ባለሀብቶች በስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እንዲሳተፉ ጥረት ይደረጋል

ከቅርብ ዓመታ ወዲህ ከፍተኛ ገቢ በማመንጨት ለሀገራት ኢኮኖሚ ዋልታ ከሆኑ ዘርፎች መካከል አንዱ ስፖርት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዘርፍ የግል ባለሀብቱ ተሳትፎ ከፍተኛ ሲሆን፤ በርካቶችም ረብጣ ዶላሮችን በማፈስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ያህል እጅግ ታዋቂ በሆነው የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ሊግ ተሳታፊ የሆኑ ባለሀብቶች እአአ በ2021 ብቻ 2 ቢሊዮን ዶላር ማትረፋቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ። በዘርፉ እግጅ ከፍተኛ ወጪ በሚጠይቀው የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሀብቶችም ካወጡት እጥፍ በመሰብሰብ ላይ ይገኛሉ።

ይህ ሁኔታ እንደ ኢትዮጵያ ሲታይ ግን ምንም ያልተሠራበት ሊባል የሚችል ነው፡፡ እንደ ወልዲያ ስታዲየም እንዲሁም ጥቂት የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች በሆቴሎችና ሌሎች ሥፍራዎች ከመኖራቸው ባለፈ በዝርዝር ሊቀርብ የሚችል አይደለም፡፡ ነገር ግን በ1990 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲ ባለሀብቶች በስፖርት ኢንቨስት እንዲያደርጉ በተለያየ መንገድ እንደሚደግፍ ይጠቁማል፡፡ ሀገራዊ የስፖርት ፍኖተ ካርታውም በተመሳሳይ የስፖርት ማዘውተሪያ ልማት ከትኩረት አቅጣጫዎቹ አንዱ መሆኑን ያሳያል፡፡

ባለሀብቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ልማት ላይ መሳተፋቸው የውጭ ምንዛሬን በመቀነስ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም ኢኮኖሚውን ከመደገፍ አንጻር መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ሆኖም ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ለትርፋማነት አስቦ አለመሥራት፣ አትራፊ የሚያደርግ የማዘውተሪያ

 ሥፍራዎች አጠቃቀም መመሪያና ደንብ ያለመኖር፣ ባለሀብቱ በዚህ ዘርፍ ተሳታፊ እንዲሆን ቅስቀሳና ማበረታቻ አለመደረጉ እንዲሁም የስፖርት ፈንዶችንና ዓለም አቀፍ ማህበራትን የስፖርት ማስፋፋትና ኢንቨስትመንት ድጋፎችን አለመጠቀምንም በፍኖተ ካርታው እንደ ችግር ይነሳል፡፡

ነገር ግን አሁን ላይ ይህንን ችግር ለመቅረፍና ባለሀብቱንም በስፖርት ዘርፍ ተሳትፎ ትርፋማ ሊሆን በሚችልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል፡፡ መንግሥት በቻለው መጠን በተለያዩ ደረጃዎች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ላይ በመሥራት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ይህ ሥራ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ የግል ዘርፉም ተሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን፤ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ጠቁመዋል፡፡

ከስፖርት ማዘውተሪያ ግንባታዎች ጋር የተያያዘው ሥራ እጅግ ሰፊ እንደመሆኑ መንግሥት ብቻውን ፍላጎቱን ሊያሟላ አይችልም፡፡ በመሆኑም ስፖርትን ለልማት በመጠቀም የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ገንብቶ የገቢ ምንጭ በሚሆንበት ሁኔታ ላይ እየተሠራ ይገኛል። ሌሎች ሀገራት ላይ ይህ የተለመደ ሲሆን፤ ስፖርት የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆን መንግሥትን እስከመደገፍ ይደርሳል፡፡ በመሆኑም የግል ባለሀብቶች በተለያዩ ስፖርቶች መዋዕለነዋይ በማፍሰስ ማዘውተሪያዎችን በመገንባት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ የገቢ ማመንጫ መንገዶችን በመጠቀም ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታቅዷል፡፡ ይህንን እቅድ ወደ ሥራ ለማስገባትም እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን፤ የስፖርት ፈንድ አዋጅን አጽድቆ ለመተግበር የሚያስችለው ረቂቅ በመዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡ ከስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ ባለፈ በሌሎች የስፖርት ዘርፎች ላይ ባለሀብቶች በመግባት ስፖርቱን እንዲጠቅሙም ታስቧል፡፡

ሚኒስትሩ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ፣ ከስፖርት ማዘውተሪያዎች ጋር በተያያዘ አሁን ያለውን ሁኔታ ጠቁመዋል፡፡ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ በርካታ ስታዲየሞች የተገነቡ ቢሆንም መገኘት ባለባቸው ደረጃ ግልጋሎት እየሰጡ አይደለም። በመሆኑም ሚኒስትሩ መታደስ ባለባቸው ላይ ትኩረት ሰጥቶ አንጋፋውን የአዲስ አበባ ስታዲየም የማሳደስ ሥራውን በማጠቃለል ላይ ይገኛል፡፡ ሌላው ግንባታው ያልተጠናቀቀውና ከኮንትራክተሮች ጋር በተፈጠረው አለመግባባት (ከዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ እና ሌሎች ጉዳዮች) ምክንያት የተቋረጠው የብሄራዊ ስታዲየም ነው፡፡ ግንባታውን ለመቀጠልና ስታዲየሙ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲችልም ለማድረግ ከሌላ ኮንትራክተር ጋር በሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱ በቢሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያስፈልግ ቢሆንም በተለያየ መንገድ ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚደረግም ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

ከትልልቅ ስታዲየሞች ባለፈም ሚኒስትሩ በየአካባቢው ባሉ ትንንሽ የስፖርት ማዘውተሪያ ላይም እየሠራ ነው፡፡ በተለይ ህጻናትና ታዳጊዎች የሚሳተፉባቸው ትንንሽ ስታዲየሞች በየወረዳው እንዲስፋፉ ጥረት ይደረጋል፡፡ በዚህም ላይ ስኬታማ ከሆኑ ሀገራት ጋር ግንኙነት ተፈጥሯል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You