እአአ ከ1988 አንስቶ በዓለም አትሌቲክስ መሪነት የሚካሄደው የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች ምርጫ ከአፍሪካ ጥቂት ሀገራት የተወጣጡ አትሌቶች ብቻ ተሸላሚዎች ሆነውበታል። ከወር በኋላ ይፋ በሚደረገው የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች ምርጫ ላይ ግን አፍሪካዊያን አትሌቶች ቀዳሚ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። በተለይም በሴቶች በሚጠበቀው ምርጫ ላይ የዓለምን ክብረወሰን በመሰባበር ብቃታቸውን ያስመሰከሩ ሶስት አፍሪካውያን አትሌቶች በእጩነት መቅረባቸው የአሸናፊነት ግምት እንዲያገኙ አድርጋል።
ሴት አፍሪካዊት አትሌት ለመጨረሻ ጊዜ በዘርፉ ተሸላሚ የሆነችው ከ7 ዓመታት በፊት ሲሆን፤ በመካከለኛና ረጅም ርቀት አትሌቲክስም ከዓመታት ወዲህ የሚያሸንፍ አትሌት ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል። ከ11ዱ እጩ አትሌቶች አሸናፊ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት መካከል በተጠናቀቀው የመስከረም ወር ሁለት ታላላቅ የዓለም ክብረወሰኖችን የሰበሩት ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ጉዳፍ ጸጋይ እና ትዕግስት አሰፋ ናቸው። ሌላኛዋ አትሌት ደግሞ ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕዮጎን ናት።
ከቡዳፔስቱ የዓለም ቻምፒዮና አስቀድሞ ድንቅ አቋምና ፈጣን ሰዓት ስታስመዘግብ የቆየችው ኢትዮጵያዊቷ ኮከብ አትሌት ጉዳፍ፤ በዓለም ቻምፒዮና በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቋ የሚታወስ ነው። ዓመቱን በምርጥ ብቃት ያሳለፈችው ጉዳፍ በዳይመንድ ሊግ የ5ሺ ሜትር ውድድር በኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕዬጎን ተይዞ የነበረውን የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን 14:00.21 በሆነ ሰዓት ዩጂን ላይ ማስመዝገቧ ይታወቃል። ይህም በዓመቱ በ5ሺ ሜትር እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች የዓመቱ ንግስት ያደረጋት ሲሆን፤ የዓለም አትሌቲክስም በዚሁ ምክንያት ለዓመታዊው ክብር አጭቷታል።
የዓለም የማራቶን ክብረወሰንን ባለፈው ወር የጨበጠችው አትሌት ትዕግስት አሰፋም የዓመቱ ምርጥ ሴት አትሌቶች የመጨረሻዎቹ አስራ አንድ ዝርዝር ውስጥ ከመካተት ባለፈ አሸናፊ ትሆናለች የሚለው የስፖርቱ ቤተሰብ ግምት አግኝታለች። ትዕግስት 2019 ቺካጎ ማራቶን ላይ በኬንያዊቷ አትሌት ብሪጊድ ኮስጌ የተመዘገበውን ክብረወሰን በዘንድሮው የበርሊን ማራቶን ከሁለት ደቂቃ በላይ በማሻሻል 2:11:53 በሆነ ሰአት አዲስ የማራቶን ክብረወሰን ማስመዝገቧ ይታወቃል። አትሌቷ ቀደም ሲል የ800 ሜትር ተወዳዳሪ በመሆን ወደ አትሌቲክስ ገብታ ፊቷን ወደ ጎዳና ውድድሮች ብትመልስም በከባድ ጉዳት ምክንያት ለረጅም ጊዜ ከውድድር ውጪ ነበረች። ሩጫ እንድታቆም በሃኪሞች ቢነገራትም ተስፋ ሳትቆርጥ በማራቶን ታሪክ ክብረወሰን የሰበረች የመጀመሪያዋ ሴት ኢትዮጰያዊት አትሌት ልትሆን ችላለች። ይህ ጽናቷ እንዲሁም ከጉዳት ተመልሳ ለማመን የሚከብድ አስደናቂ ብቃቷን በማሳየቷም ለዓመቱ ምርጥ አትሌትነት ክብር ለመታጨት በቅታለች።
በተለያዩ ርቀቶች ስመጥር አትሌቶች እጩ በሆኑበት ዝርዝር ፌይዝ ኪፕዬጎን የምታሸንፍ ከሆነ ደግሞ በታሪክ የመጀመሪያዋ ኬንያዊት ሴት አትሌት ትሆናለች። 22ቱ አትሌቶች በዓመቱ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና፣ በቤት ውስጥ፣ በመምና ጎዳና ውድድሮች ባስመዘገቡት ውጤትና ባሳዩት አቋም በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች ሊመረጡ ችለዋል።
በዚህ ዘርፍ ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈችው ኢትዮጵያዊት የረጅም ርቀት ሯጯ አትሌት አልማዝ አያና እአአ በ2016 ሲሆን፤ በ2007 አትሌት መሰረት ደፋር ምርጥ አትሌት በመባል የመጀመሪያዋ ሴት አትሌት ናት። በ2015 ደግሞ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ የዓመቱ ምርጥ ሴት አትሌት መባል ችላለች።
በወንዶችም የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች እጩ ይፋ ቢሆንም አንድም ኢትዮጵያዊ አትሌት ሳይካተት ቀርቷል። ሞሮኮዋዊ የ3 ሺ ሜትር መሰናክል ቻምፒዮን እና ለ6 ተከታታይ ፍጻሜ ያልተሸነፈው ሶፍያን ኤል ባካሊ እና ኬንያዊው የችካጎ ማራቶን ባለ ክብረወሰን ኬልቪን ኪፕቱን ከአፍሪካ ተካተዋል። ኢትዮጵያዊው የረጅም ርቀት ኮከብ ቀነኒሳ በቀለ በ2004 እና 2005 ባሳየው ብቃትና የዓመቱ ምርጥ አትሌት ሊባል ችሏል። ከዛ ቀደም ብሎ እአአ በ1998 ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የዓመቱን መርጥ አትሌትነት በመጎናጸፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ነው። በታዳጊ አትሌቶች ዘርፍም የዓመቱ ምርጥ ወንድ አትሌቶች ምርጫ እአአ 2005 የተጀመረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰለሞን ባረጋ በወጣቶች ዘርፍ 2019 የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ወጣት አትሌት በመሆን ተመርጧል።
በምርጫው የዓለም አትሌቲክስ ምክር ቤት 50 ከመቶ ድምጽ ያለው ሲሆን፤ የዓለም አትሌቲክስ ቤተሰቦች እንዲሁም የማህበራዊ ድረገጽ ተከታዮች ቀሪውን ድምጽ ይሰጣሉ። የድምጽ መስጫ ጊዜው ለሁለት ሳምንት ሲቆይ፤ ከወር በኋላ ውጤቶቹ ተጠናቀው ኮከብ አትሌቶች የሚለዩ ይሆናል። አሸናፊዎቹ ደግሞ በመጪው ታህሳስ ወር/2016ዓ.ም ይፋ ይደረጋሉ።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም