በኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛዎቹ ክልልና ከተማ አስተዳደሮች ስታዲየሞች ቢገነቡም ሁሉም ማለት ይቻላል ሙሉ በሙሉ ሳይጠናቀቁ በመቅረታቸው ለአገልግሎት አልበቁም። በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የፈሰሰባቸው እነዚህ ስታዲየሞች አንድ ደረጃውን የጠበቀ የመጫወቻ ሜዳ ማሟላት የሚኖርበትን መስፈርት ያሟሉ አይደሉም። ይህም ኢትዮጵያ የካፍና ፊፋን ደረጃ የሚያሟላ ሜዳ እንዳይኖራት በማድረጉ ብሔራዊ ቡድኑና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ክለቦች ከሀገር ውጪ ለመጫወት ተገደዋል።
የሀገሪቱ ትልቅ ውድድር የሆነው ፕሪሚየር ሊግ ላይም የመጫወቻ ሜዳ አለመኖር ስጋትን ደቅኗል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሌሎች በርካታ ችግሮች ቢኖሩበትም የመጫወቻ ሜዳው በመሠረታዊነት የተፈለገውን እና ተመልካች የሚናፍቀውን ፉክክር እንዳይመለከት እንቅፋት ነው። ሊጉ የብሮድካስት ሽፋን አግኝቶ በመላው ዓለም የሚታይ እንደመሆኑ የሜዳው ደረጃ ለዚያ የሚመጥን እንዳልሆነ ባለፉት ዓመታት መታዘብ ተችሏል። የመጨዋቻ ሜዳው ደረጃውን የጠበቀ ባለመሆኑ ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር እየጨቀየ ለሊጉ መቋረጥና መቀዛቀዝ ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል። ነገሩ እልባት ሳያገኝም የ2016 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በመጀመሩ የሊጉ ከፍተኛ ጥያቄ መሆኑን ቀጥሏል።
በእድሳት ላይ ያሉ ስቴድየሞች በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻላቸው ሊጉ በተደጋጋሚ በአንድ አካባቢ በሚገኙ ሜዳዎች እንዲካሄድ አስገድዷል። ይህም ሜዳዎች ጫና እንዲበዛባቸውና ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል። በ2015 ዓ.ም ከሜዳ ጋር በተያያዘ ጉዳይ አስቸጋሪ ጊዜን ያሳለፈው ሊጉ አሁንም መሻሻል አለማሳየቱን አክሲዮን ማኅበሩ ባደረገው ግምገማ መዳሰሱ ይታወሳል።
ይኸው ጉዳይ ክለቦች ከደጋፊ የሚያገኙትን የሜዳ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ሊያሳጣም ችሏል። በተለይ ከሕዝብ በሚገኝ ድጋፍ የሚንቀሳቀሱትን ክለቦች በእጅጉ ተጎጂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የአዲስ አበባ ክለቦች ግንባር ቀደም የችግሩ ተጋላጭ ናቸው። በጥቂት ከተሞች ውድድር መደረጉ ደግሞ ከሜዳ የሚገኘውን ገቢ ከማሳጣቱም በላይ ክለቦችን ለተጋነነ የሆቴልና ሌሎች ወጪዎች እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል።
አክሲዮን ማኅበሩም የሜዳ ጉዳይ አለመሻሻሉንና በዚህ የውድድር ዓመት መለወጥ እንደሚኖርበት አስገንዝቦ ጥረቱንም እንደሚቀጥል አስታውቆ ነበር። ችግሩን ለመቅረፍም ከኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር ውይይት እያደረገ ሲሆን ችግሩን ለመቅረፍም እየሠራ ይገኛል። በእድሳት ላይ የሚገኙ ሜዳዎች አለመጠናቀቃቸውና ያሉት ሜዳዎችም ደረጃቸው ማሽቆልቆል እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ የፀጥታ ስጋቶች ሊጉ የሜዳ አማራጮቹን ቁጥር ቀንሶበታል።
ውድድር በሚደረግበት ወቅት 16ቱም ክለቦች አንድ ቦታ በመከተማቸው ምክንያት አክሲዮን ማኅበሩ ከሚገለገልባቸው እንደ ሜዳ፣ የልምምድ ቦታ፣ ሆቴልና ጸጥታ ጋር ውስንነቶች እያጋጠሙትም ነው። ለዚህም ውድድሮቹ በሚደረጉበት ስፍራ ያሉ ክለቦች በቂ ድጋፍ እያደረጉ አለመሆናቸውም ሌላው ችግር በመሆኑ ሁኔታው መስተካከል እንደሚኖርበት አክሲዮን ማኅበሩ በጉባኤው መወሰኑን ጠቅሶ ነበር።
አክሲዮን ማኅበሩ ይህ ጉዳይ አጽንኦት እንዲሰጠውና በትኩረት እንዲሠራ የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይም ይገኛል። ማኅበሩ ባደረገው ግምገማ መሠረት የሜዳው ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ የማሽቆልቆል ሁኔታ ተስተውሎበታል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ሊጉ ሲጀመር በሀገሪቱ ውስጥ አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ባህር ዳር፣ መቐሌ፣ ድሬዳዋና ሃዋሳ እንደነበሩ ይናገራሉ፤ ከነዚህም ውስጥ በአሁኑ ወቅት አራቱ ሜዳዎች አለመኖራቸውን ተናግረዋል። ምናልባት በዚህ ዓመት አዲስ አበባ ይመለስ ይሆናል። ነገር ግን ሦስቱ በቅርብ ጊዜ ይመለሳሉ በሚለው ላይ የቦርዱ ሰብሳቢ ስጋት አላቸው።
የስጋታቸው ዋንኛ ምክንያትም የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳቱ እስከ አሁን መጠናቀቅ አለመቻልና በድጋሚ የመጫወቻው ሜዳ ማሻሻያ ይደረግለታል መባሉ ነው። የባህር ዳር ስታዲየም በበኩሉ የካፍን ደረጃ ለማሟላት በእድሳት ላይ በመሆኑም አገልግሎት አይሰጥም። የሃዋሳ ስታዲየምም እንዲሁ ከአዲሱ የክልሉ መንግሥት ጋር ርክክቦች ባለመካሄዳቸው የአክሲዮን ማኅበሩን የሜዳ ችግር በቶሎ እንዳይፈታ ከሚያደርጉ ችግሮች ውስጥ ነው። 10ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ያስተናገደው ሌላኛው የድሬዳዋ አንጋፋ ስቴድየምም የሜዳ ጥገና እየተደረገለት በመሆኑ የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ከወዲሁ ፈታኝ ጊዜን እንዲያሳልፍ ሊያደርገው ይችላል። በዚህም የተነሳ ፕሪሚየር ሊጉን ወደ ኋላ እንዳይጎትተው ያሰጋል።
የሜዳ ጉዳይ የክለቦቹን አህጉር አቀፍ ተሳትፎንም ማስተጓጎሉ የማይቀር ነው። በመሆኑም የክለቦችን ደረጃ ጥያቄ ውስጥ አስገብቶቷል። ካፍ ሁሉም የአፍሪካ ሀገሮች በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ውድድራቸውን እንዲጀምሩ እቅድ በመያዙ የሜዳ ጉዳይ አፋጣኝ መፍትሔን ይሻል። በቶሎ የማይፈታ ከሆነ ግን ለአፍሪካ ክለቦች ውድድር የሚያልፉ ክለቦች ከውድድሩ የመሰረዝ አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መስከረም 30/201