
በኒጀር የተከሰተውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ፈረንሳይ አምባሳደሯን እንደምታስወጣ እና ከሀገሪቷ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር እንደምታቆም ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ተናገሩ።
ማክሮን ፈረንሳይ ከኒጀር አምባሳደሯን ለማስወጣት ወስናለች። በሚቀጥሉት ሰዓታት አምባሳደራችን እና በርካታ ዲፕሎማቶች ወደ ፈረንሳይ ይመለሳሉ ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ጨምረውም ከሀገሪቷ ጋር የሚኖረው ወታደራዊ ትብብር ማብቃቱንና የፈረንሳይ ወታደሮች በሚቀጥሉት ወራት ከሀገሪቷ እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ሐምሌ ወር ላይ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠረው የኒጀር ወታደራዊ ኃይል ውሳኔውን ተቀብሎታል።
የወታደራዊ ኃይሉ መሪ በሰጡት መግለጫም በአሁኑ እሑድ ኒጀር ወደ ሉዓላዊነቷ እያመራች ያለችበትን አዲስ ርምጃ እናከብራለን ማለታቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የፓሪስ ውሳኔ የተሰማው በሀገሪቷ የፈረንሳይ መገኘትን
በመቃወም ለወራት በዋና መዲናዋ ኒያሚ በተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰልፎች ከተካሄዱ፣ ግጭትና ተቃውሞ ከተከሰተ በኋላ ነው።
የባህር በር በሌላት የምዕራብ አፍሪካዊ ሀገር ከአንድ ሺህ 500 በላይ የፈረንሳይ ወታደሮች ይገኛሉ። ፈረንሳይ
ወታደሮቿን ከሀገሪቷ የማስወጣት ውሳኔዋ በሳህል ቀጠና በእስላማዊ ታጣቂዎች ላይ እየወሰደች ያለችው ርምጃ ላይ እንዲሁም ፓሪስ በሀገሪቷ ያላት ሚና ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ተብሏል።
ሆኖም ማክሮን ለሀገራቸው መገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ ፈረንሳይ በመፈንቅለ መንግሥት ፈጻሚዎች አትታገትም ብለዋል።
ማክሮን ጨምረውም ከሥልጣን የተወገዱትንና በመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ የታሰሩትን ፕሬዚዳንት መሃመድ ባዙምን የኒጀር ሕጋዊ ባለሥልጣን አድርገው እንደሚመለከቷቸው ገልጸው፣ ውሳኔውንም እንዳሳወቋቸው ተናግረዋል።
ኒጀር በቅርቡ መፈንቅለ መንግሥት ከተፈፀመባቸው በምዕራብ አፍሪካ ከሚገኙ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ከነበሩ ሀገራት መካከል አንዷናት።
ቀደም ብሎ በቡርኪና ፋሶ፣ በጊኒ፣ በማሊ እና በቻድ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደ ሲሆን ወታደራዊ ኃይሎች ሥልጣን ተቆጣጥረዋል። ነሐሴ ወር ላይም በተመሳሳይ በጋቦን መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዷል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በቀጠናው ፀረ ፈረንሳይ ተቃውሞዎች በርትተዋል። የየሀገራቱ በርካታ ፖለቲከኞች ፓሪስ የድህረ ቅኝ ግዛት ፖሊሲዎችን ትተገብራለች ሲሉ ይከሳሉ። ፈረንሳይ ግን ክሱን ውድቅ አድርገዋለች።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2016