
የሆሊውድ ፀሐፊዎች የሥራ ማቆም አድማቸውን ለማቆም የሚያስችል ጊዜያዊ ስምምነት ከስቱዲዮ ኃላፊዎች ጋር መድረሳቸውን ተናገሩ።
ፀሐፊዎቹ ለአምስት ወራት ያህል የዘለቀ የሥራ ማቆም አድማም ካደረጉም በኋላ ነው ስምምነት ላይ ተደርሷል የተባለው።
የአሜሪካ ፀሐፊዎች ማህበር (ደብልዩጂኤ) ስምምነቱን በተመለከተም “ለፀሐፊዎች ትርጉም ያለው ጥቅም እና ጥበቃ የሚሰጥ፤ ልዩ ነው” ብሎታል።
ሆኖም በመጨረሻም ውሳኔው የማህበሩ አባላት ይሆናል። ይህ የሥራ ማቆም አድማ በሆሊውድ ውስጥ በአስርት አመታት ውስጥ ከተከሰቱት ረጅሙ ነው።
ለወራት ቀጥሎ በነበረው የሥራ ማቆም አድማ አብዛኛው የፊልም እና የቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ቀጥ እንዲል ሆኗል።
ከፀሐፊዎቹ በተጨማሪ የፊልም ተዋናዮችም የሥራ ማቆም አድማ ላይ ይገኛሉ።
ሚያዝያ መጨረሻ አካባቢ የተጀመረው የሥራ ማቆም አድማ ሆሊውድ የሚገኝባት የካሊፎርኒያ ግዛት ምጣኔ ሀብት በቢሊዮኖች በሚቆጠር ዶላር አስወጥቷታል።
የአሜሪካ ፀሐፍያን ማህበር አባላት ወደ ሥራ ከመመለሳቸው በፊት ‘አሊያንስ ኦፍ ሞሺን ፒክቸር ኤንድ ቴሌቪዥን ፕሮዲውሰርስ’ ከተሰኘው እና ከ350 በላይ የቴሌቪዥን እና የፊልም ፕሮዳክሽን ኩባንያዎችን ከሚወክለው የንግድ ማህበር ጋር በሶስት ዓመት ውል መስማማት አለባቸው።
ማህበሩ በቀረበው የድርድር ሁኔታ በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮች መጠናቀቅ እንዳለባቸው አሳውቆ አድማውም አልቆመም ብሏል።
ነገር ግን “ከዛሬ ጀምሮ ማህበሩ እያደረገ ያለውን ተቃውሞ አቁሟል” በማለት አስታውቋል።
በተነሳው ውዝግብ ምክንያት በርካታ ታዋቂ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ተከታታይ ፊልሞች እና ሌሎች ትዕይንቶች እንዲቋረጡ ምክንያት ሆኗል።
ከፊልም ኢንዱስትሪው ጋር በተዛማጅነት የሚሰሩ ምግብ የመዋቢያ እና አልባሳት አቅራቢዎች፣ አናጢዎች፣ የካሜራ ኦፕሬተሮችም ክፉኛ ተጎድተዋል።
በባለፉት ጥቂት ቀናት ታዋቂዎች የፊልም ማሳያዎቹ ኔትፍሊክስ፣ ዲዝኒ፣ ዩኒቨርሳል እና ዋርነር ብሮስ ኩባንያ ኃላፊዎች በድርድሩ በግላቸው መገኘት አዲስ ተስፋን ፈንጥቋል።
የሆሊውድ ፀሐፊዎችና ተዋናዮች ይህንን አድማ ለመምታት ዋነኛ ምክንያት የሆናቸው ክፍያ፣ የሥራ ሁኔታ እና በፊልሞች ላይ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) መጠቀም የፈጠረው ስጋት ናቸው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2016