አዲስ ዘመን ድሮ ዛሬም ተመዘው የማያልቁ ብዙ የትናንት ትውስታዎች አሉት። ከእነዚህም መካከል ለዛሬ ቆየት ያሉና በይዘታቸው ወጣ ያሉ አስገራሚ ክስተቶችን ከጋዜጣው የዘገባ ማህደሮች መዘን እናስታውሳለን። በአለቃው አይን ሚጥሚጣ ጨምሮ በጩቤ የወጋው ግለሰብ ለፍርድ ስለመቅረቡ፣ የተሰረቀ የበግ ስጋ የበሉት ግለሰቦች የተከተላቸውን መዘዝ፣ “የስም ነገር ሲነሳ” ከአድማስ ገጽ ልዩ እትም እንዲሁም ደግሞ ከዚህም ከዚያም የተወሰደች አንዲት ሃሳብ በማሳረጊያው ተካተዋል።
በአለቃው አይን ሚጥሚጣ ጨምሮ 5 ዓመት ተቀጣ
ደመወዝ አላስጨመርክልኝም፤ በየጊዜው ትጨቀጭቀኛለህ በማለት ቂም ወርሶ በአለቃው ሁለት አይን ውስጥ ሚጥሚጣ ጨምሮ በጩቤ የወጋው አባተ አካሉ በአምስት ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ትናንት ተፈረደበት።
ተከሳሹ ታህሳስ 10 ቀን 1963 ዓ.ም ከጠዋቱ 1 ሰዓት ላይ ከአለቃው አስቀድሞ ገብቶ እጅ እንደ መንሳት ሞክሮ፣ ሚጥሚጣ በወረቀት ጩቤና ቆንጨራ ይዞ ሚጥሚጣውን በአለቃው አይን ጨመረ። አለቃው ዓይናቸውን በሁለት እጃቸው ሲሸፍኑ፤ በጩቤ ከጀርባቸው ላይ ወግቶ ማቁሰሉን የቀረበበት የአቃቤ ሕግ ክሰ ያስረዳል።
አባተ ወንጀሉን የፈጸመው በመናገሻ አውራጃ አቃቂ በሰቃ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኢንዶ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ መስርያ ቤት ውስጥ ነው። አለቃውን አቶ ተስፋዬ በቀለን ለመግደል ሲሞክር የገላገሉትን አቶ ንጉሴ ለማን በጩቤ ከግራ ጭናቸው ላይ ማቁሰሉንና በሕዝብ መተባበር የተያዘ መሆኑን የአዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበበት የዓቃቤ ሕግ ክስ ይዘረዝራል።
ወንጀለኛው መጀመሪያ ፍርድ ቤት ሲቀርብ፤ጥፋተኛ አይደለሁም ወንጀሉንም አልፈጸምኩም በማለት ክዶ፤ ችሎቱ አቃቤ ሕግ በማስረጃ ስለተረጋገጠበትና በመከላከያ ስላልተደገፈ፤ጥፋተኛነቱ ተረጋግጦበት ቅጣቱ ተወስኖበት ወይኒ ቤት ገብቷል።
(አዲስ ዘመን መስከረም 4 1964 ዓ.ም)
መኪናዋ ስትጋጭ ነጂው በመስኮት ሾልኮ ሕይወቱ ዳነ
ኅዳር 16 ለ17 አጥብያ ከለሊቱ 6 ሰዓት ላይ በደብረዘይት መንገድ ከመሿለኪያ በታች ጆንዊሊያም ዳርሊን የተጋጩበት አውቶሞቢል መላ አካሏ ተንከታክቶ፤ ግንባሯ ወደ ኋላ ተመልሶ ሞተሯ ተበታትኖ ከአውራ መንገድ ላይ ተዝረክርኳል።
መኪናዋ ከቀኝ ወደ ግራ በመተጣጠፍ ከመሃል ጎዳናው የሚገኘውን የፍሎረሰንት መብራት መያዣ ምሰሶ ገጭታ ስታጎብጠው መላ አካሏ ተሰባብሮ የአንድ እግሯ ጎማ ከቀኝ ወደ ግራ 30 ሜትር ተሽከርክሮ ከጉድጉአድ ውስጥ ገብቷል።
በአሰቃቂ ሁኔታ በደረሰው አደጋ 29 ዓመት የሚሆነው እንግሊዛዊ መምህር ከፊት በደረሰው ቁጥር 21094 በሆነች አነስተኛ ሬኖ መኪና ከመብራት ምሰሶ ጋር በአደገኛ ሁኔታ ተጋጭታ ብትንትኗ ወጥቶ ከአገልግሎት ውጪ ስትሆን፤ በግጭት ምክንያት ወደኋላ ተስፈንጥሮ መስኮቱ ተከፍቶ ሲወድቅ ምንም የመቁሰል አደጋ ሳይደርስበት መዳኑ ታውቋል።
(አዲስ ዘመን ሕዳር 18 ቀን 1964ዓ.ም)
የተሰረቀ የበግ ስጋ የበሉት ሰዎች 500 ብር ተቀጡ
ደብረብርሃን (ኢ-ዜ-አ) ተሰርቆ የታረደ በግ ስጋውን ተመግበዋል ተብሎ ክስ በቀረበባቸው የወረዳው ምክትል ገዢና የወረዳው ፖሊሰ ጣቢያ ምክትል አዛዥ፤ እያንዳንዳቸው 500 ብር መቀጫ እንዲከፍሉ የተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ፈረደ።
በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የገንዘብና የእስራት ቅጣት የተበየነባቸው በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ጋዛት በሞረት ወረዳ የጅሑር ምክትል ወረዳ ገዥ የሆኑት አቶ ስሜ አልታዬና የዚሁ ምክትል ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ የሆኑት 50 አለቃ ነጋሽ ሀብተ ሚካኤል ናቸው።
በሁለቱም ተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስ እንደሚከተለው ግንቦት 8 ቀን 1962 ዓ.ም የአቶ ሸዋረጋ ተክሌ ንብረት የሆነ አንድ በግ ሙክት ተሰርቆ ሰው በማይኖርበት ወና ቤት ውስጥ እንደታረደ፤ በነጭ ለባሽ ወታደሮች መከታተል ተገኘ። ከዚያም የታረደው ሙክት ወደ ወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ተወስዶ በኢግዚቢትነት እንደተቀመጠ ሁለቱ ሰዎች ቆዳውን አስገፍፈው ስጋውን በመመገባቸው የወንጀሉን ምርመራ አደናቅፈዋል።
በቀረበው ክስ ምርመራው ተጣርቶ የሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ እንደየጥፋታቸው እያንዳንዳቸው 500 ብር መቀጫ እንዲከፍሉ ተበይኖባቸዋል። ነገር ግን ገንዘቡን ባይከፍሉ እያንዳንዳቸው በስድስት ወር እስራት እንዲቀጡ የተፈረደባቸው ሲሆን ገንዘቡን ባለመክፈላቸው ወደ ወይኒ ቤት መላካቸውን የአውራጃው ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ታደሰ አልቴ ገለጡ።
የስም ነገር ከተነሳ
በአንድ ወቅት በእሁድ የራዲዮ ፕሮግራም ሁለት ኢትዮጵያውያን ልጃቸውን አፍ ያስፈቱት በእንግሊዝኛ ቋንቋ መሆኑንና ስሙም ጆንሰን መባሉን ስንሰማ አንዳንዶቻችን አስገርሞናል። የራስን ንቆ የሰውን ማክበር መሰለንና።
በአንዳንድ አካባቢ የልጆች ስም ከአባት ስም ጋር እንዲገጥም ወይንም ደግሞ የአባትና የልጅ ተመሳሳይነት እንዲኖረው ሆኖ ይወጣል። ይህንን አይነቱን ለማየት ለወደፊቱ እንቃጠርና ለዛሬው የመንዞችን ስም አወጣጥ ለአይነት ያህል ላቅርብ።
ለወንድ- ሺናባቸው፣ አብጠው፣ አጋጨው፣ ደምለው፣ ጠምሰው፣ ውቃው፣ አምለው፣ ግፋው፣ ጨቡዴ፣ ጠፍሬ፣ አባርቄ፣ አጉኔ፣ አይተንፍሱ፣ ጭጭይበሉ፣ ይፍሩ፣ይሸበሩ፣ ይጨነቁ፣ ላንትይደሩ።
ለሴት- ይብረኩ፣ ይስገዱ፣ ውርጭአለቁ፣ አብረው ያምሹ፣ ይሰለፉ፣ ይሻሙ፣ ማን ከልክሎሽ፣ አንቺ አያህሎሽ፣ ሁሉግርጌሽ፣ እርገጭ ይጠለሉብሽ፣ ይዝበጡ።
(አዲስ ዘመን ጥቅምት 4 ቀን 1977ዓ.ም)
ከዚህም ከዚያም
“ጠረነ ተባዕት ለእንስት ጤንነት”
“ሴቶች የወንዶችን የአካል ጠረን ይላመዳሉ። መላመድ ብቻ ሳይሆን ከተባዕቱ አካል በተለይም ከብብት አከባቢ በላቦት ታጅቦ የሚወጣው ጠረን በሚተኙበት በሚተቃቀፉበትና በፍቅር ጭውውት ወቅት ሁሉ እየመነጨ ስለሚያውዳቸው ለዛውን ጠንቅቀው ያውቁታል። ማወቅ ብቻ ሳይሆን የተባውን ስሜታቸውን በማነቃቃት ወደ ፍትወት ይወስዳቸዋል።
የወንዶች የአካል ጠረን ጉልበት በዚህ ብቻ አይወሰንም። ሌላም ዓቢይ ጥቅም አለው… በማለት ወ/ሮ ዊኒፊሬድ ኮትለር የጠረንን ሚስጥራዊ ኃይል በዝርዝር የሚያትት ድርሳናቸውን ለአደባባይ አውለውት ተቀባይነት እያገኘ ነው።
(አዲስ ዘመን ሰኔ 7 ቀን 1979 ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2016