የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዳርት ቻምፒዮናን ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ ነው

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ዳርት ቻምፒዮና ለማዘጋጀት ጥረት እያደረገች መሆኑን የኢትዮጵያ ዳርት ፌዴሬሽን አስታውቋል። በዚህም ውድድር ኢትዮጵያን በመወከል በዓለም ዳርት ቻምፒዮና ሳይሳተፍ የቀረው ብሄራዊ ቡድን እንደሚሳተፍ ተገልጿል።

በአፍሪካ አህጉር ደረጃ የዳርት ካውንስል ባለመቋቋሙ የሀገራት ዳርት ቻምፒዮና ማካሄድ እንዳልተቻለ ይታወቃል። ባለፈው ዓመት የተደረገውን የካውንስል ምስረታ ተከትሎም ዘንድሮ የመጀመሪያ ጉባኤውን የሚያካሂድ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም በተወካይዋ በኩል እንደምትሳተፍ ተረጋግጧል። በካውንስሉ አለመኖር ምክንያት በአህጉሪቷ የግል ክፍት ውድድሮች ብቻ ሲደረጉ ቆይተዋል። አሁን ባለው ሁኔታም በአህጉር አቀፍ ደረጃ የዳርት ቻምፒዮናን ለማካሄድ በጉባኤው ይወሰናል ተብሎ ይጠበቃል። ይካሄዳሉ ተብሎ ከሚጠበቁት የዳርት ውድድሮች ደግሞ በየዞኑ የሚደረጉትን ቻምፒዮናዎች ያካትታል። ከእነዚህም ውስጥ የምስራቅና መካከለኛ አፍሪካ ዳርት ቻምፒዮና አንዱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም የመጀመሪያውን ውድድር ለማዘጋጀት ጥረት እያደረገች መሆኑን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በዴንማርክ አስተናግጅነት በተካሄደው የዓለም ዳርት ቻምፒዮና ለማሳተፍ ብሄራዊ ቡድኗን ስታዘጋጅ ብትቆይም ከቪዛ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በጊዜ ባለመጠናቀቃቸው ተሳትፎዋ መሰረዙ ይታወሳል። በወቅቱ ቡድኑ ከሁሉ ስፖርት በተደረገለት ድጋፍ በሆቴል ተሰባስቦ ዝግጅት ቢያደርግም የዴንማርክ ኤምባሲ ጊዜው አጭር በመሆኑና ከፍተኛ ወረፋ በመኖሩ ጉዳዩን መጨረስ እንደማይችል በማሳወቁ የኢትዮጵያ ተሳትፎ እውን ሊሆን አልቻለም። ሆኖም ለአዘጋጅነት ጥረት እየተደረገ ባለው የምስራቅ አፍሪካ ዳርት ቻምፒዮና እንዲሁም በሌሎች ውድድሮች ብሄራዊ ቡድኑ እንዲሳተፍ የማድረግ እድል ተፈጥሯል።

ለብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የትጥቅ ድጋፍ በማድረግ የተሻለ ዝግጅት ተደርጎ እንደነበረም ተጠቁሟል። ኢትዮጵያን በዓለም ዳርት ቻምፒዮና ለመወከል በ2015 ዓም ከተካሄደው የኢትዮጵያ ዳርት ቻምፒዮና የተመረጡ አራት ወንድና ሶስት ሴቶች በድምሩ 7 ስፖርተኞች ዝግጅታቸውን ሲያደርጉም ቆይተዋል። የኢትዮጵያ ዳርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ቢልልኝ መቆያ ብሄራዊ ቡድኑ በገጠመው ችግር ምክንያት በዓለም ቻምፒዮናው ባይሳተፍም የምስራቅ አፍሪካ ዳርት ቻምፒዮናን በማዘጋጀት እንዲወዳደር ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል። በዚህም የስፖርተኞቹ ሞራል እንደይነካ በቀጣይ በሚደረጉት ውድድሮች እንዲሳተፉም እድል ተሰጥቷል። በስፖርት ዓለም የቪዛ ጉዳይ የሚያጋጥም በመሆኑ ተስፋ መቁረጥ እንደማያስፈልግና ፌዴሬሽኑ በዓለምና አፍሪካ ውድድሮች እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

ውድድሩን ለማዘጋጀት ዩጋንዳ ከሚገኝ የግል ውድድሮች አዘጋጅ ጋር ግንኙነት ከተጀመረ መቆየቱን የጠቆሙት አቶ ቢልልኝ፤ የዴንማርኩ ተሳትፎ ባለመሳካቱ ለስፖርተኞቹ እድል ለመስጠት ለነዚህ አዘጋጆች ጥያቄ ቀርቦላቸው ደብዳቤ እንዲላክላቸው መጠየቃቸውንም ጠቅሰዋል። የውድድሩ አዘጋጆች የግብዣ ደብዳቤ ከተላከላቸው በኋላ በጥቅምት ወር መጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከባለ ድርሻ አካላትና ከፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ጋር ተነጋግሮ በቅርብ ጊዜ የአፍሪካ ውድድሮች በተለይ የምስራቅና መካከለኛ አፍሪካ ቻምፒዮና ይዘጋጃል። የአፍሪካ ዳርት ቻምፒዮናም ለመጀመሪያ ጊዜ በግብጽ አስተናጋጅነት ሊካሄድ እንደሚችል የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ ተሳትፎዋን እንደምታደርግ ጠቁመዋል።

የዳርት ስፖርት የቤት ውስጥ ውድድር በመሆኑ ምቹ የሆነ ሆቴል ተመርጦ ለዝግጅቱ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማሟላት ውድድሩ የሚዘጋጅም ይሆናል። የአፍሪካ ዳርት ካውንስል ባለፈው ዓመት በመቋቋሙ እስከ አሁን ውድድሮች እንዳልተደረጉና የዘንድሮ ጉባኤ ከተደረገና ከተጠናከረ በኋላ በአፍሪካ ደረጃ ውድድር እንደሚካሄድ አቶ ቢልልኝ ይገልጻሉ። የግል ክፍት ውድድሮች በየሀገሩ የሚካሄዱ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች በዩጋንዳና ኬንያ በተደረጉ የግል ውድድሮች መካፈል ችለዋል። ለዚህም ፌዴሬሽኑ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የምታደርገው ተሳትፎ ባይሳካም የምስራቅ አፍሪካን ውድድር ለማዘጋጀት ፌዴሬሽኑ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የዳርት ስፖርት በሁሉም ክልሎች የሚከወን ቢሆንም ከመንግስትና ከባለ ድርሻ አካለት የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛና እንደ ስፖርት የሚመለከቱት አካላት ጥቂት በመሆናቸውም ለስፖርቱ ዕድገት እንቅፋት ሆኗል። ዳርት የአእምሮ ብልጽግናን፣ እርግጠኝነትንና ትኩረትን የሚያሳድግ ስፖርት በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ስፖርቱ እንዲያድግ ትኩረት በመስጠት አጠናክሮ ይሰራል።

 ዓለማየሁ ግዛው

 አዲስ ዘመን መስከረም 22/2016

Recommended For You