ወጣቶች በኢሬቻ በዓል

‹‹ወጣት የነብር ጣት›› የሚለው አባባል በምክንያት ነው፡፡ በጉልበትም፣በአዕምሮም ያለውን አቅም ለማሳየት ነው፡፡ ወጣትነት ሮጦ ማሸነፊያ ዕድሜ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ ነገሮች ይጠበቃል። ተምሮ እራስን በኑሮ ለመቀየር፣ሀገርምን ወደላቀ ደረጃ ለማሻገር የወጣትነት ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ይመከራል፡፡

‹‹ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ አየወጣም›› እንደሚባለው የወጣትነት ዕድሜን ጉልበት ማሳያ አድርጎ ለመጠቀም መሞከር የኋላ ኋላ የሚያስከትለውን ጉዳት ከወዲሁ ግንዛቤ መያዝም ሌላው ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ወጣትነት ላይ የተሠራ ጠንካራ መሠረት ለውጤት ያበቃል፡፡ በተበላሸ መስመር የተጓዘ ደግሞ ቀጣይ ኑሮውም የተበላሸ ይሆናል። ለዚህም ነው ወጣቶች የነገ መሠረታቸው እንዳይበላሽ ታላላቆች፣ምሁራን አበክረው ምክር የሚሰጡት፡፡

ወጣቶች ለነገሮች ችኩል በመሆናቸው፣ ዛሬ ሀገር ለማተራመስና ለእኩይ ተግባር ተኝተው የማያድሩ አንዳንዶች ወጣቶችን ለእኩይ ተግባራቸው ማስፈጻሚያ ሲጠቀሙባቸው ይስተዋላል፡፡ አስተዋይ የሆኑ ወጣቶች ግን ለራሳቸውም ለሀገርም በሚጠቅም ተግባር ላይ ተሰማርተው ሌላውንም ያድናሉ፡፡የሚፈለገውም እንዲህ ያለ ወጣት ነው፡፡

ወጣትነታቸውን በአግባቡ ተጠቅመው፤ የተማሩ፣ የሠሩ፣ ጥሪት የያዙ፣ ቤተሰብ የመሠረቱ ለሀገራቸው በሚችሉት ሁሉ አስተዋጽኦን ያበረከቱ ኋላ ማምሻ ዕድሜያቸው ላይ የዘሩትን የሚያጭዱ፣ አዝመራቸውን በጥሩ ሁኔታ የሚሰበስቡ ይሆናሉ፡፡ እንዲህ ያሉ የሀገር ባለውለታዎች ክብርና ሞገስ ያገኛሉ፡፡ ይዘከራሉ።ለተተኪ ትውልድም በአርአያነት ይጠቀሳሉ፡፡ ተሞክሮአቸውም ለተተኪው ትምህርት ይሆናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ ስማቸው ከፍ ብሎ የሚነሳ በተለያየ መንገድ ባለውለታዎችን አፍርታለች፡፡ ወጣትነት ይህ ሁሉ በረከቶች የሚገኝበት እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛት ከፍተኛውን ቁጥር የያዘው ወጣት ኃይል ነው፡፡ ይህ ኃይል በማኅበራዊ እሴት፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካው ከፍተኛ ለውጥ እንዲያመጣ ይጠበቃል፡፡ መንግሥት ይህ ኃይል በተለያየ አደረጃጀት ሆኖ እራሱንና ሀገሩን እንዲጠቅም የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱም አይዘነጋም፡፡ሆኖም ግን የሚፈለገውን ፍሬያማ ውጤት በማምጣት ደረጃ ብዙ ሥራ ይጠበቃል፡፡

ወጣቶች የልማትና የሰላም ሞተር የሆኑትን ያህል በትንሽ ነገር ስሜታዊ የሚሆኑበት አጋጣሚዎች የበዙ ናቸው፡፡ ጠያቂዎችም ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ላቀረቧቸው ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ታጋሽ አይደሉም፡፡ በዚህም ስህተት ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላል፡፡ ነገሮችን ከማመዛዘን ቁጣና ፀብን አማራጭ ያደርጋሉ፡፡እኩይ ተግባር ያላቸው አንዳንድ አካላትም እነዚህን ድክመቶቻቸውን በመጠቀም ለጥፋት መሥሪያቸው ያደርጓቸዋል፡፡

ወጣቶች በዕድሜያቸው ሊያገኟቸው የሚፈልጓቸውን ነገሮች ማሟላት የቻሉ እንደሚጠቀሙ መዘንጋት የለበትም፡፡ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ግን የሀገር አቅምና ከፍተኛ ቁጥር ካለው የወጣት ኃይል ጋር የተጣጣመ ነገር ለማድረግ አዳጋች ነው፡፡ ወጣቱ የሚፈልገውን የትምህርት ዓይነትና የሥራ ዕድል ተደራሽ ማድረግ በአቅም የሚወሰን በመሆኑ የተሟላ ምላሽ ላይገኝ ይችላል። በዚህም በወጣቱ ሁለተናዊ ተጠቃሚነት ላይ ክፍተቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡

ወጣቱ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሀገሩን ለጥቃት አሳልፎ የሚሰጥ እንዳልሆነ በተለያየ ጊዜ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የተነሱ ኃይሎች እንዳይሳካላቸው በመታገል በተግባር አሳይቷል፡፡ ኢትዮጵያ በሚጠራበት ሁሉ ‹ሆ› ብሎ የሚነሳ ወጣት ያላት መሆኗ ምስክር መጥራት አያሻም፡፡

እንዲህ ያለውን መልካም ወጣት ጭምር ለእኩይ ተግባራቸው ለመጠቀም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በተለይም ቀደም ብለን ባሳለፍነው የጥምቀት፣ አሁን ደግሞ ከፊታችን ለምናከብረው እሬቻና ሌሎችም የዓደባባይ በዓላትን ለመረበሽ መሠረት አድርገው ይንቀሳቀሳሉ፡፡

በነዚህ ወቅቶች ወጣቶች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ከአጓጉል ነገሮች እራሳቸውን በመጠበቅ፣ ለእኩይ ተግባራቸው መሣሪያ ሊያደርጓቸው የሚፈልጉ አካላትንም ፊት ነስተው፣ ለሀገራቸው ሰላም ዘብ መቆም ያለባቸው ጊዜ አሁን ነው። ለሀገራቸው ሰላም ዘብ መቆም መቻላቸው ደግሞ ለነገ እነሱነታቸው ብሎም በሀገራቸው ተከብረውና በአቅማቸው ሠርተው ከበሬታንም አትርፈው ለመኖር እርሾው የሚሠራው ዛሬ መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡

በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ባህላዊና ሃይማኖታዊ እንደምታውን ባልለቀቀ፣ ከእኛ እልፎ ለሌሎች ደስታን በሚፈጥር መልኩ ይከበር ዘንድ የወጣቶች ሰላም ወዳድነት አብሮ ተቀናጅቶ ለሰላም መሥራት ከምን ጊዜውም በላይ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም፡፡

በዋናነት ግን በኢትዮጵያ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ፤ በቢሾፍቱ ከተማ ደግሞ የሆራ ሃር-ሰዲ መስከረም 25 እና 26 ቅዳሜ እና እሁድ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በታደመበት በዓሉ ይከበራል። የኢሬቻ በዓል ላይ በሰላምና በፍቅር ለመታደም በመጠባበቅ ላይ ያሉትን ወጣቶች አነጋግረናል። ከዚያ በፊት ግን በዓሉን በተመለከተ ትንሽ ነገር እንበል።

ኢሬቻ ምንድን ነው?

ኢሬቻ የምስጋና በዓል ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ምድር እና ሰማይን ለፈጠረው ፈጣሪው ዋቃ ምስጋናውን ለማድረስ የኢሬቻ በዓልን ያከብራል ይላሉ የማኅበረሰቡ ባህላዊ መሪዎች። የኦሮሞ ሕዝብ ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ነው ኢሬቻ።

የኦሮሞ ታሪክ ምሁራን እንደሚሉት፤ «ኢሬቻ ማለት ዋቃ (ፈጣሪ) የፈጠረውን ማመስገን ማለት ነው»። በዓሉም ማኅበራዊ ደረጃ እና የዕድሜ ልዩነት ሳይፈጠር የኦሮሞ ሕዝብ የኢሬቻ በዓልን ለዘመናት በጋራ ሲያከብር ቆይቷል። ኢሬቻ የዘመን መለወጫ በዓልም ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በማለፉ በኢሬቻ ቀን ምስጋናውን ለፈጣሪ ያቀርባል።

በክረምት ወራት ተራርቆ ሳይገናኝ የቆየ ዘመድ አዝማድ መስከረም ላይ ይገናኛል። ሕዝቡም ክረምቱን በፈጣሪ ፍቃድ የሞላው ውሃ ጎድሎ ከዘመድ አዝማድ አገናኘን ብሎ ምስጋና ያቀርባል። ከጨለማ ወደ ብርሃን ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና ያቀርባል።

«ክረምት ሌሊት ነው። ሌሊት ደግሞ ጨለማ ነው። ጨለማ ለአውሬ እንጂ ለሰው ልጅ አይሆንም። ጨለማው ሲነጋ ደግሞ ብርሃን ነው፤ ብርሃን ሲሆን ሃሳብ የለም ደስታ ይሆናል። ‘መስከረም በረ’ባ ማለት ይህ ነው» በማለት የኦሮሞ ሕዝብ ከክረምት መገባደድ በኋላ የኢሬቻ በዓልን የሚያከብርበትን ምክንያት እነዚሁ ምሁራን ያስረዳሉ።

የኢሬቻ በዓልን ለማክበር የሚወጣ ታዳሚ እንደ ሳር ወይም አበባ ያለ እርጥብ ነገር በእጁ ይዞ መገኘቱም አንዱ መገለጫው ነው። «’ፈጣሪያችን ሆይ አንተ ያጸደቅከው ነው አብቦ ፍሬ ያፈራው፤ ለዚህም እናመስግንሃለን’ በማለት እርጥብ ነገር ተይዞ ይወጣል» ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ይናገራሉ።

ኢሬቻ ለሠላም እና እርቅ

በኢሬቻ በዓል ላይ የኦሮሞ ሕዝብ ለመላው የሰው ልጅ ሠላምና ደኅንነት ፈጣሪውን ዋቃን ይለምናል፤ ያመሰግናል። «የተጣላ ታርቆ፣ ቂሙን ትቶ በነፃ ልቦና ፈጣሪ ንጹህ ወዳደረገው የውሃ አካል ይሄዳል። ኢሬቻ ቀልብ የሚነጻበት ቦታ ነው» ስለመሆኑ ይገልጻሉ።

መልካ እና ቱሉ

የኢሬቻ በዓል ሁለት ጊዜ ይከበራል። እነዚህም የክረምት ወራት እንዳበቃ የሚከበረው ኢሬቻ መልካ (የውሃ አካል ዳርቻ የሚከበር) እና በዓመቱ አጋማሽ ላይ የሚከበረው ኢሬቻ ቱሉ (በተራራማ ቦታ) የሚከበሩ ናቸው።

የታሪክ ምሁራኑ ኢሬቻ መልካ የምስጋና በዓል ሲሆን ኢሬቻ ቱሉ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ፈጣሪውን የሚለምንበት በዓል ነው ይላሉ። «በበጋው የፀሐይ ሃሩር ሰው እና ከብት በሚቃጠልበት ጊዜ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ እንዲዘንብ የኦሮሞ ሕዝብ ወደ ተራራ ወጥቶ ፈጣሪውን ይለምናል። ተራራ ላይ ተወጥቶ ሲለምን ፈጣሪ ቶሎ ይሰማል የሚል እምነትም አለ» ይላሉ።

«ይህን ተራራ የፈጠርክ ፈጣሪ ወቅቱን የሠላም አድርግልን፣ የሠላም ዝናብ አዝንብልን፣ ጎርፍን ያዝልን፣ የተዘራው ፍሬ እንዲያፈራ እንለምንሃለን» እያለ በኢሬቻ ቱሉ ላይ ፈጣሪውን ይለምናል በማለት ምሁራኑ ያስረዳሉ።

ወጣት ድሪባ ደምሴ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖር የኦሮሞ ተወላጅ ሲሆን በጉጉት የሚጠብቀው የኢሬቻ በዓልም እየደረሰ በመሆኑ እጅግ መደሰቱን በመግለጽ ከሦስት ዓመት በፊት ሆራ ሀርሰዲ (ቢሾፍቱ) በመሄድ ያከብረው የነበረው በዓል አሁን ላይ በሚኖርበት ከተማ ላይ መከበሩ እጅግ እንዳስደሰተውም ይናገራል።

በዓላት ሁሉ ልዩ ናቸው፡፡ ኢሬቻ የምስጋና፣ የደስታ፣ የሰላም የፍቅር፣ ወር የአብሮነት በዓል ከመሆኑም በላይ የተነፋፈቁ ዘመዳሞች ጓደኞች የሚገናኙበት፣ወጣቶች የሚተጫጩበትና የነገውን ሀገር ገንቢ ቤተሰብ ለመመስረት ቃል የሚያስሩበት ልዩ ቀን ነው። የኦሮሞ ሕዝብም ይህንን በዓል ለዘመናት ተዋዶ በሠላምና በፍቅር ከመላው የኢትዮጵያ ልጆች ጋር ሲያከብር ቆይቷል፡፡ ወደፊትም ያከብራል ይላል።

ወጣት ድሪባ እንደሚለው አሁን ያለንበት ጊዜ እንደ ሀገር ብዙ ችግሮችና መከራዎች ያሉበት ቢሆንም፣ በዓሉን የሰላም እሴቶችን አጠናክሮ ለመቀጠል፣ የተጣላን ለማስታረቅ ሠላምና ፍቅርን የሚያጎለብቱ ሥራዎችንና ሀሳቦችን ለማመንጨትና ለመናገር ጥረት የሚደረግበት እንዲሆንም ፍላጎቱ መሆኑን ያብራራል።

‹‹ሀገራችን ላይ ብዙ ፍላጎቶች አሉ፡፡ እነዚህ ፍላጎቶች ደግሞ እንዲስተናገዱ የሚፈለገው ኢሬቻን በመሳሰሉ የአደባባይ በዓላት ላይ ወጣቶችን በመጠቀም ነው፡፡ ይህ ግን ፍጹም ስህተት የሆነ አካሄድ ከመሆኑም በላይ እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ የሚያስከፍለን ነው። እነዚህን የእኩይ ተግባር ነጋዴዎች ለመዋጋትና ሀሳባቸውን ውድቅ ለማድረግ ደግሞ ወጣቶች ትልቅ አቅም አለን›› በማለት ሃሳቡን ሰጥቷል።

ስሜትን ሳይሆን ሀገርን ማስቀደም እንደሚገባና በየአመቱ ተናፍቆ የሚመጣውን የኢሬቻ በዓል የእኩይ ነጋዴዎች መጠቀሚያ እንዳይሆን ወጣቱ ከምን ጊዜውም በላይ የነቃ ሊሆን እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

ወጣት አለማየሁ ሙለታ በበኩሉ ኢሬቻ ሁሌም ተናፋቂና በየዓመቱ ሲመጣም ዕድሜና ጾታ ሳይለይ ሁሉንም የሚያስደስት አንድነትና ፍቅር የሚጠነክርበት የሰላምና የምቾት በዓል ነው ይላል።

ወጣት አለማየሁ ‹‹ኢሬቻ ከዘመናት ናፍቆት በኋላ በምንኖርበት መዲና መከበሩ ብዙ ደስታን ፈጥሮልናል፡፡ በዓሉም የምስጋና እንደመሆኑ እኛም ለዚህ ነገር ባገኘነው አጋጣሚ እናመሰግናለን። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በዓሉ የሚጠይቀውን ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴት በሳተ መልኩ ፖለቲካዊ ይዘት ሲሰጠው ይታያል፡፡ ይህ ግን ፍጹም ኢሬቻን የማይገልጽ ከመሆኑም በላይ ሊታረም የሚገባው ነገር ነው›› ሲል ያስረዳል፡፡

‹‹ኢሬቻን ከእኛ በፊት ያሉ እናት አባቶቻችን እህት ወንድሞቻችን በጥሩና ሁኔታ በፍቅርና በሠላም ሲያከብሩት ኖረዋል›› አለማየሁ ምንም እንኳን የአሁኑ ትውልድም የእነሱን ፈለግ በመከተል በዓሉን እያከበረ ቢሆንም የእነሱን ያህል ግን ባህላዊ ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቋል ለማለት እንደሚቸገር ይናገራል፡፡ በዓሉ እንደቀደመው ጊዜ በብዙ ፍቅርና መተሳሰብ እንዲከበር ከወጣቶች ብዙ እንደሚጠበቅ ነው ያስረዳው፡፡

እንደ ኢሬቻ ዓይነት የአደባባይ በዓላት በተለይም የሀገርን ሠላምና አንድነት ለማወክ የሚፈልጉ አካላት መጠቀሚያ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው ያለው ወጣት አለማየሁ እነዚህ የችግር ቸርቻሪዎች ደግሞ በዋናነት መጠቀሚያ የሚያደርጉት ወጣቱን ኃይል እንደሆነ በመጥቀስ፣ ወጣቱ ለእኩይ ተግባራቸው ጆሮ ሳይሰጥና ሳያዳምጥ በዓሉ ከምን ጊዜውም በላይ በሠላምና በደስታ በፍቅር እንዲከበር የበኩሉን ማድረግ እንዳለበትም አመልክቷል።

‹‹በዓላት ምን ጊዜም ቢሆን የደስታና የፍቅር የሠላምና የአንድነት ናቸው። ነገር ግን አንዳንድ የጥፋት ኃይሎች እነዚህን መልካም እሴቶች ለእኩይ ተግባር ስለሚጠቀሙበት ከማንም በላይ ይህንን ሴራ በማክሸፍ የበዓላቱን ሠላማዊነት ሊያስጠብቁ የሚችሉት ደግሞ ወጣቶች ብቻ ናቸውና በዚህ ልክ ወጣቶች ወደራሳቸው በማየት በዓላቱ ሠላማዊ ሆነው እንዲጠናቀቁ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው›› ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

 እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን  መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You