«ይቺ ናት ኢትዮጵያ!»

ክፍል 2

ከሁለት ሳምንት በፊት መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም ‹‹ይቺ ናት ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ስለኢትዮጵያ የተፈጥሮ ብዝሃነት አስገራሚነት ማስነበባችን ይታወሳል። በአንድ ወር ውስጥ፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ፣ በአንድ ሰዓትና ደቂቃ ውስጥ፤ በአጠቃላይ በአንድ ቅጽበት ውስጥ እንደ ሰሜን ተራሮች ዓይነት በረዶ ያዘለ ቅዝቃዜ እና እንደ ዳሎል ያለ እሳት የሚተፋ ሙቀት ያለባት ናት ኢትዮጵያ!

ይህ በተፈጥሮ የተገኘ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብዝሃነት ግን በማህበራዊ ሕይወትም እንደዚሁ ነው፡፡ ሰሜኑ ከደቡብ፣ ምዕራቡ ከምሥራቅ የተለያየ ዓይነት ሰዋዊ ጥበባት የሚገኙበት ነው፡፡ የተለያዩ ባህልና ወጎች፣ ሃይማኖቶች የሚገኙበት ነው፡፡ በአንድ ትዕይንት ውስጥ ብዙ ነገሮች የሚታዩበት ነው፡፡ ለሥራ ከአንዱ አካባቢ ወደሌላ አካባቢ የሄደ ሰው ሌላ ሀገር ጎብኝቶ እንደመምጣት ነው፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ የብዙ ሀገር ሀብቶች ማለት ነው፡፡

ዛሬ መስከረም 16 ነው፡፡ ይህ ቀን በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ የደመራ በዓል ነው፡፡ እነሆ ዘንድሮ ደግሞ ሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች እስልምና እና ክርስትና አንድ ቀን በዓል የሚያከብሩበት ቀን ተገጣጠመ፡፡ ዛሬ በእስልምና እምነት ተከታዮች የሚከበረው በዓል መውሊድ ነው፡፡ ሁለቱ ሃይማኖቶች የአንዱ በዓል ለአንደኛውም በዓል ነበር፤ ዘንድሮ ግን አንድ ቀን ተገጣጥሟል፤ እንዲህ አይነት አጋጣሚዎችን ነው ‹‹ይቺ ናት ኢትዮጵያ!›› ሲባል የምንሰማው፡፡

በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን አንድ ምሁር ማብራሪያ ሲሰጡ አሳዘኑኝ፡፡ ምሁሩ ስለኢትዮጵያ ብዝሃነት እያብራሩ ነው፡፡ የሚያብራሩትን ነገር ሲያስቡት በፖለቲከኞች በተደጋጋሚ የሚባል ነገር ሆኖባቸዋል መሰለኝ፡፡ መረር ብለው እያብራሩ ‹‹ይህን የምልህ እንዲያው ዝም ብዬ ለፖለቲካል ኮሬክትነስ (political Correctness) እንደሚባለው አይደለም፤ የምርም ስለሆነ ነው›› እያሉ ተናገሩ፡፡

ሰውዬው ያሳዘኑብኝ ምክንያት ስሜታቸውን ስለተረዳኋቸውና ስለተጋረኋቸው ነው፡፡ ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያበጣብጡት ሁሉ ለፖለቲካ ትክክለኝነት (political Correctness) ይጠቀሙታል፡፡ ለፖለቲካ ብልጠት ሲባል መደጋገሙ ነገርዬውን አቀለለው፡፡ ስለብዝሃነት የሚወራው በብዛት በፖለቲከኞች ስለሆነ ብዙ ሰዎች እንደ ፖለቲካ ቃል አዩት፡፡ ምናልባትም አንዳንድ ሰዎች የፖለቲካ ቃል ይመስልብኛል በሚል ለመናገር ይፈሩት ይሆናል፤ ነገርዬው ግን ተፈጥሯዊ ነው፤ የኢትዮጵያ ትክክለኛ ምንነትና ማንነት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚታይና ተጨባጭ የሆነ ሀቅ ነው፡፡ ተፈጥሯዊና ማህበራዊ ሁኔታዎችን ብቻ እናስተውል፡፡

ከአለባበስና አመጋገብ ጀምሮ የአንዱን አካባቢ የኢትዮጵያ ክፍል ከሌላው አካባቢ ጋር ማነፃፀር ይቻላል፡፡ ሁለቱን ትልልቅ ሃይማኖቶች ክርስትና እና እስልምና ማየት ይቻላል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ነገሮች ካየን እንደ ኢትዮጵያ ብዝሃነት ያለበት ሀገር ያለ አይመስልም። የተዋሃደ ብዝሃነት ማለት ነው፡፡ ይህ የተዋሃደ ብዝሃነት በውርርስ ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው አካባቢ ይሄዳል፤ ከዚያም ተወዳጅ ይሆናል፡፡ ይህ ብዝሃነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀገሩን እንዲወድ ያደርጋል፤ ምክንያቱም አዳዲስ የሆነ ነገር ያያል ማለት ነው፡፡ የራሱ ሀገር ብዙ አስደናቂ ነገሮች አሉት ማለት ነው፡፡

ከስድስት ዓመታት በፊት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር ባዘጋጁት አንድ የባህል መድረክ ላይ ታድሜ ነበር፡፡ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የውይይት መነሻ ጽሑፍ ሲያቀርቡ የተናገሩት ነገር በየአጋጣሚው ትዝ ይለኛል። ሃሳባቸው ሲጠቃለል፤ አንድ ሀገር አንድ ዓይነት ነገር ካለው ማንም አይጎበኘውም የሚል ነበር፡፡ በሌላ በኩል አውሮፓውያኑን ለመምሰል የራስን ባህል መበረዝ ማንም እንዳያየው ማድረግ ነው የሚል ነበር። ምክንያቱም የሌላ ሀገር ጎብኚ የሚመጣው አዲስ ነገር ለማየት እንጂ ከራሱ ሀገር ያለውን ነገር ለማየት አይደለም፡፡ ከአውሮፓ ሀገራት አንዷ የመጣ ጎብኚ ወደ ኢትዮጵያ መጣ እንበል፡፡ ኢትዮጵያ ሲመጣ የሚያየው ነገር ሁሉ የራሱ ሀገር አለባበስ፣ የራሱ ሀገር አጨፋፈርና የራሱ ሀገር አመጋገብ ከሆነ ምንም አልጎበኘም ማለት ነው፡፡ በራሱ ሀገር የሰለቸውን ነገር እየደገምንለት ነው ማለት ነው፡፡

ይህን ብዝሃነት ልናስጠብቀው የሚገባ ከውጭ ጎብኚ አንፃር አይደለም፡፡ ከራሳችን አንፃር ነው፤ ለራሳችንም ውበት ስለሆነ ነው፡፡ የዳሽን እና የዳሎል ልዩነት ያስደመሙኝን ያህል ዙምባራ እና እስክስታም ስለሚያስደምሙኝ ነው፡፡ ምንም እንኳን የእምነቱ ተከታይ የበለጠ በጉጉት እንደሚጠብቀው ግልጽ ቢሆንም፤ የእስልምናውም ሆነ የክርስትናው በዓላት የአንዱ ለሌላው በጉጉት የሚጠብቁት ነው። ከምግብ ጋር ለተያያዘው ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ማህበራዊ መስተጋብሩ ያስገድዳቸዋል፡፡ ልጅ እያለሁ ያስተዋልኩትን ልጥቀስ፡፡

በአካባቢያችን ሙስሊሞች ነበሩ፡፡ በአካባቢው የማህበራዊ ሕይወት ልማድ መሠረት ሠርግ ወይም የዓመት በዓል ሲያጋጥም መተጋገዝ የተለመደ ነው። ሰዎች ደግነታቸውን፣ ሙያቸውን፣ ውለታ ከፋይ መሆናቸውን… የሚያሳዩበት ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ሠርግ ሲያድረግ ለሙስሊሞች ለብቻ በሬ ወይም ፍየል ወይም በግ ይገዛል፡፡ ይህ የሚሆነው ራሳቸው ማረድ ስላለባቸው ነው፡፡ ይህን የሚያደርገው የቀበሌውን ሊቀመንበር ፈርቶ አይደለም፤ ወይም ለማንም አድርባይ ለመሆን ብሎ አይደለም፡፡ ከእነዚያ በክፉ በደጉ ጊዜ አብረውት ከኖሩ ሙስሊም ጎረቤቶቹ መለየት ስለማይችል ነው፡፡

ሙስሊም ሠርግ ሲያድርግ ወይም ሌላ የዓመት በዓል ሲሆንም እንደዚሁ ነው፡፡ ለክርስቲያኖች ለብቻ በሬ ይገዛል፡፡ እኔ ባደኩበት አካባቢ ክርስቲያን ይበዛል። ከሩቅ አካባቢ ካልተጠራ በስተቀር በቅርብ ያሉት ሙስሊሞች የአንድ መንደር ብቻ ናቸው፡፡ ክርስቲያኑ በጣም ብዙ ስለሆነ ብዙ ጊዜ ሙስሊሞች ሠርግ ሲያደርጉ ለክርስቲያኑ በሬ ነው የሚገዙ፤ የሚያርዱትም ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ክርስቲያን ሠርግ ሲያደርግ ግን እንደ ግለሰቡ አቅም ይወሰናል፡፡ ከሩቅ ያሉትን መጥራት የማይችል ከሆነ ቅርብ ያሉት ሙስሊሞች የአንድ መንደር ብቻ ስለሆኑ የፍየል ሙክት ይገዛል፡፡ እዚህ ላይ ታዲያ የሚገርሙኝ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ ገና ምን እንደሚገዛ ሳያውቁት አስቀድመው ‹‹አደራህን ለአንድ ቤተሰብ ብለህ ከብት እንዳታበላሽ፤ ፍየል ይበቃል›› እያሉ ሰውዬውን (ባለጉዳዩን) ያስጠነቅቁታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በምክክር ሁሉ ያደርጉታል፡፡

የሃይማኖትን ልዩነት ሳይለቁ በዚህ ልክ አንድ መሆን አይገርምም? እነዚህ ሰዎች ስለልዩነት አያቁም ቢባል ‹‹የተማረ›› የሚባለው ፖለቲከኛ ያምን ይሆን? ለእነዚህ ሰዎች ስለአንድነት ማስተማር ለቀባሪ ማርዳት አይሆንም?

‹‹ይቺ ናት ኢትዮጵያ!›› ሲባል ትዝ የሚሉኝ እነዚህ በአካባቢዬ ያየኋቸው ማህበረሰባዊ አብሮነቶች ናቸው፡፡ ትዝ የሚለኝ ለመስቀል በዓል የተጣላ ጎረቤት የሚያስታርቀው ሙስሊሙ ጋሼ አሕመድ ነው፡፡ ትዝ የሚለኝ የሮመዳን ጾም ሲገባ ፀሐይ ሲመታቸው ውሃ ይጠማቸዋል በሚል ክርስቲያኖች የሙስሊሞችን ጤፍ ሲያጭዱላቸው ነው፡፡ ታዲያ ይህ ‹‹ይቺ ናት ኢትዮጵያ!›› አያስብልም?

ለሙስሊሙም ለኦርቶዶክሱም መልካም በዓል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን መስከረም 16/2026

Recommended For You