
ታይዋን በራሷ አቅም የሠራቻቸውን ባህር ሰርጓጅ መርከቦች ይፋ አደረገች።
የታይዋን ፕሬዚዳንት ሳይ ኢንዌን የደሴቷን የመከላከያ አቅም ያጠናክራሉ የተባሉትን ባህር ሰርጓጅ መርከቦች አስተዋውቀዋል።
ፕሬዚዳንቷ በይፋ ያስተዋወቋቸው ስምንት ባህር ሰርጓጅ መርከቦች በሁለት አመት ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገቡም ነው የተገለጸው። «ከዚህ በፊት በሀገር ቤት ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን መሥራት የማይቻል ይመስል ነበር፤ አሁን ግን በራሳችን አቅም ዲዛይን ተደርገው የተሠሩ መርከቦችን በዓይናችን መመልከት ችለናል» ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሳይ ኢንግዌን።
መርከቦቹን መሥራቱ የራሱ ፈተና ቢኖረውም የደሴቷን ራስን በመከላከያው ዘርፍ የመቻል ጥረት ለማሳካት መሰል እርምጃዎችን መውሰድ የግድ መሆኑንም ነው ያነሱት። ታይዋን በ1980ዎቹ ከኔዘርላንድስ የገዛቻቸውን ሁለት ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን የሚቀላቀሉት አዳዲሶቹ ታይዋን ሠራሽ መርከቦች የደሴቷን የባህር ኃይል ይበልጥ እንደሚያጠናክሩ ይጠበቃል።
ታይፒ የባህር ሰርጓጅ መርከቦቹን በመሥራት ረገድ ከተለያዩ ሀገራት ልምዶችን መቅሰሟን ብትገልጽም የትኞቹ ሀገራት ድጋፍ እንዳደረጉላት ግን አልጠቀሰችም። የታይዋን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሴፍ ው በታይፒ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከቻይና የሚደርሰው ጫና እየተበራከተ መሄዱንና የደሴቷን ወታደራዊ አቅም ማሳደጉ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
ታይዋንን እንደ ሉዓላዊ ሀገር በመቁጠር የመሣሪያ ሽያጭ ያጸደቀችው አሜሪካ የባህር ሰርጓጅ መርከቦቹ በይፋ ሲተዋወቁ ባለሥልጣኗን መላኳን ሬውተርስ አስነብቧል።
ታይፒ ሚሳኤል የሚታጠቁትን ባህር ሰርጓጅ መርከቦች ከ2025 ጀምሮ ወደ ሥራ ለማስገባት አቅዳለች። እያንዳንዳቸው 1 ነጥብ 53 ቢሊዮን ዶላር ያወጣሉ የተባሉት መርከቦች ጥቃት ለማድረስ የአሜሪካውን ሎክሄድ ማርቲን ኩባንያ ቴክኖሎጂ እንደሚጠቀሙ ተገልጿል።
ባህር ሰርጓጅ መርከቦቹ በቀጣይ ወር ሙከራ እንደሚያደርጉ የተገለጸ ሲሆን፥ ቤጂንግ እስካሁን ስለአዳዲሶቹ መርከቦች መግለጫ አላወጣችም። በተያያዘ ቻይና የሉዓላዊ ግዛቴ አካል ናት ወደምትላት ታይዋን በየዕለቱ የጦር ጄቶቿን እየላከች መሆኑን ታይፒ ገልጻለች ሲል የዘገበው አል ዓይን ኒውስ ነው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም