
አዲስ አበባ፡- በጎንደር ከተማ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው መረጃ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ መሆኑን የጎንደር ከተማ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል ማርዬ በየነ ገለጹ፡፡
ኮማንድ ፖስቱ ጽንፈኛ ቡድኑ ላይ እየወሰደ ካለው እርምጃ ባሻገር የከተማዋን ነዋሪዎች በማወያየት ባከናወነው ሥራ የከተማዋ የሰላም ሁኔታ መሻሻሉንም ነው የተናገሩት፡፡
ጽንፈኛ ቡድኑ የኢትዮጵያን ህልውና እና ሰላም ከማይፈልጉ አካላት የሚላክለትን ፍርፋሪ በመጠቀም ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽም የሕዝብ ጠላት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኮማንድ ፖስቱ ከሕዝብ ጋር ባደረገው ውይይትም፤ ኅብረተሰቡ የጽንፈኛ ቡድኑን እኩይ ድርጊት በግልጽ ማንሳቱን ጠቅሰዋል፡፡
ነገር ግን ከጽንፈኛ ቡድኑ ጎን የተሰለፉ አንዳንድ አካላት በማኅበራዊ ሚዲያ የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ሕዝብ ለማደናገር እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም ባለፉት ቀናት “ብርጋዴር ጄኔራል ማርዬ ተገድለዋል” በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ የሀሰት መረጃ ሲያሰራጩ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም “ክፍለ ጦር ደመሰስን፣ ታንክ ማረክን፣ አውሮፕላን ጣልን” የሚሉ የበሬ ወለደ መረጃዎችን ሲያሰራጩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም ኅብረተሰቡ ሆነ ብለው የሀሰት መረጃ በሚያሰራጩ የጽንፈኛው ቡድን አባላት መደናገር የለበትም ነው ያሉት፡፡
ኮማንድ ፖስቱ በጽንፈኛ ቡድኑ ላይ ከሚወስደው እርምጃ ባሻገር ሕዝብን በማወያየት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየሠራ መሆኑንም ብርጋዴር ጄኔራል ማርዬ ተናግረዋል፡፡
በዚህም የመከላከያ ሠራዊቱ የተሰጠውን ግዳጅ በብቃት እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡
በቅርቡ በጎንደር ከተማ በአንድ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ተኩስ በመክፈት ለማምለጥ በሞከሩ የጽንፈኛው ኃይል አባላት ላይ እርምጃ በመውሰድ የከተማዋን ሰላም ማስጠበቅ መቻሉንም ብርጋዴር ጄኔራል
ማርዬ ገልጸዋል፡፡
ሠራዊቱ ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ሥራ እያከናወነ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ደጀኑ ሕዝባችን ምስክር ነው ብለዋል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2016 ዓ.ም