የአደባባይ በዓላት አይነታቸው ብዙ ነው። መንፈሳዊ የሆኑ እንዳሉ ሁሉ፣ ዓለማዊ የሆኑም ሞልተዋል፤ ልዩነታቸው የሚታወቀው ሚዛን ላይ ሲቀመጡ ብቻ ነው።
በዓለማችን ላይ አገራት “ያደጉ” (የበለፀጉ) እና “በማደግ ላይ ያሉ” (በቅርብ ጊዜ ውስጥ እየተለወጠ ከመምጣቱ በፊት “ኋላ ቀር” ነበር የሚባሉት፤ በተለይ አፍሪካን ከ“ኋላ ቀር”ም ባለፈ “ጨለማይቱ አህጉር” (ዘ ብላክ ኮንቲኔንት) ሁሉ ይሏት እንደ ነበር ራሳቸው የፃፏቸው ታሪኮች ይናገራሉ) በሚሉ ምድቦች ስር ይወድቃሉ፤ ቢያንስ እስካሁን ያለው አፈራረጅ ይህ ነው።
ይህ አፈራረጅ የራሱ የሆኑና ስር የሰደዱ አጨቃጫቂ ጉዳዮች ያሉትና እጅግም ሊያነጋግር የሚችል ቢሆንም፣ የዛሬ አነሳሳችን ግን ሰሞኑን በደማቁ የተከበሩትን የአደባባይ በዓላት (ሮብ (መውሊድ) እና ሐሙስ (መስቀል)፤ እንዲሁም በሚቀጥሉት ቀናት የሚከበረውን እሬቻ የተንተራሰ ሲሆን፣ ከመንፈሳዊ አንድምታና ፋይዳቸው፣ ማህበረ-ባህላዊ እሴትነታቸው፤ እንዲሁም ድባብና ድምቀታቸው ባለፈ በአገር፣ አህጉርና ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እያጎናፀፉን ያሉትን ወግ ማእረጋት መዳሰስ በመሆኑ በዚሁ ላይ አተኩረን ሀሳብ እንለዋወጣለን።
እንደ መታደል ሆኖ እነዚያ “ኋላ ቀር”፣ “ጭለማ” የተባሉት አገርና አህጉራት በአደባባይ በዓላት የበለፀጉ ሲሆኑ፤ እንደ አለመታደል ሆኖ “የበለፀጉ”፣ “የተመነደጉ” – – – የተባሉት አገርና አህጉራት ግን ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መልኩ በአደባባባይ በዓላት የደኸዩ ናቸው።
“ጭለማ”ዎቹ አገራትና አህጉራት በመንፈሳዊ ሀብት (የአደባባይ በዓላት መንፈሳዊ ሀብት ናቸው) “የበለፀጉ” ሲሆኑ፤ አደጉ የተባሉቱ ከቁሳዊ ሀብት የዘለለ መንፈሳዊ ሀብቶችን ሊጎናፀፉ አልተቻላቸውም። “ለምን?” ከተባለ፣ መልሱ “ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም” ነው ሊሆን የሚችለው።
እርግጥ ነው፣ “የበለፀጉ” የተባሉቱ ካላደጉቱ በተሻለ የቁሳዊ ሀብት ባለቤቶች ናቸው፤ በተቃራኒው “ጭለማ”ዎቹ አገራትና አህጉራት በቁሳዊ ሀብት የደቀቁ ናቸው (“በገዛ እጃቸው ነው” የሚሉ መኖራቸው እንዳለ ሆኖ)። በተፈጥሮ ሀብት የደለቡ፣ የፈጣሪን ፀጋ የተላበሱቱ እነዚሁ “ኋላ ቀር” የተባሉቱ ሆነው ሳለ፣ በቁሳዊ ሀብት የደቀቁትም እነሱ መሆናቸው “ለሰሚ ግራ” የመሆኑን ጉዳይ ከራሳቸው በስተቀር ማንም ሊፈታው አይችልምና ወደ አደባባይ በዓላቶቻችን እንመለስ።
የአደባባይ በዓላት የሕዝብ በዓላት ናቸው። የአደባባይ በዓላት የጋራ እሴቶች ናቸው። የአደባባይ በዓላት የጋራ መድረኮች ናቸው። የአደባባይ በዓላት በጋራ የሚከበሩ በዓላት ናቸው። በኢትዮጵያ ሁኔታ፣ የአደባባይ በዓላት ኃይማኖታዊ መሰረት ያላቸው እንደ መሆናቸው መጠን ሲበዛ መንፈሳዊ ናቸው። ቱባ እሴት ናቸው። ከስርዓተ አከባበራቸው ጀምሮ በጥብቅ ዲስፕሊን ተጀምረው በዛው ጥብቅ ዲስፕሊን የሚጠናቀቁ ናቸው። የአደባባይ በዓላት ከ“የቤት ውስጥ በዓላት” (ፋሲካ፣ ገና፣ – – -) የተለዩ ሲሆን፣ ይህ ልዩነታቸውም እንደየ ስያሜያቸው የተለያየ፣ እንደየ ባህርያቸው የሚስተናገዱ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
የዚህ ጽሑፍ አቢይ ተግባር ሰሞኑን የተከበሩትን ሁለት ታላላቅ የአደባባይ በዓላት ውሎና የአከባበር ሁኔታቸውን ማብራራት ሳይሆን፣ እነዚህ ሁለቱና ሌሎችም (ጨምበላላ፣ ጊፋታ ወዘተ) ተደማምረው የአገራችንን ገፅታ ከመገንባትና ዓለም አቀፍ እውቅናን ከማስገኘት አኳያ የተጫወቱትን ሚና መግለፅ ነው።
ከላይ ለመጥቀስ እንደ ሞከርነው፣ ያደጉቱ አገራት በአደባባይ በዓላት ሳይሆን በኮሚቴ በተዘጋጁ ዝግጅቶች (ካርኒቫሎች፣ ኮንሰርቶች —) የደመቁ ሲሆን፣ ያላደጉቱ (ኋላ ቀሮች ተብዬዎቹ)፣ በተለይም አፍሪካ በአደባባይ በዓላት ያሸበረቁ ሆነው ስለመገኘታቸው የሁሉም የእለት ተእለት እማኝነት የተቸረው ጉዳይ ነው። ያደጉቱ በዓመት አንዴ በ“አዘጋጅ ኮሚቴ”ዎች ወይም ኢቨንት (ሁነት) አደራጆች አማካኝነት በተዘጋጁ ካርኒቫሎች (የ“carnival” አቻ የአማርኛ ቃል ለጊዜው አልመጣልኝም) ላይ አስረሽ ምችውን ሲያጧጡፉት ስለመኖራቸውም እንዲሁ በየጊዜው የምንመለከተው ፈንጠዝያ ነው።
ጉዳዩ “በእጅ የያዙት ወርቅ – – -” በመሆኑ ነው እንጂ፣ ከካርኒቫልና ኮንሰርት በላይ የሚያደምቁት፣ የሚያኮሩት፣ መንፈስን የሚያረኩት፤ ከሁሉም በላይ ለዓለም አደባባይ የሚያበቁት የአደባባይ በዓላት (ዝቅ ብለን እንደምናየው) ናቸው። የሚያሸልሙት፣ ገንዘብ የሚያስታቅፉት (በቱሪዝሙ ገፅታቸው)፣ ዓለም አቀፍ እውቅናን የሚያስገኙት፣ ለታሪክ ምስክርነት የሚበቁት ወዘተ እነዚሁ እየተነጋገርንባቸው ያሉት የአደባባይ በዓላት ናቸው።
በየዓመቱ ከነሐሴ 16 እስከ 18 ለሶስት ቀናት የሚከበረው፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ልጃገረዶች የሚሳተፉበት አሸንዳ /ሻደይ/ የተሰኘው የአደባባይ በዓል (በዛው በትግራይ አንዳንድ አካባቢዎች ሌላ ስያሜ ያለው ሲሆን፤ በአማራ፣ በተለይ በዋግ ህምራ በዓሉ ሻደይ በሚል ስያሜ ይጠራል። በራያ ደግሞ ሶለል ይባላል። በተለያየ ስያሜ ይጠራ እንጂ በዓሉ ተመሳሳይ ነው) አንዱ የአገራችን እሴትና የማንነታችን መገለጫ ነው።
በዩኔስኮ የማይጨበጥ የዓለም ቅርስነት ለመመዝገብ የበቁትንና ያልተመዘገቡትን የአደባባይ በዓላት ጨምሮ (ፊቼ ጨንበላላ፣ የገዳ ስርዓት መገለጫ፣ የዘመን መለወጫና የመመሰጋገኛ እለት የሆነው እሬቻ መልካ፣ ጥምቀት፣ ዳመራ፣ ፊቼ ጨንበላላ፣ እሬቻን የመሳሰሉ የአደባባይ በዓላቶቻችን) የማንነታችን መገለጫዎች ብቻ ሳይሆኑ የባህልና ታሪካችን አሻራዎችም ናቸውና በዓለም አደባባይ እኛን የመወከል፣ እኛን የማስተዋወቅ፣ እኛን ሆኖ ስለ እኛ የማውራት አቅማቸው ከከፍተኛ ነው።
ይህ ብቻም አይደለም፣ ቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተጠቅሞ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ቱሪስቶችን በመሳብ ከድህነት መላቀቅ እንደሚቻልም ይታወቃልና አለመስራታችን የጎዳን ከመሆኑ በስተቀር ተፈጥሮ ያጎደለችብን ነገር የለም።
የአደባባይ በዓላት በርካታ መሰረታዊ ፋይዳዎች ያሏቸው ሲሆን፣ በህዝብ ውስጥ ማህበራዊ ትስስር ከመፍጠር የማህበረሰብን አንድነት ከማጠናከር፤ ለአንድ አገር ኪነጥበብ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከማድረግ፤ ቅርስን ለዓለም ከማስተዋወቅ ወዘተ አኳያም የሚወዳደራቸው የለም። ወደ ካርኒቫል መለስ ብለን (ለንፅፅር ያመች ዘንድ) አንዳንድ ጉዳዮችን እናንሳ።
“ካርኒቫል“ን አስመልክተው ብ∙ነጋሽ የተባሉ ፀሀፊ “የአደባባይ በዓላት ለቱሪዝም” በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቁት ጽሑፋቸው ውስጥ የሚከተሉትን አገራት አስመልክተው ያሰፈሩት ሀሳብ የሚከተለውን ይመስላል (የብ∙ነጋሽ ጽሑፍ ችግር ለካርኒቫል ከእኛዎቹ የአደባባይ በዓላት ጋር እኩል ብያኔንና ደረጃን መስጠቱ ነው)።
የብራዚል የሪዮ ዲ ጄኔሮ የአደባባይ በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀዳሚነት ይቀምጣል። ይህ በዓል ከትንሳኤ በዓል 40 ቀናት ቀደም ብሎ የሚውል ሲሆን፣ በሪዮ ጎዳናዎች ላይ ለአራት ቀናት ያህል ነው የሚከበረው። በዓሉን ለመመልከት እስከ 2 ሚሊዮን ሰዎች ይገኛሉ። በበዓሉ ላይ ከ200 የሳምባ ዳንስ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡና በብዙ ሺህ የሚቀጠሩ ወጣት ዳንሰኞች፤ እንዲሁም ከአጎራባች አካባቢዎች የሚመጡ የጎዳና ሙዚቀኞች የዳንስና የሙዚቃ ትዕይንት ያቀርባሉ።
በአውሮፓ የእንግሊዝ፣ ለንደን፣ ኖቲንግ ሂል የአደባባይ በዓል ተጠቃሽ ነው። በዚህ የአደባባይ በዓል ላይ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎች ይታደማሉ። ከ50 ሺህ በላይ ዳንሰኞችና ሙዚቀኞች ትርኢት ያቀርቡበታል። በበዓሉ ላይ የተለያዩ የካሪቢያን ምግቦችም ለገበያ ይቀርባሉ። የጀርመን ኮሎኝ የአደባባይ በዓልም በአውሮፓ ተጠቃሽ ከሆኑት አንዱ ነው። በዚህ የአደባባይ በዓል ላይ ከአንድ ሚሊየን በላይ ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ሰዎች ይታደማሉ። ለስድስት ተከታታይ ቀናት በሚከበረው በዚህ አደባባይ በዓል ላይ ታዋቂ ግለሰቦችና ፖለቲከኞችም ይገኛሉ።
ከዚሁ ከአውሮፓ ሳንወጣ የፈረንሳይ ናይስ የአደባባይ በዓል ለ15 ቀናት የሚከበር ሲሆን በሚሊየን የሚቆጠሩ ታዳሚዎችና ከ1 ሺህ በላይ ሙዚቀኞች ይሳተፉበታል። በዚህ የአደባባይ በዓል ላይ ከ100ሺህ በላይ አበባዎች ይበተናሉ። የጣሊያን ቨኒስ ቬንዚያ የአደባባይ በዓል የጥምቀት በዓልን አስታኮ ይካሄዳል። በዚህ በዓል ላይ በ100ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉ ሲሆን ለሃያ ቀናት የሚከበር ነው።
(ከላይ ባቀረብናቸው የካርኒቫል የአደባባይ በዓላት አከባበር ሂደት አንባቢያን የኛ አይነቶቹን ሥነስርዓታት፣ ለምሳሌ “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበረው ጥምቀት ካህናት፣ ቀሳውስት፣ የሰንበት ተማሪዎች፣ ህጻናት፣ አዛውንትና ሌሎችም በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በአደባባይ ወጥተው በዓሉን በታላቅ ድምቀት ያከብሩታል። ታቦታቱ በዝማሬ ታጅበው ከመንበረ ክብራቸው ተነስተው ወደ ባሕረ ጥምቀቱ አምርተው ያድራሉ።” የሚል ጠብቀው ከሆነ ይቅርታ። ይህ በቅንፍ ያስቀመጥነው ሀሳባችንም በእኛዎቹ የአደባባባይ በዓላትና የበለፀጉት አገራት ካርኒቫሎች መካከል ያለውን ልዩነት በቀላሉ ለመረዳት ያገለግላል ብለን እናምናለን።)
ይህንን ጽሑፍ ይዘን ወደ እዚህ ገፅ እንድንመጣ ገፊ ምክንያት የሆኑን ከላይ የዘረዘርናቸው የአደባባይ በዓላቶቻችን ወይም የአደጉ አገራት ንብረት (አስረሽ ምችው፤ በነገራችን ላይ ትክክለኛው አገላለፅ “ሰረር አድርገሽ ምችው” ሲሆን፣ እሱም ሰፊና ጥልቅ የሆነ ታሪካዊ ዳራ ያለው ነው) የሆኑት ካርኒቫሎች አይደሉም፤ ይህንን ሀሳባችንን ይዘን ወደ እዚህ ገፅ እንድንመጣ ገፊ ምክንያት የሆነን የሰሞኑ የዩኔስኮ ዜና ሲሆን፣ እሱም በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶቻቸውን ያስመዘገቡ አገራትን ደረጃና ያስመዘገቧቸውን ቅርሶች ቁጥር ይፋ ማድረጉ ነው።
የዓለም ቅርሶችን እያጠና በሚዳሰሱና በማይዳሰሱ ዘርፎች መዝግቦ እውቅና የሚሰጠው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ሰሞኑን በድረ ገፁ ላይ ለንባብ እንዳበቃው የማይዳሰሱ ቅርሶቻቸውን በተቋሙ ካስመዘገቡ አገራት መካከል 10ሩን (ቶፕ ቴን) ያስታወቀ ሲሆን የመጀመሪያዋ አገር፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቅርስ ያስመዘገበች ሆና በመገኘት ዓለም እጁን አፉ ላይ እንዲጭን ማድረጉ ነው።
እዚህ ላይ የሚገርመው የኢትዮጵያ አንደኛ መሆን አይደለም፤ የሚደንቀው ሁሌም ስማቸው የሚነሳላቸውና የስልጣኔ የመጀመሪያው ረድፍ ላይ እንደ ሆኑ ተቆጥሮ ስማቸው የሚጠራው ከኢትዮጵያ ስር ሆነው መገኘታቸውን በየዩኔስኮ ይፋዊ ሰነድ (ሴፕቴምበር 20/2023) ላይ ማወጁ ነው።
በዚሁ እወጃ መሰረት፣ ኢትዮጵያ 11 ቅርሶችን በማስመዝገብ 1ኛ፣ ደቡብ አፍሪካ 12 (2ኛ)፣ ቱኒዚያ 9 (3ኛ)፣ – – – ግብፅ 8 (7ኛ) – – – (እያለ ይቀጥላል) መሆናቸው ታውቋል። በዚሁ ምክንያትም እነዚህ አገራት (በተለይም ኢትዮጵያ) የአለሙ መነጋገሪያ፣ የሰሞኑ አጀንዳ ለመሆን በቅተዋል። ታዲያ ከዚህ ወዲያ ምን አይነት ገፅታ ግንባታ አለ?
ከማጠቃለላችን በፊት (ጉዳዩን ከመስቀል በዓል ጋር አያይዘን ስንመለከተው ማለት ነው)፣ ዲ/ን ዶ/ር አክሊሉ ደበላ “የዐደባባይ በዓላት መንፈሳዊነትና ተግዳሮቶቻቸው” በሚል ርዕስ ስር ካሰፈሯቸው ሀሳቦች መካከል አንዱን እንጥቀስ።
እንደ ዲ/ን ዶ/ር አክሊሉ ደበላ አገላለፅ የአደባባይ በዓላት በሁለት የሚከፈሉ ሲሆን፣ “ዓበይትና ንዑሳን በዓላት ተብለው ይከፈላሉ። ዓበይት በዓላት የሚባሉት፡- መጋቢት ፳፱ የሚከበረው በዓለ ትስብእት (ጽንሰት)፣ ታኅሣሥ ፳፱ የሚከበረው በዓለ ልደት፣ ጥር ፲፩ የሚከበረው በዓለ ጥምቀት፣ ነሐሴ ፲፫ የሚከበረው በዓለ ደብረ ታቦር፣ በዓለ ሆሣዕና፣ በዓለ ስቅለት፣ በዓለ ትንሣኤ፣ በዓለ ዕርገትና በዓለ ጰራቅሊጦስ ናቸው። ንዑሳት በዓላት የሚባሉት ደግሞ፡- ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ፣ በዓለ ጌና (ታኅሣሥ ፳፰)፣ ግዝረት፣ ልደተ ስምዖን፣ ቃና ዘገሊላ፣ ደብረ ዘይትና መስቀል ናቸው። ከዓበይት በዓላት ውስጥ ደብረ ታቦርና ጥምቀት፣ እንዲሁም በንዑሳት በዓላት ውስጥ ደግሞ በዓለ ጌና፣ ቃና ዘገሊላ እና መስቀል በአደባባይ ከቅጥረ ቤተ ክርስቲያን ውጭ የሚከበሩ ናቸው።” የሌሎች ሀይማኖቶችንም እንዲሁ መረጃዎችን ስናገኝ የምናቀርብ ይሆናል።
በመጨረሻም፣ ፈጣሪ እስላም፣ ክርስቲያን ሳይል እኛ ኢትዮጵያውያንን ያላጎናፀፈን ፀጋ የለም፤ ያልሰጠን በረከት የለም፤ ያላንበሸበሸን ሀብትና ንብረት የለም። አያት ቅድመ አያቶቻችንም ያልሰሩት ስራ፣ ያላከናወኗቸው ተግባራት የሉም። ማከናወን ብቻም በእጃችን ቆጥረው ያላስረከቡን ስራዎቻቸው የሉም። በመሆኑም ገና ብዙ ብዙ በዩኔስኮ እናስመዘግባለን። አስመዝግበንም የመንፈሳዊና ቁሳዊ ተጠቃሚነታችንን የበለጠ እናረጋግጣለን። ለዚህ ሁሉ ግን አንዳንድ ወሳኝ ጉዳዮች እጅጉን ያስፈልጉናል – ሠላም !!! ፍቅር!!! ወንድማማችነት !!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 19 ቀን 2016 ዓ.ም