በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የመስከረም ወር ብቻ አራት ትልልቅ የዓለም ክበረወሰኖች በአትሌቲክስ ስፖርት ተሰብረዋል፡፡ ከእነዚህ ክብረወሰኖች መካከል ሶስቱ በኢትዮጵያዊያን ሴት አትሌቶች በአንድ ማይል፣ በ5ሺ ሜትር እንዲሁም በማራቶን የተሰበሩ ሲሆን፤ አራተኛው ክብረወሰን ደግሞ ከትናንት በስቲያ በኬንያዊው አትሌት ቺካጎ ማራቶን ላይ ተመዝግቧል። ይህም በቀናት ልዩነት የማራቶን ፈጣኑ ሰዓት በሁለቱም ጾታ በአዲስ እንዲተካ አድርጓል፡፡
የአትሌቲክስ ውድድሮች አውራ በሆነው ማራቶን ውድድሮችን ማሸነፍ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በአርባ ሁለት ኪሎ ሜትሩ ፈታኝ ፉክክር የዓለምን ክብረወሰን ማሻሻል ደግሞ ዋጋው ቀላል አይደለም። ማራቶን እጅግ ከባድና ጠንካራ ዝግጅትን የሚፈልግ ውድድር እንደመሆኑ በተደጋጋሚ የዓለም ክብረወሰኖችን መመልከት የተለመደ አይደለም፡፡ ያም ሆኖ የተለየ አቅም ያላቸው አትሌቶች በጽናታቸው አንድ ርምጃን ቀድመው በመገኘት በዚህ ወር ብቻ እየሰባበሩ ስፖርቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገር እየቻሉ ይገኛሉ፡፡
በተለይም በሁለት ሳምንት ልዩነት በሁለቱም ፆታ የተመዘገቡት አዲስ የማራቶን የዓለም ክብረወሰኖች ለዓለም አትሌቲክስና ለዓለም አትሌቶች የማይቻል ነገር እንደሌለና የሰው ልጅ ብቃት ገደብ እንደሌለው በማመላከት ትልቅ ዐሻራ ያሳረፉ ናቸው፡፡ በማራቶን መሳተፍ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት በርካታ ዓመታት ለማመን የሚከብድ ብቃት በማሳየት የኬንያዊውን አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌን የሚደርስበት የለም፡፡
አትሌቱ በጎዳና ላይ የሩጫ ሕይወቱ ለሁለት ጊዜያት የራሱን ክብረወሰን ማሻሻሉ በርቀቱ ቀዳሚ ደረጃ እንዲያገኝ ረድቶታል፡፡ ናይኪ የስፖርት ትጥቅና ቁሳቁስ አቅራቢ ድርጅት ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች በመግባት ሙከራንም ያሳካል በሚል የመረጠው ይህንኑ አትሌት ነበር፡፡ በእርግጥም አትሌቱ ማራቶንን ከ2ሰዓት ከ2 ደቂቃ ከ57 ሰከንድ ወደ 2ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ9ሰከንድ በማውረድ ልዩነት መፍጠር ችሏል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም የሰው ልጅ 42 ኪሎ ሜትርን በአንድ ሰዓት መሸፈን ይችላል የሚለውን ማሳየት ይችላል የሚለው የስፖርት ቤተሰቡ ግምት ነበር፡፡ ይሁንና አትሌቱ የበርሊን ማራቶንን ካሰበው በታች በሮጠ በሁለተኛ ሳምንቱ የሀገሩ ልጅ በሆነው ሌላኛው አትሌት አዲስ ክብረወሰን ሊሰበር ችሏል፡፡ ባለፈው እሁድ በተካሄደው የቺካጎ ማራቶን ኬልቪን ኪፕቱም 2:00:35 በመሮጥ ግምቱን የሚያጠናክር እንዲሁም የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን የሆነ ሰዓት ሊያስመዘግብ ችሏል።
የዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃን በሰጠውና ዘንድሮ ለ45ኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ውድድር ማራቶንን ከ2ሰዓት በታች ለመሮጥ 35 ሰከንዶች ብቻ የቀሩት መሆኑ ታይቷል፡፡ የ23 ዓመቱ ወጣት አትሌት በቅርቡ ይህንን ሰዓት የማሻሻል እድል እንደሚኖረው እንዲሁም የወንዶች ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች የማጠናቀቅ ሙከራ በአጭር ጊዜ ሊሳካ እንደሚችል ይገመታል፡፡
ኬንያዊያን አትሌቶች እአአ ከ2011 አንስቶ ክብረወሰኑን በተከታታይ ለስድስት ጊዜያት በመስበር የሚደርስባቸው አልተገኘም፡፡ ከዚያ አስቀድሞ በነበሩት ሁለት ዓመታት ክብረወሰኑ በኢትዮጵያዊው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ የተያዙ ነበሩ፡፡ የበላይነቱ በኬንያዊያን ከተያዘ ከዓመታት በኋላም ግን ወደ ኢትዮጵያ ሊመለስ አልቻለም። በርቀቱ ከኪፕቾጌ እኩል ትልቅ ግምት ይሰጠው የነበረው ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ነበር፡፡ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድ አትሌቶች በአንጻሩ ክብረወሰን ለመስበር በሚያስችል ሁኔታ ላይ ናቸው ብሎ ለመናገር አዳጋች ነው፡፡
በቺካጎ ማራቶን ሴቶች በኩል ሁለተኛው ፈጣን ሰዓትም ሊመዘገብ ችሏል፡፡ በቅርቡ ማራቶንን የተቀላቀለችው ድንቅ አትሌት ሲፈን ሃሰን 2:13:44 በሆነ ሰዓት ልትገባ ችላለች፡፡ አትሌቷ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በመምና ጎዳና ሩጫዎች በተለያዩ ርቀቶች በነበራት ተሳትፎ ምናልባትም ብዙዎች ሊያደርጉት በማይችሉት ሁኔታ የብቃቷን ጥግ ማስመስከር ችላለች፡፡ የርቀቱን ክብረወን በቅርቡ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ የግሏ ማድረግ ብትችልም ሲፈን ካላት አቅም አንጻር ለማሻሻል የምትችልበት ሁኔታ ላይ ትገኛለች ሊባል ይችላል፡፡
በዓለም አትሌቲክስ የዘንድሮ ውድድር ዓመት ብቻ ከ6 በላይ የሚሆኑ የዓለም ክብረወሰኖች በአፍሪካዊያን አትሌቶች መስበራቸው ይታወቃል። ይኸውም በመካከለኛ ርቀት የመምና የጎዳና ላይ ውድድሮች ሲሆን፤ በቅርቡ የተካሄደውን የዓለም የጎዳና ላይ ቻምፒዮና ድሪቤ ወልተጂ ያስመዘገበችው የማይል ክብረወሰንን ጨምሮ በጉዳፍ ፀጋይ የተመዘገበው የ5ሺ ሜትር ክብረወሰን የዓለም አትሌቲክስን ደረጃ ከፍ ያደረጉ ሆነዋል፡፡ ይህም ከወራት በኋላ በፓሪስ የሚካሄደውን የ2024 ኦሊምፒክ ከወዲሁ አጓጊ አድርጎታል፡፡ በዚህ ዓመት የተሰበሩትን ክብረወሰኖች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ወቅታዊ የአትሌቲክ ተፎካካሪነትን መነሻ በማድረግም በኦሊምፒኩ አዳዲስ ክስተቶች ይታያሉ የሚለውን ግምት አሳድጎታል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2016