።

በተቃራኒው የተናጠል ጉዞ ደግሞ የራስን ስሜት ብቻ ለመከተል የሚገፋፋ ነው። በብቸኝነት ውስጥ ሊነግስ የሚችለው እኔነት ነው። ብቸኝነት በራሱ ጎዶሎነት ነው። ሁልጊዜ እኔነት የሚንጸባረቅ ከሆነ ለሌላው አካል ምንም አይነት ቦታ እንዳይኖር የሚያደርግ ይሆናል። ይህ ደግሞ ኅብረትንና ትብብርን የሚንድ እንደሆነ እሙን ነው።

አሁን አሁን በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው ከእኛነት ይልቅ እኔነት እየጎለበተ መምጣቱ ነው። ብዙዎቹ የራሳቸውን ጉዳይ ብቻ ለማጉላት ሲፍጨረጨሩ ይታያል። ከዚህ የተነሳ በኢትዮጵያውያን መካከል አለመግባባት እየተፈጠረ ይገኛል። ሁሉም ጥያቄዬ አልተመለሰም በሚል ሌላውን ማዳመጥ ትቷል። “አሻፈረኝ!” በሚልም ለየትኛውም አይነት ጥያቄው በመነጋገር ከመፍታት ይልቅ ነፍጥ ማንገብ እንደ አማራጭ መታየት ጀምሯል።

ለዚህም ይመስላል የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ ባደረጉት ንግግር ላይ፤ አለመግባባቶችና ጥያቄዎች ሁሉ በንግግር ሲፈቱ ድሉ የሁላችንም መሆኑን በመረዳት በየትኛውም አካባቢ የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶችን እና ግጭቶችን በማቆም የሠላም አማራጮችን ከመጠቀም ውጪ የተሻለ አማራጭ እንደሌለ መገንዘብ ይገባል ያሉት።

ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ያነጋገርናቸው በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪ አቶ ሰለሞን ተፈራ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አለመግባባቶች በርካታ ናቸው፤ በተለይም ከታሪክ ጋር እንዲሁም ከአገረ መንግስት ግንባታ ጋር ተያይዞ በርካታ አለመግባባቶች እንዳሉ ይታወቃል።

በታሪክ ውስጥ ያለ አለመግባባት ሲባል በተደጋጋሚ ሲሰበክ የነበረ እንደሆነ የሚጠቅሱት አቶ ሰለሞን፣ ከዚህም ውስጥ አንዱ የሆነው አንዱን ጨቋኝ፤ ሌላውን ተጨቋኝ አድርጎ የመሳል ነገር አለ ብለዋል። ሁለተኛው ደግሞ የአገረ መንግስት ግንባታ ላይ ልዩነት አለ። የአገር ግንባታ ላይ የተለያየ ሐሳብ አለ፤ ለአብነት የባንዲራ ጉዳይ እንዲሁም የድንበር እና የማንነት ጉዳይ ተጠቃሽ ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው፤ በአገራችን የአለመግባባት ችግር የሆኑብን ጉዳዮች በርካታ መሆናቸውን ይናገራሉ። የችግሮቻችንን ምንጭ ከሆኑት መካከል የቅርቦቹን ችግሮች ብንጠቅሳቸው የተሳሳቱ ትርክቶች ተጠቃሾች ናቸው። ከትርክቶቹ አንዱ የማንነትና የብሔር ፖለቲካን እናስፋፋለን የሚሉ ኃይሎች የፈጠሩት አንድ ቁጭት ተጠቃሽ መሆኑን ያለመክታሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ በመጀመሪያ ደረጃ መታወቅ ያለበት በእኛ አገር ብዙ ማንነቶች እንዳሉ አስመስለው የውሸት ፖለቲካ የሚያስወሩ አካላት መኖራቸው ነው። የውሸት ብዙ ማንነት እንዳለ የሚያስመስሉ አሉ። ከእኛ በቅርብ ርቀት ያለችውና በሕዝብ ቁጥርም በጣም የምታንሰው ደቡብ ሱዳን ከእኛ የበለጠ ማንነት አላት። ቢያንስ እኛ አንድ የሚያደርገን ኢትዮጵያዊ የሆነ ትልቅ ስም ያለን ሕዝብ ነን።

ብዙዎች የሚያቀራርበንና የሚያመሳስለንን ከምንወስድ ይልቅ የሚያጣላን ላይ እንድናተኩር ይጎተጉቱናል። ለመጣላት ሁሉንም ልዩነት ይሰብካሉ። ይህ ልዩነት ግን ላለመግባባታችን መንስኤ ሊሆን የሚችል አይደለም። ችግሩ ልዩነት መኖሩ አይደለም፤ ልዩነታችንን እንዴት እናስቀጥለዋለን በሚለው ላይ መስማማትና መተጋገዝ አለመቻላችን ነው ይላሉ።

አቶ ሰለሞን በበኩላቸው፤ የተነሱት አለመግባባቶችና ጥያቄዎቹ አንደኛ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይፈቱ እየተሸጋገሩ የመጡም ናቸው። ሁለተኛ ደግሞ ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎችም እንዳሉ ይጠቅሳሉ፤ ለምሳሌ የዛሬ 60 ዓመት ሲጠየቅ የነበረ ጥያቄ እና ዛሬ 70 እየተጠየቀ ያለው ጥያቄ አንድ አይደለም ይላሉ። ይህ ማለት የየሰው ፍላጎት ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ የሚቀያየር በመሆኑ እንደሆነም ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል ከሌሎች አገሮች ጫና የተነሳ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዳሉ የሚናገሩት የፖለቲካ ምሁሩ፣ ለምሳሌ የኑሮ ውድነት ያመጣው ጥያቄ እንደሚነሳ ጠቅሰው ይህ ግን በውጭም በውስጥም በተፈጠረ ሁኔታ ሊሆን እንደሚችል ያብራራሉ። ያም ሆኖ በየትኛውም ሁኔታ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችም ሆኑ የሚነሱ ጥያቄዎችን መስተናገድ የሚችሉት ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ አምጥተን ልንነጋገርባቸው ስንችል ነው ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ አለመግባባታቸውን በንግግር ሳይሆን በጠብመንጃ አፈሙዝ ለመፍታት የተጓዙ አገሮች እንዳሉ ሁሉ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የነበሩ አገሮች ደግሞ ቁጭ ብለው ነገሮቹን በታሪክ ዙሪያ በአገረ መንግስት ግንባታ ዙሪያ ተነጋግረው በመፍታታቸው ዛሬ የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በመነጋገር ችግሮቻቸውን የፈቱ በርካታ አገራት በአሁኑ ወቅት ሰላም ሰፍኖባቸው የተሻለ እድገት ላይ የደረሱ ናቸው።

ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካን መጥቀስ ይቻላል። ደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች እና ነጮች ጎራ ለይተው የሚፋጁበት የነበረችና አንዱ እንደ ዜጋ ሌላው እንደ መጤ ይቆጠርበት የነበረች አገር ናት። በተመሳሳይ ሩዋንዳንም መጥቀስ ይቻላል። በሩዋንዳ የእርስ በእርስ ግጭት እና የብሔር ግጭት እንዲሁም የዘር ጭፍጨፋም ሁሉ ነበር። ይሁንና እነዚህ አገራት ቁጭ ብለው በመነጋገር ችግራቸውን መፍታት የቻሉ ናቸው።

በተቃራኒው ደግሞ ሲታይ ሰላም አይሻልም፤ ችግራችንን በጠብመንጃ ነው መፍታት የምንፈልገው ብለው አንዱ አንዱን በመደፍጠጥ የራሳችንን መብት እናረጋግጣለን ብለው የሚያስቡ አገሮችን ማየት ይቻል። ለአብነት ያህል የመንን መውሰድ እንችላለን፤ አንዳንድ አገሮች በጠብመንጃ ብቻ በማስገደድ የተጓዙ ቢሆንም ለጊዜው የሰፈነ ሰላም ያለ ይመስል እንጂ ዘላቂ ሰላም የላቸውም።

ስለዚህ በጦርነት ችግርን ወይም ግጭትን ለመፍታት ማሰብ እርስ በእርስ ከመጠፋፋት የሚያንስ አይደለም። በጦርነት ውስጥ የትኛውም አካል አሸናፊ አይሆንም። አሸናፊነት የሚመጣው በንግግር ችግርን መፍታት ሲቻል ነው። በንግግር ውስጥ የትኛውም አካል ተሸናፊ መሆን አይችልም።

መታወቅ ያለበት ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ጥያቄ ሊኖረው ይችላል። በታሪክም ሆነ በሕግ ዙሪያ በማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዙሪያ ጥያቄ ሊኖር ይችላል፤ ጥያቄ ለምን ኖረ አይባልም። ሁሉም ኦሮሞው አማራው፣ ጉራጌው፣ ወላይታው፣ ሲዳማው.፣ ትግሬ ጥያቄ ይኖረዋል። ስለዚህ እነዚህ በተለያየ ምክንያት የሚነሱ ጥያቄዎች መፈታት ያለባቸው በሰላማዊ መንገድ ነው ሲሉ አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።

የትኛውንም ጥያቄ ለማስመለስ “ዘራፍ!” ማለት ተገቢ አይደለም የሚሉት ደግሞ አቶ ግርማ ናቸው። ከ”ዘራፍ!” በፊት “ለምን ይህ ሆነ” በሚለው ላይ መነጋገር ትልቅነት እንደሆነ ነው የሚናገሩት። ተበድያለሁ የሚል የትኛውም አካል የሚካሰው ጠብመንጃ ስላነሳ ሳይሆን በመነጋገር በሚመጣ መደማመጥ ነው። የበደለኝን አካል ፈልጌ ቁጭቴን ልወጣ በሚል ሒሳብ ለማወራረድ መሄድ የበለጠ ከመቁሰል ውጭ የሚያመጣው ትርፍ አይኖረውም።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ በንግግራቸው ወቅት እንዳሉት፤ ያደጉ የምንላቸው ሀገራት ዛሬ ላይ የደረሱት ልዩነቶች ስለሌሏቸው አይደለም። ልዩነቶቻቸውን በማቻቻል፤ ልዩነቶቻቸውን ከግጭት በመለስ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ስለቻሉ ነው። ልዩነትም አንድነትም ተፈጥሯዊ ነው። የሰው ልጅ የመልክ፣ የእምነት፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የመኖሪያ አካባቢ፣ የአስተሳሰብ ልዩነት አለው። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የሚያደርጉት የሰውነት ጉዳዮችም አሉ።

ወሳኙ ነገር ልዩነትን እንደ ጌጥ አንድነትን እንደ ማስተሳሰሪያ ኃይልና አቅም መጠቀሙ ነው። ትናንት ለነገ ዕንቅፋት መሆን የለበትም። ትምህርት እንጂ። የትናንት ታሪክ የአብሮነት መገንቢያ እንጂ። የልዩነት መነሻ እንዳይሆን መሥራት አለብን። እየተደማመጥን፤ እየተመካከርን፤ ለሃሳብና ለውይይት በራችንን ክፍት እያደረግን እንጓዝ። ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን እናጠንከር፤ ለሀገራችን መፃኢ ዘመን በጋራ እንትጋ። ከትናንት ይልቅ ጉልበታችንንና ጊዜያችንን በነገ ላይ እናውል። ይህ ነው የዚህ ትውልድ ትልቁ ኃላፊነት ሲሉ ተናግረዋል።

የፖለቲካ መምህሩና ተመራማሪው አቶ ሰለሞን በበኩላቸው፤ ባሉን አለመግባባቶች ላይ ተቀምጠን መነጋገር ካልቻልን ግን እርስ በእርስ መጠፋፋት ይሆናል ብለዋል። በተለይ ኢትዮጵያ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባት በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን በዙሪያዋ ያሉ አገራት ያላቸው የሰላም ሁኔታ በጣም ተለዋዋጭ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ ለራሷ ስትል ጠንካራ አገር መሆን የሚጠበቅባት ነው። ችግራችንን በንግግር መፍታት የማንችል ከሆነ የኢትዮጵያውያን ኑሮ በፍጹም ሊሻሻል አይችልም።

የሰላም እጦት ሲባል፤ ሁለት ነገሮች በአግባቡ መታየት መቻል አለባቸው። አንደኛ ለምሳሌ ዜጎች ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ ሲፈናቀሉ የሚሄዱት ያላቸው ንብረት ጥለው ነው። ስፍራውን ጥሎ የሚፈናቀለው አምራች ኃይል ነው። በሚፈናቀልበት ጊዜ ማምረት የሚችለው ስፍራ ለቆ ስለሚሄድ ከራሱ አልፎ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ሚና ያለውን ጥቅም ትቶ ይሄዳል። ስለዚህም አንዱ ሌላውን ከማሳደድ ሊቆጠብ ይገባዋል። ችግር ካለም በመነጋገር መግባባትን ማምጣት ይመረጣል።

ሁለተኛው ደግሞ ከነበረበት ስፍራ ለቆ ሲፈናቀል የሚሄድበት የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጥገኛ መሆን ይጀምራል። ጥገኝነት ደግሞ የኢኮኖሚ ድቀትን የሚያመጣ ነው። እኛ ችግራችንን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት የተሻለ አማራጭ የለንም። ስለዚህ ችግሮቻችንን በንግግር መፍታት ውዴታ ሳይሆን የውዴታ ግዴታ መሆን አለበት ሲሉ አቶ ሰለሞን ያስረዳሉ። ይህን መረዳት ያለብን የተወሰንን ዜጎች ብቻ መሆን የለብንም፤ ፖለቲከኛው ይህን አሳምሮ መገንዘብ ይጠበቅበታል። ከዚህ በተጨማሪ አገሪቱ ያለችበትንና ቀጣናው ያለበትን ሁኔታ መረዳት መቻል አለብን ብለዋል። ሁሉም አዕምሮ ያለው ሰው እነዚህ ሁሉ ችግሮች ከተረዳ ችግሮች መፈታት ያለባቸው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ እንደሆነ ይረዳል ሲሉም አክለዋል።

በአገራችን ያሉ አብዛኞቹን እሴቶቻችንን ስለማንጠቀምባቸው ነው እንጂ በተለያዩ ማኅበረሰቦች ዘንድ ያሉን ሀብቶቻችን ናቸው የሚሉት አቶ ግርማ፣ ካሉን እሴቶች መካከል አንዱ የሆነው ሽምግልና አለመግባባትን በቅጡ መፍታት የሚችል እንደሆነ አመልክተዋል። በሁሉም ማኅበረሰብ ዘንድ ሽምግልና የራሱ ዮሆነ የአካሄድ ስርዓት አለው።

በአንድ ጀምበር ተጀምሮ በአንድ ጀምበር ላይጠናቀቅ ስለሚችል ለሌላ ጊዜ ይቀጠራል፤ በምልልስ ውስጥ እርስ በእርስ የበለጠ ለመተዋወቅ እድል ይሰጣል። በዚያ አጋጣሚ ሽማግሌዎች በተገናኙ ቁጥር ማኅበራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ ይወያያሉ። በየአካባቢያቸው ስላለ አለመግባባትም ሆነ ጥያቄ ዙሪያ ይነጋገራሉ። ይህ በምልልስ ብሎም በቅርርብ የሚገኝ ውይይት ነው ሲሉ ይናገራሉ።

እርሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ በተቃራኒ ያለው የ‹‹ዘራፍ!›› ነገራችን የሽምግልና እሴቶቻችንን እየበላው መጥቷል። በአሁኑ ወቅት ከጊዜ ወደጊዜ እየፋፋ የመጣው ‹‹የዘራፍ!›› ጉዳይ ነው። ስለዚህ የ‹‹ዘራፍ!››ን እሴት ማስታገስ ያለብን በእነዚህ መልካም በሆነ እሴቶቻን በመታገዝም ጭምር ነው።

አቶ ሰለሞን እያንዳንዱ ሰው የጦርነትን መጥፎነትና የሚያስወጣውን ወጪ ከተረዳ ወደመነጋገር መምጣት አይከብደውም። ባለመግባባት የሚፈጠርን መጥፎ ገጽታ ከማስታመም ደግሞ ጥያቄም ካለ በቀላሉ ሁሉም ነገር ወደጠረጴዛ ዙሪያ መምጣት ቢችል ውጤታማ መሆን ያስችላል። ዋናው ነገር የሐሳብ ልዩነት ለምን ኖረ አይደለም። ያንን የሐሳብ ልዩነት እንዴት ተነጋግሮ መግባባት ይቻላል ነው። የሐሳብ ልዩነት መኖሩ ሳይሆን የችግር አፈታት ዘዴ ላይ ነው ማተኮር የሚገባው ይላሉ።

አቶ ሰለሞንም ሆኑ አቶ ግርማ፣ ጥያቄዎቻችንንም ሆነ አለመግባባቻችንን በንግግር የማንፈታ ከሆነ አገራችንን የሚያጋጥማት ነገር ከባድ ነው ይላሉ። ሰላም ከመታጣቱ ጎን ለጎን የአገር ኢኮኖሚ የሚቀጭጭ እንደሆነ ተናግረዋል። ሰላም ጠፋ እና ኢኮኖሚ ከተዳከመ አገር እንደ አገር መቆም ስለማይችል የውጭ ጣልቃ ገብነት ያለከልካይ ሊንሰራፋ ይችላል።

መንግሥት ምንጊዜም ከማንኛው ኃይል ጋር ችግሮችን በመወያየትና በንግግር የመፍታት ቁርጠኝነት እንዳለው በተግባር ያስመሰከረበት ነው ሲሉም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የተናገሩ ሲሆን፣ ምንጊዜም ቢሆን ለንግግርና ለሠላም የሚረፍድ ጊዜ እንደሌለም አስረድተዋል።

ተነጋግረን ባንግባባ እንኳን ጦርነት አማራጭ ሆኖ መቅረብ የለበትም። በጦርነት ሜዳ አንድ አሸናፊን ይፈጥራል። ውይይት ግን ሁሉን አሸናፊ ያደርጋል። አለመግባባቶችና ጥያቄዎች ሁሉ በንግግር ሲፈቱ ድሉ የሁላችንም መሆኑን በመረዳት በየትኛውም አካባቢ የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶችን እና ግጭቶችን በማቆም የሠላም አማራጮችን ከመጠቀም ውጪ የተሻለ አማራጭ እንደሌለን መገንዘብ ይኖርብናል ብለዋል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2016

Recommended For You