የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ከኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር ያከናውናል። ቡድኑ በመጀመሪያው ጨዋታው የነበሩበትን ክፍተቶች ለመቅረፍ ዝግጅት ማድረጉንም አስታውቋል።
24 ቡድኖች ለሚካፈሉበት የዓለም ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች በማከናወን ላይ ይገኛሉ። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንም (ካፍ) አህጉሪቱን በመወከል የሚካፈሉ 4 ቡድኖችን ለመለየት በማጣራት ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድንም በዓለም ዋንጫው ተሳታፊ ለመሆን የሚያስችለውን የማጣሪያ ጨዋታ እያደረገ ሲሆን፤ ከኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር ሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታውን ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያካሂዳል።
የሁለተኛውን ዙር የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ከሜዳው ውጪ ማላቦ ስታዲየም ላይ ከሳምንት በፊት ከኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር ያደረጉት የሉሲዎቹ ተተኪዎች አንድ እኩል በሆነ ውጤት መመለሳቸው ይታወሳል። ቡድኑን አቻ ያደረገውን ብቸኛ ግብም በ9ኛው ደቂቃ ላይ እሙሽ ዳንኤል ማስቆጠሯም የሚታወስ ነው። ቡድኑ ከጨዋታ በኋላ ወደ ሃገሩ ከተመለሰ በኋላም ባሉት ጥቂት ቀናት ዝግጅቱን ቀጥሎ ቆይቷል። በዚህ ዝግጅቱም በመጀመሪያው ጨዋታው የነበሩበትን ክፍተቶች ለመቅረፍ የሚያስችለውን ልምምድ ማድረጉንም አሰልጣኝ ፍሬው ሀይለገብርዔል በተሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
አሰልጣኝ ፍሬው ከኢኳቶሪያል ጊኒ መልስ ተጫዋቾቹ ከነበረባቸው ጫና እንዲያገግሙ ለአንድ ቀን እረፍት ከተሰጣቸው በኋላ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እና በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ልምምድ ሲያደርጉ መቆየቱን ይገልጻሉ። ከዚህ ቀደም የነበረው የመለማመጃ ሜዳ ችግር በዚህ የዝግጅት ወቅት ያላጋጠመ በመሆኑ ቡድኑ ሙሉ ትኩረቱን በልምምዱ ላይም አድርጎ ነበር። በመጀመሪያው ጨዋታ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ኒቦኝ የን እና መሳይ ተመስገን ጉዳት ያጋጠማቸው ቢሆንም አሁን ላይ ማገገም ችለዋል። ስለዚህም የቡድኑ አባላት በሙሉ ጤንነት በዛሬው ጨዋታ ላይ ይሰለፋሉ።
ቡድኑ በመጀመሪያው ጨዋታ አስቀድሞ ግብ ቢያስቆጥርም የተፈጠሩለትን በርካታ የግብ እድሎች ባለመጠቀሙ ግን በአቻ ውጤት ሊለያይ ችሏል። ከዚህ ጋር በተያያዘም አሰልጣኙ ቡድናቸው ቀድሞ ከሚታወቀበት በተቃራኒ ግብ በማስቆጠር ላይ ክፍተቶች እየተስተዋሉበት መሆኑን አልሸሸጉም። ይህንን ችግር ለመፍታትም የችግሩን ምንጭ በመለየት በንድፈ ሃሳብ ትምህርት ተሰጥቷቸዋል። ከዚህ ባለፈ ከተጫዋቾች ጋር በመነጋገርና ሜዳ ላይም በተግባር ችግሩን የመፍታት ጥረቶች ተደርገዋል። ቡድኑን ዋጋ የሚያስከፍሉ በርካታ የግብ እድሎች የሚመክኑት ተጫዋቾቹ ቡድኑን አሸናፊ ለማድረግ ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎትና ጭንቀት የተነሳ ነው። በእርግጥ ቡድኑ የወጣት እንደመሆኑ በርካታ ስህተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ ነገር ግን እንደ አሰልጣኝ ምን ማድረግ ይገባል በሚለው ላይ ስለተሰራ ችግሩ ይቀረፋል የሚል እምነታቸውን አንጸባርቀዋል።
ቡድኑ ከዚህ ቀደም በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጫፍ መድረስ መቻሉ እንዲሁም በተለያዩ ጨዋታዎች ላይ አመርቂ የሚባሉ ጉዞዎችን ማድረጉ የሚታወስ ነው። ከዚያ ቡድን ጥቂት ተጫዋቾች ከቡድኑ ጋር ከመቀጠላቸው ባለፈ የተቀሩት አዳዲስና የውድድር ልምድም ብዙም የሌላቸውና ከእረፍት የተመለሱ ናቸው። በኢኳቶሪያል በነበረው ሞቃታማ የአየር ሁኔታ የተነሳ ቡድኑ ጫና ነበረበት። ይሁንና ለረጅም ጊዜ በወዳጅነት ጨዋታዎች የታጀበ ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርግ ከቆየው ተቃራኒ ቡድን ጋር ጥሩ የሚባል ፉክክር አድርጓል። በርካታ የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች የሚታወቁበት የጉልበት አጨዋወት የሚከተሉ እንደመሆኑ ለዛሬው ጨዋታ በምን መልክ መሰለፍ ይገባል በሚለው ላይ ሲሰሩ መቆየታቸውንም አሰልጣኝ ፍሬው ጠቁመዋል።
በሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሁለተኛ ዙር ኢትዮጵያ ከኢኳቶሪያል ጊኒ የሚያደርጉት የመልስ ጨዋታ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዩቲዩብ ቻናል የሚተላለፍም ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2016