ኢትዮጵያ ስኬታማ ከሆነችበት የአትሌቲክስ ስፖርት ባሻገር በቦክስና በብስክሌት ስፖርቶች በተደጋጋሚ በኦሊምፒክ መድረክ ላይ መሳተፍ ችላለች:: በእነዚህ ስፖርቶች ከተሳትፎ ባለፈ ውጤት ሊመዘገብ ግን አልቻለም:: ሆኖም በስፖርቶቹ ላይ ትኩረት ተደርጎ ቢሰራ እምቅ አቅም ያላት መሆኑን ባለሙያዎች ይመሰክራሉ:: በቅርቡ በአፍሪካ የቦክስ ቻምፒዮና ላይ ለ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ማጣሪያ በ57 ኪሎ ግራም የብር ሜዳሊያ ያጠለቀው ቦክሰኛ ፍቅረማርያም ያደሳም ለዚህ ማሳያ ይሆናል::
በስፖርት ዘርፍ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ከመሆን ባለፈ ተቋማቱን በመምራትም ሃገርን መወከል ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል:: ለዚህ ደግሞ ‹‹የአፍሪካ ስፖርት አባት›› እስከመባል የደረሱትን ታላቁ የስፖርት ሰው ይድነቃቸው ተሰማን ማስታወስ ይቻላል:: የስፖርት ተሳታፊነት እና ማሕበራትን በማቋቋም በአፍሪካ የጎላ ሚና ያላት ኢትዮጵያ ከዓመታት ወዲህ ግን አህጉር አቀፍ የስፖርት ማሕበራትን ከመምራት ጋር ያላት ዝምድና እምብዛም እየሆነ መጥተል:: በጥቂቱ ሊጠቀሱ የሚችሉና በዞን እና በአፍሪካ የስፖርት ተቋማት ውስጥ የመምራት እድልን ያገኙ የስፖርት አመራሮችም ቢሆኑ እንቅስቃሴያቸው የተቀዛቀዘ ሊባል የሚችል ነው::
አህጉር አቀፍ የስፖርት ማሕበራት መሪነት ሚናን በተለያዩ ስፖርቶች ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የቦክስ ስፖርት ፌዴሬሽን ተጠቃሽ ነው:: ይኸውም ዛሬ የሚከናወነውን የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተከትሎ ኢትዮጵያዊ ተፎካካሪ ማቅረብ ተችላል:: የአፍሪካን የቦክስ ስፖርት የሚመራው ኮንፌዴሬሽን በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ምትክ ዛሬ ምርጫ ያካሂዳል:: 50 አባል ሃገራት ያሉት ኮንፌዴሬሽኑ ምርጫውን ባለፈው ወር ለማድረግ ያቀደ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ተራዝሞ ነው ዛሬ የሚደረገው::
በደቡብ አፍሪካዋ ከተማ ደርባን በሚካሄደው በዚህ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይም አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው የተገኙ አራት እጩዎች መቅረባቸው ተረጋግጧል:: እነሱም ከኢትዮጵያ አቶ እያሱ ወሰን፣ ካሜሮናዊው ሜንዶጋ ቤርትራንድ ሮናልድ፣ ሞሮኳዊው አል ካቡሪ ሞሃመድ እንዲሁም ከዚህ ቀደም በኮንፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲሰሩ የቆዩት ናይጄሪያዊው ኦሞ አጌጌ አዛኒያ ናቸው:: ኢትዮጵያን በመወከል በምርጫው ላይ የሚሳተፉት የፓራዳይዝ ሎጅ እና የኦሞቲክ ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤትና ባለሀብቱ አቶ እያሱ ከፍተኛውን ድምጽ በማግኘት የመመረጥ እድላቸው የሰፋ እንደሚሆን ተጠቁማል::
አቶ ኢያሱ ለቦክስ ስፖርት ካላቸው ፍቅር የተነሳ ስፖርቱን በእውቀታቸው እንዲሁም በገንዘባቸው ለማገዝ እንደተቀላቀሉ ይታወቃል:: ይህንንም በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ ተገኝተው ለአሸናፊዎች በሚያደርጉት የገንዘብ ሽልማትና ድጋፍ በተደጋጋሚ ማስመስከር ችለዋል:: አሁን ደግሞ በዚህ ስፖርት የአፍሪካ ፕሬዚዳንት በመሆን የሃገራቸውን ስም ለማስጠራት በእጩነት ቀርበዋል:: የመወዳደሪያ መሪ ሃሳባቸው ‹‹ነፃ አፍሪካ አንድ የቦክስ ራዕይ›› ሲሆን፤ ነጻ አህጉር የሆነችው አፍሪካ ነጻ መሪ ያስፈልጋታል የሚል መርህ እንደሚከተሉም አስተዋውቀዋል::
እጩው አቶ ኢያሱ የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት በመሆን ቢመረጡ ለኢትዮጵያ የቦክስ ልማት ከሚኖረው ጠቀሜታ ባለፈ በስፖርት ዲፕሎማሲ ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠቁማሉ:: በተጨማሪም በገጽታ ግንባታ፣ በገንዘብ፣ የስፖርት ማዕከላትን በማስገንባት እንዲሁም ዓለም አቀፍ እንዲሁም አህጉር አቀፍ ውድድሮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የሚሰሩ መሆናቸውንም የምርጫ እንቅስቃሴ ባደረጉበት ወቅት ጠቁመዋል:: አክለውም ‹‹ምርጫው አህጉር አቀፍ ስፖርትን ለመምራት የሚደረግ በመሆኑ ለኢትዮጵያ የቦክስ ስፖርት መልካም ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል። የኮንፌዴሬሽኑ አባላት ለአፍሪካ የቦክስ ስፖርት ትክክለኛና የሚበጀውን ሰው መምረጥ አለባቸው›› ሲሉም ተናግረዋል።
የምርጫ እንቅስቃሴያቸውን ተከትሎም የታንዛኒያ እና ሶማሊያ ቦክስ ፌዴሬሽኖች ድጋፋቸውን ያሳዩ ሲሆን፤ አቶ ኢያሱ በንግዱ ዓለም ያገኙትን ስኬት በኮንፌዴሬሽኑም መቀዳጀት እንደሚችሉ እንዲሁም ስፖርቱንም ያሳድጋሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2016