የባርሴሎና ኦሊምፒክ ከተካሄደ ሶስት አስርት ዓመታትን ተሻግሯል፡፡ ይህ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በሎስአንጀለስ እና ሴኡል ኦሊምፒኮች ሳትሳተፍ ቀርታ ዳግም ወደ ታላቁ የውድድር መድረክ የተመለሰችበት መሆኑ ይታወሳል፡፡ ከዚህ በተለይ ደግሞ እንቁዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ በሴቶች 10ሺ ሜትር ወርቅ ያጠለቀች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት የሆነችበት ታሪካዊ ክስተት ሆኖ ይበልጥ ይታወሳል። ይህ ታሪክ የኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በዘመናዊው ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ሩጫ የወርቅ ሜዳሊያን ያጠለቀች የመጀመሪያዋ ጥቁር አትሌት በመሆንም ለአህጉረ አፍሪካ በወርቅ ቀለም ተከትቦ ሲዘከር እየኖረ ነው፡፡
በዚያ የኦሊምፒክ ውድድር ላይ ደራርቱ ባታሸንፍ ድሉ ምናልባትም የሌላኛዋ አፍሪካዊት አትሌት የመሆን እድሉ የሰፋ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ደቡብ አፍሪካዊቷ አትሌት ኤላና ሜየር የነበራት አቋምና ተፎካካሪነት ነው። በወቅቱ የብር ሜዳሊያውን የግሏ ያደረገችው አትሌቷ በደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ሥርዓት መጠናቀቅ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው በዚህ የኦሊምፒክ ተሳትፎ የሀገሯን ስም ለማስጠራት ከደራርቱ ጋር የነበራት ትንቅንቅም ከአትሌቲክስ ቤተሰቡ ትዝታ የሚፋቅ አይደለም፡፡ ሁለቱ አትሌቶች ከዓመታት በኋላ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በአንድ መድረክ ተገናኝተው ትዝታቸውን ተጋርተዋል፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ ደቡብ አፍሪካዊቷ አትሌት በተፎካካሪዋ ሀገር በሚደረገውና በአፍሪካ በግዝፈቱ ቀዳሚ በሆነው የጎዳና ላይ ሩጫ በክብር እንግድነት ተጋብዛለች፡፡
ኤለና ሜየር ጎልቶ ከሚታወሰው የባርሴሎና ኦሊምፒክ ድሏ ባለፈ እአአ በ1994 የዓለም ግማሽ ማራቶን ቻምፒዮን ስትሆን፤ እአአ በ1999 የቶኪዮ ግማሽ ማራቶንን 1፡06፡44 በሆነ ሰዓት በመሮጥ ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች፡፡ አትሌቷ በተለያዩ ርቀቶች እአአ በ1991፣ 1997፣ 1998 እና 1999 ክብረወሰኖች ባለቤትም ልትሆን ችላለች፡፡ አንጋፋዋ አትሌት ለ22ኛ ጊዜ ዘንድሮ ኅዳር 9/2016 በሚካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በኦሊምፒክ፣ ዓለም ቻምፒዮና እንዲሁም ሌሎች ውድድሮች ብቃታቸውን ካስመሰከሩ አትሌቶች ጋር በክብር እንግድነት ትገኛለች፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና ስኬታማ የሆኑ አትሌቶች በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በክብር እንግድነት ሲጋበዙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ በየዓመቱ የጎረቤት ሀገር ኬንያን ጨምሮ የእንግሊዝና ሌሎች ሀገራት ድንቅ ብቃታቸውን ያስመሰከሩና ከኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ጋርም ፉክክር በማድረግ የሚታወቁ አትሌቶች በክብር እንግድነት በመገኘት ውድድሩን በተደጋጋሚ አስጀምረዋል፡፡ ይህም የሩጫውን ዓለም አቀፍ ይዘት ይበልጥ የሚጨምር ሲሆን፤ ከሌሎች ሀገራት ተሳታፊ ለመሆን የሚመጡ ሯጮችንም በይበልጥ የሚያበረታታ ይሆናል፡፡ ‹‹ክትባት ለሁሉም ሕጻናት›› በሚል መሪ ሃሳብ ከ44 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የሚታደሙበት ውድድር ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል በርካቶቹ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ በእርግጥ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ተወዳጅ ከሆኑ የጎዳና ሩጫዎች መካከል አንዱ ከመሆኑ ባለፈ በዓለም ማራቶንና የጎዳና ሩጫዎች ማህበር (AIMS) እውቅና ያገኘ እንደመሆኑ ሌሎች አትሌቶች ለተሳታፊነት ፍላጎት ማሳደራቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ በ10 ኪሎ ሜትር የሚደረገው ውድድር ከመዝናኛነቱ ባለፈ ሯጩ የሚያስመዘግበው ውጤት እንዲሁም ሰዓት ተቀባይነት ያለውና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የሚያገኝ በመሆኑ ለአትሌቶችንም ጭምር ተሳታፊ ለመሆን አነሳሽ ምክንያት ነው፡፡ በዚህም በየዓመቱ በርካታ የሌሎች ሀገራት አትሌቶች እንዲሁም በሩጫ መዝናናት የሚመርጡ ሀገራት ዜጎች በስፋት ተሳታፊ ሲሆኑና ይህንንም ተከትሎ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ሲሰጡት ይስተዋላል። አንድ ወር ብቻ በሚቀረው በዘንድሮው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ላይም እንዳለፉት ዓመታት በርካታ የውጭ ሀገራት ሯጮች ተካፋይ ይሆናሉ፡፡
በዚህም መሠረት ከ10 በላይ ከሆኑ ሀገራት (ከሁሉም አህጉራት የተወጣጡ) ተሳታፊዎች ምዝገባቸውን አጠናቀው ሩጫው የሚካሄድበትን ቀን እየጠበቁ መሆኑን ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ ከነዚህም ሯጮች ውስጥ የጎረቤት ሀገር ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ህንድ፣ ብራዚል፣ ስዊዘርላንድ፣ አውስትሪያ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ይገኙበታል፡፡
ከተሳታፊዎቹ መካከል በእድሜ ትንሹ ከአሜሪካ የሚመጣው ማይክ ዴሪክ የ20ዓመት ወጣት ሲሆን፤ አንጋፋው ተሳታፊ ደግሞ የ72ዓመት ባለጸጋው እንግሊዛዊው ዶን ብራድሊ ናቸው፡፡ ይህም ሩጫው በሁሉም የዕድሜ ደረጃ የሚገኙትን ያማከለ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ያላትን የሩጫ ባህል በበጎ ጎን ለማሳየት የሚያስችልም ነው፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም