ትምህርት ቤቶችን የማደስ ትሩፋት

በሕይወት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ “ውበት ነው። ውበት ስንል ቁንጅና ማለት አይደለም። ቁንጅና የተፈጥሮ ጉዳይ ነው። የተፈጠረውን ጉዳይ በአግባቡ መያዝ፣ ንፅህናውን መጠበቅ፣ መንከባከብ፣ ለዓይን እንዲያምር ማድረግ፣ በአጠቃላይ አምስቱንም የስሜት ሕዋሳቶቻችንን እንዲያረካ ማድረግ ማለት ነው – ማስዋብ። በመሆኑም ማንነትን፣ ተፈጥሮን አጉልቶ ከማውጣት ጀምሮ፣ ፅዳትና ውበት፤ ወይም ማፅዳትና ማስዋብ ከዕለት ተዕለት ተግባሮቻችን መካከል ናቸው ማለት ነው።

ከተረትና ምሳሌያዊ አነጋገራችን እንኳን ብንነሳ፣ ከፍትፍቱ ፊቱ፣ ሲያዩት ያላማረ ሲበሉት ያቅራል – – – ወዘተ የሚሉት ሰፊ ቦታ ተሰጥቷቸውና በዕለት ተዕለት ኑሯችን ውስጥ ተገቢውን አገልግሎት ሲሰጡ ነው የምንመለከተው። ይህ የሚነግረን አቢይ ጉዳይ ቢኖር የአንድ ነገር ፋይዳ ወይም ጥቅም መመዘኛው ውስጡ ብቻ ሳይሆን ላዩም እንደ ሆነ ነው። የተያዘው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን መያዣውም ወሳኝ መሆኑን።

ነገሩን ሰፋና ዘርጠጥ አድርገን እንየው ከተባለ ጉዳዩ ብዙ የሚያነጋግር ሲሆን፣ አንዱም አብዛኞቹ ነገሮቻችን ፅዳትና ውበትን አብዝተው የሚፈልጉ መሆናቸው ነው።

መንገዶቻችን ፅዳትና ውበት ይጎድላቸዋል፤ በመሆኑም ፅዳትና ውበት ያስፈልጋቸዋል። ከመኖሪያ ቤታችን ጀምሮ አካባቢዎቻችን ሁሉ ፅዳትና ውበትን የተራቡ ናቸውና ፅዳትና ውበት ያስፈልጋቸዋል፤ ጣራ ግድግዳዎቻችን ሁሉ፣ ሆቴሎቻችን ሁሉ፣ መስሪያ ቤቶቻችን ሁሉ (አሁን እየተሰሩ ያሉ ስራዎች መኖራቸው እንዳለ ሆኖ) – – – ጥገና፣ እድሳት፣ ፅዳትና ውበት ያስፈልጋቸዋል።

እንደ ባህርይ ሆኖም ይሁን እንጃ፣ ብዙ ፅዳትና ውበት የሚያስፈልግ የሚመስለን እይታዊ (ውጫዊ) ለሆኑ ጉዳዮች ብቻ እስኪመስለን ድረስ ለመኪናችን የምንጨነቀውን ያህል፣ ለሰውነታችን አንጨነቅም። ለጫማችን የምንጨነቀውን ያህል ለካኒቴራችን አንጨነቅም፣ ወዘተርፈ። በመሆኑም ለእድሳት፣ ፅዳትና ውበት ብዙም ትኩረት ሳንሰጥ ቆይተናል። በትምህርት ቤቶችም የሚስተዋለው ይሄው ነበር።

ድሮ ድሮ፣ በንጉሱ ጊዜ፣ በሂደቱ ያለፉ አንጋፋውያን ሲናገሩ እንደሚሰማው በትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የሰውነት ንፅህና አጠባበቅ በየጊዜው በጤና ባለሙያዎች ይፈተሻል። ተማሪዎች ጠዋት ሰልፍ ላይ እያሉ፣ መዝሙር ሳይዘመርና ወደ ክፍል ሳይገባ፣ ኮሌታ ይታያል። በነጭ መሀረብ አንገት ይታሻል። ጥፍር ይታያል። ፀጉር (መበጠር አለመበጠሩ፣ መቀጨም አለመቀጨሙ – – -) ይጎበኛል። ጫማ (ከአስተሳሰር ጀምሮ) ይታያል። ሁለመናው (ዋ) ጥንቅቅ ያላለ (ች) ተማሪ ከተገኘ (ች) ቅጣቱ ከትምህርት ቤት እስከ መባረር ድረስ የዘለቀ ነበር። ዛሬስ? እንለፈው።

“ለውጥ በሚል ወደ ተግባር ከተገባ ወዲህ በየዘርፍና ሴክተር መስሪያ ቤቶች በርካታ ስራዎች እየተሰሩ የሚገኙ ሲሆን፣ አንዱም ፅዳትና ውበት ነው።

ቴሌ የዘንድሮውን “የበጎነት ቀንን አስመልክቶ በድረ ገፁ ላይ ባሰፈረው መልዕክት እንደገለፀው “ማሕበራዊ ፋይዳ ባላቸው ዘርፈ ብዙ ማሕበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ የበኩሉን መልካም አሻራ እያሳረፈ ሲሆን፣ በተለይም የሕብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ተጠቃሚነት ማጠናከር በሚችሉ እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማት እና ማስዋብ በመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ላይ በስፋት የተሳተፈ ሲሆን፤ ለዚህም “በድምሩ 439.9 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡ ይህ የሚያሳየን ሴክተር መስሪያ ቤቶች አካባቢን፣ ተቋማትን – – – የማስዋብ ጠቀሜታን የተረዱ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን፤ በተለይ የትምህርት ተቋማትን ማደስና ማስዋብ ላይ የሚጠበቅባቸውን እያበረከቱ መሆኑን ነው።

ጉዳዩ በቀጥታ ወደሚመለከተው ትምህርት ሴክተር እንምጣ።

በወቅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን በላይ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ26 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ቤት ውጪ በማድረግ እቤት እንዲውሉ ያደረገው ኮቪድ-19 መከሰትን ተከትሎ፣ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ሲመለሱ ዳግም በወረርሽኙ እንዳይጠቁ (ወረርሽኙን ለመከላከል) “ወረርሽኙን እንከላከላለን፣ እየተከላከልን እናስተምራለን በሚል መሪ ቃል የትምህርት ተቋማት ወደ ስራ መገባታቸው ይታወሳል።

አስፈላጊ ግብአቶችን በማሟላት፣ ማለትም ውኃ እንዲኖር የማድረግ (የውኃ ማጠራቀሚያ ታንከር በመግዛትና ውኃ በሌለባቸው አካባቢዎች የክረምት ውኃን የመያዝ)፣ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን፣ ወንበር እና ጠረጴዛ የማሟላት ሥራዎች፣ የንጽህና መጠበቂያ አቅርቦቶችን የማሟላት ሥራ በማከናወን ወረርሽኙን ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ እንደ ነበር የሚዘነጋ አይደለም (በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሁሉ በተሳተፉበት ሁኔታ)። አንዳንድ ተቋማት በዛው በመቀጠል ተቋማቸውን ማስዋብና ለስራ ምቹ እና ማራኪ፤ እንዲሁም፣ ተስማሚ የእውቀት መገብያ ስፍራ እንዲሆኑ፤ ተቋማቱ ግቡ ግቡ እንጂ ውጡ ውጡ – – – የሚሉ እንዳይሆኑ ማድረጉን እንደተያያዙት ለማየት ተችሏል።

ትምህርት ሚኒስቴርም ይህንኑ ለውጥ ተከትሎ እያከናወናቸው ካሉት ተግባራት አንዱ የትምህርት ተቋማትን (ት/ቤቶችን) ማስዋብ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። የመንግሥትም ሆኑ የግል ትምህርት ቤቶች ይህንኑ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን አቅጣጫ በመከተል ትምህርት ቤቶችን የማደስና ማስዋብ ስራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውም ግልፅ ነው።

ነሐሴ 25 ቀን 2015 ዓ∙ም የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ የአዲሱን ዓመት (2016 ዓ∙ም) የትምህርት አጀማመር ዝግጅት አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት ይህ የትምህርት ተቋማትን የማደስና ማስዋብ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

“ለእድሳትና ማስዋብ እየተባለ ከሕዝብ እየተሰበሰበ ያለው ገንዘብ በትክክል ስራ ላይ ስለመዋሉና ቀደም ሲል በሕዝብ ገንዘብ ሲመዘበር ከነበረው ጋር በማያያዝ የተጠየቁት ሚኒስትር ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ “መንግሥት (የሚመሩት ተቋም) ከማስተባበርና ምክረሀሳብ ከማቅረብ ውጪ ገንዘብ ውስጥ እጁን አያስገባም። ሁሉም ነገር እዛው አካባቢው ማሕበረሰብ ጋ ነው የሚያልቀው። በአካባቢው ሕብረተሰብ የተመረጡ ኮሚቴዎች አሉ። ሁሉንም ነገር እነሱ ናቸው እያከናወኑ ያሉት። በዚህ በኩል ምንም የሚያሳስብ ነገር የለም። በማለት መልስ ሰጥተዋል።

ባለፈው ዓመት ተጀምሯል። አሁንም በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው። በሕዝቡ በኩል ያለው ተነሳሽነት ጥሩ ነው። በእኛ በኩል መደረግ ያለበትም ሁሉ ይደረጋል። ባጭሩ የትምህርት ተቋማትን የትምህርት ተቋማት (ትምህርት ቤት) የማድረጉ፤ የማደስ፣ ማፅዳትና ማስዋብ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ሲሉም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

የ2016 ዓ∙ም ትምህርት ቤቶች መከፈትን አስመልክተን ምን ያህል ዝግጅት እንዳደረጉ ካነጋገርናቸው የትምህርት አስተዳደር ሰዎች መካከል በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት እና አፀደ ህፃናት፣ የትምህርት ቤቱ መምህርና የመምህራን ልማት ምክትል ርዕሰ መምህር መስፍን ገብረእግዚአብሔር አንዱ ሲሆኑ፣ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረጋቸውን ከገለፁልን በኋላ፤ “ተማሪዎችን በጥሩ ሁኔታ ለመቀበል የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው።

በተለይም የትምህርት ቤቱን አጠቃላይ ሁኔታ መቀየርን በተመለከተ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ያሉ ሲሆን፣ አንዱም የመማሪያ ክፍሎችን ከማስዋብና ምቹ ከማድረግ ይጀምራል። በማለት ነግረውናል። እኛም በስፍራው ተገኝተን እንደተመለከትነው ሁሉ ነገር አልቆ የመማሪያ ክፍሎች ለእድሳት ዝግጁ ተደርገዋል። ጨረታውን ያሸነፈው አዳሽ ድርጅትም ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ስራ በመግባት ላይ ይገኛል።

ም/ር/መ/ር መስፍን እንደነገሩን ከሆነ ዘንድሮን ከአምናው ከሚለዩትም አንደኛው ይኸው የመማሪያ-ማስተማሪያን ስፍራ ምቹና ማራኪ ለማድረግ እየተሰራ ያለው ስራ ነው። ይህ ደግሞ ተማሪዎች ሲመጡ ልዩ ስሜትን እንደሚፈጥርባቸውና ከአምናው የበለጠ ዘንድሮ በትምህርታቸው ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

የፅዳትና ማስዋብ ጉዳይ ሲነሳ የተቋማት ውስጣዊ ገፅታና ይዞታ ብቻ አይደለም አብሮ መነሳት ያለበት። ውጫዊ ይዞታና ገፅታቸውም መታየት አለበት። ለምሳሌ አንድ የትምህርት ተቋም ጋ (አካባቢ) ምን ምን ጉዳዮች ይስተዋላሉ? ጫት ቤት ነው ያለው፣ መጠጥ ቤት ነው ያለው፣ ሙዚቃ ቤት ነው ያለው፣ ዘመን አመጣሹ ሺሻስ በአካባቢው አለ? የሚሉት መታየትና በማፅዳትና ማስዋብ ፕሮግራሙ አማካኝነት ከአካባቢው ሊፀዱና ሊወገዱ ይገባል ማለት ነው። በጉዳዩ ላይ ጠለቅ ብለው የሄዱት ሲናገሩ እንደሚሰማው፣ እነዚህ ባሉበት፣ እንኳን የተሳካ የመማር-ማስተማር ተግባር፣ ምንም አይነት ጤና የለም።

አብዛኛውን ጊዜ የእንደዚህ አይነቱ ችግር ሰለባ ሆነው የምናገኛቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ሲሆኑ፣ በተለይ በክልሎች አካባቢ ያሉቱ ገና የመሰረት ድንጋይ ሲጣል የመሰረት ድንጋዮቻቸውን አብረው የጣሉ እስኪመስል ድረስ ተንሰራፍተው፤ የየካምፓሶቹን በር ግራና ቀኝ፣ እንዲሁም ፊት ለፊት መልህቃቸውን ጥለው እናገኛቸዋለን። በመሆኑም፣ የትምህርት ተቋማት እድሳት፣ ፅዳትና ማስዋብን አስመልክተን ስንነጋገር እነዚህንም ታሳቢ አድርገን መሆን አለበት። ይህንን ካላደረግን ያስዋብነውን የትምህርት ተቋም አካል ወደ ራሳቸው ጥቅም ይቀይሩትና የባሰ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ።

ከንፅህናና ውበት ባለፈ የበርካታ ትምህርት ቤቶቻችን ችግር ከአጥር ጋር የተያያዘ ሆኖ እንመለከታለን። አጥር የሌላቸው፣ ወይም ድክም ባሉ ቆርቆሮዎች የተጋረዱ፤ አልያም አጥራቸው (ግንባቸው) የተቦደሱ ትምህርት ቤቶች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።

በአንድ ወቅት ለስራ ጉዳይ ያነጋገርኳቸው፣ ወደ ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ የሚገኝ ትምህርት ቤት ርዕስ መምህር እንዳነገሩ (በወቅቱ ለንባብ በቅቷል) ትምህርት ቤታቸው አጥር የሌለው፣ የነበረውም የፈረሰ በመሆኑ ብቻ ወላጆች ከዛ ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን በማስወጣት ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ወስደው ያስገቡ ነበር። ከታጠረ በኋላ ግን ያ ሁኔታ በጣም ተሻሽሏል። ልጆቹም ትምህርታቸው ላይ ማተኮር ጀምረዋል። የዲስፕሊን ሁኔታውም ተለውጧል። ይህ የሚነግረን በትምህርት ቤቶች እድሳትና ማስዋብ ወቅት አጥርም ልዩ ትኩረትን የሚሻ መሆኑን ነውና ሊታሰብበት ይገባል ማለት ነው።

ከዚሁ ከእድሳት ጋር በተያያዘ የመፀዳጃ ቤቶች ጉዳይ ሊታሰብባቸው ከሚገቡት ተግባራት መካከል አንዱ ሲሆን፣ በተለይም የአካታችነቱ ጉዳይ ከምንም በላይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

በትምህርት ቤቶች አካባቢ የመፀዳጃ ቤቶች አካታች ሆኖ አለመገኘት በሚያስጨንቅ መልኩ ስሜትን የሚነካ ሲሆን፣ በዚሁ በእድሳትና ማስዋብ ፕሮግራሙ መፍትሄ ያገኛል፤ በግልፅ ቋንቋ የትምህርት ተቋማት መፀዳጃ ቤቶች ሁሉም የሚስተናገድባቸው ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከማጠቃለላችን በፊት፣ የትምህርት ተቋማት (ትምህርት ቤቶች) ጉዳይ ሲነሳ በርካታ ጉዳዮች አብረው እንደሚነሱ ይታወቃል። ስለተሳካ የትምህርት ውጤት ሲታሰብ ከተማሪው፣ መምህር ጀምሮ እስከ የትምህርት ግብዓት ድረስ ያሉት ሁሉ እንደሚነሱ ግልፅ ነው። ድሮም መኖር ነበረበት መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ ዛሬ ደግሞ ትምህርት ቤቶችን ማደስ እና ማስዋብ እንደ አንድ አቢይ ተግባር ሆኖ፣ በጀት ተይዞለትና በእቅድ እየተመራ ብቅ ብሏል። መሆን ያለበት በመሆኑ ትክክል ነው። ተጠናክሮም ሊቀጥል ይገባዋል የሚለው የሚያበረታታ ነው።

በመጨረሻም፣ በተደረጉ ጥናቶች ሁሉ እንደ ተረጋገጠው፣ ከግል ልምድም ይሁን ምልከታ መገንዘብ እንደሚቻለው የትምህርት ተቋማት ውብ እና ማራኪ መሆን ለተሻለ የመማር-ማስተማር ተግባራት የሚያደርገው አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ነው። ለተማሪዎች የትምህርት አቀባበል የሚያደርገው ድጋፍ ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም። ለመምህራን አጠቃላይ እርካታ፣ የመንፈስ ተሀድሶና የተቋም ፍቅር መኖር የሚኖረው ድርሻ ጉልህ ነው። ለአካባቢው ማህበረሰብም የሚያጎናፅፈው እርካታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል። በመሆኑም፣ በድጋሚ፣ እየተካሄደ ያለው ትምህርት ቤቶችን የመጠገን፣ ማደስና ማስዋብ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እንላለን። የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላትም የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ሊያደርጉ ይገባል ስንል ጉዳዩን የተሻለ የመማር-ማስተማር አካባቢና የተሻለ ትውልድ ከመፍጠር አኳያ በማየት ነው።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You