የ«ኢሬቻ-ኢሬፈና» የቱሪዝም ፋይዳ ሲቃኝ

ትናንት በአዲስ አበባ ዛሬ ደግሞ በቢሾፍቱ ከተማ እየተከበረ የሚገኘው የ“ኢሬቻ” በዓል ከመላው ዓለም ሊመጡ የሚችሉ ቱሪስቶች ሊታደሙበት የሚፈልጉት ደማቅ ሥነ ሥርዓት ነው። የኢሬቻ ክብረ በዓልን አካቶ የያዘው የገዳ ሥርዓትም በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም ግዙፍነት በሌላቸው ባህላዊ ቅርሶች ወካይ መዝገብ (ሪፕረዘንታቲቭ ሊስት ኦፍ ዘ ኢንታንጀብል ካልቸር ኦፍ ሒውማኒቲ) መስፈሩ ኅዳር 2009 ዓ.ም ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ይህ በራሱ ብቻ ቱሪስቶች ከመላው ዓለም እንዲመጡ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ለረጅም ዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲቀባበላቸው ከቆዩ የአኗኗር ብልሃቶች እና ሥርዓቶች መካከል አንዱ የገዳ ሥርዓትና የኢሬቻ ፈጣሪን የማመስገን ሥርዓት አንዱ ነው። የገዳ ሥርዓት በዋናነት የአስተዳደር ሥርዓት ሲሆን፣ የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለመምራት የሚረዱ ዕሴቶችን አካትቷል።

ኢሬቻ ደግሞ በዓመት አንድ ጊዜ በመስከረም ወር ላይ ፈጣሪ የሚመሰገንበት፣ በአባገዳዎች የሚመራ ባህላዊ ፌስቲቫል ነው። ይህ የኦሮሞ ሕዝብ ባህላዊ እሴት ዋና ምሰሶ የሆነ ሥርዓት ሃይማኖታዊ እና የሕግ ሥርዓቶችን በውስጡ አካቶ ይዟል። በተጨማሪም የገዳ ሥርዓት ከውልደት እስከ ሽምግልና ድረስ በእድሜ በመከፋፈል የተለያዩ የማኅበረሰብ ኃላፊነቶችን፣ እና የሥልጣን ድርሻዎችን ይሰጣል። በገዳ ሥርዓት ውስጥ ዋቄፈና እና ኢሬቻ የተሰኙ የእምነትና ባህላዊ ሥርዓቶች ይገኙበታል።

የዝግጅት ክፍላችን በዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ ከተማ በድምቀት እየተከበረ የሚገኘውን “ኢሬቻ” ለቱሪዝም እድገት የሚኖረውን ፋይዳ በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ለማቅረብ ወዷል። በዚህ ዳሰሳ ውስጥ ከላይ በመግቢያችን ላይ ከነሳናቸው ከዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነውን ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ማበልፀግ የሚኖረውን ጠቀሜታ እንቃኛለን።

በዋናነት ኢሬቻ እንዴትና በምን መልኩ እንደሚከበር ያነጋገርናቸው በኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የሀብት ማሰባሰብና የቱሪዝም ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ሂክሰን ደበሌ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ትናንትና እና ዛሬ እየተከበረ የሚገኘውን የኢሬቻ በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪስት መስህብ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ። ዘንድሮ በተለየ ሁኔታ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ አንድምታን በዓሉ እየያዘ እንዲመጣ በማሰብ ከካናዳ፣ ከአሜሪካ፣ ከቻይና፣ ከአውሮፓና ከተለያዩ ሀገራት እንግዶች እንደገቡም ይናገራሉ። ኮሚሽኑም ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ስለ ኢሬቻ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ዲጂታል ሚዲያውን በመጠቀም ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራዎች መሰራቱን ይገልፃሉ።

“ኢሬቻ በሚከበርበት ወቅት እለቱ ለቱሪዝም ያለውን አንድምታ ለማጉላት በማሰብ የተለያዩ ሁነቶችን አከናውነናል” የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በ2015 ዓ.ም በነበረው ክብረ በዓል ላይ እንደተደረገው ከኬንያ ናይሮቢ እስከ ኦሮሚያ ቢሾፍቱ ከተማ ድረስ ‘የኦሮሞ ቦረና ወይም በኬንያ የሚኖሩ ኦሮሞዎች’ የሚያደርጉት ጉዞ የዘንድሮ የኢሬቻ ክብረ በዓል አካል እንደሆነም ይናገራሉ። ከዚህ ባሻገር ሁነቱ የቱሪዝም ፋይዳው እንዲጎላ ለሳምንታት የዘለቁ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች መካሄዳቸውን ይገልፃሉ። ከዚህ ውስጥ የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት “ፋሽን ሾው፣ የቱሪዝም ምርት ኤክስፖ” የባህል እና ልዩ ልዩ ደማቅ ሁነቶች መካሄዳቸውን ይጠቅሳሉ። እነዚህ ተደማምረው ኢሬቻ የቱሪዝም እሴት እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ይገልፃሉ።

ኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ አንድ ዓለም አቀፍ ቱሪስት ሲገኝ በርካታ እሴቶችን እና አዝናኝ ሁነቶችን ተመልክቶ እና እውቀትን ገብይቶ እንደሚመለስ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ የመጀመሪያው ትናንትና እና ዛሬ እየተከናወነ የሚገኘውን የኢሬቻ አከባበር (ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ እና ኢሬቻ ሆራ አርሰዴ) ሥነ-ሥርዓት መመልከት ነው። በዚህ ውስጥ አባ ገዳዎች፣ አባቶች እና እናቶች በኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ሲመርቁና ክብረ በዓሉን በባህሉ መሠረት ሲያስኬዱ መመልከት ይችላል። ሌላው ደግሞ የበዓሉ ታዳሚዎች “ኢሬፈና” ወይም ለምለም ሣር ይዘው ምስጋና ሲያቀርቡ የሚኖረው ለእይታ ማራኪ ሥርዓት ቱሪስቱ የሚያገኘው ትልቅ አጋጣሚ ነው።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ኢሬቻ የምስጋና በዓል ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ሁሉን ነገር ለፈጠረው ሰውን፣ እንስሳትን፣ መሬትና ሰማይን፣ ቀንና ሌሊትን፣ ወንዝና ባህርን፣ ብርሃንና ጨለማን፣ ዝናብ፣ ዕጽዋት፣ ሕይወትና ሞትን ለፈጠረ፣ ሁሉን ነገር ማድረግ ለሚችል ዋቃ (አምላክ) ምስጋናና ክብር የሚያቀርብበት ሥርዓተ በዓል ነው። ቱሪስቱ ይህንን ሥርዓት ለመመልከት ትልቅ እድል ያገኛል።

የኦሮሞ ሕዝብ ላገኘው ጸጋና በረከት፣ ሰላምና ደስታ፣ ጤናና ዕድሜ፣ ፍቅርና ክብር ለሚያምንበት አንድ ዋቃ (አምላክ) ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ላይ አንድ ዓለም አቀፍ ቱሪስት ሲታደም፤ ከዘመን ወደ ዘመን ከአንድ ወቅት ወደ ሌላ ወቅት በሰላም ያሸጋገረውን አምላኩን የሚያመሰግንበትና መጪውን ዘመን የሰላም የደስታ እንዲሆንለት የሚለምንበት ሥርዓተ በዓል ተመልክቶ ያንን ልምድ አግኝቶና አድንቆ መመለስ ያስችለዋል።

“ኢሬቻ በአዲስ አበባ፣ በዙሪያውም ይሁን በቢሾፍቱ ከተማ ሲከበር ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ሊጎበኙ የሚችሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች እግረ መንገድ መመልከት ይቻላል” የሚሉት የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የሀብት ማሰባሰብና ፈንድ ዳይሬክተሩ አቶ ሂክሰን ደበሌ፤ እንደ ቱሪዝም ተቋም እነዚህ ሥፍራዎች በማስተዋወቅ ከበዓሉ ጎን ለጎን የማስተዋወቅ ኃላፊነትን ወስደው እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ ባሻገር ትላልቅ አቅም መፍጠር የሚችሉና መዋለ ንዋያቸውን በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ላይ ማዋል የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንም ይሁኑ የውጭ ዜጎች እግረ መንገዳቸውን ይህንን እድል መመልከት እንዲችሉ አጋጣሚውን ተጠቅሞ የማስተዋወቅ ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም ይገልፃሉ። ቱሪስቱ ኢሬቻ በዓል ላይ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ዙሪያና በመላው ኦሮሚያ ያሉ የቱሪስት መስህቦችን መመልከት እንዲችልም እድሉ እንደተመቻቸ ያስረዳሉ።

በኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ ከሚታዩ ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የማህበረሰቡን ባህላዊ እሴት የሚያሳዩ አልባሳት፣ ጌጣጌጦችና ተጨማሪ የቱሪዝም ምርቶችን ማግኘት መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ እነዚህ ምርቶች በበዓሉ ላይ የሚሳተፈው የኦሮሞ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች በቀላሉ እንዲያገኟቸው እድሉ እንደተፈጠረ ይናገራሉ። በተለይ የቱሪዝም ምርቶችን በባህላዊና ዘመናዊ መልኩ በማዘጋጀት የኦሮሞን ባህልና እሴት የሚያሳዩ ሥራ ፈጣሪዎች ኢሬቻ ልዩ የገበያ እድል እንደሚከፍትላቸውና የቱሪዝም በጎ የኢኮኖሚ ተፅእኖም እግረ መንገድ የሚታይበት መሆኑን ያስረዳሉ። በተጨማሪ የቱሪዝም ኮሚሽን ከሆቴሎች እና ልዩ ልዩ የሆስፒታሊቲ ዘርፍ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር ቅንጅት በመፍጠር ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችና ከውጭ የሚገቡ ጎብኚዎች በተሻለ መስተንግዶ አቀባበል እንዲደረግላቸው መሥራቱን ይናገራሉ። እነዚህ ሥራዎች ለቀጣይ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምርና በኢኮኖሚው ላይ መነቃቃት እንዲፈጠር የራሱ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረውም ይገልፃሉ።

“የኢሬቻ ክብረ በዓል ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት መንሸራሸር እና የሥራ እድል የሚፈጠርበት ወቅት ነው” የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በበዓሉ ወቅት አንድ ሰው በዝቅተኛ ስሌት ኢሬቻን አንድ ሺህ ብር አውጥቶ ቢያከብር ‘በዓሉ ላይ የሚታደመው ሰው ሁለት ሚሊዮን ነው’ የሚል እሳቤ ቢኖር በትንሹ ሁለት ቢሊዮን ብር በክብረ በዓሉ ወቅት ብቻ በኢኮኖሚው ላይ ፈሰስ ይሆናል። በዚህ ስሌት ብቻ በዓሉ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳን አጉልቶ የሚያሳይ ነው። በተጨማሪ ከተለያዩ ዓለም ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ቱሪስቶች የጊዜ ቆይታ የሚኖረው የኢኮኖሚ ፋይዳ በተመሳሳይ የላቀ ነው።

እንደ መውጫ

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ የጋራ ባህሉንና ታሪኩን፣ አንድነቱንና ወንድማማችነቱን የሚገልጽበት የሚያድስበትና የሚያጠናክርበት መድረክ ነው። የጾታ የፖለቲካ አመለካከትና የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድበው የማንነቱ መገለጫ ባህሉን ታሪኩን የሚያስታውስበትና የሚዘክርበት በዓል ነው። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚከበሩት ሃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ የሕዝብ-በዓላት መካከል በአሳታፊነቱ የሚጠቀስ ነው። በዚህ ረገድ ከማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርስ የአንድ ሕዝብ ማንነት መገለጫ ለመሆኑ ኢሬቻ ህያው ማረጋገጫ ነው ሊባል ይቻላል።

የኢሬቻ በዓል በተለያዩ ቦታዎች የሚከበር ቢሆንም ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት የኦሮሞ ሕዝብ አንድ ላይ ሆኖ በጋራ የሚያከብረው በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሳዲ (አርሳዲ ሐይቅ) ላይ ነው። በሆራ አርሳዲ ላይ በሚከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ ከመላው ኦሮሚያ ከሁለት እስከ አምስት ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ ይሳተፋል። ወንድ ሴት፣ ሕጻን ሽማግሌ ሳይል፣ የፖለቲካ አመለካከትና የሃይማኖት ልዩነት ሳይወስነው፣ ጊዜና የቦታ ርቀት ሳያግደው በደቡብ ከቦረናና ከጉጂ በሰሜን እስከ ራያ፣ ከሐረርጌ እስከ ምዕራብ ቄለም ኢሉባቦራ ከዚያም ባሻገር እስከ ወንበራ ድረስ ያሉት የኦሮሞ ሕዝብ የሚሳተፍበት ታላቅ በዓል ነው።

በወርሀ መስከረም የመጨረሻ ሳምንት ውስጥ በሚከበረው የሆሬ ኢሬቻ በዓል የሁሉም ኦሮሞ ሕዝብ ትኩረት ነው። በዚህ ወቅት መንገዶች ሁሉ ወደቢሾፍቱ ያመራሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሚሊዮን የሚሆን የተለያየ ሃይማኖት የሚከተል ሕዝብ ለአንድ ዓላማ ለአንድ በዓል በአንድ ጊዜ ወደ አንድ መዳረሻ የሚጓጓዝበት ብቸኛ ክስተት ነው።

ይህ በሀገሪቱ ውስጥ በአንድ የተወሰነ ወቅት የሚደረግ የሕዝብ ጉዞ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም (domestic tourism) አንዱ ገጽታ ነው። በሚደረገውም እንቅስቃሴ እጅግ ብዙ ገንዘብ በኢኮኖሚ ውስጥ ይዘዋወራል። በዚህ ያገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴ ከተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖችና ከሌሎች ክልሎች በዓሉን ለማክበር ሲንቀሳቀሱ ለትራንስፖርት ለምግብ ለመጠጥና ለተለያዩ መዝናኛዎች የሚያወጡት ገንዘብ በቢሊየን የሚቆጠር እንደሚሆን መገመት አያዳግትም።

የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የሃብት ማሰባሰብና ፈንድ ዳይሬክተር ከሰጡን ግምታዊ ምሳሌ በተጨማሪ የራሳችንን ስሌት ብንወስድ በበዓሉ ላይ የሚሳተፍ ሶስት ሚሊዮን ሕዝብ ለትራንስፖርት፣ ለምግብ፣ ለባህላዊ አልባሳትና ማጌጫ፣ ለመዝናኛ፣ ወዘተ እያንዳንዱ ሰው 1000 ብር በአማካይ ቢያወጣ በአጠቃላይ ሶስት ቢሊዮን ብር በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ፈሰስ እንደሆነ መረዳት እንችላለን። በዚህ ሁኔታ በዓሉ ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎችን የትራንስፖርት፣ የሆቴል፣ የዕደ-ጥበብ፣ የንግድና መሰል ተቋማትን ያነቃቃል። ይህ የገንዘብ ፍትሀዊ ሥርጭት (evenly distributed) ፋይዳ እንዳለውም መገንዘብ ይቻላል። በተለይ ከጥቃቅን አገልግሎት ሰጪዎች እስከ ትላልቅ ድርጅቶች ተካፋይ ስለሚሆኑበት የኢሬቻ ቱሪዝም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ያመለክታል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን መስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You