ባህላዊ እሴቶቻችንን ጠብቀን ለቀጣይ ትውልድማስተላለፍ የሁላችንም ሃላፊነት ነው

በዓለም ላይ ታዋቂ ከሆኑ ተጓዦችና ይህንንም በተንቀሳቃሽ ምስል አማካይነት በማህበራዊ ድረገጾች ለተቀረው ዓለም በማጋራት ከሚታወቁት መካከል አንዱ የሆነው ዊሊያም ሶንባችነር (ሶኒ) የቅርብ ጊዜ መዳረሻው ኢትዮጵያ ነበረች። ይህ አሜሪካዊ የቀድሞ ፊልም ባለሙያ ትኩረቱን በምግብ፣ በመጠጥና አዘገጃጀቱ ላይ ያደረገ ‹‹ቤስት ኤቨር ፉድ ሪቪው ሾው›› በሚል የሚጠራ ድረገጽ አለው ፤ በዩቲዩብ ገጹ 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ተከታዮች አሉት።

በመላው ዓለም ባሉ ሀገራት በመዘዋወር ባህልን እና የባህል አመጋገብን ለሌሎች ያጋራል። በዚህም በአጠቃላይ 2 ነጥብ 29 ቢሊዮን እይታ ሲኖረው፤ እአአ በ2020 ከኢንተርኔት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ዕውቅና በሚሰጠው ‹‹ዌብ አዋርድስ›› የክብር ሽልማት ተበርክቶለታል። ታዲያ ይህ ተጓዥ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ እንዲሁም በደቡብ ክልሎች (ዶርዜ እና ኦሞ አካባቢዎች) በመዘዋወር የመልከዓምድር አቀማመጡን በወፍ በረር እያስቃኘ፤ በተገኘባቸው ሥፍራዎች ያለውን የምግብና መጠጥ አዘገጃጀት፣ አቀራረብ፣ አመጋገብ እንዲሁም የጉርሻ ባህላችንን ሳይቀር ተመልክቷል፣ ለተቀረው ዓለምም አስመልክቷል።

እንደዚህ ያሉና ትኩረታቸውን በመሰል ጉዳዮች ላይ ያደረጉ የባህል ተጓዦች (ጎብኚዎች) በተለያዩ ሀገራት በመገኘት መንፈሳዊም ሆኑ ሌሎች ባህላዊ በዓላትንና አከባበሮች ላይ ይታደማሉ። ማህበረሰቡ ውስጥ በመግባትም የአኗኗር ሥርዓቱንና ባህላዊ ክዋኔዎች ላይ ተሳትፎ በማድረግም ጭምር ዳሰሳ ያደርጋሉ፤ የተመለከቱንም ለሌሎች ያጋራሉ።

ሶኒ በሚል ቅጽል የሚታወቀው ይህ ተጓዥ በዩቲዩብ በመቶ ሺዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠር እይታ ያለው እንደመሆኑ፤ በመላው ዓለም ካለው ተደራሽነቱ አንጻር የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ባህል ምን ያህል ሊታይ እንደሚችል በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ኢትዮጵያን ከማስተዋወቅና መረጃ ከመስጠት ባለፈም በርካቶችን ሊያነሳሳና ኮምፓሳቸውን ወደ ምስራቅ አፍሪካ እንዲያቀኑ ሊያደርግ እንደሚችልም ግልጽ ነው።

ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ እጅግ እያደገ ያለ የቱሪዝም ዘርፍ ሀገርና ባህልን ከማስተዋወቅ ባለፈ ከጎብኚዎች የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የባህል መገኛ የሆኑ ሀገራት ባህላቸውን በመጎብኘት ለሚዝናኑ ጎብኚዎች ሳቢ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።

ከሌላው ዓለም የተለየ የቀንና የዓመት አቆጣጠር ያላት ኢትዮጵያ አዲስ ዓመቷን ተከትሎ እንደ መስቀል እና ኢሬቻ ያሉ ባህሎች በድምቀት ይከበሩባታል። ታዲያ ይህ አከባበር እንዲሁም በዓሉን ተከትሎ የሚከወኑ ባህላዊ ጉዳዮች ለጎብኚዎች የስበት ማዕከላት ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ፣ የባህል እና የትምህርት ድርጅትም (ዩኔስኮ) በዚሁ ምክንያት በዓላቱና ሥነሥርዓታቸው የኢትዮጵያውዊያን ብቻም ሳይሆኑ የዓለምም ብርቅዬ ቅርሶች ናቸው በሚል እንደመዘገባቸው ይታወቃል።

እነዚህ በዓላት እሴቶቻቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ማለትም መስቀል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው፤ ኢሬቻም የገዳ ሥርዓቱን ተከትሎ እንዲከበር የህብረተሰቡ አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው። በዓላቱ የአንድ ዕለት አከባበሮች ብቻ ሆነው አያልፉም፤ ይልቁንም በርካታ ኢትዮጵያዊ ጉዳዮችን በተግባር የሚያስቃኙ አለፍ ሲልም በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ የሚችሉ ናቸው።

ሃይማኖታዊ በዓል የሆነው መስቀል የዳመራ ሥነሥርዓቱ በአደባባይና በአጥቢያዎች የሚከወን እንደመሆኑ ከሃይማኖታዊ ጉዳይ ባለፈ የኢትዮጵያውያን አንድነትና አብሮነት የሚንጸባረቅበት መስታወት ነው። ባህላዊ አለባበሱ፣ አመጋገቡ፣ … ለጎብኚዎች አስደሳች የሆነ ትዕይንትም ነው። በዓሉ በተለይ በድምቀት በሚከበርባቸው የደቡብ፣ ሰሜንና ማዕከላዊ የሀገሪቷ ክፍሎች ቤተሰብ ተሰባስቦ ማክበሩ የግድ እንደመሆኑ ማህበረሰባዊ አብሮነትን ይፈጥራል። ይህንኑ ጊዜ ጠብቆ እንደ እርቅ እና ጋብቻ ያሉ ሥርዓቶች በስፋት ይከናወናሉ። ይኸም በሌላው ዓለም የሌለ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለመደ ባህላዊ ሁነት መሆኑ ጎብኚዎችን በእጅጉ ይስባል።

የአደባባይ በዓል የሆነው ኢሬቻም በተመሳሳይ፤ የኦሮሞ ህዝብን ብቻም ሳይሆን በርካቶችን ከሌሎች ብሄረሰቦችም ጭምር በማሰባሰብ አብሮነት በእጅጉ የሚንጸባረቅበት ነው። የገዳ ሥርዓት ከሚያዘው የበዓሉ አከባበር ባለፈ አንዱ ከሌላው የሚተዋወቅበት የባህል ፌስቲቫልም ጭምር ነው። በዓሉ በሚከወንበት ሥፍራ የሚገኝ የትኛውም ጎብኚ ኢትዮጵያ ያሏትንና በአዘቦት ጊዜያት ሊያገኛቸው የማችላቸውን ባህላዊ አለባበሶችን፣ ጌጦችን፣ የጸጉር አሠራርን፣ የባህል ቁሳቁስን፣ ሙዚቃ፣ አጨፋፈር፣… በስፋት ሊመለከት ይችላል። በሌላ አነጋገር ለዘመናት ሲገነቡ የኖሩትን የኢትዮጵያ ባህሎች በአንድ ቀን ለመመልከት ይችላል። ጎብኚዎችም ይህንን ዕድል ለመጠቀም እነዚህን ወቅቶች እንደሚመርጡ አስቀድሞ ስለበዓላቱ በቂ ግንዛቤ መያዝ ያስፈልጋል።

እነዚህን ባህላዊ ሁነቶች ኢኮኖሚ ፋይዳቸውን ከተመለከትንም ፤ የጎብኚዎች ማረፊያና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን የሚያቀርቡ ተቋማት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ሊገኝ እንደሚችል ማብራሪያ የማያሻው ጉዳይ ነው። ከዚህ ባለፈ ግን የበዓላቱ ታዳሚ ለመሆን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ጎብኚዎች የባህሉ አካል የመሆን ፍላጎት ስለሚያድርባቸው አልባሳቱን፣ ጎጣጌጦቹን እንዲሁም ሌሎች ኢትዮጵያን የሚያስታውሱ ቁሳቁሶችን የሚሸጡ አካላትም በገንዘብ ተጠቃሚ ያደርጋሉ። በዚህም ጎብኚዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚኖራቸውን ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው።

በመሆኑም መዳረሻቸው እንድንሆን ያደረጉትን እንዲሁም የዓለም ቅርስ በሚል ተመዝግበው በርካቶችን እንድንስብ ያስቻሉንን ባህሎቻችንን ከምንም በላይ ልንጠብቃቸው ይገባናል። ሌላው ዓለም ላይ የጠፋውንና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ግን አሁንም ድረስ ያሉ ባህሎችን ከዘመኑ ጋር ማስኬድ እንጂ መበረዝም ሆነ እርግፍ አድርጎ በመተው ዘመንኛውን መከተል ማንነትን የመካድ ያህል ነው።

“ባለቤቱ ያቀለለውን …..ባለእዳ” እንደሚባለው ሁሉ ዩኔስኮ የመዘገባቸው/በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኙ / ቅርሶቻችን ከጠፉ ወይም የመበረዝ አደጋ ካጋጠማቸው ከ መዝገብ መሰረዛቸው የማይቀር ነው። ከዚህ የተነሳ ዘመናትን ተሻግረው እዚህ የደረሱ መገለጫዎቻችንን ለቀጣይ ትውልድ ጠብቀን ማስተላለፍ የሁላችንም ሃላፊነት ነው ። “በእነሱ ጊዜ ጠፉ” የሚል ጠባሳ በታሪካችን ላይ እንዲያርፍ መፍቀድ የለብንም። በተለይ ወጣቱ ትውልድ ባህሎቹን እንደ ዓይኑ ብሌን ሊጠብቃቸውና ሊንከባከባቸው ይገባል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You