ታላቁ ሩጫ የበጎነት መገለጫ

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የጎዳና 10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር መካሄድ ከጀመረ እነሆ 23 ዓመታትን አስቆጥሯል:: በእነዚህ ዓመታት ከፍተኛ ተሳታፊን በማፍራትና ከትልልቅ ዓለም አቀፍ የጎዳና ውድድሮች ተርታ መሰለፍም ችሏል:: ውድድሩ ከተጀመረበት ወቅት አንስቶ ከውድድር ባሻገር በርካታ በጎ ምግባሮችን በማድረግ ለበርካታ ወገኖች አለኝታነቱን አሳይቷል:: የዘንድሮ ውድድሩን ሲያካሂድም ይሄንኑ አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል:: ከዋናው የጎዳና ሩጫ ጎን የሚካሄደው የሕፃናት ውድድርም ይሄንኑ ዓላማ አንግቦ ይካሄዳል::

የዚህ ዓመት ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻ በይፋ የተጀመረ ሲሆን ከሕፃናቶች ውድድር የሚገኘው ገቢ የፖሊዮ በሽታን ለመጥፋትና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ሴቶች፣ ሕፃናትና አካል ጉዳተኞችን ለመርዳት እንደሚውል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስታውቋል። ታላቁ ሩጫ ከሚያካሂዳቸው ውድድሮች ውስጥ አንዱ የሆነው የሕፃናት ውድድር ፖሊዮን ለማጥፋት እና ለእሷ ቢዝነስ (for her business) በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉትን ሕፃናት፣ ሴቶችና አካልጉዳተኞችን ማገዝ ዓላማ በማድረግ ይካሄዳል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ የጎዳና 10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር በየዓመቱ የተለያዩ ዓላማና መልዕክቶችን በመያዝ ከሩጫው ጎን ለጎን በብዙ ችግርና መከራ ውስጥ ያሉ ወገኖችን ለመርዳት የሚያደርገውን እገዛ ከጀመረ 18 ዓመታትን አስቆጥሯል። የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አካል የሆነው የ2016 ዓ.ም ፖሊዮን ጨርሰን እናጥፋ የሕፃናት ሩጫ እና ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በችግር ውስጥ ያሉትን በርካታ ሴቶች፣ ሕፃናትና አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ ያደርጋል። በዋናው ሩጫ ዋዜማ የሚካሄደው የሕፃናት ውድድር ‹‹በጋራ ፖሊዮን እናጥፋ›› እና ‹‹ክትባት ለሁሉም ሕፃናት›› በሚል ሃሳብ ይካሄዳል። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ2016 ዓ.ም ውድድር ኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን፤ የሕፃናት ውድድር ኅዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም ይካሄዳል።

በዚህ ፖሊዮን ጨርሰን እናጥፋና ለሷ ቢዝነስ (for her business) በሚለው የሕፃናት ውድድር ላይ 3 ሺ 500 ዕድሜያቸው ከ11 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ይሳተፉበታልም ተብሏል:: ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ2016 ዓ.ም ምዝገባ ከተጀመረ ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን የሕፃናት ውድድሩ ምዝገባ በዛሬው ዕለት መስከረም 28/2016 ዓ.ም የሚጀመር ይሆናል:: ለሩጫው የሚመዘገቡት ተሳተፊዎች 360 ብር በመክፈል መመዝገብ እንደሚችሉም ተጠቅሷል::

የዚህ ዓመት ሌሎችን ለመርዳት ሮጣለሁ የገቢ ማሰባሰቢያ ውድድር ዘመቻ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በአማራ፣ ትግራይና አፋር ክልል በጦርነቱ ምክንያት ከሥራቸው የተፈናቀሉ አንድ ሺህ የሚሆኑ ሴቶችን መልሶ ለማቋቋም እንደሚውልም ተገልጿል። የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ ታላቁ ሩጫ በጎ ነገር ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን በማስተባበር የገቢ ማሰባሰቢያ ሲደረግ እንደቆየ ገልጻለች:: በዚህም እስከ ዛሬ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል:: በተጨማሪም በአንድ ወቅት ከዚሁ ውድድር በተገኘው ገንዘብ ትምህርት ቤት መገንባቱንም አስታውሳለች:: አንድ ሺ ሴቶችን ተጠቃሚ በሚያደርገው ለሷ ቢዝነስ በሚለው መርሐ ግብር ደግሞ አንድ ሺ ሴቶችን ለማገዝና መልሶ ለማቋቋም እንደታቀደም ተጠቁሟል:: በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ የዘመቻ ሩጫም 500 ሺ ዶላር ለመሰብሰብ ታቅዷል። ለእያንዳንዱ ግለሰብም 500 ዶላር ድጋፍ በማድረግ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ይሠራል::

እንደ ሥራ አስኪያጇ አስተያየት ታላቁ ሩጫ በአንድ ቀን ውድድር ብዙ ሰው የሚያሰባስብ በመሆኑ እና ብዙ ሚሊዮን ተመልካች ያለው በመሆኑ እንደዚህ ዓይነት በጎ ምግባሮች ለመሥራት ቀላል ይሆናል:: በ2015 ዓ.ም በተደረገው ጥናት ኢትዮጵያ ወደ 1 ሚሊዮን ዶላር እንድታገኝ አድርጓል:: ይህም የውጭ ምንዛሬ ፍሰትን በማሳደግ ሀገሪቷ ያለባትን የምንዛሬ ክፍተት ይሸፍናል:: ኅብረተሰቡን ከማገዝ፣ ቱሪዝምን ከማስፋፋትና የምንዛሬ ፍሰትን ከማሳደግ በተጨማሪ ብዙ ተዘርዝረው የማያልቁ ሥራዎችን ማበርከት እንደቻለም ሥራ አስኪያጇ ታስረዳለች:: ይህ ለበጎነት የሚደረገው ሩጫ ሲጀመር 88 ሺ ብር ብቻ ነበር የተሰበሰበው:: ለዚህም ብዙ ሥራዎችን መሥራትና ግንዛቤ መፍጠር አስፈልጎ ነበር:: አሁን ግን ካስቆጠረው ዕድሜና ቆይታ አንጻር ለውጦች አሉ::

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ በአፍሪካ ከሚካሄዱ የጎዳና ውድድሮች ሁሉ ቀዳሚና ትልቅ ሲሆን ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ማስጠራት የቻሉትን ኮከቦች በማፍራት ተጠቃሽ ነው። በተሳታፊ ቁጥርና በዓለም ከሚገኙት ታላላቅ የጎዳና ላይ ውድድሮች አንዱ የሆነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በርካታ ተሳታፊዎች ይካፈሉበታል።ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You