በዓለም ላይ በርካታ ታዋቂ ሞዴሎችን በሞዴሊንግ ሙያ ማፍራት ተችሏል:: በአገራችንም እንዲሁ በራሳቸው ጥረት ነጥረው የወጡ ሞዴሎች አሉ:: ከእነዚህም መካከል ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኙ እንደ ሊያ ከበደ፣ገሊላ በቀለ እና ሀያት አሕመድ ተጠቃሽ የሞዲሊንግ ሙያ ፍሬዎች ናቸው:: ዘርፉ አገርን በማስተዋወቅ ረገድ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ቢታወቅም፣ እንደ አገር ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራበት እምብዛም አይስተዋልም::
አሁን ላይ ግን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለውጦች እየታዩ ለመሆናቸው ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል:: ሙያው እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ እንዲሰጥ በማድረግ በርካታ ባለሙያዎችን ለማፍራት እየተደረገ ያለው ጥረት ለውጦች ለመኖራቸው ማሳያዎች ናቸው:: በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም ወንዶችም እየተሰማሩበት ያለ ሙያ እየሆነ መምጣቱ ደግሞ ሌላው ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል፤ እንዲያም ሆኖ ግን በሙያው ብዙ መስራት ያስፈልጋል::
በአሁኑ ወቅት በሞዴሊንግ ሙያ እውቅና ካተረፉ የዓለም አገራት አልፎ አፍሪካውያን በሙያው ገብተው በደንብ እየሰሩበት ይገኛሉ:: የሞዴሊንግ ሙያ አገርን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ ጉልህ አበርክቶ ያለው እንደመሆኑ ብዙ መሰራት እንዳለበት የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ::
ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም በሙያው ተሰማርተው ዘርፉን ለማሳደግ የራሳቸውን ጥረት እያደረጉ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሞዴሎች አይታጡም:: ከእነዚህ መካከልም ሞዴል አብርሃም ዮሐንስ አንዱ ነው::
ሞዴል አብርሃም በሞዴሊንግ ኢትዮጵያን ወክሎ በበርካታ ዓለም አገራት ተወዳድሯል:: አሁን ላይ የተለያዩ ማስታወቂያዎች እየሰራ ይገኛል:: በርካታ የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችንም ሰርቷል:: ከ23 በላይ በሚሆኑ የተለያዩ የፋሽን ትርዒቶች ላይ ተሳትፏል:: በተጨማሪም ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በመሄድ ለሞዴሎች ትምህርትና ስልጠና ይሰጣል:: የአፍሮ ፊንገር ሜካፕና ሞዴሊንግ ስኩል መስራችና ባለቤትም ነው::
በሞዴሊንግ ሙያ ለ11 ዓመታት ያህል የሰራ ሲሆን፣ በሞዴሊንግ ውድድር ምስራቅ አፍሪካን ወክሎ በቤልጅየም በተካሄደ ውድድር አሸናፊ መሆኑን አጫውቶናል:: በዚህ የተነሳ በወቅቱ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና መጽሔቶች ላይ የመውጣት እድል አግኝቷል:: ከእነዚህ ውስጥ ‹ቢቢሲ› እና ‹አፍሪካን ፋሽን ኔትወርክ› በተሰኙ መጽሔቶች ላይ ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት እንደነበር ያስታውሳል::
ሞዴል አብርሃም፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ያጠናው የትምህርት ዘርፍ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ቢሆንም፣ የሞዴሊንግ ሙያ ውስጣዊ ፍላጎቱ አሸንፎታል፤ ወደ ሙያው ለመግባት ምክንያቱም ይሄው ሆኗል:: ከሲቪል ኢንጀነሪንግ ትምህርቱ በተጨማሪ ሌሎች ተያያዥ ኮርሶችን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ይውሰድ እንጂ የነፍስ ጥሪው ግን የሞዴሊንግ ሙያ እንዲሆን የግድ ብሎታል::
‹‹የሞዴሊንግ ሙያ ከተመረኩበት የሲቪል ኢንጂነሪንግ ትምህርትም ሆነ ከወሰድኳቸው አጫጭር ትምህርቶች ሁሉ በላይ ለሰው ልጆች አስፈላጊ ነው ብዬ እንዳምን አድርጎኛል›› ያለው ሞዴል አብርሃም፣ ወደ ሙያው ከገባ በኋላም የሰው ልጆች የሞዴሊንግን ሙያ መሠረታዊ እውቀት ቢያገኙ ለአኗኗራቸው የሚጠቅማቸው መሆኑን መገንዘብ ችያለሁ›› ይላል::
ሞዴል አብርሃም የብዙ ሙያዎች ባለቤት ነው፤ የፈጠራ ሥራዎችን ይሰራል:: በኮቪድ ወቅት የቫይረሱን መተላለፍ ሊቀንስ የሚችል የፈጠራ ሥራ ሰርቶም ነበር:: የፈጠራ ሥራው ጫማ ላይ የሚደረግ ሶል ሲሆን፣ ሰዎች ቫይረሱን ወደ ቤት ይዘው እንዳይገቡ የሚያደርግ ነው:: በዚህ የፈጠራ ሥራ ከአእምሮአዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የአእምሮ የፈጠራ ባለቤትነት መብት ማግኘቱን ይናገራል::
ሞዴሉ በቅርቡ ለአንድ ወር ያህል የአፍሪካ የፋሽን ከተማ በመባል ወደ ምትታወቀው ናይጄሪያ በመሄድ ለናይጀሪያ ሞዴሎች የሞዴሊንግ ስልጠና መስጠቱን ይናገራል:: ‹‹ፋሽን ኢንዱስትሪ ራሱን የቻለ ትልቅ ዘርፍ ነው:: በናይጄሪያም ሆነ በሌሎች የውጭ ሀገራት ያሰለጠንኳቸው ሞዴሎች ወደ ተለያዩ አውሮፖ ሀገራት ስማቸው ታዋቂ በሆኑ ትልልቅ ድርጅቶች በስም የሚሄዱ ናቸው:: እነዚህ ሞዴሎች ከኛ ሀገር ሞዴሎች የተሻለ ቁመና ወይም ተክለሰውነት ኖሯቸው አይደለም ከኛ ተሽለው የተገኙት፤ የተሻለ የተደራሽነት እድል የማግኘት አቅም ስላላቸው ብቻ ነው›› ሲል ያብራራል::
እነዚህ ሞዴሎች ወደ ሌላ ሀገር ሄደው ሰርተው የውጭ ምንዛሪ ይዘው እንዲመጡ ይደረጋል የሚለው ሞዴል አብረሃም፤ በእኛም ሀገር በሙያው ወደ ውጭ ሀገር ሄደው የሚሰሩበት ሁኔታ ቢመቻች የሚመለከታቸው ተቋማትና አካላት ድጋፍ ቢያደርጉ ሀገርን ማስተዋወቅ ይቻል ነበር›› ይላል:: ሞዴሊንግ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማምጣት የሚያስችል ሙያ መሆኑ ታውቆ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝቦ፤ ሙያው አንድ ሰው ሲታወቅ ማነው/ች? ከየት ነው የመጣው/ችው? የሚሉትን ነገሮች ሁሉ በደንብ በማስተዋወቅ ሀገር ማስተዋወቅ የሚቻልበት አንዱ መንገድ እንደሆነ ይናገራል::
‹‹ናይጄሪያ ለስልጠና በሄድኩበት ወወቅት ናይጄሪያውያን ኢትዮጵያን አያውቋትም›› ያለው ሞዴሉ፣ በሙያው እነሱ ሀገራቸውን ለማስተዋወቅ በደንብ እንደተጠቀሙበት ይናገራል:: ‹‹እኛ ግን ምንም እንደሌለን ዝም ማለታችን የሚያስቆጭ ነው::›› ይላል::
በሙዚቃ፣ በስፖርት፣ በፋሽን ዘርፍ ቢሰራ ሀገር ከማስተዋወቅ ባሻገር የውጭ ምንዛሪ ለሀገር ማምጣት ይቻላል፤ ድጋፍ ቢደረግ ከዚህ የተሻለ ሥራ መስራት ይቻላል:: በተለይ ደግሞ ሞዴሎች ወደ ውጭ አገራት በመሄድ እንዲሰሩ ቢደረግ አገርን ከማስተዋወቅ አንጻር በጣም ብዙ ሥራ መስራት እንደሚቻል አብራርቷል::
ሞዴል አብርሃም እንዳለው፤ በአገሪቱ ብዙ የሞዴሊንግ ተቋማት ቢኖሩም፣ ብዙ ሞዴሎች ከአገር ውጭ ወጥተው አገራቸውን እንዲያስተዋወቁ ማድረግ የሚችል እውቀትና ክህሎት እያላቸው ካላቸው አቅም አንጻር ይህንን ለማድረግ
እየቻሉ አይደለም:: ለሞዴሎቹ ከሚሰጡት ትምህርቶች መካከል በሙያው እንዴት ወደ ውጭ ሀገር ሄደው መስራት እንደሚችሉ፣ እንዴት ሙያውን ወደ ቢዝነስ መለወጥ እንደሚችሉ መሆኑን ይገልጻል::
ከአፍሮ ፊገር ሜካፕና ሞዴሊንግ ተማሪዎች መካከል በሞዴሊንግ ሙያ አንድ ተማሪ ውጭ ሀገር ሄዶ ተወዳድሮ አሸንፎ መምጣቱን በአብነት ጠቅሷል:: ‹‹እንደ ተቋም ለተማሪው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና እገዛ አድርገንለታል:: ሙያውን ለመማር ወደ ተቋማችን የሚመጡ ተማሪዎች በቂ እውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው ለማድረግ በጣም ብዙ ሥራዎች በመስራት ጥረት እናደርጋለን:: የሚለው ሞዴል አብርሃም፤ ተማሪዎቹ ላይ ሰፊ ሥራ በመሥራት ውጤታማ እንዲሆኑ እየሠሩ መሆኑን አመላክቷል::
በሞዴሊንግ ዘርፍ እጅግ ጥቂትና በጣት የሚቆጠሩ ባለሙያዎች ያሉበት እንደሆነ ያነሳው ሞዴል አብርሃም፤ እነዚህ ባለሙያዎች ተባብረው አንድ ላይ መስራት እንዳለባቸው ይናገራል:: አዲስ አበባ ውስጥ የሚሰሩ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት በጣም ብዙ ጥሩ አማራጮች እንዳላቸው ጠቅሶ፣ እነዚህ ግለሰቦችና ተቋማት በተለያየ አጋጣሚ ሀገራቸውን ማስተዋወቅ እንዳለባቸው አስገንዝቧል:: ብዙ ሞዴሎችን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ሀገሪቱን በማስተዋወቅ በሥራዎቻቸው ጎልተው እንዲወጡ ማድረግ እንደሚቻልም አመላክቷል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም