የዓለማችን ትልቁና ተወዳጁ ስፖርታዊ ውድድር የሆነው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ አንድ ምዕተ ዓመት ሊያስቆጥር ተቃርቧል። እአአ በ1930 ኡራጓይ ላይ የተጀመረው ይህ ውድድር ለዓመታት ሲከተለው ከነበረው የተለየ የውድድር አካሄድ 100ኛ ዓመቱ ላይ ሊተገብር መሆኑን እግር ኳስን በበላይነት የሚመራው ፊፋ ከሰሞኑ አስታውቋል። ይህንን ተከትሎም የ2030 ዓለም ዋንጫ በሶስት አህጉራት የሚካሄድ ሲሆን፤ አፍሪካም በአዘጋጅነቱ ላይ ሚና ተሰጥቷታል፡፡
ሀገራት ለእግር ኳስ የበላይነት የሚፋለሙበትን የውድድር መድረክ በጥምረት ለማዘጋጀት የተለያዩ ሀገሮች ለፊፋ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፤ አውሮፓውያኑ ስፔንና ፖርቹጋል እንዲሁም አፍሪካዊቷ ሞሮኮ ዋነኞቹ አዘጋጆች መሆናቸው በፊፋ ተረጋግጧል። ሁለቱ የአውሮፓ ሀገራትና ሰሜን አፍሪካዊቷ ሞሮኮ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎም በሁለቱ አህጉራት አውሮፓ እና አፍሪካ የሚዘጋጅ ይሆናል፡፡ ሶስተኛዋ አህጉር ደቡብ አሜሪካ ስትሆን ኡራጓይ፣ ፓራጓይና አርጀንቲና ሶስቱን የመክፈቻ ጨዋታዎች የማስተናገድ እድል ተሰጥቷቸዋል። ይኸውም ዓለም ዋንጫ በኡራጓይ የተጀመረበትን መቶኛ ዓመት ለማሰብ ነው፡፡
በስድስቱ ሀገራት የዓለም ዋንጫውን በማስተናገድ ሂደትም አፍሪካ ዳግም ታላቁን ውድድር በምድሯ የማካሄድ እድል ማግኘቷ ሌላኛው ታሪካዊ ሁነት ሆኗል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ዓለም ዋንጫን እአአ 2010 እጅግ ደማቅና የአህጉሪቷን አቅም ባንጸባረቀ ሁኔታ ማስተናገዷ የሚታወስ ነው፡፡ በ2020 የካታር ዓለም ዋንጫ ባልተጠበቀ ሁኔታ አስደናቂ አቋም ያሳየችው ሞሮኮ ደግሞ በአህጉሪቷ የእግር ኳስ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫውን እንደምታስተናግድ ተረጋግጧል፡፡ ይህንን ተከትሎም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞሴፔ ‹‹ካፍ ሞሮኮና የዓለም ዋንጫ ዝግጅት አጋሮቿ ፖርቹጋል እና ስፔን የፊፋ ምክር ቤት በ2030 የዓለም ዋንጫን እንዲያስተናግዱ በመመረጣቸው እንኳን ደስ አለን ለማለት እወዳለሁ። ይህ አጋርነት አፍሪካን እና አውሮፓን በእግር ኳስ የሚያገናኝ እና ሁላችንም እንድንተባበር እንዲሁም ዓለምን የተሻለች ለማድረግ ያነሳሳናል። የሞሮኮው ንጉስ መሀመድ ስድስተኛ፣ መንግሥት እና የሞሮኮ ሕዝብ ላሳየው ድጋፍም እናመሰግናለን። ለሞሮኮ ድጋፍ ላደረጉት የካፍ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና የካፍ አባላት የሆኑትን 54 የአፍሪካ ሀገራት የሚወክሉ አባል ማህበራትንም እናመሰግናለን። ሞሮኮ የ2030 የፊፋ የዓለም ዋንጫን ማዘጋጀቷ ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ካፍ ያምናል፡፡ በተለይም ከሕዝባቸው የወጣት ቁጥራቸው በፍጥነት እያደገ ለሚገኘው የአፍሪካዊያን ውድድሩ በመቶ ዓመታት ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አፍሪካ መምጣቱ ትልቅ ጥቅም አለው›› ብለዋል።
የዓለም ዋንጫን 100ኛ ዓመት እንዲሁም ይፋ የሆነውን የውድድር አካሄድ ይፋ መሆን ተከትሎ የ203ኛው ውድድር መነጋገሪያ ሆነ እንጂ ከሁለት ዓመታት በኋላ ዓለም ዋንጫ እንደሚካሄድ ይታወቃል፡፡ ይህ በነበረው አካሄድ የሚደረገው የመጨረሻው የዓለም ዋንጫ ውድድርም በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጥምረት ይካሄዳል፡፡ በአዲሱ የውድድር ሥነ ሥርዓት ከዓመታት በኋላ የሚካሄደው እአአ የ2034ቱ የዓለም ዋንጫ ደግሞ የታላቂቷ አህጉር እስያ እንዲሁም ትንሿ አህጉር ኦሺንያ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽኖች የአዘጋጅነት እድሉን በስፋት እንደሚያገኙ ታውቋል፡፡ ይህንን ተከትሎም ሳውዲ አረቢያ ያላትን ከፍተኛ የአዘጋጅነት ፍላጎት አንጸባርቃለች፡፡ የሀገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባወጣው መግለጫ መሠረትም ሳውዲ ጥያቄውን ያቀረበችው ደረጃውን የጠበቀ ውድድር ለማካሄድ ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎን እያስመዘገበች ያለውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንዲሁም ሀገሪቱ በእግር ኳስ ያላትን ጥልቅ ፍቅር ለማነሳሳት መሆኑን ገልጿል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም